ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ
ከብሪታንያ የንቁ! መጽሔት አጠናቃሪ
‘ግቤ’ ይላል የፊሊፕንስ ተወላጅ የሆነው ጁልያን ‘45 ዓመት ዕድሜ ላይ ስደርስ ሚልየነር ለመሆን ነበር።’ የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ የሆነችው ካረል ደግሞ “ሁለመናዬ ሀብታም በመሆን ምኞት ተውጦ ነበር” ብላለች።
እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች ሚልየነር መሆንን የሕልም እንጀራ ሆኖባቸው ባይፈልጉትም በሕይወታቸው ለመደሰትና የሚፈልጉትን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችላቸውን በቂ ንብረትና ገንዘብ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ኪቺሳቡሮ የተባለው ጃፓናዊ ነጋዴ ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ነበረው። “እነዚህ ነገሮች ደስታ ያስገኙልኛል ብዬ አስብ ነበር” ብሏል።
ካናዳዊዋ ሊዝም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ነበራት። “ወጣት ሳለሁ ገንዘብ ማንኛውንም ጭንቀት የሚያጠፋ ይመስለኝ ነበር” በማለት ትተርካለች። ባለቤትዋ ቶምም ገንዘብ “ከማንኛውም ችግር የሚያወጣኝ . . . ወንጀል፣ የአካባቢ መበከል፣ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች በሌሉበት ሊያኖረኝ የሚችል ይመስለኝ ነበር” ብሏል።
ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ
በታሪክ ዘመናት በሙሉ ሀብት ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወሩ ኖረዋል። ቅኝ ገዥነት ተስፋፍቶ በነበረበት ዘመን የብሪታንያ ነጋዴዎች እንደ አፍሪካ ያሉትን አህጉሮች የማዕድን ሀብት በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ሲሉ አሳሾችን ተከትለው ይጓዙ ነበር። የቅኝ አገዛዝ ካከተመ ወዲህ ደግሞ በተለይ የኢኮኖሚ ችግር በተስፋፋበት በአሁኑ ዘመን የጋራ ንብረት አገሮች ዜጎች በተቃራኒው አቅጣጫ በመጓዝ ሀብታም ለመሆን ፈልገው ባይሆንም ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ወደ ብሪታንያ ይፈልሳሉ።
በሺህ የሚቆጠሩ የፊልፒንስ ወንዶችና ሴቶች ሥራ ለመፈለግ አገራቸውን ትተው ወደተለያዩ አገሮች ይሄዳሉ። ብዙዎቹም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ በሚገኙ አገሮችና በሌሎች አገሮች ሥራ ያገኛሉ። የሜክሲኮ፣ የመካከለኛውና የደቡብ አሜሪካ ተወላጆች የሆኑ ብዙ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ ሠርተን ገንዘብ እናገኛለን በሚል ተስፋ ወደ ሰሜን ይፈልሳሉ። ብዙ የአውሮፓ አገሮችም ከመካከለኛው ምሥራቅና ከሰሜን አፍሪካ የሚመጡ ሰዎችን ይቀበላሉ።
በጥር 1987 ታትሞ የወጣው ማን ፓወር ሪቪው የተባለው የደቡብ አፍሪካ መጽሔት እንዳለው በዚያች አገር እስከ ሰኔ 30, 1985 371,008 ይፋ እውቅና አግኝተው የተመዘገቡ የውጭ አገር ሠራተኞች ነበሩ። ይሁን እንጂ ሪፖርቱ አክሎ እንደገለጸው “የደቡብ አፍሪካን ሀብት ለመሻማት በሕገወጥ መንገድ ሾልከው የገቡ 1.5 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች እንዳሉ ይገመታል።”
