የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 7/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አለርጂ ያለባቸውን ሰዎች የሚረዱ ነገሮች
  • ቡራኬ በገንዘብ
  • የምግብ ፍላጎት መዛባት እየጨመረ ነው
  • አስተማሪዎችን ተወዳጅ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው?
  • የወባ ትንኝን የሚከላከል ሬዲዮ?
  • የጥርስ ሐኪምህን ጠይቀው
  • ጭስ ባለበት እሳት አለ
  • ጠበኛ አሽከርካሪዎችን በጠባይ መያዝ
  • ኤድስ በደም አማካኝነት?
  • የወላጅና የልጅ ግንኙነት ሊባል ይችላልን?
  • የይሖዋ ምሥክሮች በኩባ
  • ድካም የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ስውር ወጥመድ
    ንቁ!—1998
  • መኪና ስታሽከረክር ራስህን ከአደጋ ትጠብቃለህ?
    ንቁ!—2002
ንቁ!—1995
g95 7/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

አለርጂ ያለባቸውን ሰዎች የሚረዱ ነገሮች

የዓለም የጤና ድርጅት በገለጸው መሠረት ከዓለም ሕዝብ መካከል 20 በመቶው የሚሆኑት አለርጂ አለባቸው ሲል ግሎቦ ሴንሲያ የተባለው የብራዚል መጽሔት ዘግቧል። ስለ ሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ የሚያጠኑት ዡሊዮ ክሮስ “አለርጂ ሥልጣኔ ያመጣው በሽታ እንደሆነ ሁሉም ሁኔታዎች ያመለክታሉ” ብለዋል። “በአየር ውስጥ ከአሥር ሺህ የሚበልጡ ጎጂ ንጥረ ነገሮች አሉ።” እንደ ቅንቅንና ብክለት ካሉት የተለመዱ መንስኤዎች ሌላ ውጥረት፣ መድኃኒቶች ከመጠን በላይ መውሰድና በምግብ፣ በመኳኳያዎችና በመጠጦች ውስጥ የሚገቡት የኬሚካል ውጤቶችም መንስኤዎች ናቸው። ሌላው ቀርቶ ከመጠን በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት እንኳ የአስም በሽታን ሊያመጣ ወይም ሊያባብስ ይችላል። ይሁን እንጂ ሰዎች ትክክለኛ አተነፋፈስ የሚያውቁ ከሆነ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአለርጂውን ኃይል ለመቀነስና በበሽታው በተደጋጋሚ ከመጠቃት ለመዳን ሊረዳ ይችላል” በማለት ዶክተር ክሮስ ተናግረዋል። አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ክፍላቸውን በንጽሕና መያዝና ንጹሕ አየር ወደ ክፍላቸው እንዲገባ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ውሾችን፣ ድመቶችን ወይም ወፎችን ከመሳሰሉ የቤት እንስሳት ጋር መነካካትም ሆነ ሽቶዎችንና ኃይለኛ ጠረን ያላቸውን ነገሮች መጠቀም የለባቸውም። በተጨማሪም ድንገተኛ የአየር ለውጥ ከማድረግ፣ ከማጨስና ከአልኮል መጠጦች መቆጠብ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም በሐኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት ብቻ መውሰድ ይገባቸዋል።

ቡራኬ በገንዘብ

ብዙ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄሶች ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ላይ ስለወደቁ ቡራኬ ሲፈጽሙ ማስከፈል ጀምረዋል፤ እርግጥ ይህ ገንዘብ ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ መከፈቱን የሚደግፉት ሁሉም ቄሶች አይደሉም። ዘ ሞስኮ ታይምስ አንድ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ “ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ለእድሳት የሚሆን ገንዘብ ተቸግረዋል” በማለት የተናገሩትን ጠቅሶ ዘግቧል። ስለዚህ ቄሶች መደብሮችን፣ አፓርታማዎችን፣ ቡና ቤቶችንና የቁማር መጫወቻ ቤቶችን ሲባርኩ ያስከፍላሉ። መኪናዎችም ቡራኬ ይደረግላቸዋል። የሠሩ መኪናዎች በሚሸጡበት አንድ ገበያ አጠገብ የሚሠራ አንድ ቄስ ቡራኬ ለመፈጸም እንደ መኪናው ሁኔታ ከ30,000 እስከ 50,000 ሩብልስ (ከ15 ዶላር እስከ 25 ዶላር) ያስከፍላል። ቡራኬው ጸሎት፣ ዕጣን ማጨስና “ጸበል” መርጨት የሚጨምር ነው።

