ጥቅምት
ረቡዕ፣ ጥቅምት 1
ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ለመታዘዝ ዝግጁ . . . ነው።—ያዕ. 3:17
አንዳንድ ጊዜ መታዘዝ ያታግልሃል? ንጉሥ ዳዊት እንደዚህ ተሰምቶት ያውቃል። በመሆኑም “አንተን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አድርግ” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (መዝ. 51:12) ዳዊት ይሖዋን ይወደው ነበር። ያም ቢሆን ዳዊት መታዘዝ የከበደው ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ እኛም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ያለመታዘዝ ዝንባሌ ወርሰናል። ሁለተኛ፣ ሰይጣን ልክ እንደ እሱ እንድናምፅ ሁልጊዜ ሊገፋፋን ይሞክራል። (2 ቆሮ. 11:3) ሦስተኛ፣ የምንኖረው የዓመፀኝነት ዝንባሌ በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ነው፤ ይህ ዝንባሌ “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኤፌ. 2:2) ያለብንን የኃጢአት ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን ዲያብሎስና ይህ ዓለም እንዳንታዘዝ የሚያደርጉብንን ጫናም መዋጋት ይኖርብናል። ለይሖዋና እሱ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች ለመታዘዝ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። w23.10 6 አን. 1
ሐሙስ፣ ጥቅምት 2
ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል።—ዮሐ. 2:10
ኢየሱስ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ ከቀየረበት ተአምር ምን ትምህርት እናገኛለን? ስለ ትሕትና ግሩም ትምህርት እናገኛለን። ኢየሱስ ስለ ተአምሩ ጉራ አልነዛም። በመሠረቱ ኢየሱስ፣ ያከናወናቸውን ነገሮች በተመለከተ ፈጽሞ ጉራ ነዝቶ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ምስጋናውና ውዳሴው ወደ አባቱ እንዲሄድ በማድረግ ትሕትና ያሳይ ነበር። (ዮሐ. 5:19, 30፤ 8:28) እኛም ትሑት በመሆንና ስለ ራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ኢየሱስን የምንመስል ከሆነ ያከናወንናቸውን ነገሮች በተመለከተ ጉራ አንነዛም። በራሳችን ሳይሆን በምናገለግለው ታላቅና ክብራማ አምላክ እንኩራራ። (ኤር. 9:23, 24) ለእሱ የሚገባውን ምስጋና እንስጠው። ደግሞስ ይሖዋ ባይረዳን ኖሮ ምን ማከናወን እንችል ነበር? (1 ቆሮ. 1:26-31) ትሑት ከሆንን፣ ሌሎችን ለመርዳት ስንል ላደረግናቸው መልካም ነገሮች እውቅና እንዲሰጠን አንጠብቅም። ይሖዋ የምናከናውነውን ነገር እንደሚያየውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ማወቃችን ብቻ ይበቃናል። (ከማቴዎስ 6:2-4 ጋር አወዳድር፤ ዕብ. 13:16) በእርግጥም ትሕትና በማሳየት ኢየሱስን ስንመስል ይሖዋ ይደሰትብናል።—1 ጴጥ. 5:6፤ w23.04 4 አን. 9፤ 5 አን. 11-12
ዓርብ፣ ጥቅምት 3
ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።—ፊልጵ. 2:4
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጡ በመንፈስ ተመርቶ መክሯቸዋል። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎችም እንደ እኛ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልጉ በማስታወስ ነው። ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከጓደኞቻችሁ ጋር ስትጨዋወቱ ሌሎቹ የማውራት አጋጣሚ እስኪያጡ ድረስ ያለማቋረጥ ታወራላችሁ? እንዲህ እንደማታደርጉ የታወቀ ነው! እነሱም በጭውውቱ እንዲካፈሉ ትፈልጋላችሁ። በተመሳሳይም በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ሐሳብ እንዲሰጡ እንፈልጋለን። እንዲያውም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማበረታታት ከምንችልባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ እምነታቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ መስጠት ነው። (1 ቆሮ. 10:24) እንግዲያው አጭር መልስ በመመለስ ብዙ ሰዎችን ለማሳተፍ የሚያስችል ጊዜ እንዲገኝ አድርጉ። አጭር መልስ በምትመልሱበት ጊዜም ቢሆን ብዙ ነጥቦችን ከመጥቀስ ተቆጠቡ። በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ነጥቦች በሙሉ ከጠቀሳችሁ ሌሎች ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት አይችሉም። w23.04 22-23 አን. 11-13
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 4
ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።—1 ቆሮ. 9:23
ሌሎችን መርዳት በተለይም በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን መበርታት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን መርሳት የለብንም። በአገልግሎታችን ላይ ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ ይጠቅመናል። የተለያየ እምነትና አመለካከት እንዲሁም አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር እንገናኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደአስፈላጊነቱ ለውጥ የሚያደርግ ሰባኪ ነበር፤ ከእሱ የምናገኘው ብዙ ትምህርት አለ። ኢየሱስ ጳውሎስን ‘ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ’ እንዲሆን ሾሞታል። (ሮም 11:13) ጳውሎስ ይህን ተልእኮውን ሲወጣ አይሁዳውያን፣ ግሪካውያን፣ የተማሩ ሰዎች፣ ተራ ገበሬዎች፣ ሹሞችና ነገሥታት አጋጥመውታል። ጳውሎስ የእነዚህን ሁሉ ሰዎች ልብ ለመንካት “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” ሆኗል። (1 ቆሮ. 9:19-22) የአድማጮቹን ባሕል፣ አስተዳደግና ሃይማኖታዊ አመለካከት ለማስተዋል ጥረት አድርጓል፤ አቀራረቡንም እንደሁኔታው አስተካክሏል። እኛም በአገልግሎታችን ዘዴኞች በመሆንና አቀራረባችንን እንደ አድማጮቻችን ሁኔታ በመቀየር ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንችላለን። w23.07 23 አን. 11-12