በልጽገዋል በሚባሉት አገሮች እንኳን ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ከቦታ ወደ ቦታ ይዘዋወራሉ። በብሪታንያም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ብዙ ሰዎች መኖሪያቸውን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሆኖ ሳለ ወደ ደቡቡ የአገሪቱ ክፍል እየሄዱ ይሠራሉ። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በመካከለኛው ለንደን (በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል) “የወፍ ጎጆ የሚያክል” 61 ካሬ ጫማ ብቻ ስፋት ያለው ጠባብ የአፓርተማ ቤት በቅርቡ በ54,000 ዶላር [270,000 ብር] ተሽጧል። ይሁን እንጂ ይህን በሚያክል ገንዘብ ከለንደን 28 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ክልል ውስጥ ሦስት መኝታ ቤት ያለው መኖሪያ መግዛት ይቻላል።
ብራድፎርድ በምትባል በእንግሊዝ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኝ ከተማ ውስጥ 60,000 የሚያክሉ እስያውያን ይኖራሉ። ከእነዚህ የውጭ አገር ሰዎች ብዙዎቹ ወደዚህ የኢንዱስትሪ አካባቢ የመጡት በሱፍ ፋብሪካዎች ተቀጥረው ለመሥራት ነበር። ይሁን እንጂ በሰው ኃይል የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች በአውቶማቲክ መሣሪያዎች እየተተኩ በመሄዳቸው ምክንያት ሥራ አጥ የሆኑት ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚተዳደሩት ከመንግሥት በሚያገኙት ድጎማ ነው። በዚህ ምክንያት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች
በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮችም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ አስተማማኝ ሥራ እናገኛለን በሚል ተስፋ ይኖሩበት የነበረውን የገጠር አካባቢ ትተው ወደ ትላልቅ ከተሞች ይፈልሳሉ። እርግጥ ብዙዎቹ ሥራ ያገኛሉ። ይሁን እንጂ የሚያገኙት ገንዘብ ደስታ አስገኝቶላቸዋልን?
ሠራተኞቹ ከሚያገኟት አነስተኛ ገቢ አብዛኛውን ጊዜ በከተማ ዳርቻዎች ለሚገኙትና ተጨናንቀው ለተሠሩት ጠባብ ጎጆዎች ውድ ኪራይ መክፈል ይኖርባቸዋል። ከኪራዩ የተረፈው ገንዘብ ገጠር ለሚገኙት ችግረኛ ቤተሰቦቻቸው መላክ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ በየወሩ መጨረሻ ላይ ፖስታ ቤቶች ገጠር ለሚገኙ ዘመዶቻቸው ገንዘብ በሐዋላ በሚልኩ ሰዎች ይጨናነቃሉ።
ቤተሰቦች ሳይነጣጠሉ አንድ ላይ በከተሞች ውስጥ በሚኖሩበትም ጊዜ ቢሆን በከተሞች ውስጥ የሚያጋጥሙ ሌሎች የኢኮኖሚ ጭነቶች አሉ። ለመታከሚያ፣ ለምግብ፣ ለመጓጓዣ፣ ለትምህርት ቤትና ለመኖሪያ ገንዘብ ያስፈልጋል። ገንዘብ የሚወጣበት ምክንያት ማለቂያ ያለው አይመስልም። በዚህ ምክንያት ብዙ የከተማ ነዋሪዎች ሁለት ሥራ ለመሥራት ተገድደዋል።
ታዲያ እንዲህ ያለው ሁኔታ ደስታ ያስገኛል ብሎ ለማሰብ ይቻላልን? አይቻልም። ስለዚህ ወደ ሌላ ቦታ ብትሄድም ሆነ በተወለድክበት አካባቢ ብትኖር ገንዘብ በሕይወትህ ውስጥ ምን ሚና ይጫወታል? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል። ደስታ ለማግኘት ከፈለግህ የዚህን መልስ ማወቅ ያስፈልግሃል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ፍቅር ሰልችቶኛል። ግጥምም ይበልጥ ሰልችቶኛል። ገንዘብ ግን ምን ጊዜም ያስደስተኛል።”—ፋቲግ በሂለሪ ቤሎክ
በየትኛውም በምንኖርበት የዓለም ክፍል ገንዘብ አንደኛ ቦታ ይሰጠዋል። ብዙ ሀብታሞች ይታመኑበታል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ድሆች ይጎመጁታል። ይሁን እንጂ ወደ ደስታ የሚያስገባ የይለፍ ወረቀት ነውን? የሚከተሉት ርዕሶች መልሱን ይሰጡናል።