የምግብ ፍላጎት መዛባት እየጨመረ ነው

የምግብ ፍላጎታቸው ተዛብቶ ከመጠን በላይ የሚበሉና እንዳይወፍሩ በመፍራት በቂ ምግብ የማይመገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው? “አስፈሪና ከቁጥጥር ውጪ” በሆነው ዓለም ውስጥ ከባድ ጭንቀት በሚፈጥረው ግራ የመጋባት ስሜት የተነሳ ነው በማለት ዩር ፋሚሊ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። የጭንቀታቸው መንስኤዎች አንድ ነገር እንዲያከናውኑ ወላጆቻቸው የሚያሳድሩባቸው ግፊት፣ የወላጆች መፋታት፣ የሚፈጸምባቸው ግፍና በደል እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉ የተወሳሰቡ ነገሮች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎች ቀጭን ለመሆን በሚያደርጉት የማያቋርጥ ጥረት የፋሽን መጽሔቶችን በመከታተልና ስለ አመጋገብ በማጥናት ወይም ሥርዓት ያልጠበቀ የአመጋገብ ልማድ በማዳበር የምግብ ፍላጎታቸው ተዛብቷል በማለት የናሽናል ኢቲንግ ዲስኦርደርስ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር ዳኒ ለ ግራንዥ ገልጸዋል። ሌላው ቀርቶ ትንንሽ ልጆች የሆኑ በ8 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሕሙማን እንኳ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም በይበልጥ ለዚህ ችግር የተጋለጡት ከ18 እስከ 22 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ናቸው። “ሙሉ በሙሉ ከዚህ ችግር መላቀቅ ይቻላል” በማለት ፍላጎቱ እስካላቸው ድረስ ሕሙማኑ ስኬታማ በሆነ መንገድ እርዳታ ሊያገኙ እንደሚችሉ ዶክተር ለ ግራንዥ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የምግብ ፍላጎታቸው እንዲዛባ ከተዳረጉት ሰዎች መካከል እስከ 18 በመቶ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚሞቱ አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።

አስተማሪዎችን ተወዳጅ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው?

“ምንም እንኳ ብዙ ልጆች በተደጋጋሚ በትምህርት ቤት ላይ እሮሯቸውን የሚያሰሙ ቢሆንም አብዛኛዎቹ በጣም የሚወዱት አስተማሪ አላቸው” በማለት ናሳውእሼ ኖዬ ፕሬሴ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። በእርግጥም ከልጃገረዶች መካከል 91 በመቶ የሚሆኑትና ከወንዶቹ ልጆች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት በጣም የሚወዱት አስተማሪ አላቸው። ከ7 እስከ 16 ዓመት ዕድሜ ላይ በሚገኙ 2,080 ተማሪዎች ላይ በተካሄደ አንድ ጥናት አስተማሪዎችን በተማሪዎቻቸው ተወዳጅ እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው ባሕርያት ምን እንደሆኑ ለማወቅ ተሞክሯል። “ብዙ የቤት ሥራ የማይሰጥ አስተማሪ ሁልጊዜ የበለጠ ተወዳጅነትን ያተርፋል ማለት አይቻልም።” ይህ ብዙዎችን ሊያስገርማቸው ይችላል። ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊው ነገር አስተማሪው ሁሉንም በአንድ ዓይን የሚመለከት፣ ተጫዋችና ትምህርቱን ስሜት ቀስቃሽ አድርጎ የሚያቀርብ መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ ተማሪዎች ግልጥልጥ አድርጎ ማስረዳት የሚችል፣ ረጋ ያለና ችግራቸውን የሚረዳላቸው አሳቢ አስተማሪ ይወዳሉ።

የወባ ትንኝን የሚከላከል ሬዲዮ?

በፖላንድ ውስጥ የሚገኝ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ የረጅም ጊዜ ጠላት የሆነችውን የወባ ትንኝ ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ዘዴ እንደፈለሰፈ ተነግሯል። ስለ ተፈጥሮ የሚዘግበው ቴር ሶቫዥ የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት በፖላንድ ውስጥ የወባ ትንኞች የሚፈለፈሉበት ወቅት ሲደርስ ሬዲዮ የሚያዳምጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምንም ዓይነት የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ሳይጠቀሙ እነዚህን በጣም የሚያበሳጩ በራሪ ነፍሳት መከላከል ችለዋል። የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ሬዲዮአቸውን ሬዲዮ ዜት የተባለ ጣቢያ ላይ ማስተካከል ብቻ ነው። ቴር ሶቫዥ እንዳለው ከሆነ ሬዲዮ ጣቢያው ሰዎች ሊሰሙት ባይችሉም የወባ ትንኞቹ የሚሰሙትን ድምፅ ያለማቋረጥ ያስተላልፋል። የሚተላለፈው ድምፅ የወባ ትንኞችን የሚመገቡት የሌሊት ወፎች የሚያሰሙትን ቀጭን ድምፅ የሚመስል ኤሌክትሮኒክ ድምፅ ነው። ይህ ድምፅ ማንኛዋም የወባ ትንኝ ድምፁን እንደሰማች ወደ ኋላ እንድትመለስ ያደርጋል።