እሁድ፣ ጥቅምት 5
የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር [ሊሆን ይገባዋል]።—2 ጢሞ. 2:24
ገርነት የጥንካሬ እንጂ የድክመት ምልክት አይደለም። በሚፈታተን ሁኔታ ውስጥ መረጋጋት ውስጣዊ ጥንካሬ ይጠይቃል። ገርነት “የመንፈስ ፍሬ” አንዱ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22, 23) “ገርነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ከተገራ ፈረስ ጋር በተያያዘም ተሠርቶበታል። አንድ የዱር ፈረስ ሲገራ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ለማሰብ ሞክር። ጠንካራ ሆኖም ገራም ይሆናል። እኛ ሰዎችስ ገርም ጠንካራም መሆን የምንችለው እንዴት ነው? በራሳችን ጥረት እንዲህ ማድረግ አንችልም። አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠን እንዲሁም ይህን ግሩም ባሕርይ ለማዳበር እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። ገርነትን ማዳበር እንደሚቻል ተሞክሮዎች ያሳያሉ። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ተቃዋሚዎች ሲያጋጥሟቸው በገርነት ምላሽ መስጠት ችለዋል፤ ይህም ሁኔታውን ለተመለከቱ ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል።—2 ጢሞ. 2:24, 25፤ w23.09 14 አን. 3
ሰኞ፣ ጥቅምት 6
ጸልዬ ነበር፤ ይሖዋም የለመንኩትን ሰጠኝ።—1 ሳሙ. 1:27
ሐዋርያው ዮሐንስ 24 ሽማግሌዎች በሰማይ ይሖዋን ሲያመልኩ የሚያሳይ አስደናቂ ራእይ ተመልክቷል። ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች አምላክ “ግርማ፣ ክብርና ኃይል” ሊቀበል እንደሚገባው በመግለጽ አወድሰውታል። (ራእይ 4:10, 11) ታማኝ መላእክትም ይሖዋን ለማወደስና ለማክበር የሚያነሳሳ ስፍር ቁጥር የሌለው ምክንያት አላቸው። በሰማይ ከእሱ ጋር ስለሚኖሩ በሚገባ ያውቁታል። ከሚሠራው ነገር ባሕርያቱን ማስተዋል ይችላሉ። ይሖዋ የሚያከናውናቸውን ነገሮች ሲመለከቱ እሱን ለማወደስ ይነሳሳሉ። (ኢዮብ 38:4-7) እኛም በጸሎታችን ላይ ይሖዋን እንድንወደውና እንድናከብረው የሚያደርጉንን ምክንያቶች በመጥቀስ ልናወድሰው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና ስታጠና አንተን ይበልጥ የሚማርኩህን የይሖዋ ባሕርያት ለማግኘት ሞክር። (ኢዮብ 37:23፤ ሮም 11:33) ከዚያም ስለ እነዚህ ባሕርያት ምን እንደሚሰማህ ለይሖዋ ንገረው። በተጨማሪም ይሖዋን ለእኛም ሆነ ለመንፈሳዊ ቤተሰባችን ላደረገው ነገር ልናወድሰው እንችላለን።—1 ሳሙ. 2:1, 2፤ w23.05 3-4 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 7
ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ [ተመላለሱ]።—ቆላ. 1:10
በ1919 የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ ወጡ። በዚያው ዓመት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተሾመ፤ በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አዲስ በተከፈተው “የቅድስና ጎዳና” ላይ እንዲጓዙ መርዳት ጀመረ። (ማቴ. 24:45-47፤ ኢሳ. 35:8) ባለፉት ዘመናት ለኖሩት ታማኝ “የመንገድ ሠራተኞች” ምስጋና ይግባቸውና በአዲሱ አውራ ጎዳና ላይ የሚጓዙ ሁሉ ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ያላቸው እውቀት እያደገ መጣ። (ምሳሌ 4:18) ሕይወታቸውን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መምራትም ቻሉ። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ሁሉንም ለውጥ በአንድ ጊዜ እንዲያደርጉ አልጠበቀባቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ በጊዜ ሂደት ሕዝቡን ማጥራት ጀመረ። ወደፊት፣ በምናደርገው ነገር በሙሉ አምላካችንን ማስደሰት ስንችል በጣም ደስተኞች እንደምንሆን ምንም ጥያቄ የለውም! ሁሉም መንገዶች በየጊዜው እድሳት ሊደረግላቸው ይገባል። ከ1919 ወዲህ ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ የሚከናወነው የመንገድ ሥራ ቀጥሏል፤ በዚህም የተነሳ ተጨማሪ ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ችለዋል። w23.05 17 አን. 15፤ 19 አን. 16
ረቡዕ፣ ጥቅምት 8
ፈጽሞ አልተውህም።—ዕብ. 13:5
የበላይ አካሉ በተለያዩ የበላይ አካሉ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ረዳቶችን በግለሰብ ደረጃ ሲያሠለጥን ቆይቷል። እነዚህ ረዳቶች በአሁኑ ወቅት ከባድ ኃላፊነት እየተወጡ ነው። የክርስቶስን በጎች የመንከባከቡን ሥራ ለማስቀጠል ዝግጁ ናቸው። በታላቁ መከራ መደምደሚያ አካባቢ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ሄደው ሲያልቁ ንጹሕ አምልኮ በምድር ላይ ይቀጥላል። ኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ስለሚሰጣቸው የአምላክ ሕዝቦች ሥራቸው አይስተጓጎልም። እርግጥ ነው፣ በዚያ ወቅት የማጎጉ ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ብሔራት ከባድ ጥቃት ይሰነዝሩብናል። (ሕዝ. 38:18-20) ሆኖም ይህ አጭር ጥቃት ይከሽፋል፤ የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን ማምለካቸውን እንዲያቆሙ አያደርጋቸውም። ይሖዋ ይታደጋቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ የክርስቶስን ሌሎች በጎች ያቀፈውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በራእይ ተመልክቷል። ዮሐንስ እነዚህ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ‘ታላቁን መከራ አልፈው እንደመጡ’ ተነግሮታል። (ራእይ 7:9, 14) ስለዚህ ይሖዋ እንደሚያድናቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w24.02 5-6 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ጥቅምት 9
