-
ማቴዎስ 22:15-22አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
15 ከዚያም ፈሪሳውያን ሄደው በንግግሩ ሊያጠምዱት ሴራ ጠነሰሱ።+ 16 ስለዚህ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች+ ጋር ወደ እሱ በመላክ እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር እንዲሁም ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ እናውቃለን። 17 እስቲ ንገረን፣ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”* 18 ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? 19 እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ።” እነሱም አንድ ዲናር* አመጡለት። 20 እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። 21 እነሱም “የቄሳር” አሉ። እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው።+ 22 ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ከዚያም ትተውት ሄዱ።
-
-
ማርቆስ 12:13-17አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
13 ከዚያም በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው አንዳንድ ፈሪሳውያንን እና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ወደ እሱ ላኩ።+ 14 እነሱም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?* 15 እንክፈል ወይስ አንክፈል?” እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር* አምጡና አሳዩኝ” አላቸው። 16 እነሱም አመጡለት፤ እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉት። 17 ከዚያም ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣+ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ+ ስጡ” አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ።
-