“ከሕዝብ አድናቆት ያተረፈ የዓለማችን ምርጥ መጽሔት”
በዚህ መንገድ ነበር ባለፈው ዓመት ለናይጄሪያው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የደረሰው ደብዳቤ ንቁ! መጽሔትን የገለጸው። ጸሐፊዋ እንዲህ ብላለች:-
“በናይጄሪያ ውስጥ ሰፊ ተነባቢነት ያለው ዓለም አቀፉ ኒውስዎች ለከተማው የሚያዘጋጀው ዕትም ከሆነው ኤኮ መጽሔት ጋር አብሬ እሠራለሁ። ከምሥክሮቹ አንዷ ባልሆንም ከ1985 ጀምሮ የንቁ! መጽሔት ኮንትራት አለኝ። አንድ ቀን የኤኮ መጽሔትን ቀጣይ ዕትም እያዘጋጀን ሳለ አነበው የነበረውን ንቁ! [ሚያዝያ 22, 1991] ለትንሽ የሥራ ጉዳይ ስል ጠረጴዛ ላይ ትቼው ወጣሁ።
“አንዲት የሥራ ባልደረባዬ አየት አየት ለማድረግ በማሰብ መጽሔቱን ታነሣለች፤ ሆኖም ስለ ፍቺ የወጣውን ርዕስ በሙሉ አነበበችው። ሌላ ሰው መጽሔቱን ከርሷ ወሰደ፤ እንዲህ እንዲህ እያለ ካንዱ ወደ ሌላው ይሸጋገር ጀመር። ከመካከላቸው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የሆነች ሴት ንቁ! መጽሔትን ችላ ትለው እንደነበረና ‘ይህን ያህል የሚማርክ፣ አስደናቂ ትምህርት የሚሰጥ ርዕሶች ያሉት’ ጽሑፍ ታዘጋጃላችሁ ብላ በፍጹም አስባ እንደማታውቅ ነገረችኝ። ወዲያው እንዴት ኮንትራት መግባት እንደሚቻል ጠየቀችኝ። ሌላው ደግሞ መጽሔቶቹ በደረሱኝ ቁጥር እርሱም እንዲያነበው የራሴን ቅጂ እንዳውሰው ጠየቀኝ።
“እርግጥ ከምሥክሮቹ አንዱ ለመሆን ፍላጎቱ የሌለኝ ቢሆንም የንቁ! መጽሔት ኮንትራት ለመግባት ባደረግሁት ውሳኔ በፍጹም አልጸጸትም። ከሕዝብ አድናቆት ላተረፈው የዓለማችን ምርጥ መጽሔታችሁ አመሰግናችኋለሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ።”
የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ ዓላማዎች ሰዎች በይበልጥ እንዲማሩ ለመርዳት ራሳቸውን ያቀረቡ ከአራት ሚልዮን በላይ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚገኙበት ዓለም አቀፍ ድርጅት ናቸው።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ለማጥናት የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ.ሣ.ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።