የመንፈስን እሳት አታጥፉ።—1 ተሰ. 5:19
መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን መጸለይ፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ማጥናት እንዲሁም በአምላክ መንፈስ ከሚመራው ድርጅቱ ጋር መተባበር እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን “የመንፈስ ፍሬ” እንድናፈራ ይረዳናል። (ገላ. 5:22, 23) አምላክ መንፈሱን የሚሰጠው ንጹሕ አስተሳሰብና ንጹሕ ምግባር ላላቸው ሰዎች ብቻ ነው። በርኩስ ሐሳቦች ላይ ካውጠነጠንን ወይም ርኩስ ምግባር ከፈጸምን አምላክ ለእኛ መንፈሱን መስጠቱን ያቆማል። (1 ተሰ. 4:7, 8) መንፈስ ቅዱስን ማግኘታችንን መቀጠል ከፈለግን ‘ትንቢቶችን ከመናቅ’ መቆጠብም ይኖርብናል። (1 ተሰ. 5:20) በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “ትንቢቶች” የሚለው ቃል በአምላክ መንፈስ የተነገሩ መልእክቶችን ያመለክታል። ይህም ከይሖዋ ቀንና ከጊዜው አጣዳፊነት ጋር የተያያዙ መልእክቶችን ይጨምራል። አርማጌዶን በእኛ የሕይወት ዘመን እንደማይመጣ በማሰብ ያንን ቀን አርቀን አንመለከትም። ከዚህ ይልቅ በየቀኑ ጥሩ ምግባር በማሳየትና ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮችን በመፈጸም’ ያንን ቀን በአእምሯችን አቅርበን እንመለከተዋለን።—2 ጴጥ. 3:11, 12፤ w23.06 12 አን. 13-14
ዓርብ፣ ጥቅምት 10
የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው።—ምሳሌ 9:10
የፖርኖግራፊ ምስሎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያችን ላይ ድንገት ቢመጡብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ወዲያውኑ ምስሉን ማየታችንን ማቆም ይኖርብናል። ከሁሉ በላይ ትልቁ ሀብታችን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና መሆኑን ማስታወሳችን እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ ይረዳናል። እንዲያውም እንደ ፖርኖግራፊ የማይቆጠሩ አንዳንድ ምስሎችም እንኳ የፆታ ስሜትን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። እንዲህ ካሉ ምስሎች መራቅ ያለብን ለምንድን ነው? በልባችን ምንዝር ወደመፈጸም የሚመራ ትንሽ እርምጃ እንኳ መውሰድ ስለማንፈልግ ነው። (ማቴ. 5:28, 29) በታይላንድ የሚኖር ዴቪድ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “‘ምስሎቹ እንደ ፖርኖግራፊ የሚቆጠሩ ባይሆኑም እንኳ እነሱን ማየቴን ብቀጥል ይሖዋ ይደሰታል?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። እንዲህ ብዬ ማሰቤ የጥበብ እርምጃ ለመውሰድ ይረዳኛል።” ይሖዋን ላለማሳዘን መፍራታችን የጥበብ እርምጃ ለመውሰድ ይረዳናል። አምላክን መፍራት “የጥበብ መጀመሪያ” ወይም መሠረት ነው። w23.06 23 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 11
ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ።—ኢሳ. 26:20
“ውስጠኛው ክፍል” የተባለው ጉባኤዎቻችንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ቃል የገባውን ጥበቃ የምናገኘው ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት ካለን ነው። እንግዲያው ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መቻል ብቻ በቂ አይደለም፤ ከአሁኑ ከልብ ለመዋደድም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው! “ታላቁ የይሖዋ ቀን” ለመላው የሰው ዘር አስጨናቂ ጊዜ ይሆናል። (ሶፎ. 1:14, 15) የይሖዋ አገልጋዮችም ፈተናዎች እንደሚያጋጥሟቸው ግልጽ ነው። ከአሁኑ ከተዘጋጀን ግን ያን ጊዜ አንረበሽም፤ እንዲያውም ሌሎችን ለመርዳት እንበቃለን። ምንም ዓይነት ፈተና ቢመጣ እንጸናለን። የእምነት ባልንጀሮቻችን ሲቸገሩ ርኅራኄ እናሳያለን፤ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። ደግሞም ከአሁኑ ፍቅርን ካዳበርን ያን ጊዜ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተቀራርበን መኖር አይቸግረንም። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል፤ ያን ጊዜ አደጋና መከራ ታሪክ ይሆናሉ!—ኢሳ. 65:17፤ w23.07 7 አን. 16-17
እሁድ፣ ጥቅምት 12
[ይሖዋ] ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
