ግፍ ለተፈጸመባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ
“በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለአካለ መጠን የደረሱም ሆኑ ያልደረሱ ሴቶች ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። አንቺ ከእነዚህ መካከል አንዷ ነሽ? አምላክ የአንቺ ደህንነት ምን ያህል እንደሚያሳስበውና በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል ለማስቆም ምን እርምጃ እንደሚወስድ እንድታነብቢ እንጋብዝሻለን።”
በjw.org ላይ የሚገኘው “የሴቶች ደህንነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” የሚለው ርዕስ የሚጀምረው እንዲህ በማለት ነው። በርዕሱ መጨረሻ ላይ ያለው ሊንክ ርዕሱን በPDF ፎርማት ለማውረድ ያስችላል፤ ከዚያም ጽሑፉ ታትሞ ሲታጠፍ ባለ አራት ገጽ ትራክት ይሆናል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ስቴሲ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ትራክቱን ካተምኩት በኋላ ከአንዲት እህት ጋር ሆነን በጉባኤያችን ክልል ውስጥ ወደሚገኝ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ጥበቃ የሚያደርግ ተቋም ወሰድነው።”
በተቋሙ የምትሠራ አንዲት ሴት በዚያ ለሚኖሩት ሴቶች ትራክቱን ለማሰራጨት ተጨማሪ ቅጂዎችን ማግኘት ትችል እንደሆነ ጠየቀች። በዚህም የተነሳ እህቶች 40 ተጨማሪ ትራክቶችንና 30 የjw.org የአድራሻ ካርዶችን ወሰዱ። ከጊዜ በኋላ የተቋሙ ኃላፊ፣ እህቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራው እንዴት እንደሆነ በዚያ ለሚኖሩት ሴቶች እንዲያሳዩአቸው ጠየቀች።
ስቴሲና ሌሎች ሁለት እህቶች በሌላ ተቋምም ተመሳሳይ ውጤት አግኝተዋል። በዚያ አምስት ትራክቶችን ያበረከቱ ሲሆን ተጨማሪ ትራክቶችን እንዲያመጡ ተጠይቀዋል። በዚያ የምትሠራ አንዲት ሴት “ይህ ፓምፍሌት እዚህ ያሉትን ሴቶች ይረዳቸዋል። . . . በጣም የሚያስፈልገን ነገር ነው” ብላለች። እህቶች ተመልሰው ሲመጡ በዚያ የሚኖሩ በርካታ ሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራው እንዴት እንደሆነ ለመመልከት ተሰበሰቡ፤ ሁለት ሴቶች ደግሞ በቀጣዩ የሳምንቱ መጨረሻ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ፍላጎት አሳዩ።”
ስቴሲ እንዲህ ብላለች፦ “ለዚህ ግሩም ርዕስ የተሰጠው ምላሽ በጣም አስደንቆናል። ጽሑፉን አትሞ በማጠፍ የሚዘጋጀው ትራክት ግፍ ለተፈጸመባቸው ሴቶች የመንግሥቱን መልእክት ለማካፈል የሚያስችል ማራኪ መንገድ ነው። ሰዎቹ በሰጡት አዎንታዊ ምላሽ ልባችን ተነክቷል፤ ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ማካፈላችንን ለመቀጠል የምናደርገውን ጥረት እንዴት እንደሚባርከው ለማየት እንጓጓለን።”