የጥርስ ሐኪምህን ጠይቀው

በጥርስ ሕክምና ወቅት ኤድስ ሊተላለፍ ይችል ይሆናል የሚለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰነዘረ ግምታዊ ሐሳብ ሰዎችን ድንጋጤ ላይ እየጣለ ነው። አሜሪካን ዴንታል ሃይጅኒስትስ አሶሲዬሽን ባካሄደው አንድ ጥናት 83 በመቶ የሚሆኑት የጥርስ ሕሙማን የጥርስ ሕክምና በምናደርግበት ጊዜ ተላላፊ የሆነ በሽታ ሊይዘን ይችላል የሚል ጭንቀት እንዳለባቸው ገልጿል። አሜሪካን ሄልዝ የተባለው መጽሔት በገለጸው መሠረት ታካሚዎች የጥርስ ሐኪሞቹ ጓንቶችና ጭንብሎችን ማጥለቃቸውን ብቻ ሳይሆን ታካሚዎች በተለዋወጡ ቁጥር እነዚህን ነገሮች መቀየርና አለመቀየራቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። እንደገና የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች ከእያንዳንዱ ታካሚ በኋላ በፈላ ውኃ በሚገባ በመቀቀል ጀርሞቹን ማጥፋት አለባቸው። አሜሪካን ሄልዝ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “መሣሪያውን በአልኮል መጥረግን በመሳሰሉ ዘዴዎች በመጠቀም በፈላ ውኃ ሳይቀቅሉ ከጀርም ለማጽዳት መሞከር በቂ አይደለም።” መጽሔቱ አክሎ ሲናገር “የጥርስ ሐኪምህ ጥያቄዎችህን ለመመለስ ፈቃደኛ ካልሆነ ሌላ የጥርስ ሐኪም ፈልግ” ብሏል።

ጭስ ባለበት እሳት አለ

ማጨስ የሚያስከትላቸው የታወቁ ጠንቆች ብዙ ናቸው፤ ከእነዚህም መካከል ብዙውን ጊዜ ትኩረት የማይሰጠው አንድ ነገር አለ:- እርሱም ቃጠሎ ነው። የዩ ኤስ ብሔራዊ የእሳት አደጋ መከላከያ ማኅበር በገለጸው መሠረት በእሳት የተለኮሱ የትምባሆ ውጤቶች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ1991 ብቻ ወደ 187,000 የሚጠጉ የእሳት አደጋዎችን ያስከተሉ ሲሆን በዚህም ሳቢያ 951 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል (ይህ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞችን ሳይጨምር ነው)። በመሆኑም በዚያ ዓመት በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ በእሳት አደጋ ከሞቱት ሰዎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች የሞቱት በሲጋራ ሳቢያ በተነሳ የእሳት አደጋ ነው፤ ይህም በሌላ በማንኛውም ምክንያት በተከሰቱት አደጋዎች ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። በዚያው ዓመት በማጨስ ምክንያት በተከሰቱት የእሳት አደጋዎች 3,381 ሰዎች አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 552 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት ወድሟል። በአብዛኛው በቀላሉ በእሳት የሚቀጣጠሉት የቤት ዕቃዎች እንደ ወንበርና ሶፋ ያሉ ምቾት ያላቸው ቁሳቁሶች፣ ፍራሾችና የአልጋ ልብሶች እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል።