የአምላክ ቃል ታማኝ ሰዎች ጠንካራ እንደሆኑ ይናገራል። ይሁንና በጣም ጠንካራ የሆኑት የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ጠንካራ እንዳልሆኑ የተሰማቸው ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ‘እንደ ተራራ ጠንካራ’ እንደሆነ ተሰምቶት ያውቃል፤ ሆኖም ‘የተሸበረበት’ ጊዜም አለ። (መዝ. 30:7) መንፈስ ቅዱስ ለሳምሶን ለየት ያለ ጥንካሬ ሰጥቶታል፤ ያም ቢሆን አምላክ ኃይል ባይሰጠው ኖሮ ‘አቅም እንደማይኖረውና እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እንደሚሆን’ ያውቅ ነበር። (መሳ. 14:5, 6፤ 16:17) እነዚህ ታማኝ ሰዎች ጠንካራ ሊሆኑ የቻሉት ይሖዋ ኃይል ስለሰጣቸው ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እሱም ከይሖዋ ኃይል ማግኘት እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። (2 ቆሮ. 12:9, 10) ከጤና ችግሮች ጋር ይታገል ነበር። (ገላ. 4:13, 14) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የከበደው ጊዜም አለ። (ሮም 7:18, 19) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይጨነቅና ስጋት ያድርበት ነበር። (2 ቆሮ. 1:8, 9) ያም ቢሆን ጳውሎስ ሲደክም ያን ጊዜ ብርቱ ሆኗል። እንዴት? ይሖዋ ለጳውሎስ የጎደለውን ኃይል ስለሰጠው ነው። ጳውሎስን አጠንክሮታል። w23.10 12 አን. 1-2
ሰኞ፣ ጥቅምት 13
ይሖዋ . . . የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
አልፎ አልፎ ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር የምንታገል ከሆነ አንድ እውነታ እናስታውስ፤ ይሖዋን እያገለገልን ያለነው እሱ ራሱ ስለሳበን ነው። (ዮሐ. 6:44) እኛ እንኳ እንዳለን የማናውቀውን መልካም ነገር በውስጣችን አይቷል፤ ልባችንንም ያውቃል። (2 ዜና 6:30) ስለዚህ በፊቱ ውድ እንደሆንን ሲነግረን ልናምነው ይገባል። (1 ዮሐ. 3:19, 20) አንዳንዶቻችን እውነትን ከመስማታችን በፊት ባደረግናቸው ነገሮች የተነሳ አሁንም የበደለኝነት ስሜት ይደቁሰን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3) ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ ከኃጢአት ዝንባሌዎች ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። አንተስ ልብህ እየኮነነህ ይሆን? ከሆነ አይዞህ፤ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር ታግለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስላሉበት ድክመቶች ሲያስብ ስሜቱ ተደቁሶ ነበር። (ሮም 7:24) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ተጠምቋል። ያም ቢሆን ስለ ራሱ ሲናገር “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” እንዲሁም “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” ብሏል።—1 ቆሮ. 15:9፤ 1 ጢሞ. 1:15፤ w24.03 27 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14
የይሖዋን ቤት [ተዉ]።—2 ዜና 24:18
ንጉሥ ኢዮዓስ ካደረገው መጥፎ ውሳኔ የምናገኘው አንዱ ትምህርት፣ ይሖዋን የሚወዱና እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ጓደኞችን መምረጥ እንዳለብን ነው። እንዲህ ያሉ ጓደኞች በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። ጓደኛ የምናደርገው የግድ እኩዮቻችንን መሆን የለበትም። ኢዮዓስ ከጓደኛው ከዮዳሄ በዕድሜ በጣም ያንስ እንደነበር አስታውስ። ጓደኛ አድርገህ ከምትመርጣቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት እንዳጠናክር ይረዱኛል? በአምላክ መሥፈርቶች እንድመራ ያበረታቱኛል? ስለ ይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ያወራሉ? ለአምላክ መሥፈርቶች አክብሮት ያሳያሉ? የሚነግሩኝ መስማት የምፈልገውን ነገር ብቻ ነው ወይስ ትክክል ያልሆነ ነገር ሳደርግ በድፍረት እርማት ይሰጡኛል?’ (ምሳሌ 27:5, 6, 17) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጓደኞችህ ይሖዋን የማይወዱ ከሆነ ለአንተም አይበጁህም። ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ካሉህ ግን አጥብቀህ ያዛቸው፤ ይጠቅሙሃል!—ምሳሌ 13:20፤ w23.09 9 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ጥቅምት 15
እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ።—ራእይ 1:8
“አልፋ” የግሪክኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ፊደል፣ “ኦሜጋ” ደግሞ የመጨረሻው ፊደል ነው። ይሖዋ “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” ማለቱ አንድ ነገር ከጀመረ በተሳካ ሁኔታ ዳር እንደሚያደርሰው ያመለክታል። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው። (ዘፍ. 1:28) በዚህ ወቅት ይሖዋ “አልፋ” እንዳለ ሊቆጠር ይችላል። ፍጹምና ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ምድርን የሚሞሉበትና ገነት የሚያደርጉበት ጊዜ እንደሚመጣ በግልጽ ተናግሯል። ወደፊት ይህ ዓላማው ሲፈጸም ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ “ኦሜጋ” ይላል። ይሖዋ “ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ነገር ሁሉ” የመፍጠሩን ሥራ ሲያጠናቅቅ አንድ ዋስትና ሰጥቷል። ለሰዎችና ለምድር ያወጣው ዓላማ በእርግጥ እንደሚፈጸም ዋስትና ሰጠ። በሰባተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ዓላማው ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።—ዘፍ. 2:1-3፤ w23.11 5 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ጥቅምት 16
የይሖዋን መንገድ ጥረጉ! በበረሃ ለአምላካችን አውራ ጎዳናውን አቅኑ።—ኢሳ. 40:3
