አንተ ሕሊና፣ ለምን ታሠቃየኛለህ?
“አንተ ፈሪ ሕሊና፣ ይህን ያህል የምታሠቃየኝ ለምንድን ነው?” እነዚህ በሼክስፒር ተውኔት ውስጥ ንጉሥ ሪቻርድ ሳልሳዊ የተናገራቸው ዝነኛ ቃላት ሰብዓዊ ሕሊና ሊያስከትል የሚችለውን የጸጸት ስሜት ይገልጻሉ። ሕሊና የብዙ ሰዎችን ሕይወትና አኗኗር አናግቷል ወይም ለውጧል።
በቅርቡ በአንድ ኢጣልያዊ ወጣት ላይ የደረሰው ሁኔታ ሕሊና ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያሳያል። ሥራው ፀጥታ አስከባሪነት ስለነበረ መጠኑ በዛ ያለ ገንዘብ በማጓጓዝ ሥራ ይካፈል ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ገንዘቡን ለመውሰድ ባደረበት ፍላጎት ተሸንፎ 300,000,000 ሊሬ [185,000 የአሜሪካ ዶላር] የያዘ ጆንያ እስከ ሰረቀበት ጊዜ ድረስ ምንም ችግር አልነበረም። አብረውት የሚሠሩ ሌሎች ሁለት የሥራ ባልደረቦች ስለነበሩ ማንኛቸው እንደሰረቁ ለማወቅ ስላልተቻለ ሦስቱም ከሥራ ተባረሩ።
ነገሩ ከተረሳሳ በኋላ እጠቀምበታለሁ ብሎ በማሰብ ገንዘቡን ደብቆ አስቀመጠው። ይሁን እንጂ ያልጠበቀው ሥቃይ ደረሰበት። ምንም ያላደረጉ የሥራ ባልደረቦቹ ስለመባረራቸው ያስብ ጀመር። ሕሊናው ለአንድ አፍታ እንኳን ሰላም ሊሰጠው አልቻለም። መተኛት አልቻለም፤ መብላትም አቃተው። ከሰው ጋር መግባባትም ጨርሶ ተሳነው።
በመጨረሻም በተሰማው የበደለኛነት ስሜት በመሸነፉና በውስጡ በተፈጠረው ትግል በመዳከሙ የሰረቀውን ገንዘብ ለፖሊሶች ወስዶ አስረከበ። “ያደረብኝ ጸጸት በጣም ከፍተኛ ነበር። ልቋቋመው አልቻልኩም!” አላቸው። ቀጥሎም “ሌባ ነህ እያለ የሚከስስ ሕሊና ይዞ በነፃነት ከመኖር በሐቀኝነት በእስር ቤት መኖር ይሻላል” አላቸው።
ሕሊና ለሁሉም የሰው ልጆች የተሰጠ የአምላክ ስጦታ ነው። ሊከስሰን ወይም ነፃ ሊያወጣን ይችላል። ሕሊናችንን ካዳመጥን ሰበብ ፈጥረን ከባድ በደል ከመፈጸም ልንጠበቅ እንችላለን። ስለዚህ የሕሊናችንን ጉትጎታ ችላ ከማለት ወይም የሼክስፒር ንጉሥ ሪቻርድ ሳልሳዊ እንዳደረገው ከሕሊናችን ጋር ከመጣላት ይልቅ ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል።— ሮሜ 2:14, 15
ስለ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው ተግባራዊ ምክር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለጉ በአካባቢዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው ወይም በገጽ 5 ላይ በሚገኘው አድራሻ ጽፈው ይጠይቁ።