11 “እስራኤል ገና ልጅ ሳለ ወደድኩት፤+
ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት።+
2 እነሱ ደጋግመው በጠሯቸው መጠን
በዚያው ልክ ከእነሱ ራቁ።+
ለባአል ምስሎች መሠዋታቸውን፣+
ለተቀረጹት ምስሎችም መሥዋዕት ማቅረባቸውን ቀጠሉ።+
3 እኔ ግን ኤፍሬምን መራመድ አስተማርኩት፤+ በክንዶቼም ተሸከምኳቸው፤+
የፈወስኳቸውም እኔ እንደሆንኩ አምነው አልተቀበሉም።
4 በሰዎች ገመድ፣ በፍቅርም ማሰሪያ ሳብኳቸው፤+
ደግሞም ከጫንቃቸው ላይ ቀንበር እንደሚያነሳ ሰው ሆንኩላቸው፤
ለእያንዳንዳቸውም በደግነት ምግብ አቀረብኩላቸው።
5 እነሱ ወደ ግብፅ ምድር አይመለሱም፤ ሆኖም አሦር ንጉሣቸው ይሆናል፤+
ምክንያቱም ወደ እኔ ለመመለስ አሻፈረን ብለዋል።+
6 በጠነሰሱት ሴራ የተነሳ በከተሞቹ ላይ ሰይፍ ያንዣብባል፤+
መቀርቀሪያዎቹንም ይሰባብራል፤ ይበላቸዋልም።+
7 ሕዝቤ በእኔ ላይ ክህደት ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም።+
ወደ ላይ ቢጠሯቸውም ማንም አይነሳም።
8 ኤፍሬም ሆይ፣ እንዴት ልተውህ እችላለሁ?+
እስራኤል ሆይ፣ እንዴት አሳልፌ ልሰጥህ እችላለሁ?
እንዴትስ እንደ አድማህ አደርግሃለሁ?
ደግሞስ እንዴት እንደ ጸቦይም ላደርግህ እችላለሁ?+
ስለ አንተ ያለኝ አመለካከት ተለወጠ፤
የርኅራኄ ስሜቴም ተቀሰቀሰ።+
9 የሚነድ ቁጣዬን አልገልጽም።
ኤፍሬምን ዳግመኛ አላጠፋም፤+
እኔ አምላክ እንጂ ሰው አይደለሁምና፤
በመካከልህ ያለሁ ቅዱስ አምላክ ነኝ፤
በአንተም ላይ በቁጣ አልመጣም።
10 እነሱ ይሖዋን ተከትለው ይሄዳሉ፤ እሱም እንደ አንበሳ ያገሳል፤+
እሱ ሲያገሳ ልጆቹ ከምዕራብ እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ።+
11 ከግብፅ ሲወጡ እንደ ወፍ፣
ከአሦርም ምድር ሲወጡ እንደ ርግብ ይርገፈገፋሉ፤+
እኔም በየቤታቸው እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ” ይላል ይሖዋ።+
12 “ኤፍሬም በውሸት፣
የእስራኤልም ቤት በማታለል ከበበኝ።+
ይሁዳ ግን አሁንም ከአምላክ ጋር ይሄዳል፤
እጅግ ቅዱስ ለሆነውም አምላክ ታማኝ ነው።”+