ከባቢሎን ወደ እስራኤል የሚወስደው መንገድ አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ አራት ወር ገደማ ይወስዳል። ሆኖም ይሖዋ ወደዚያ እንዳይመለሱ ሊያግዳቸው የሚችለውን ማንኛውንም እንቅፋት እንደሚያስወግድላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። በታማኞቹ አይሁዳውያን ዓይን ወደ እስራኤል መመለስ የሚያስገኘው ጥቅም ከሚከፍሉት ከማንኛውም መሥዋዕት እጅግ የላቀ ነው። የሚያገኙት ትልቁ በረከት ከአምልኳቸው ጋር የተያያዘ ነው። በባቢሎን የይሖዋ መቅደስ አልነበረም። እስራኤላውያን በሙሴ ሕግ መሠረት የሚጠበቅባቸውን መሥዋዕት ማቅረብ የሚችሉበት መሠዊያ አልነበረም፤ እንዲሁም እነዚህን መሥዋዕቶች የሚያቀርብ የተደራጀ የክህነት ሥርዓት አልነበረም። በተጨማሪም በዚያ የነበሩት ጣዖት አምላኪዎች ቁጥር ከይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር በእጅጉ ይበልጣል፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ለይሖዋም ሆነ ለመሥፈርቶቹ አክብሮት አልነበራቸውም። በመሆኑም ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ንጹሕ አምልኮን መልሰው ለማቋቋም ጓጉተው ነበር። w23.05 14-15 አን. 3-4
ዓርብ፣ ጥቅምት 17
የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:8
‘ከብርሃን ልጆች’ የሚጠበቀውን ምግባር እያሳየን ለመኖር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ሥነ ምግባር በጎደለው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው። (1 ተሰ. 4:3-5, 7, 8) መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ ፍልስፍናዎችንና አመለካከቶችን ጨምሮ የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን በምናደርገው ትግል ያግዘናል። “ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት [እና] ጽድቅ” እንድናፈራም ይረዳናል። (ኤፌ. 5:9) መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ ነው። ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን [እንደሚሰጣቸው]” ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:13) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ስናወድስም መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን። (ኤፌ. 5:19, 20) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ይረዳናል። w24.03 23-24 አን. 13-15
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 18
ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።—ሉቃስ 11:9
ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን ትፈልጋለህ? ከሆነ ጸልይ። ትዕግሥት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። (ገላ. 5:22, 23) በመሆኑም ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን እንዲሁም የመንፈስ ፍሬ ለማፍራት እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን። ትዕግሥታችንን የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን ትዕግሥተኛ ለመሆን የሚረዳንን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን ‘ደጋግመን እንለምነዋለን።’ (ሉቃስ 11:13) በተጨማሪም ይሖዋ ሁኔታውን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። ከጸለይን በኋላ ደግሞ በየዕለቱ ትዕግሥተኛ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። ትዕግሥት ለማዳበር በጸለይን እንዲሁም ትዕግሥተኛ ለመሆን ጥረት ባደረግን መጠን ይህ ባሕርይ በልባችን ውስጥ ይበልጥ ሥር በመስደድ የማንነታችን ክፍል እየሆነ ይሄዳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንም ይጠቅመናል። መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት ያሳዩ በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን ትዕግሥት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች ለማወቅ ይረዳናል። w23.08 22-23 አን. 10-11
እሁድ፣ ጥቅምት 19
መረቦቻችሁን ጥላችሁ አጥምዱ።—ሉቃስ 5:4
ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ እንደሚደግፈው አረጋግጦለታል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በድጋሚ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲያጠምዱ አድርጓቸዋል። (ዮሐ. 21:4-6) ይህ ተአምር፣ ጴጥሮስ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ሁሉ ይሖዋ በቀላሉ ሊሰጠው እንደሚችል አረጋግጦለት እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ‘ከሁሉ አስቀድመው መንግሥቱን ለሚፈልጉ’ ሁሉ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታውሶ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 6:33) በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ ዓሣ ከማጥመድ ሥራው ይልቅ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ መስጠት ጀመረ። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በድፍረት ምሥክርነት በመስጠት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ረድቷል። (ሥራ 2:14, 37-41) በኋላ ደግሞ ሳምራውያንና አሕዛብ ክርስቶስን እንዲቀበሉ ረድቷል። (ሥራ 8:14-17፤ 10:44-48) በእርግጥም ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ጉባኤው ለማምጣት ጴጥሮስን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። w23.09 20 አን. 1፤ 23 አን. 11
ሰኞ፣ ጥቅምት 20
ሕልሙን ከነትርጉሙ የማታሳውቁኝ ከሆነ ሰውነታችሁ ይቆራረጣል።—ዳን. 2:5
ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ካጠፉ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር አንድን ግዙፍ ምስል የሚያሳይ አስፈሪ ሕልም ተመለከተ። ሕልሙን ከነትርጉሙ ካልነገሩት ዳንኤልን ጨምሮ ሁሉንም ጠቢባን እንደሚገድል ዛተ። (ዳን. 2:3-5) ዳንኤል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አለዚያ ብዙዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። ስለዚህ “ወደ ንጉሡ ገብቶ የሕልሙን ትርጉም ለእሱ የሚያስታውቅበት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።” (ዳን. 2:16) ይህን ለማድረግ ድፍረትና እምነት ጠይቆበታል። ምክንያቱም ዳንኤል ከዚያ በፊት ሕልም እንደተረጎመ የሚገልጽ ዘገባ የለም። ዳንኤል፣ ጓደኞቹን “የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያሳያቸውና ሚስጥሩን እንዲገልጥላቸው ይጸልዩ ዘንድ ነገራቸው።” (ዳን. 2:18) ይሖዋ ጸሎታቸውን መልሶላቸዋል። ዳንኤል በአምላክ እርዳታ የናቡከደነጾርን ሕልም ተረጎመለት። የዳንኤልና የጓደኞቹ ሕይወትም ተረፈ። w23.08 3 አን. 4
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 21
እስከ መጨረሻው የጸና . . . ይድናል።—ማቴ. 24:13
ትዕግሥት ማሳየት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አስብ። ትዕግሥተኛ ከሆንን ይበልጥ ደስተኛና የተረጋጋን ሰዎች እንሆናለን። በመሆኑም ትዕግሥት አእምሯዊና አካላዊ ጤንነታችንን ሊያሻሽለው ይችላል። ሌሎችን በትዕግሥት የምንይዝ ከሆነ ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል። ጉባኤያችን ይበልጥ አንድነት ያለው ይሆናል። አንድ ሰው ቢያበሳጨን ለቁጣ የዘገየን መሆናችን ሁኔታው እንዳይባባስ ያደርጋል። (መዝ. 37:8 ግርጌ፤ ምሳሌ 14:29) ከሁሉ በላይ ደግሞ የሰማዩን አባታችንን ለመምሰልና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳናል። በእርግጥም ትዕግሥት በጣም ማራኪና ጠቃሚ ባሕርይ ነው! መታገሥ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆንልን ቢችልም በይሖዋ እርዳታ ይህን ባሕርይ ማዳበራችንን መቀጠል እንችላለን። በተጨማሪም አዲሱን ዓለም በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ወቅት “የይሖዋ ዓይን የሚፈሩትን፣ ደግሞም ታማኝ ፍቅሩን የሚጠባበቁትን በትኩረት” እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 33:18) እንግዲያው ሁላችንም ትዕግሥትን መልበሳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። w23.08 22 አን. 7፤ 25 አን. 16-17
ረቡዕ፣ ጥቅምት 22
በሥራ ያልተደገፈ እምነትም በራሱ የሞተ ነው።—ያዕ. 2:17
ያዕቆብ እንደገለጸው አንድ ሰው እምነት አለኝ ሊል ይችላል፤ ሆኖም ሥራው በእርግጥ ይህን ያሳያል? (ያዕ. 2:1-5, 9) በተጨማሪም ያዕቆብ፣ ‘አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ልብስ ወይም ምግብ እንደተቸገሩ’ አይቶ ምንም እርምጃ ስላልወሰደ ሰው ተናግሯል። እንዲህ ያለው ሰው እምነት አለኝ ቢልም እንኳ እምነቱ በሥራ አልተደገፈም፤ ስለዚህ እምነቱ ምንም ዋጋ የለውም። (ያዕ. 2:14-16) ያዕቆብ በሥራ የተደገፈ እምነት በማሳየት ረገድ ረዓብ ጥሩ ምሳሌ እንደሆነች ገልጿል። (ያዕ. 2:25, 26) ረዓብ ስለ ይሖዋ ሰምታለች፤ እሱ እስራኤላውያንን እየረዳቸው እንደሆነም ተገንዝባለች። (ኢያሱ 2:9-11) ከዚያም አደጋ ላይ የነበሩትን ሁለቱን እስራኤላውያን ሰላዮች በመታደግ እምነቷን በሥራ አሳየች። በዚህም የተነሳ፣ እስራኤላዊ ያልሆነችው ይህች ፍጽምና የጎደላት ሴት ልክ እንደ አብርሃም ጻድቅ ሆና መቆጠር ችላለች። እሷ የተወችው ምሳሌ እምነታችንን በሥራ መደገፍ ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። w23.12 5-6 አን. 12-13
ሐሙስ፣ ጥቅምት 23
ሥር እንድትሰዱና በመሠረቱ ላይ እንድትታነጹ ያስችላችሁ።—ኤፌ. 3:17
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስን ላይ ላዩን በመረዳት ብቻ ረክተን አንቀመጥም። በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” ጭምር መመርመር እንፈልጋለን። (1 ቆሮ. 2:9, 10) ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ሊረዳህ የሚችል የግል ጥናት ፕሮጀክት ለምን አትጀምርም? ለምሳሌ ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩ አገልጋዮቹ ፍቅር ያሳያቸው እንዴት እንደሆነ ልትመረምር ትችላለህ፤ ከዚያም እነዚህ ታሪኮች ይሖዋ አንተንም እንደሚወድህ የሚያረጋግጡት እንዴት እንደሆነ ቆም ብለህ አስብ። አሊያም በጥንቷ እስራኤል የይሖዋ አምልኮ ይከናወን የነበረው እንዴት እንደሆነ ከመረመርክ በኋላ ይህን ዝግጅት በአሁኑ ጊዜ ካለው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር ለማወዳደር ሞክር። ወይም ደግሞ ከኢየሱስ ምድራዊ ሕይወትና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ስላገኙ ትንቢቶች ጥልቀት ያለው ጥናት ልታደርግ ትችላለህ። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮችን ተጠቅመህ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ምርምር በማድረግ ታላቅ ደስታ ማግኘት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናትህ እምነትህን ሊያጠናክረውና ‘ስለ አምላክ እውቀት እንድትቀስም’ ሊረዳህ ይችላል።—ምሳሌ 2:4, 5፤ w23.10 18-19 አን. 3-5
