የማርቆስ ወንጌል
16 ሰንበት+ ካለፈ በኋላም መግደላዊቷ ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና+ ሰሎሜ ሄደው አስከሬኑን ሊቀቡ ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞች ገዙ።+ 2 ከዚያም በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በማለዳ ፀሐይ ስትወጣ ወደ መቃብሩ መጡ።+ 3 እርስ በርሳቸውም “በመቃብሩ ደጃፍ ላይ ያለውን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል?” ይባባሉ ነበር። 4 ቀና ብለው ሲመለከቱ ግን በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከቦታው ተንከባሎ አዩ።+ 5 ወደ መቃብሩ ሲገቡ ነጭ ልብስ የለበሰ አንድ ወጣት በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። 6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “አትደንግጡ።+ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ። እሱ ተነስቷል።+ እዚህ የለም። ተመልከቱ፣ እሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውና።+ 7 ይልቁንስ ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል።+ እንደነገራችሁም እዚያ ታዩታላችሁ’ በሏቸው።”+ 8 እነሱም ከመቃብሩ ከወጡ በኋላ በአድናቆት ተውጠው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ሸሽተው ሄዱ። ከፍርሃታቸውም የተነሳ ለማንም ምንም ነገር አልተናገሩም።*+