ሕይወቷ በመትረፉ በጣም ደስተኛ ነች!
በደቡብ ጀርመን የምትኖረው ጤናማዋ የዘጠኝ ዓመት ልጃገረድ በርኒስ “ሕይወቴ በመትረፉ ደስተኛ ነኝ!” በማለት በደስታ ስሜት ተውጣ ተናግራለች። የምትደሰትበት ለየት ያለ ምክንያት አላት።
አንድ ቀን በርኒስ ገና በእናቷ ማኅፀን ውስጥ በማደግ ላይ ሳለች እህቷ ታመመች። ጀርመን ሚዝልዝ የተባለ የኩፍኝ በሽታ ይዟት ነበር! ይህ ተላላፊ በሽታ በእርግዝና ወቅት በማኅፀን ውስጥ ወዳለ ሕፃን ሊተላለፍ የሚችል በመሆኑና በልጁ ላይ መጥፎ አካለ ስንኩልነት ሊያስከትል ስለሚችል እናትዬዋ በጣም ፈራች።
የደም ምርመራ ከተደረገ በኋላ ወዲያውኑ ዶክተሩ ጽንሱን እንድታስወርድ አጥብቆ አሳሰባት። ዶክተሩ የደም ምርመራውን ውጤት በመመልከት እናቲቱም ሆነች በማኅፀን ውስጥ ያለው ልጅ ጀርመን ሚዝልዝ የተባለው በሽታ እንደያዛቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኖ ነበር። በተጨማሪም የተደረጉት ምርመራዎች ሕፃኑ አካለ ስንኩል ሆኖ የመወለዱ አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ ወላጆቹ ውርጃ የአምላክን ሕግጋት የሚቃረን እንደሆነ ያምናሉ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናቸው መጠን እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ለመፈጸም ፈቃደኞች አልሆኑም። ያም ሆኖ ግን ዶክተሩ ድርጊቱን ለመፈጸም እምቢ ማለታቸው ምን ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳይ የሚዘገንን ሥዕል ሥሎ በማሳየት ፈቃደኞች እንዲሆኑ ለማድረግ ሞከረ። ለአሠቃቂ አካለ ስንኩልነት የተዳረገን ልጅ ሲያሳድጉ የሚኖረውን ችግር ገለጸ። ይሁን እንጂ ወላጆቹ ውርጃን በተመለከተ ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት በመግለጽ በአቋማቸው ጸኑ። ማንኛውንም ዓይነት ሁኔታ ለመጋፈጥም ሆነ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ልጃቸውን በፍቅር ለመንከባከብ ዝግጁ ነበሩ።
ዶክተሩ በጣም ተደነቀ። እሱ ራሱ ውርጃ ከሥነ ምግባር ደንብ አንጻር ስህተት እንደሆነ ስለሚያምን ድርጊቱን እንደማይደግፈው ገለጸላቸው። ሆኖም እውነታዎቹንና የተከሰተው ችግር የሚያመጣቸውን መዘዞች በሚገባ የመግለጽ ግዴታ ነበረበት።
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ጤናማዋ ልጅ በርኒስ ዶክተር ፊት ቀርባ ምርመራ ማድረግ ነበረባት። በደሟ ላይ የተደረገው ምርመራ ውጤት ጀርመን ሚዝልዝ የሚባለው የኩፍኝ በሽታ ፈጽሞ ይዟት እንደማያውቅ የሚያሳይ ነበር። ከመወለዷ በፊት የተደረገላት ምርመራ ውጤት ስህተት የነበረ ይመስላል። ወላጆቿ በእምነታቸው ጸንተው መቆማቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው! በርኒስ “ሕይወቴ በመትረፉ በጣም ደስተኛ ነኝ!” ብላ መናገሯ ምንም አያስደንቅም።