ዓለምን ስንመለከታት
ረጅም ዕድሜ የሚኖሩት ጃፓናውያን
የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ስታትስቲክስ መሠረት በምድር ላይ ካለው ከየትኛውም ሕዝብ የበለጠ ዕድሜ ያላቸው ጃፓናውያን ናቸው። የጃፓን ሴቶች የሕይወት ዘመን በአማካይ 82. 5 ዓመት ሲሆን የወንዶቹ ግን 76. 2 ዓመት ነው። ከሴቶች መካከል ረጅም ዕድሜ በመኖር የሁለተኛነትን ደረጃ የያዙት ፈረንሳውያን ሲሆኑ አማካይ የሕይወት ዘመናቸው 81. 5 ዓመት ነው፤ ፈረንሳይን በተቀራራቢ ቁጥር የምትከተለው ስዊዘርላንድ ናት፤ በዚህች አገር የሚኖሩት ሴቶች የሕይወት ዘመናቸው በአማካይ 81. 0 ዓመት ነው። በወንዶች የሁለተኛነትን ደረጃ የያዘችው አይስላንድ ስትሆን የወንዶቹ ዕድሜ በአማካይ 75.4 ዓመት ነው፤ 74. 3 ዓመት በማስመዝገብ ግሪክ ትከተላታለች። 350 ገጾች ያሉት ይህ ስታስቲካዊ የዓመት መጽሐፍ ትኩረትን የሚስቡ ሌሎች እውነታዎችንም ይዟል። በዓለም ውስጥ ብዙ ልጆች የሚወለዱባት አገር ሩዋንዳ ስትሆን እያንዳንዷ ሴት በአማካይ 8. 3 ልጆች አሏት። የራስን ሕይወት በራስ እጅ በማጥፋት ዝቅተኛው ቁጥር የተመዘገበው በባሃማስ ሲሆን ከእያንዳንዱ 100,000 ሕዝብ መካከል 1.3 ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ፤ ከ100,000 ሕዝብ መካከል 38. 2 የሚሆኑ ነዋሪዎቿ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉባት ሀንጋሪ የራስን ሕይወት በማጥፋት ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበባት አገር ሆናለች። አነስተኛ ነዋሪዎች ያሉባት በደቡብ አሜሪካ የምትገኘው አገር ሱሪናም በመኪና አደጋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አልቆባታል፤ ከእያንዳንዱ 100,000 ሕዝብ መካከል 33.5 ያህሉ በዚህ አደጋ ሕይወታቸው ያልፋል። አነስተኛው ቁጥር የተመዘገበው የት ነው? ማልታ በተባለችው አገር ውስጥ ሲሆን ከእያንዳንዱ 100,000 ሕዝብ መካከል 1.6 የሚሆኑት በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አልፏል።
ጥርስ ራሱን በራሱ ይጠግናልን?
ሥራውን ማከናወን እንዲችል በቂ ጊዜ ከተሰጠው ጥርስ የራሱን ቀላል ጥገና ያካሄዳል። ሺኬ ቴንቦ (የጥርስ ሕክምና ቡድኖች አመለካከት) በተባለ የጃፓን የሕክምና ጋዜጣ ላይ ይህን የገለጹት ፕሮፌሰር ታዳሺ ያማዳ ናቸው። መጠኑ አነሰም በዛ ስኳር ወደ አፍ ከገባ በኋላ በጥርስ ላይ የሚከማቸው ነገር ከ8 እስከ 20 ባሉት ደቂቃዎች ውስጥ ወደ አሲድነት ይለወጣል። የተከማቸው አሲድ የጥርስን ካልሺየም ያሟሟውና ያማዳ “ጥቃቅን ቀዳዳዎች” ብለው የጠሯቸውን የጥርስ መበስበስን የሚያመለክቱ ቀዳዳዎችን ያስከትላል። ሆኖም ያማዳ እንዳሉት ከሆነ የጠፋውን ካልሺየም በምራቅ ውስጥ ያለው ካልሺየም ቀስ በቀስ ይተካዋል፤ ስለዚህ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጥርሶቹ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ። በአብዛኛዎቹ ምግቦች ውስጥ ስኳር በተወሰነ መጠን ስለሚኖር ዘወትር በተለይም ደግሞ ከመኝታ በፊት ጥርስን መፋቅና ጥርስ የራሱን የጥገና ሥራ ለማከናወን በቂ ጊዜ ያገኝ ዘንድ በቁርስ፣ በምሣና፣ በእራት መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ምግብ መብላትን ማስወገድ እንደሚገባ በመግለጽ ያማዳ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
የተበከሉ እጆች
