የትዳር ጓደኛቸውን በጥበብ እንዲመርጡ እርዷቸው
ወጣት ልጆቻችሁ የትዳር ጓደኛ ሲመርጡ ምን ዓይነት ባሕርያትን መመልከት እንዳለባቸውና እንዴት በጥበብ ሊመርጡ እንደሚችሉ ያውቃሉን? ይህ ጉዳይ የወደፊት ኑሯቸው ደስታ የተሞላበት በመሆኑ ረገድ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ስለሆነ ስለዚህ ጉዳይ አጥብቆ ማሰብና የጥበብ ውሳኔ እንዲያደርጉ መርዳት በጣም አስፈላጊ ነው።
የተቃራኒ ጾታዎች መቀጣጠርና አብሮ መዋል በተለመደባቸው አገሮች ወጣቶች ገና በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ከተቃራኒ ጾታ ጋር እንዲቆራኙ የሚያነሳሳ ተጽእኖ ይደርስባቸዋል። በኒው ዮርክ ውስጥ የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሮናልድ ደብልዩ ታፈል “የ10 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ወላጆች ልጆቻቸው ከተቃራኒ ጾታዎች ጋር እንዲቀጣጠሩ እንዲፈቀድላቸው ከፍተኛ ግፊት እንደሚያደርጉባቸው ይነግሩኛል” ብለዋል። “ወላጆች ልጆቻቸው ጉርምስና ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያጋጥሙናል ብለው ባላሰቧቸው ጉዳዮች ሲወዛገቡ ይገኛሉ።”
በልጆቻችሁ ግፊት ተሸንፋችሁ ገና በአፍላ ዕድሜያቸው ከተቃራኒ ጾታ ጋር መቀጣጠር እንዲጀምሩ ብትፈቅዱላቸው ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን መዲካል አሶሲዬሽን “በዕድሜ ሳይበስሉ አዘውትሮ መቀጣጠር [ሩካቤ ሥጋ] ወደ መፈጸም ይመራል” ብሏል። ምናልባት “በ10 እና በ14 ዓመት ዕድሜ መካከል ሳሉ የሚያረግዙ ልጆች ቁጥር እየበዛ ስለመሄዱ” አንብባችሁ ይሆናል።
ታዲያ ልጆቻችሁን ለመርዳት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?
ገና ከትንሽነታቸው ጀምራችሁ አስተምሯቸው
ወላጆች በልጆቻቸው ልብና አእምሮ ውስጥ በጎ ክርስቲያናዊ ባሕርያት እንዲቀረጹና እነዚህም ባሕርያት እንዲዳብሩ መርዳት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ በጎ ባሕርያት ለትዳር ጓደኛነት በሚመርጧቸው ዘንድ የሚገኙ መሆናቸውን ለይተው ለማወቅ እንዲችሉ መርዳት ይገባቸዋል። ልጃችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስለመቀጣጠር በሚያነሳበት ጊዜ ይህ ጉዳይ ገና ጉርምስና ዕድሜ ላይ ያልደረሱም ሆኑ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ሊያዩት የሚገባ ነገር እንዳልሆነ አስረዷቸው። መቀጣጠር የሚችሉት በቁም ነገር የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የሚፈልጉ ብቻ እንደሆኑ ግልጽ አድርጉላቸው።
ልጆች ራሳቸው በሚገባ እንደሚያውቁት የሰዎችን ባሕርይ በመመዘን ረገድ በቂ ተሞክሮ ያላቸው አይደሉም። አንዲት የሕንድ ልጃገረድ ለአንድ የጋብቻ አማካሪ እንደሚከተለው ብላ ነበር:- “ወላጆቻችን ከእኛ በዕድሜም በጥበብም ይበልጣሉ። በመሆኑም የእኛን ያህል በቀላሉ አይታለሉም። . . . የማገባው ወንድ ለእኔ የሚስማማኝ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ራሴ የምመርጠው ከሆነ በቀላሉ ልሳሳት እችላለሁ።” በእርግጥም ወጣቶች በዕድሜ የሚበልጧቸው ሰዎች ከሚሰጧቸው እርዳታ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ!
አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች የትዳር ጓደኞቻቸው እንዲኖሯቸው የሚፈልጓቸው ባሕርያትና ብቃቶች ጥሩ ባል ወይም ሚስት ከመሆን ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የሌላቸው ናቸው። ወንዶች ልጆች በቆንጆ ፊትና በጥሩ ቁመና ሊሳቡ ይችላሉ። በኋላ ግን ምን ይሆናል? የሰውነት ቅርጽና የፊት ቁንጅና የሚለዋወጥ ከመሆኑም በላይ ልጁ ራሱ በዕድሜ ሲገፋ ብልህነትንና ኃላፊነት ለመሸከም መቻልን ጨምሮ የጎለመሰች ሴት ሊኖራት የሚገባትን ባሕርያት መፈለጉ አይቀርም። ብዙ ጊዜ ልጃገረዶች ወንዱ ልጅ ደግና ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ያለው ለመሆኑ ሳይሆን ለውበቱ፣ ለጥሩ አለባበሱና ተጫዋች ለመሆኑ ቅድሚያ ይሰጣሉ።
ታዲያ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ልጆቹ የሚያውቋቸው ጥሩ ትዳር ያላቸው ሰዎችን እንዲያስተውሉ ለማድረግ ትችላላችሁ። እነዚህ ሰዎች የመረጧቸው የትዳር ጓደኞች በቁንጅናቸውና በውበታቸው በጣም የሚደነቁ ሳይሆኑ ጥሩ ባሕርያት ያሏቸው፣ ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር የሚመሳሰል ፍላጎት፣ ግብና ዓላማ ያላቸው እንደሆኑ ልትጠቁሟቸው ትችሉ ይሆናል።
ለምን ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከልጆቻችሁ ጋር አትወያዩም? አን የ13 ዓመት ልጅ በነበረችበት ጊዜ እናትዋ የወደፊት ባልዋ ምን ዓይነት ባሕርያት እንዲኖሩት እንደምትፈልግ ጠየቀቻት። ስለዚህ ጉዳይ ከተወያዩ በኋላ ወደፊት የምታገባው ሰው ሊኖሩት የሚገባቸውን ባሕርያት ዘረዘረች። ይህ ዝርዝርዋ ተጨባጭ ሊሆን የማይችል ዝርዝር አልነበረም። ከምትፈልጋቸው ብቃቶች መካከል ልታከብረው የምትችል፣ ፍላጎቱና ስሜቱ ከራስዋ ጋር የሚስማማ መሆኑ ይገኝበታል። አን በአሁኑ ጊዜ ደስተኛ አያት ስትሆን ሌሎችም የራስዋን ምሳሌ ቢከተሉ ጥሩ እንደሚሆን ትመክራለች።
አንድ ክርስቲያን ‘ጋብቻችሁ በጌታ ብቻ ይሁን’ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ችላ ማለት አይገባውም። (1 ቆሮንቶስ 7:39) “በጌታ” የሆነ ሰው ራሱን የወሰነና የተጠመቀ፣ ኢየሱስ ያከናውን በነበረው ሥራም የተጠመደ ሰው ነው። ይህን በጌታ ብቻ እንዲያገቡ የተሰጠውን ትእዛዝ ችላ የሚሉ ሰዎች አሳዛኝ የሆነ ሁኔታ ይደርስባቸዋል። ስለዚህ ወጣት ልጆቻችሁ ለትዳር ጓደኝነት የሚመርጧቸው እነርሱ የሚከተሏቸውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ሥርዓቶች የሚከተሉና እነዚህንም ባሕርያት ወደፊት ለሚወልዷቸው ልጆቻቸው ሊያስተላልፉ የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸው አጥብቃችሁ አስገንዝቧቸው።
አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም እንዲችሉ አዘጋጁአቸው
ልጆቻችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ለመቀጣጠር በሚያስችል ዕድሜ ላይ ደርሰዋል ብላችሁ ስታስቡ ከሚቀጣጠሩት ጓደኛቸው ጋር ብዙ ሰው ወደሚገኝባቸው ቦታዎች፣ ወደ ምግብ ቤቶች፣ ቤተ መዘክሮች፣ አራዊት ወደሚታዩባቸው ቦታዎችና ብቻቸውን ሳይነጠሉ ለመነጋገርና ለመተዋወቅ ወደሚያስችሏቸው ሌሎች ቦታዎች መሄድ ጥበብ መሆኑን አስገንዝቧቸው። እንዲህ ማድረግ መኪና ጥግ አስይዞ ከመቀመጥና ማንም ሌላ ሰው በሌለበት ቦታ ለብቻ ከመሆን በጣም የተሻለ የሚሆንበትን ምክንያት እንዲገነዘቡ እርዷቸው። በተጨማሪም ከተቀጣጠሩበት ቦታ ተመልሰው በሚሰነባበቱበት ጊዜ ራሳችሁ ቤት ውስጥ ከሌላችሁ በስተቀር ወደ ቤት ከማስገባት ይልቅ ከበር ውጭ ደህና እደር(ሪ) ተባብለው መለያየት አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯቸው።
ልጆቻችሁ ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል አስጠንቅቋቸው። ለምሳሌ ያህል አንድ የዜና ዘገባ አንዲት ተማሪ ከአንድ ልጅ ጋር ከተቀጣጠሩና አብረው ራት ከበሉ በኋላ ለመደነስና ለመነጋገር ወደ ክፍልዋ እንዲገባ እንደጋበዘችው ይናገራል። አብሯት ለመባለግ ደጋግሞ ቢቃጣም ከክፍልዋ እንዲወጣ አላደረገችውም። ከዚህ ይልቅ ድርጊቱን በምትቃወምበት ጊዜ ይቅርታ እየጠየቃት እርስዋን ለማሳት ደጋግሞ ይሞክር ነበር። ዘገባው “በመጨረሻ ወደ ንጋት አካባቢ ላይ አስገድዶ ደፈራት” ይላል። ምንኛ የሚያሳዝን ነገር ነው!
ስለዚህ ልጆቻችሁ ገና ብልግና የመፈጸም ሐሳብ ሲሰሙ እንኳን እንዴት ወሳኝ እርምጃ እንደሚወስዱ የሚያውቁ መሆናቸውን አረጋግጡ። ወጣቱ ዮሴፍ ትጎተጉተው ከነበረችው የጶጢፋር ሚስት እንደሸሸ እነርሱም ፈጥነው ከሁኔታው መሸሽ ይገባቸዋል። (ዘፍጥረት 39:7–12) “በእውነት የምትወጂኝ ብትሆኝ ኖሮ . . .” የሚለው ጊዜ ያለፈበት የልመና አነጋገር አብዛኛውን ጊዜ የአታላዮች አነጋገር እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል። እንዲህ የሚሉ ሰዎች ምናልባት በዚህ አነጋገራቸው ደጋግመው ሌሎችን ያሳቱና ከዚያ በኋላ ወደሌሎች የሚረማመዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ወንድ ወይም ሴት ልጃችሁ ብልግና ለመፈጸም ጥያቄ ሲቀርብላቸው ከሁሉ የሚሻለው መልስ በማያሻማ ሁኔታ አይሆንም ማለት እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል።
ሴት ልጃችሁ ተገዳ ልትደፈር ከምትችልባቸው ሁኔታዎች እንዴት መራቅ እንደምትችል ማስተማር ይኖርባችኋል። የሚቀጥራት ማንኛውም ወንድ ደህና አድርጋ የምታውቀውና እናንተም ወላጆች አሳምራችሁ የምታውቁት ሰው መሆኑ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧት። ልጆቻችሁ የሚኖሩት በእናንተ አካባቢ ካልሆነ የትዳር ጓደኛቸው ስለሚሆነው ወይም ስለምትሆነው ሰው እንዲነግሯችሁ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችን ጠይቁ። ዛሬም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያን ነን እያሉ ወደ ጉባኤው ሾልከው የሚገቡ አታላዮች እንደሚኖሩ አስታውሱ።— 2 ጴጥሮስ 2:13–15, 17, 18
