የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 10/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች የማይሳኩት ለምንድን ነው?
  • በሕፃናት ላይ አደጋ እያስከተሉ ያሉ ነገሮች
  • ንዴትና የልብ ድካም
  • የተናጋ ዓለም
  • በአራስ ልጆች ፀጉር ላይ የተገኙ መርዘኛ ንጥረ ነገሮች
  • በመጀመሪያ ያየው ማን ነው?
  • የአልትራቫዮሌት ጨረር የሚያስከትላቸው ችግሮች
  • የቋንቋ እየቀነሰ መሄድ
  • ብዙ ማየት ጥቂት ማንበብ
  • አማራጭ ሃይማኖት ለማግኘት የሚደረግ ፍልሰት
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንስሐ ልትገባ?
  • እግር ኳስን ከልክ በላይ ማፍቀር
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1995
  • እየተመናመነ የሚገኘው የምድር የተፈጥሮ ሀብት
    ንቁ!—2005
ንቁ!—1994
g94 10/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች የማይሳኩት ለምንድን ነው?

“ዓለም ወደ 1994 ያሸጋገረቻቸው 35 ጦርነቶች ቅዱሳን ጽሑፎች ጦርነትና የጦርነት ወሬ ምን ጊዜም አይጠፋም ሲሉ የተናገሩትን ትንቢት ያረጋግጣሉ” ሲል ቶሮንቶ ስታር ያወጣው አንድ ርዕስ ገለጸ። (ይህ አነጋገር ትክክል አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ጦርነቶች በሙሉ እንደሚቆሙ ትንቢት ይናገራል። ኢሳይያስ 2:​2–4 ተመልከት።) “ዛሬ ባለው ዓለም ላይ የሚካሄዱት ሦስት ደርዘን ጦርነቶች በጠቅላላ ­በነጠላ መንግሥታት ውስጥ የሚደረጉ ናቸው።” አንዱም እንኳ ቢሆን በመንግሥታት መካከል የተደረገ አይደለም። የእነዚህ የእርስ በርስ ጦርነቶች መጧጧፍ የዓለም ወኪሎች አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አቅም እንደሌላቸው የሚጠቁም ነው። “ተፋላሚ ወገኖች የተባበሩት መንግሥታት የእሱ አባል በሆኑት መንግሥታት መካከል እንኳ የተወሰነ የሥነ ምግባርና የሰብአዊ መብቶችን ሊያስከብር እንደማይችል ስለሚያውቁ ጥያቄያቸውን ለማስፈጸም የኃይል እርምጃ መውሰዳቸውን ይገፉበታል” ሲል ርዕሱ ያትታል። “እንደ እውነቱ ከሆነ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሦስተኛው ዓለምም ሆነ በሌላ በየትም ቦታ እርስ በርስ ወይም በአገር ውስጥ የሚደረጉትን ግጭቶች ለማስቆም በተሳካ ሁኔታ ያገለገለ በምሳሌነት የሚጠቀስ የሰሜን መንግሥታት አንድም ወታደራዊ ኃይል የለም።” እንዲያውም እርስ በርስ ለሚደረጉ ጦርነቶች ዝግጅት የሚውለው ገንዘብ ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊመሩ የሚችሉትን ሁኔታዎች ለማሻሻል መዋል ሲገባው የእርስ በርስ ግጭት እንዲባባስ እያደረገ ነው።