በቅርብ ጊዜ የወጣ አንድ ጥናት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የጤና እንክብካቤ ሠራተኞች በሽተኞቻቸውን ከመመርመራቸው በፊት እጃቸውን ለመታጠብ ቸልተኞች ናቸው ሲል ገልጿል። በተጨማሪም ዘ ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው “ዶክተሮች ጓንቶቻቸውን መቀየር በሚኖርባቸው ጊዜ የማይቀይሩ መሆናቸውን ሌሎች ጥናቶች ጠቁመዋል።” ይህ ችግር ለበሽታ መዛመት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ምንም ጥርጥር የለውም። ፖስት የተባለው ይኸው ጋዜጣ የዶክተሮችና የነርሶች ያልታጠቡ እጆች “ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሕሙማን ለመዳን በዓመት እስከ 10 ቢልዮን ዶላር የሚጠይቁ ተላላፊ በሽታዎችን ለምን እየሸመቱ እንደሚመጡ በቀላሉ መልስ ለማግኘት ሊረዱ ይችላሉ” ሲል ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን ያለውን መሠረት በማድረግ ዘግቧል።
ድሃ የሆኑ ልጆች በአሜሪካ
በዓለም ላይ ካሉት በጣም የበለጸጉ አገሮች አንዷ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስም ቤሳ ቤስቲን የሌላቸው የአንዳንድ ልጆች መኖሪያ ናት። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በዘገበው መሠረት ልጆችን ከአደጋ ለመጠበቅ ገንዘብ በሚያሰባስበው ድርጅት (ችልድረን ዲፌንስ ፈንድ) አማካኝነት የተካሄደው አንድ ጥናት የሚከተለው ውጤት ላይ ደርሷል:- “በ33 ክፍለ ሀገሮች ውስጥ በድህነት የሚኖሩት አሜሪካውያን ልጆች ቁጥር በ1980ዎቹ ዓመታት ከነበሩት በ1 ሚልዮን ጨምሯል።” በ1989 በአርካንሰስ፣ በሉዊዚያና፣ በኒው ሜክሲኮና በዌስት ቨርጂኒያ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ከ25 በመቶ በላይ የሚሆኑ ልጆች ከአገሪቷ የድህነት ጣራ በታች የሆነ ገቢ በነበራቸው ቤተሰቦች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ድሃ የሆኑ ልጆች ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበባት ሚሲሲፒ ስትሆን በግዛቷ ውስጥ ካሉት ልጆች መካከል 33.5 በመቶ የሚሆኑት በድህነት ተቆራምደው የሚኖሩ ናቸው።
የሳምባ ነቀርሳ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ
በተለይ በጣም አደገኛ የሆኑት የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መዛመታቸው የመንግሥት የጤና ባለሙያዎች በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል ብለው በይፋ እንዲናገሩ አስገድዷቸዋል። “በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የሳንባ ነቀርሳ የአሁኑን ያህል ከፍተኛ ጭንቀት ያስከተለበት ጊዜ የለም” ሲሉ በበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የሳንባ ነቀርሳ ኤክስፐርት የሆኑት ዶክተር ዳያክሴ ስኒደር ተናግረዋል፤ “ምክንያቱም በዚህች አገር ውስጥ የሳንባ ነቀርሳ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል።” ምንም እንኳን የሳንባ ነቀርሳ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት እስከነበሩት ጊዜያት ድረስ ብዙ በሽተኞችን በመግደል ተወዳዳሪ ያልነበረው በሽታ ሆኖ ቢቆይም ፀረ–ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ በማዋልና ከዚህም ጋር ጎን ለጎን የቤትንና የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ከ1984 ጀምሮ የበሽተኞች ቁጥር እንደጨመረና በሽታውን የሚያመጡት ህዋሳት በጣም በቅርብ ጊዜ የተሠሩትን መድኃኒቶች እንኳን እየተቋቋሟቸው መምጣታቸውን አብዛኛዎቹ ክፍለ ሀገሮች ሪፖርት አድርገዋል። በሽታው ከአንዱ ወደ ሌላው የሚዛመተው በሽተኛው በሚስልበት ጊዜ በአየር ላይ በሚበተኑት ጥቃቅን ጠብታ የመሰሉ ነገሮች አማካኝነት ነው። በበሽታው ለመያዝ ምክንያት የሚሆነው ሕዋስ ምንም በሽታ ሳያስከትል በጤነኛ ሰዎች ሰውነት ውስጥ ለዓመታት ሊቆይ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በመጀመሪያ የተያዘው ሰው ካልታከመ ብዙ ሰዎች በበሽታው ሊያዙ ይችላሉ።