በተጨማሪም ለወንዶች ልጆቻችሁ እውነተኛ ወንድነት ያላቸው ሰዎች ለሰዎች ይከላከላሉ ወይም ይጠብቋቸዋል እንጂ ሆን ብለው በሌሎች ላይ ጉዳት እንደማያደርሱ አስተምሯቸው። እውነተኛ ወንድነት ያላቸው ሰዎች የስሜታቸው ጌቶች እንጂ ባሪያዎች አይደሉም። ተቃራኒ ጾታ ያላቸውን ሁሉ ልክ እንደ ገዛ እናቶቻቸውና እህቶቻቸው በአክብሮት ይይዟቸዋል።— 1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
ልጆቻችሁ “መጥፎ ጓደኛ ጥሩውን ጠባይ ያበላሻል” የሚለውን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ፈጽሞ እንዲዘነጉ አትፍቀዱ። (1 ቆሮንቶስ 15:33 የ1980 ትርጉም ) ስለዚህ ልጆቻችሁ በንጹሕ ሥነ ምግባር ከማይመላለስ ማንኛውም ሰው መራቅ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ገና ከሕፃንነታቸው ጀምራችሁ የሚያደርጉትን ነገር ማንም ሰው ሊመለከት ባይችል እንኳን አምላክ ሁልጊዜ እንደሚመለከታቸውና ለሁላችንም እንደ ሥራችን እንደሚከፍለን ግልጽ ልታደርጉላቸው ይገባል።—ሮሜ 2:6
በሥነ ምግባር በቆሸሸ ዓለም ንጹሕ ሥነ ምግባር ይዞ መኖር
ዓለማዊ ባለሥልጣኖች “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ያላገቡ ወጣቶች ሩካቤ ሥጋ ከመፈጸም እንዲታቀቡ መምከር እንደተሳናቸው” በምሬት ቢናገሩም ክርስቲያን ወላጆች ግን ሊደረግ የሚቻል ነገር መሆኑን ያውቃሉ። ወላጆች በልጆቻቸው ልብና አእምሮ የአምላክ ፍቅርና ለሕግጋቱ አክብሮት እንዲቀረጽባቸው በማድረግ ይህ በሥነ ምግባር የተበላሸ ዓለም የሚያመጣባቸውን ፈተና ተቋቁመው በንጹሕ ሥነ ምግባር እንዲመላለሱ ያስችሏቸዋል። የአምላክ ቃል የሚደነግገውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ ጠብቆ በመኖሩ ልዩ ሆኖ የሚታወቅ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙበት አንድ ትልቅ ማኅበር አለ። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንኳን የዚህ ማኅበር “የጋብቻና የጾታ ሥነ ምግባር በጣም ጥብቅ ነው” ብሏል።— ጥራዝ 7፣ ገጽ 864
በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙና በንጹሕ ሥነ ምግባር የሚመላለሱ ወጣቶች በወላጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያን ባልደረቦቻቸው ጭምር የሚወደዱና የሚፈለጉ መሆናቸውን ያውቃሉ። በማንነታቸው ይደሰታሉ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ይካፈላሉ፣ የማስተማር ችሎታቸውን ያዳብራሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትም ይሳተፋሉ። አምላካዊ በሆነ ሥነ ምግባር ይመላለሳሉ፣ ስለራሳቸው ጥሩና ገንቢ አመለካከት አላቸው፣ በአምላክ አዲስ የጽድቅ ሥርዓት ውስጥ አስደሳች ሕይወት የማግኘት ብሩሕ ተስፋ አላቸው።— 1 ዮሐንስ 2:17፤ ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሚያምር አካላዊ ቁመና ሊማርክ ቢችልም ይበልጥ አስፈላጊነት ያለው ውስጣዊ ባሕርይ ነው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነጠል ባሉ ሰዋራ ቦታዎች ከመሆን ይልቅ ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች ሆኖ መጠናናት ይበልጥ አስፈላጊ ነው