ወላጆችን የሚፈታተን ሁኔታ
የዓለም ሥነ ምግባር በጣም እየተበላሸ መጥቷል። ወሲባዊ ማስታወቂያዎች በገፍ ይቀርባሉ። ሴቶችን እንደ ርካሽ ሸቀጥ የሚያሳዩ መጽሔቶች በየግሮሠሪው ይሸጣሉ። ሴቶችን አስገድዶ መድፈርን የሚደግፉ ዘመናዊ ዘፈኖች ይደመጣሉ። በእርግጥም በየቀኑ ከሚታዩትና ከሚሰሙት ነገሮች ማረጋገጥ እንደሚቻለው ዓለማችን በሥነ ምግባር የቆሸሸች ዓለም ሆናለች!
የቤተሰብ ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ግሪር ሊተን ፎክስ “አንድ ሰው በየቀኑ ከቀኑ 7:30 እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት በቴሌቪዥን ሊመለከት ከሚችላቸው 40 የሚያክሉ” የሩካቤ ሥጋ ወይም ሩካቤ ሥጋን የሚያሳስቡ ድርጊቶች ውስጥ “በተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረጉት ከ5 በመቶ ያነሱ ናቸው” ብለዋል። መገናኛ ብዙሐን ወሲባዊ ድርጊቶችን በሚያስፋፉበት በአሁኑ ጊዜ “በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና በጣም እየበዛ መምጣቱንና ብዙ ጉዳት በማስከተል ላይ መሆኑን ማንበባችን ሊያስደንቀን አይገባም።”
በእርግጥም ልጆቻቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለሚፈልጉ ወላጆች ልጆቻቸውን በዚህ በሥነ ምግባር በተበላሸ ዓለም ውስጥ ማሳደግ በጣም አስቸጋሪ እየሆነባቸው ሄዶአል። እንዲህ ሲባል ግን ሁሉም ወጣቶች በወሲባዊ ድርጊቶች በመካፈል ላይ ናቸው ማለት አይደለም። ከ15 እስከ 19 ዕድሜ ካላቸው የአሜሪካ ሴት ወጣቶች መካከል ግማሾቹ የሩካቤ ሥጋ ልምድ ያላቸው መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፤ ይህም ግማሽ የሚሆኑት ወጣቶች ምንም ዓይነት ተሞክሮ የሌላቸው መሆኑን ያረጋግጣል! ከዚህም በላይ ሩካቤ ሥጋ ፈጽመው ከሚያውቁት እንኳን ብዙዎቹ ይህን ድርጊት በመፈጸማቸው ይጸጸታሉ። አንዲት ወጣት ሴት የአንድ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ ለሆኑት ለአን ላንደርስ እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች:-
“ከጆይ (ለመጀመሪያ ጊዜ ካፈቀርኩት ልጅ) ጋር የፈጸምኩት ሩካቤ ሥጋ ምንም ስላላስደሰተኝ እንደገና ከማይክ፣ ከዚያም ከጆርጅና ከኒል ጋር ሞከርኩ። ምን እፈልግ እንደነበረ አላውቅም። እፈልግ የነበረው ምንም ይሁን ምን አንዳችም ያገኘሁት ነገር የለም። ከመጽሔቶች፣ ከተከታታይ የቴሌቪዥን ተውኔቶችና ሲኒማዎች የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ተቀርጸውብኝ ነበር። እውነተኛው ሕይወት በእነዚህ ፕሮግራሞች ከሚታየው የተለየ ነበር።
“አምድዎን ለሚያነቡ ወጣት ሴቶች ለመናገር ብችል ኖሮ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚፈጸም ሩካቤ ሥጋ ተጨማሪ ችግሮችን ይፈጥራል እንጂ ምንም ዓይነት ችግር እንደማያቃልል እነግራቸው ነበር። አንዲት ሴት ልጅ ርካሽ እንደሆነች እንጂ እንደምትወደድ እንዲሰማት አያደርግም። ‘ሴትነትዋን’ ይቀንሳል እንጂ እንደማይጨምር አሳውቃቸው ነበር።
“ወላጆችን ማነጋገር ብችል ኖሮ ለልጆቻቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎችንና ራስን በአክብሮት የመመልከትን አስፈላጊነት አጠንክረው እንዲያሳስቡ እመክራቸው ነበር።”
በእርግጥም ከወላጆቻቸው ጋር የሚቀራረቡ፣ በቤተሰቦቻቸው የሚታመኑና ስለራሳቸው ጥሩ ስሜት የሚሰማቸው ወጣቶች ከሥነ ምግባር ውጭ በሆኑ ድርጊቶች የመሸነፋቸው አጋጣሚ ከእነዚህ የተለየ አስተዳደግ ካላቸው ወጣቶች በጣም ያነሰ ነው። በተጨማሪም ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍቶ ከሚገኘው የሥነ ምግባር ደረጃ በጣም የላቀ ደረጃ እንዲከተሉ የሚረዳ በመላው ዓለም የሚገኙ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ አባሎች ያሉት አንድ ድርጅት አለ።
እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች ልጆቻችሁ በዛሬው ዓለም ውስጥ እየጨመረ ከሄደው የሥነ ምግባር ብልግና ራሳቸውን እንዲጠብቁ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ይበልጥ አስደሳች፣ የተሻለና በሥነ ምግባር ያልቆሸሸ ኑሮ እንዲኖሩ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ይብራራል።