ለወባ በሽታ እጃቸውን ሰጡ
“ያለንበት ወቅት የወባ በሽታን ድል ማድረግ ያልተቻለበት ጊዜ ነው” ሲል ሳይንስ የተባለው መጽሔት ገልጿል። የሕክምና ኢንስቲትዩት (ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜዲስን) ያወጣው አዲስ ሪፖርት እንደሚያሳየው በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ እድገት የተደረገ ቢሆንም ከዚያ ወዲህ ግን ሰዎች በሽታውን ለሚያስከትለው ጥገኛ ሕዋስ እጃቸውን እየሰጡ ነው። በ102 አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን እያጡ ነው፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ልጆች ናቸው። ችግሩን ያባባሰው በጥቅም ላይ የዋሉት ፀረ–ወባ መድኃኒቶች በመጠኑም ቢሆን ፍቱንነታቸውን ማጣታቸውና አዳዲስ ክትባቶችን ለመፍጠር የሚደረጉት ጥረቶች መክነው መቅረታቸው ነው። በበሽታው ምክንያት የሞቱ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበባቸው የአፍሪካ አገሮች ጦርነት የሚካሄድባቸው መሆኑም በሽታውን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል፤ የበለጸጉት አገሮችም ለወባ በሽታ ምርምር እንዲውል ከመደቡት ባጀት ላይ እየቀነሱ ነው።
ፀረ–ተባይ መድኃኒቶች ያስከተሉት መመረዝ
ኒው አፍሪካን የተባለው መጽሔት በዘገበው መሠረት ፀረ–ተባይ መድኃኒቶች በታዳጊ አገሮች በሙሉ በያመቱ ወደ 25 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎችን ይመርዛሉ፤ 20,000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ሳቢያ ሕይወታቸው ያልፋል። የኬሚካል ኩባንያዎች መድኃኒቶቹ የሚያስከትሉትን አደጋ የማያውቁ ገበሬዎች ወዳሉባቸውና መንግሥታት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ በቂ ቁጥጥር ወደማያደርጉባቸው ድሃ አገሮች አደገኛ የሆኑ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን ያስገባሉ። በቅርቡ አንድ የስዊዝ የኬሚካል ኩባንያ ዲዲቲ የተባለው ኬሚካል ያለበትን የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት የያዙ 476,000 ጣሳዎችን ለታንዛንያ መሸጡን አምኗል ሲል ኒው አፍሪካን ዘግቧል። ይህ ኬሚካል በ45 አገሮች ውስጥ የታገደ ወይም በጥብቅ የተከለከለ በጣም አደገኛ የሆነ መድኃኒት ነው። በጋና የገጠር ክፍሎች ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ዲዲቲን ዓሣ ለመያዝ ይጠቀሙበታል። ኬሚካሉ ወደ ወንዞች ውስጥ ሲጨመር ዓሣዎቹን ይገድላቸውና በቀላሉ እንዲያዙ ያደርጋቸዋል። ከዚያም ዓሣው አደገኛውን መርዝ እንደያዘ በአፍሪካውያን ምግቦች ላይ ለመብልነት ይቀርባል።
በቤት ውስጥ ሥራ መተጋገዝ
ጃፓናውያን ወንዶች በባህላቸው በቤት ውስጥ ሥራ መተጋገዝ አያውቁም ነበር፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ ከጊዜ በኋላ እየተለወጠ ነው። በቅርብ ጊዜ በቶኪዮ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው በአሁኑም ጊዜ ቢሆን በዚያ የሚገኙ ወንዶች በአጠቃላይ ሲታዩ ምግብ ማብሰል፣ ልጆችን ማሳደግና ዕቃዎችን ማጠብ የሴቶች ሥራ ነው ብለው ያስባሉ፤ 60 በመቶ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚሠሩ ሥራዎች መርዳት አለብን ብለው ያምናሉ። 70 በመቶ የሚያክሉት ደግሞ ብዙውን ጊዜ ቤት ማጽዳት፣ ገበያ ወጥቶ መገብየት፣ ቆሻሻ መድፋትና የመሳሰሉትን ሥራዎች እንደሚሠሩ ይናገራሉ። ለመርዳት ይበልጥ ፈቃደኛ የሆኑት ወጣት ባሎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት “ወንዶች የሚችሉትን ያህል በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው” ይስማማሉ፤ 29 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ “ቢረዱም ባይረዱም ግድ እንደሌላቸው ይናገራሉ።” “ይሁን እንጂ በወጣት ባሎች መካከል የሚታየው ይህ ዝንባሌ እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ አይደለም” በማለት ሜይንቺ ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ ይናገራል፤ አክሎም “ የመጀመሪያ ልጃቸው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሚገኝ ቤተሰቦች መካከል በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኞች ነን ብለው የተናገሩት ባሎች ቁጥር ወደ 47 በመቶ አሽቆልቁሏል” ብሏል። ከዚህም በላይ በእነዚህ ዓይነት ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ በቤት ውስጥ ሥራዎች መርዳት አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ባሎች ቁጥር 13 በመቶ ከፍ ብሏል።
አደገኛ የቆዳ መጥቆር
የቆዳ ካንሰር የያዛቸው ካናዳውያን ቁጥር “ባለፉት ስምንት ዓመታት 235 በመቶ ጨምሯል” ሲል ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ከ7 ካናዳውያን መካከል 1 ሰው በሕይወት ዘመኑ የቆዳ ካንሰር እንደሚይዘው አዲስ ስታትስቲኮች ይጠቁማሉ። ለዚህ ዋነኛው መንስኤ ምንድን ነው? የካናዳ የቆዳ ሳይንስ ጥናት ማኅበር እንዳለው መንስኤው ለፀሐይ ሐሩር መጋለጥ ነው። የቆዳ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ጋሪ ሲባልድ “ለፀሐይ ቃጠሎ በመጋለጥህ ቆዳህ አንድ ቦታ ላይ ብቻ እንኳን ውኃ ቢቋጥር በቆዳ ካንሰር የመያዝህን አጋጣሚ በእጥፍ ያሳድገዋል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “ቆዳ በፀሐይ መጥቆሩ የጤና አይደለም። የቆዳ መበላሸትን የሚያመለክት ነው” ብለዋል። ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል እንደዘገበው ከሆነ “የቆዳ መሸብሸብ፣ መኮማተር፣ በቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስልና የቆዳ ካንሰር” ሊያስከትል ይችላል። የፀሐይ መከላከያ ማድረግ፣ ፀሐይ የሚከላከል ልብስ መልበስ፣ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ለሚኖረው የፀሐይ ሐሩር አለመጋለጥ ሊጠቅም ይችላል ተብሏል።
የኦዞን መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው
የኦዞን ንብርብር በሰሜናዊውም ሆነ በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የተደረገው ጥናት ያሳያል። ዘ ዲፕሎማቲክ ወርልድ ቡለቲን በዘገበው መሠረት ከ25 አገሮች የተሰባሰቡ 80 ሳይንቲስቶችን ባቀፈ አንድ ቡድን አማካኝነት የተገኙት አዳዲስ ግኝቶች ባለፉት አሥር ዓመታት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያለው ኦዞን 3 በመቶ እንደቀነሰ ያመለክታሉ። በያዝነው መቶ ዓመት ማብቂያ ላይ እንደገና 3 በመቶ እንደሚቀንስ ይጠበቃል። በአንታርክቲክ ክልል በበጋ አንዴ ተከስቶ የነበረው የኦዞን መጠን መቀነስ አሁን ወደ ሌሎች ወቅቶችም ተሸጋግሯል። ሳይንቲስቶች በአብዛኛው ሰዎች በሚያደርጓቸው ነገሮች ሳቢያ የኦዞን መጠን መቀነሱ የአየር ንብረት ቀውስ፣ የሰብል ጥፋትና የቆዳ ካንሰር መጨመርን ሊያስከትል ይችላል ብለው ያምናሉ።
ኤድስ የሚያስከትለው መዘዝ
በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ የዓለም አቀፍ የኤድስ ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ሚካኤል ሜርሶን የኤድስ ወረርሽኝ ከባድ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል ብለው ይሰጋሉ ሲል ላ ፕሬስ ሜዲካል የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት ተናግሯል። የዓለም ባንክ ኤድስን በተመለከተ ታይላንድ ባንኮክ ውስጥ ባደረገው ልዩ ስብሰባ ላይ ዶክተር ሜርሶን ባደረጉት ንግግር “ወጣቶችና ጎልማሶች ከሆኑት ሰዎች መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ አንድ አምስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ማለቁ የማኅበራዊ ኑሮ መፋለስ፣ የኢኮኖሚ መናጋት አልፎ ተርፎም ለፖለቲካዊ ሂደት እንቅፋት ያስከትላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ገና ከአሁኑ ብዙ የአፍሪካ ሕዝብ አምራች ዜጎች በበሽታው ሕይወታቸው እየተቀጠፈ ነው፤ በብዙ የገጠር መንደሮችም የቤተሰብ አባሎች በሙሉ በበሽታው እያለቁ ነው። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን በኤድስ ሳቢያ ሕይወታቸው ያልፋል ተብሎ ይጠበቃል። በምድር ዙሪያ በትንሹ ከ9 እስከ 11 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ኤድስን በሚያስከትለው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ተይዘዋል ተብሎ ይገመታል። ኤክስፐርቶች በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ይህ ቁጥር በሦስት እጥፍ እንደሚጨምር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቀሳውስትና የፆታ ነውር
በቅርቡ የአውስትራሊያ ቴሌቪዥን “አሳፋሪው የእምነት ማጉደል ተግባር” በሚል ርዕስ አንድ ጥናታዊ ፊልም አቅርቦ ነበር። በአውስትራሊያ ውስጥ የሚገኙ 15 በመቶ የሚሆኑ ቄሶች ልጆችን ከማስነወር አንስቶ በደብራቸው ሥር ያሉትን ሴቶችን አስገድዶ እስከ መድፈር ድረስ የጾታ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲል ፕሮግራሙ ገልጿል። የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በቀረበ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የጣቢያው የተለያዩ ማዕከሎች የፆታ ብልግናው ተፈጽሞብናል ያሉ ሰዎች ድርጊቱ አሳፋሪ መሆኑን በመግለጽ በስልክ ያወረዱትን የተቃውሞ ናዳ ማስተናገድ ጀመሩ። ስልክ ከደወሉት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ የደረሰባቸውን ነገር ለብዙ ዓመታት ደብቀው እንደቆዩ ተናግረዋል። አንዲት ሴት የደረሰባትን ሥቃይ ስትናገር በ40 ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያዋ እንደሆነ ገልጻለች! አንዲት ሌላ ሴት ደግሞ የነፍስ አባቷ በልጅነቷ በፆታ ካስነወራት በኋላ ድርጊቱን ለሌላ ሰው ከተናገርሽ በሲኦል እሳት ትቀጫለሽ ብሎ እንዳስፈራራት ተናግራለች። የተለያዩ የአብያተ ክርስቲያናት ቃል አቀባዮች 15 በመቶ ተብሎ የተገለጸውን ቁጥር ቢያስተባብሉም ቀሳውስት የሚፈጽሙት የፆታ ብልግና ትልቅ ችግር እንደሆነ ግን አምነዋል።
ለዘረኝነት ሰበብ የሚሆን ነገር የለም
ሳይንቲስቶች በቅርብ ጊዜ በተካሄዱት የጄኔቲክስ ሳይንስ እድገቶች በመታገዝ በሰው ጄኔቲክ ኮድ (ወደ ቀጣይ ዘሮች የሚተላለፉትን ሁለንተናዊ ባሕርያት የሚወስነው ንድፍ) ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተደብቀው የቆዩትን መረጃዎች መፍታት ጀምረዋል። ሳይንቲስቶች የደረሱበት ነገር የሰውን ዘር በተመለከተ ያለውን ባህላዊ አስተሳሰብ መጠራረግ ጀምሯል ሲል ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ አመልክቷል። ምንም እንኳን በሰው ልጆች መካከል ቁመትን፣ የቆዳ ቀለምንና ሌሎችንም