-
ማርቆስ 5:25-34አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
25 በዚያም፣ ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት+ የኖረች አንዲት ሴት ነበረች።+ 26 ይህች ሴት በርካታ ሐኪሞች ጋር የሄደች ሲሆን ሕክምናው ለብዙ ሥቃይ ዳርጓት ነበር፤ ያላትን ጥሪት ሁሉ ብትጨርስም ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም። 27 ስለ ኢየሱስ የተወራውን በሰማች ጊዜ በሰዎች መካከል ከኋላው መጥታ ልብሱን ነካች፤+ 28 ምክንያቱም “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ነበር።+ 29 ወዲያውም ይፈሳት የነበረው ደም ቆመ፤ ያሠቃያት ከነበረው ሕመም እንደተፈወሰችም ታወቃት።
30 ወዲያውኑ ኢየሱስ ኃይል ከእሱ እንደወጣ ታወቀው፤+ በመሆኑም ወደ ሕዝቡ በመዞር “ልብሴን የነካው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።+ 31 ደቀ መዛሙርቱ ግን “ሕዝቡ እንዲህ ሲጋፋህ እያየህ ‘የነካኝ ማን ነው?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። 32 ይሁንና ኢየሱስ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። 33 ሴትየዋ በእሷ ላይ የተፈጸመውን ነገር ስላወቀች በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ምንም ሳታስቀር እውነቱን ነገረችው። 34 እሱም “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤+ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” አላት።+
-
-
ሉቃስ 8:43-48አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
43 በዚያም፣ ለ12 ዓመት ደም ሲፈስሳት+ የኖረች አንዲት ሴት የነበረች ሲሆን ይህችን ሴት ሊፈውሳት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።+ 44 ከኋላም መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤+ ይፈሳት የነበረውም ደም ወዲያውኑ ቆመ። 45 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፣ ጴጥሮስ “መምህር፣ ሕዝቡ ከቦህ እየተጋፋህ ነው የሚሄደው” አለው።+ 46 ኢየሱስ ግን “ኃይል+ ከእኔ እንደወጣ ስለታወቀኝ አንድ ሰው ነክቶኛል” አለ። 47 ሴትየዋም ሳይታወቅባት መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ለምን እንደነካችውና እንዴት ወዲያውኑ እንደተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። 48 እሱ ግን “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ” አላት።+
-