በሕፃናት ላይ አደጋ እያስከተሉ ያሉ ነገሮች

ጃፓን የተለያዩ መርዞችን የሚውጡ “ገና በመዳኽ ላይ የሚገኙ” ሕፃናት ቁጥር በጣም እየጨመረ መምጣቱን እንደ ደረሰችበት የጤናና የሕዝብ ደህንነት ሚኒስቴር በቅርቡ ገለጸ። በ1992 ሕፃናት ከዋጧቸው መርዛማ ነገሮች መካከል ግማሽ የሚያክሉት ሲጋራን ይጨምራሉ። አንዳንዶች በመጠጥ ቆርቆሮዎች ወይም ፈሳሾች ባሉባቸው በሲጋራ መተርኮሻዎች ውስጥ የቀረውን የሲጋራ ቁርጥራጮችና የአመድ ቅልቅል ጠጥተዋል። ሕፃናት የዋጧቸው ሌሎች አደገኛ ነገሮች ባስከተሉት ጉዳት ቅደም ተከተል ሲቀመጡ መድኃኒቶች፣ መጫዎቻዎች፣ ሳንቲሞች፣ የምግብ ተዋጽኦዎችና ቅባቶች ይገኙበታል። አብዛኞቹ ሁኔታዎች ከባድ ሕመም አስከትለዋል። ከእነዚህ አደጋዎች አብዛኞቹ የሚደርሱት ብዙዎቹ የቤተሰብ አባሎች ቤት ውስጥ በሚኖሩበትና ልጆችን መጠበቅ በሚችሉበት ከምሽቱ 11 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ባሉት ጊዜያት መካከል መሆኑን ሚኒስቴሩ አስጠንቅ⁠ቋል።

ንዴትና የልብ ድካም

“የልብ ሕመም ያለባቸው ሰዎች በሚናደዱበት ጊዜ ለልብ ድካም የመጋለጣቸውን ሁኔታ ከእጥፍ በላይ የሚጨምር ሲሆን ይህም አስጊ ሁኔታ ለሁለት ሰዓት ይቆያል” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በንዴትና በከፍተኛ የልብ ምት፣ በከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም በደም ሥር መዘጋት መካከል ግንኙነት እንዳለ ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች ያመለከቱ ቢሆንም ንዴት ወዲያው ወደ ልብ ድካም ሊመራ እንደሚችል የሚጠቁም ሳይንሳዊ ጭብጥ በማቅረብ ረገድ ግን ይህ አዲስ ጥናት የመጀመሪያው ነው። የሚያናድድ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ረጋ ለማለት መሞከር አደጋውን ሊቀንሰው ይችል ይሆናል ሲሉ የጥናቱ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ማሬይ ሚትልማን ተናግረዋል። “የልብ ድካም እንዲከሰት የሚያደርገውን አደጋ የሚቀንሰውን አስፕሪንን የሚወስዱ ሰዎች በንዴት መገንፈል ከሚያስከትላቸው ውጤቶች በከፊል እንደሚድኑ ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል” ሲል የቀረበው ዘገባ ይገልጻል። ምናልባትም አስፕሪን ፕሌትሌቶች ደም እንዲረጋና የደም ሥሮች እንዲዘጉ የማድረግ አቅማቸውን ስለሚቀንስ ይሆናል። ስለሆነም ንዴት የደም ፕሌትሌቶችን ሊነካ ይችል ይሆናል ሲሉ ዶክተር ሚትልማን ተናግረዋል።

የተናጋ ዓለም

በጀርመን ውስጥ የሚገኘው የሃምበርግ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተቋም እንዳለው ከሆነ 1994 ሲጀምር ዓለም በ43 ጦርነቶች ተናግታ ነበር። የኢኩሜኒካል የሕትመት አገልግሎት በሪፖርቱ ላይ ያለውን አስተያየት ሲሰጥ በእስያ 22፣ በአፍሪካ 13፣ በላቲን አሜሪካ 5 እንዲሁም በአውሮፓ 3 ጦርነቶች እንደተነሱ ጽፏል። በተጨማሪም ተቋሙ በ19 50ዎቹ በየዓመቱ የሚደረገው ጦርነት በአማካይ ከ12 እንዳልዘለለ ደርሶበታል። በ1960ዎቹ ወደ 22 ከፍ ሲል በአሁኑ ወቅት ያ ቁጥር እጥፍ ያህል ሆኗል።

በአራስ ልጆች ፀጉር ላይ የተገኙ መርዘኛ ንጥረ ነገሮች

ሌላ ሰው ሲያጨስ የሚቦነውን የሲጋራ ጭስ የማያጨሱ እርጉዝ ሴቶች ወደ ውስጥ በሚተነፍሱበት ጊዜ ጭሱ ወደ ፅንሱ እንደሚገባ የሚያረጋግጥ ባዮሎጂካል የሆነ ማስረጃ ተግኝቷል በማለት በቶሮንቶ ካናዳ የሚታተመው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ተናገረ። በቶሮንቶ የሕፃናት ሆስፒታል ክሊንክ ውስጥ ፋርማኮሎጂስት በሆኑት በዶክተር ጊዲዮን ኮረን የሚመራ አንድ ተመራማሪ ቡድን እንደጠቆመው ከአራስ ልጆች ላይ የተወሰደው የፀጉር ናሙና ኒኮቲንና የኒኮቲን ውጤት የሆነው ኮቲኒን የተባለው ንጥረ ነገር ተገኝቶበታል። የማያጨሱ እናቶች በቤት አሊያም በሥራ ቦታ በቀን ቢያንስ ለሁለት ሰዓት ያህል ሌላ ሰው ሲያጨስ ለሚቦነው የሲጋራ ጭስ የተጋለጡ ናቸው። ዶክተር ኮረን እንደሚሉት ሌላ ሰው ሲያጨስ የሚቦነውን የሲጋራ ጭስ ዘወትር ወደ ውስጥ መተንፈስ “በቀን ከሁለት እስከ አራት ሲጋራ እንደማጨስ ያክል” ሊሆን ይችላል። ይህ አዲስ ምርምር “የሕፃናት ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ ጠባያቸውንና አእምሮአዊ እድገታቸውን ይነካል የሚል ሐሳብ ላቀረቡት ቀደም ሲል ለተደረጉት ጥናቶች ይበልጥ ክብደት ይሰጣቸዋል።” ዘ ግሎብ አክሎም ዶክተር ኮረን “አሁን በምንኖርበት የተሟጋችነት መንፈስ ባለበት ሁኔታ በ10 እና በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሲጋራ የተነሣ በትክክል እንዳልወለድ በደል ደርሶብኛል ብለው በወላጆቻቸው ላይ ክስ መሥርተው ካሳ የሚጠይቁ ሕፃናት ይታጣሉ ብዬ ልናገር አልችልም!” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘግ⁠ቧል።

በመጀመሪያ ያየው ማን ነው?

በቅርቡ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ “ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስ ከማንም በፊት ይኸውም ኢየሱስ መነሣቱን መልአኩ ለሴቶቹ ከመግለጹ በፊት ለማዶና ተገልጧል” የሚለውን እምነት በመደገፍ ተናግረዋል ሲል ኮሪየር ዴላ ሴራ ገለጸ። ይህ ወንጌሎች በጭራሽ የማይደግፉት አመለካከት በአንዳንዶች ዘንድ ምንም መደናገር አልፈጠረም። ስለ ጳጳሱ አመለካከትና ማርያም በካቶሊክ እምነት ውስጥ ስለምትጫወተው ሚና ሰርጅዎ ኩንዚዮ የተባለ ኢጣሊያዊ ጸሐፊ አስተያየት ሲሰጥ ካቶሊኮች ለማሪያም ያላቸው “ከፍተኛ ፍቅር” ሁልጊዜ “በቅዱሳን ጽሑፎች ከተላለፈልን እንዲያልፉ አድርጓቸዋል” ብሏል። አክሎ ሲናገርም ይህ በጣም በቅርቡ የወጣው “ድርቅ ያለ ድንጋጌ ጥቅሶችን እነሱ ካሉት ውጪ ያደርገዋል” ብሏል።