ጠበኛ አሽከርካሪዎችን በጠባይ መያዝ

አንድ አሽከርካሪ በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረ በጎን በኩል አልፎ ከፊት ለፊትህ ይገባብህ ይሆናል፤ ወይም መንገድ እንድትለቅለት መብራት አብርቶብህ አልፎህ ሲሄድ በአካላዊ መግለጫ መጥፎ ነገር ተናገረህ እንበል። በዚህ ጊዜ የተሳሰተ እርምጃ ከወሰድክ ሕይወትህን ልታጣ ትችላለህ በማለት ኤክስፐርቶቹ ይናገራሉ። በደቡብ አፍሪካ እየታተመ የሚወጣው ሪደርስ ዳይጀስት ባወጣው ዘገባ መሠረት ኤክስፐርቶቹ የሚከተለውን ሐሳብ ይለግሳሉ:- የረጋ መንፈስ ይኑርህ፤ አትፎካከር። የራስህን አነዳድ ብቻ ተከታተል፤ ከሌላው አሽከርካሪ ጋር ዓይን ለዓይን ለመጋጨት አትሞክር። መስተዋቶችህን ከሦስት እስከ አሥር ሰከንዶች ባለው የጊዜ ልዩነት ተመልከት። ሊከሰት የሚችለውን አደጋ አስቀድመህ አስተውልና እርምጃ ውሰድ። አሽከርካሪው አልፎህ እንዲሄድ ፍጥነትህን ቀንስ፤ ወይም ፍሬቻ አሳይና ነፃ ወደሆነው መስመር እለፍ። “ከኋላህ ለሚከተልህ ጠበኛ አሽከርካሪ የምታሳየው ምላሽ ለደህንነትህ ብሎም ለሕይወትህ መትረፍ ቁልፍ ሊሆን ይችላል” ሲል ጽሑፉ ይደመድማል።

ኤድስ በደም አማካኝነት?

ኤድስ ደም በደም ሥር ሲወሰድ ወይም በደም ውጤቶች በኩል የመተላለፉ አጋጣሚ ምን ያህል ነው? በጆሃንስበርግ እየታተመ የሚወጣው ዘ ስታር የተባለው ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ ኤድስ ተለይቶ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ 600,000 ሰዎች ወይም በበሽታው ከተለከፉት ሰዎች መካከል 15 በመቶ የሚሆኑት በበሽታው ሊያዙ የቻሉት በደም ወይም በደም ውጤቶች አማካኝነት ነው። በአሁኑ ጊዜ የኤች አይ ቪ ምርመራ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ከፍተኛ ወጪም ይጠይቃል። አንዳንዶች ደም ቢያንስ ቢያንስ ሰባት ዓይነት የተለያዩ ምርመራዎች ሊካሄድበት ይገባል ይላሉ። ብዙውን ጊዜ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እነዚህን ምርመራዎች ለመጠቀም የገንዘብ አቅሙም ሆነ የሙያው ልምድ የላቸውም። ሌላው ቀርቶ ምርመራው በሚካሄድባቸው የበለጸጉ አገሮች እንኳ ስህተቶች ይፈጸማሉ። የሆላንድ የደም ባንክ የሕክምና ኃላፊ የሆኑት ፖል ስትሬንጀርስ “ኤች አይ ቪ ቫይረስን ወይም ሄፓታይተስን በተመለከተ የትኛውም የደም ውጤት መቶ በመቶ አስተማማኝ ነው ማለት አንችልም” ብለዋል።

የወላጅና የልጅ ግንኙነት ሊባል ይችላልን?

ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው አድርገው ሊይዟቸው ይገባልን? በሳኦ ፖሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያስተምሩት ሊሳንድሬ ማሪያ ካስቴሎ ብራንኮ ኦ ኤስታዶ ዲ ኤስ ፖሎ በተባለው የብራዚል ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ወላጆች በፍጹም ከልጆቻቸው ጋር እኩል አይደሉም። ይህ ግልጽ መደረግ ይኖርበታል። . . . ሥልጣኑ ምንም ሳይሠራበት ሲቀር ልጁን ዞር ብሎ የሚያየው አይኖርም። ወላጅ አልባ ይሆናል። አንድ ልጅ ምንጊዜም ቢሆን ወላጆቹ እንደ አንድ ጎልማሳ ሰው መጠን ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ይጠብቅባቸዋል።”

የይሖዋ ምሥክሮች በኩባ

በኩባ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ለማካሄድ የሚያስችል ተጨማሪ ነጻነት አግኝተዋል። ይህም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ለማካፈል አስችሏቸዋል። ምንም እንኳ ሥራው በይፋ ሕጋዊ ዕውቅና ባያገኝም ቀደም ሲል የነበሯቸውን ቢሮዎች እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል፤ እንዲሁም የአምልኮ ሥርዓታቸውን ለማካሄድ ከበፊቱ ይበልጥ በነጻነት መሰብሰብ ችለዋል። በመሆኑም መጠነኛ ተሰብሳቢዎችን ያቀፉ የወረዳና ልዩ ስብሰባዎች አድርገዋል። መጽሔቶችን ለማተም የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተዋል። ምሥክሮቹ በቅርብ ጊዜ በተከሰቱት በእነዚህ ክንውኖች ተደስተውና በጋለ መንፈስ ተሞልተው የመጽሐፍ ቅዱስን የተስፋ መልእክት ለሌሎች ለማካፈል በመጣር የስብከት ሥራቸውን ቀጥለዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