ዓርብ፣ ጥቅምት 24
ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።—1 ጴጥ. 4:8
ሐዋርያው ጴጥሮስ የተጠቀመበት “የጠለቀ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “የተለጠጠ” የሚል ነው። የጥቅሱ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ የጠለቀ ፍቅር የሚያስገኘውን ውጤት ይገልጻል። የወንድሞቻችንን ኃጢአት ይሸፍናል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ፍቅራችንን በሁለት እጃችን እንደያዝነው የሚለጠጥ ጨርቅ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን። ፍቅራችን አንድ ወይም ሁለት ኃጢአቶችን ብቻ ሳይሆን ‘ብዙ ኃጢአቶችን’ እስኪሸፍን ድረስ እንለጥጠዋለን ማለት ነው። ‘መሸፈን’ የሚለው ቃል ይቅር ማለትን የሚያመለክት ጥሩ ዘይቤያዊ አገላለጽ ነው። አንድ ጨርቅ ቆሻሻን እንደሚሸፍን ሁሉ ፍቅርም የሌሎችን ድክመትና አለፍጽምና ይሸፍናል። በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር የእምነት አጋሮቻችንን አለፍጽምና ይቅር ለማለት የሚያስችል ጠንካራ ፍቅር ሊኖረን ይገባል። (ቆላ. 3:13) ሌሎችን ይቅር ካልን ፍቅራችን ጠንካራ እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋን ማስደሰት እንደምንፈልግ እናሳያለን። w23.11 11-12 አን. 13-15
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 25
ሳፋን መጽሐፉን በንጉሡ ፊት ማንበብ ጀመረ።—2 ዜና 34:18
ንጉሥ ኢዮስያስ አዋቂ ከሆነ በኋላ ቤተ መቅደሱን ማደስ ጀመረ። በእድሳቱ ወቅት ‘በሙሴ በኩል የተሰጠው የይሖዋ ሕግ መጽሐፍ’ ተገኘ። ንጉሡ የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ ከሰማ በኋላ የሰማውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃ ወሰደ። (2 ዜና 34:14, 19-21) አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ማንበብ ትፈልጋለህ? አሁንም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ እየሞከርክ ከሆነ ደግሞ ንባብህ እንዴት እየሄደልህ ነው? ለግል ሕይወትህ የሚጠቅሙህን ጥቅሶች ለማስታወስ ትሞክራለህ? ኢዮስያስ 39 ዓመት ገደማ ሲሆነው የሠራው ስህተት ሕይወቱን አሳጥቶታል። የይሖዋን አመራር ከመጠየቅ ይልቅ በራሱ ታመነ። (2 ዜና 35:20-25) እኛም ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለ። ዕድሜያችን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋን መፈለጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። ይህም የእሱን አመራር ለማግኘት አዘውትሮ መጸለይን፣ ቃሉን ማጥናትን እንዲሁም የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጡንን ምክር መቀበልን ይጨምራል። እንዲህ ካደረግን ትላልቅ ስህተቶችን የመሥራታችን አጋጣሚ ይቀንሳል፤ ደስተኛ የመሆናችን አጋጣሚ ደግሞ ይጨምራል።—ያዕ. 1:25፤ w23.09 12 አን. 15-16
እሁድ፣ ጥቅምት 26
አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።—ያዕ. 4:6
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ይወዱና ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ሴቶችን ታሪክ ይዟል። እነዚህ ሴቶች “በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች” ነበሩ። (1 ጢሞ. 3:11) በተጨማሪም እህቶች አርዓያ ሊሆኗቸው የሚችሉ ጎልማሳ ክርስቲያን ሴቶችን በጉባኤያቸው ውስጥ ማግኘት ይችላሉ። ወጣት እህቶች፣ ልትኮርጇቸው የምትችሏቸውን አንዳንድ የጎለመሱ እህቶች ለማሰብ ለምን አትሞክሩም? ያሏቸውን ማራኪ ባሕርያት አስተውሉ። ከዚያም እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ አስቡ። ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ባሕርያት አንዱ ትሕትና ነው። አንዲት ሴት ትሑት ከሆነች ከይሖዋም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖራታል። ለምሳሌ ይሖዋን የምትወድ ሴት የሰማዩ አባቷ ያቋቋመውን የራስነት ሥርዓት በትሕትና ትደግፋለች። (1 ቆሮ. 11:3) የራስነት ሥርዓት በጉባኤም ሆነ በቤተሰብ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ይሠራል። w23.12 18-19 አን. 3-5
ሰኞ፣ ጥቅምት 27
ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል።—ኤፌ. 5:28
ይሖዋ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲወዱ እንዲሁም አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉላቸው ይጠብቅባቸዋል። የማመዛዘን ችሎታ ማዳበራችሁ፣ ሴቶችን በአክብሮት መያዛችሁ እንዲሁም እምነት የሚጣልባችሁ መሆናችሁ ትዳር ስትመሠርቱ ይረዳችኋል። ትዳር ከመሠረታችሁ በኋላ ልጆች ትወልዱ ይሆናል። ጥሩ አባት መሆን የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ከይሖዋ ምን ትማራላችሁ? (ኤፌ. 6:4) ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን እንደሚወደውና እንደሚደሰትበት በይፋ ነግሮታል። (ማቴ. 3:17) ልጆች ከወለዳችሁ፣ ለልጆቻችሁ አዘውትራችሁ ፍቅራችሁን ግለጹላቸው። ላከናወኗቸው መልካም ነገሮች አመስግኗቸው። የይሖዋን ምሳሌ የሚከተሉ አባቶች ልጆቻቸው እድገት አድርገው የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ይረዷቸዋል። የቤተሰባችሁን አባላትና የጉባኤያችሁን ወንድሞችና እህቶች በፍቅር በመንከባከብ እንዲሁም ለእነሱ ያላችሁን ፍቅርና አድናቆት የመግለጽ ልማድ በማዳበር ለዚህ ኃላፊነት ከአሁኑ መዘጋጀት ትችላላችሁ።—ዮሐ. 15:9፤ w23.12 28-29 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 28
‘ይሖዋ አጽንቶ ያቆማችኋል።’—1 ጴጥ. 5:10
ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ብንሆንም እንኳ በሰው ሁሉ ላይ የሚደርሰው መከራና ሕመም ይደርስብናል። ከዚህም ሌላ፣ የአምላክን ሕዝቦች የሚጠሉ ሰዎች ተቃውሞ ወይም ስደት ያደርሱብን ይሆናል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይደርሱብን ባይከላከልልንም እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 41:10) በእሱ እርዳታ ደስታችንን መጠበቅ፣ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ እንዲሁም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም እንኳ ለእሱ ታማኝ ሆነን መቀጠል እንችላለን። ይሖዋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ሰላም” በማለት የሚጠራውን ሰላም እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) እንዲህ ያለው ሰላም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመመሥረት የሚመነጭ አእምሯዊና ልባዊ መረጋጋትን ያመለክታል። ይህ ሰላም “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” ነው፤ ልናስብ ከምንችለው በላይ አስደናቂ ነገር ነው። ወደ ይሖዋ አጥብቀህ ከጸለይክ በኋላ ለመግለጽ የሚከብድ ዓይነት የመረጋጋት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? “የአምላክ ሰላም” ማለት ይህ ነው። w24.01 20 አን. 2፤ 21 አን. 4
ረቡዕ፣ ጥቅምት 29
ይሖዋን ላወድስ፤ ሁለንተናዬ ቅዱስ ስሙን ያወድስ።—መዝ. 103:1
የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ለእሱ ያላቸው ፍቅር ስሙን በሙሉ ልባቸው እንዲያወድሱት ያነሳሳቸዋል። ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ስም ማወደስ ይሖዋን ራሱን ማወደስ እንደሆነ ተገንዝቧል። የይሖዋ ስም ማንነቱን ማለትም ያሉትን ግሩም ባሕርያትና ያከናወናቸውን አስደናቂ ሥራዎች ያካትታል። ዳዊት የአባቱን ስም እንደ ቅዱስ ለመመልከትና ለማወደስ ተነሳስቷል። ይህን ማድረግ የፈለገው ደግሞ ‘በሁለንተናው’ ማለትም በሙሉ ልቡ ነው። በተመሳሳይም ሌዋውያን ግንባር ቀደም ሆነው ይሖዋን አወድሰዋል። የይሖዋ ቅዱስ ስም የሚገባውን ውዳሴ በቃላት ሊገልጹት እንደማይችሉ በትሕትና ተናግረዋል። (ነህ. 9:5) ይሖዋ እንዲህ ባለው ትሕትና የተንጸባረቀበት ልባዊ ውዳሴ እንደተደሰተ ምንም ጥያቄ የለውም። w24.02 9 አን. 6
ሐሙስ፣ ጥቅምት 30
ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።—ፊልጵ. 3:16
ከአቅምህ በላይ የሆነ ግብ ላይ መድረስ ስላቃተህ ይሖዋ አያዝንብህም። (2 ቆሮ. 8:12) ካጋጠመህ እንቅፋት ትምህርት ውሰድ። እስካሁን የደረስክባቸውን ግቦች አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ሥራችሁን በመርሳት ፍትሕ አያዛባም’ ይላል። (ዕብ. 6:10) አንተም ብትሆን ልትረሳ አይገባም። ከዚህ ቀደም ስላከናወንካቸው ነገሮች አስብ። ለምሳሌ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መሥርተሃል፤ ለሌሎች ስለ እሱ መናገር ጀምረሃል፤ እንዲሁም ተጠምቀሃል። እስካሁን ድረስ እድገት ማድረግና የተለያዩ መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ እንደቻልክ ሁሉ አሁንም እድገት ማድረግህን መቀጠልና ያወጣኸው ግብ ላይ መድረስ ትችላለህ። በይሖዋ እርዳታ ግብህ ላይ መድረስ ትችላለህ። መንፈሳዊ ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ እግረ መንገድህን የይሖዋን በረከትና እርዳታ በማስተዋል ደስታ ማግኘት ትችላለህ። (2 ቆሮ. 4:7) ተስፋ ካልቆረጥክ ተጨማሪ በረከቶችንም ታገኛለህ።—ገላ. 6:9፤ w23.05 31 አን. 16-18
ዓርብ፣ ጥቅምት 31
እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝና የአምላክ ተወካይ ሆኜ እንደመጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል።—ዮሐ. 16:27
ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸውና እንደሚደሰትባቸው መግለጽ ያስደስተዋል። ለምሳሌ ይሖዋ፣ ኢየሱስን የሚወደውና የሚደሰትበት ልጁ እንደሆነ የገለጸባቸው ሁለት አጋጣሚዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተዘግበዋል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5) አንተስ ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ሲነግርህ መስማት ትፈልጋለህ? ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ አያናግረንም። በቃሉ አማካኝነት ግን ያናግረናል። ኢየሱስ በወንጌል ዘገባዎች ላይ የተናገረውን ስናነብ ይሖዋ እንደሚደሰትብን ሲናገር የምንሰማ ያህል ነው። ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በመሆኑም ኢየሱስ ፍጹማን ባይሆኑም ታማኝ የሆኑ ተከታዮቹን እንደሚወዳቸው የተናገረባቸውን ዘገባዎች ስናነብ ይሖዋ ለእኛ እነዚህን ቃላት እንደተናገረ አድርገን ማሰብ እንችላለን። (ዮሐ. 15:9, 15) መከራ ከደረሰብን የአምላክን ሞገስ አጥተናል ማለት አይደለም። እንዲያውም መከራዎች ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደውና እንደምንተማመንበት ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጡናል።—ያዕ. 1:12፤ w24.03 28 አን. 10-11