-
ማቴዎስ 12:24-30አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
24 ፈሪሳውያን ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል* ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” አሉ።+ 25 ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም። 26 በተመሳሳይም ሰይጣን ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ታዲያ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? 27 በተጨማሪም እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ* የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው? ልጆቻችሁ ፈራጆች የሚሆኑባችሁ* ለዚህ ነው። 28 ሆኖም አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ መንፈስ ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው።+ 29 ደግሞስ አንድ ሰው በቅድሚያ ሰውየውን ሳያስር ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት ገብቶ እንዴት ንብረቱን ሊወስድ ይችላል? ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። 30 ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ሁሉ ይበትናል።+
-
-
ማርቆስ 3:22-27አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
22 ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም “ብዔልዜቡል* አለበት፤ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” ይሉ ነበር።+ 23 በመሆኑም ወደ እሱ ከጠራቸው በኋላ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ሊያስወጣ ይችላል? 24 አንድ መንግሥት እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ያ መንግሥት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፤+ 25 አንድ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ጸንቶ ሊቆም አይችልም። 26 በተመሳሳይም ሰይጣን በራሱ ላይ የሚነሳና የሚከፋፈል ከሆነ ያከትምለታል እንጂ ሊጸና አይችልም። 27 ደግሞም ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት የገባ ሰው በቅድሚያ ብርቱውን ሰው ሳያስር ንብረቱን ሊሰርቅ አይችልም። ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው።
-