16 የእውነተኛውን አምላክ ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አስቀመጡት፤+ ከዚያም የሚቃጠሉ መባዎችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን በእውነተኛው አምላክ ፊት አቀረቡ።+ 2 ዳዊት የሚቃጠሉትን መባዎችና+ የኅብረት መሥዋዕቶቹን+ አቅርቦ ሲጨርስ ሕዝቡን በይሖዋ ስም ባረከ። 3 በተጨማሪም ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት አንድ ዳቦ፣ አንድ የቴምር ጥፍጥፍና አንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ።