ሐሙስ፣ ሐምሌ 31
በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።—ኤፌ. 5:10
ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ስናደርግ “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ማስተዋልና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:17) ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ስንፈልግ አምላክ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት እያደረግን ነው። ከዚያም የእሱን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን። “ክፉው” የተባለው ጠላታችን ሰይጣን በዚህ ዓለም ጉዳዮች ከመጠመዳችን የተነሳ ለአምላክ አገልግሎት ጊዜ እንድናጣ ማድረግ ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 5:19) አንድ ክርስቲያን ካልተጠነቀቀ አምላክን ለማገልገል ከሚያስችሉት አጋጣሚዎች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች፣ ለትምህርት ወይም ለሙያው ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮበታል ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት እንዳልሆኑ አይካድም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ ሊይዙ አይገባም። w24.03 24 አን. 16-17
ዓርብ፣ ነሐሴ 1
የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።—መዝ. 34:19
በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ልብ በል። (1) ጻድቅ የሆኑ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። (2) ይሖዋ ከሚያጋጥመን መከራ ይታደገናል። ይሖዋ የሚታደገን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለንን ሕይወት በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን በመርዳት ነው። ይሖዋ እሱን በማገልገል ደስታ እንደምናገኝ ቃል ቢገባልንም በአሁኑ ዘመን ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምንመራ ዋስትና አልሰጠንም። (ኢሳ. 66:14) እሱ እንድንኖር የሚፈልገውን ሕይወት ለዘላለም በምናጣጥምበት በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) እስከዚያው ግን ለእያንዳንዱ ቀን የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። (ሰቆ. 3:22-24) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ በዘመናችን የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሁላችንም ያልተጠበቁ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ ከታመንን እሱ ምንጊዜም ይደግፈናል።—መዝ. 55:22፤ w23.04 14-15 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2
ለበላይ ባለሥልጣናት [ተገዙ]።—ሮም 13:1
አመቺ ባልሆነ ጊዜ ጭምር ለበላይ ባለሥልጣናት በመታዘዝ ረገድ ከዮሴፍና ከማርያም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 2:1-6) ማርያም የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሳለች እሷና ዮሴፍ የታዛዥነት ፈተና አጋጠማቸው። የሮም ገዢ የሆነው አውግስጦስ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዘዘ። ማርያምና ዮሴፍ ዳገት ቁልቁለት አቋርጠው 150 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ቤተልሔም መሄድ ነበረባቸው። ይህ ጉዞ በተለይ ለማርያም የሚያንገላታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የማርያምና የፅንሱ ደህንነት አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል። መንገድ ላይ ሳለች ምጧ ቢመጣስ? በማህፀኗ የተሸከመችው ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ነው። እነዚህ ነገሮች መንግሥትን ላለመታዘዝ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ? ዮሴፍና ማርያም እነዚህ ምክንያቶች የመንግሥትን ሕግ ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲሉ እንዲያደርጓቸው አልፈቀዱም። ይሖዋም ለታዛዥነታቸው ባርኳቸዋል። ማርያም ወደ ቤተልሔም በሰላም ደረሰች። በዚያም ጤናማ ልጅ ተገላገለች። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጋለች።—ሚክ. 5:2፤ w23.10 8 አን. 9፤ 9 አን. 11-12