ገጽታዎች የመሳሰሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው በዓይን የሚታዩ ውጫዊ ልዩነቶች ያሉ ቢመስልም የጄኔቲክስ ሳይንስ ጠበብቶች በምድር ላይ ያሉ የሰው ልጆች በሙሉ እጅግም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ቦታ የሁሉም የጋራ ወላጆች ከሆኑ ሰዎች የመጡ መሆናቸው አያጠራጥርም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። “ዘረኝነትን በመደገፍ የቀረቡት ማብራሪያዎች ሁሉ መና ቀርተዋል” ሲል ለ ፊጋሮ ገልጿል።
ተጨማሪ ሰዎች
የተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ጉዳይ ክፍል በዓለም ዙሪያ ያለውን የሕዝብ ቁጥር እድገት አስመልክቶ በቅርብ ጊዜ በተካሄደ ጥናት የደረሰበትን ግምታዊ ዘገባ በቅርቡ አውጥቷል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ መሠረት “ወደፊት የሚሆነውን በማስመልከት የተሰጡ አዳዲስ ግምቶች እንደሚያሳዩት እስከ ያዝነው መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ ዓለም በያመቱ 97 ሚልዮን አዲስ ሰዎችን ትቀበላለች፤ ከዚያ ቀጥሎ ካለው ዓመት ጀምሮ እስከ 2025 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በያመቱ 90 ሚልዮን አዲስ ሰዎችን ታስተናግዳለች።” ከዚህ የሕዝብ ቁጥር እድገት ውስጥ ዘጠና ሰባት በመቶው በታዳጊ አገሮች ውስጥ እንደሚከሰት ይጠበቃል። ይህን የመሰለው የሕዝብ ቁጥር እድገት የሰውን ልጅ ኑሮ አስጊ ሁኔታ ላይ ይጥለዋል። “በእንዲህ ዓይነት ቁጥር የሚኖረው እድገት ከአሁኑ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ረሃብተኞችና ድሃ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ ማለት ነው፤ ወደ ከተሞችና ወደ ሀብታም አገሮች የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር ይጨምራል። ዓለም ያላት የምግብ፣ የውኃና የሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ክምችት እየቀነሰ እንዲሄድ ጫና ይፈጥራል ሲል ሪፖርቱ ያስጠነቅቃል” በማለት ታይምስ አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ ያለው 5.5 ቢልዮን የዓለም ሕዝብ በ2050 ወደ 10 ቢልዮን ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
መልካሙ መሬት እየጠፋ ነው
ሳይንስ የተባለው ጋዜጣ ባወጣው አንድ ዘገባ መሠረት ለእርሻ የሚሆነው የዓለም አፈር እየተመናመነ መጥቷል፤ “በፍጥነት በውኃ እየተሸረሸረ ወይም በንፋስ ተጠርጎ እየተወሰደ ነው።” በመጋቢት ወር በዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘው ደብሊው አር አይ (የዓለም የተፈጥሮ ሀብት ኢንስቲትዩት) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ያለው የአፈር ሁኔታ ምን ያህል እንደተለወጠ ምርምር ባደረጉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤክስፐርቶች አማካኝነት ለሦስት ዓመት የተካሄደው ጥናት ያስገኘውን ውጤት አውጥቷል። የተገኙት ውጤቶች ምንድን ናቸው? የሰው ልጅ በአብዛኛው ደንን በመጨፍጨፍ፣ የግጦሽ መሬት ከሚገባው በላይ እንዲጋጥ በማድረግና ጎጂ የሆኑ የእርሻ ዘዴዎችን በሥራ ላይ በማዋል ምድርን አላግባብ በመጠቀሙ ጠቅላላ ስፋቱ የቻይናንና የህንድን ምድር በሙሉ የሚያክል በአንድ ወቅት ለም መሬት የነበረ ቦታ አሁን ለምነቱን አጥቷል። የደብሊው አር አይ ፕሬዘዳንት የሆኑት ገስ ስፔዝ እንደሰጡት ግምት ከሆነ ከሕዝቡ ቁጥር እድገት ጋር እኩል ለመራመድ ዓለም በሚቀጥለው ግማሽ መቶ ዘመን የምግብ ምርቷን ሦስት እጥፍ ማሳደግ ያለባት በመሆኑ ይህ ሁኔታ ትልቅ ችግር እንዳያስከትል ያሰጋል።