የአልትራቫዮሌት ጨረር የሚያስከትላቸው ችግሮች

የእረፍት ጊዜህን ፀሐይ እየሞቅህ በመዝናናት ማሳለፍ ትወዳለህን? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ተጠንቀቅ! ምንም እንኳን የፀሐይን አልትራቫዮሌት ጨረር በመጠኑ ማግኘት ጠቃሚ ቢሆንም ከመጠን በላይ ለዚህ ጨረር መጋለጥ የቆዳ ካንሰር፣ የዓይን በሽታ፣ ያለ ዕድሜ የቆዳ መጨማደድ፣ ቂመኛ የቆዳ ቁስል ሊያስከትል እንዲሁም የሰውነትን በሽታን የመቋቋም ኃይል ሊያዳክም ይችላል። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳመለከተው የኦዞን ንብርብር በመሳሳቱ የተነሣ የአልትራቫዮሌት ጨረር መጠን እየጨመረ ነው። በአሁኑ ጊዜ አውስትራሊያን፣ ኒው ዚላንድንና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በብዙ የዓለም ክፍሎች የአልትራቫዮሌት ጨረር የሚያስከትላቸው ችግሮች በፍጥነት እየተስፋፉ ነው። በጣም ፀሐያማ የሆነ የአየር ጠባይ ባለበት ወቅት ራስህን የምትከላከለው እንዴት ነው? የፀሐይ ጨረር የሚከላከል ልብስ በመልበስ፣ የአልትራቫዮሌት ጨረር የሚከላከል የፀሐይ መነፅር በማድረግና የአልትራቫዮሌት ጨረር በጣም ኃይለኛ በሚሆንበት በቀትር ጊዜ ቤት ውስጥ በመሆን ነው።

የቋንቋ እየቀነሰ መሄድ

በ100 ዓመት ውስጥ ዛሬ ከሚገኙት 6,000 ቋንቋዎች መካከል ግማሽ የሚያህሉት ይጠፋሉ ሲል አትላስ ኦቭ ዘ ወርልድስ ላንጉዊጅስ የተባለው መጽሐፍ ተንብዮአል። ባለፉት 500 ዓመታት ውስጥ 1,000 የሚሆኑ ቋንቋዎች ጠፍተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ በአሜሪካና በአውስትራሊያ የሚገኙ ነበሩ። ብዙ ቋንቋዎች በትምህርት መልክ መሰጠታቸው ቀርቷል። የአገሬው ሕዝብ 20 ቋንቋዎች በሚናገርባት በአላስካ ልጆች የሚማሯቸው ቋንቋዎች 2 ብቻ ናቸው። ፓፑአ ኒው ጊኒ እያንዳንዳቸው ከ300 የሚያንሱ ተናጋሪዎች ያሏቸው 155 ቋንቋዎች ሲኖሯት በአውስትራሊያ ደግሞ ከ200 የአቦርጂናውያን ቋንቋዎች መካከል ሳይጠፉ እስከ አሁን ያሉት 135 ቋንቋዎች እያንዳንዳቸው ከ10 በሚያንሱ ሰዎች የሚነገሩ ናቸው። “እየጠፉ ያሉት ራሳቸው ቋንቋዎቹ ብቻ ሳይሆኑ በቃል ይነገሩ የነበሩትም ሆኑ በጽሑፍ የሰፈሩት ባሕሎች ጭምር ባጠቃላይ እየጠፉ ናቸው፤ ልዩ የሆኑ የሰዋስውና የቃላት ዘዴዎች ያንኑ ያህል ልዩ የሆኑ የአስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤዎችን ያንጸባርቃሉ፤ ቋንቋ በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ የሰው ባሕሎች መሠረት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ቋንቋዎች ዓለምን ይህ ነው በማይባል መጠን የባሕል ድሀ አድርገዋት ይጠፋሉ” በማለት የለንደኑ ኢንድፔንደንት ጋዜጣ ዘግቧል።

ብዙ ማየት ጥቂት ማንበብ

ቴሌቪዥን በብዛት የሚመለከቱ ተማሪዎች የማንበብ ፍላጎታቸው የሚቀንሰው ለምንድን ነው? ሲ ኤም ኩልስትራ የተባሉ ተመራማሪ በኔዘርላንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የ1,000 ልጆችን ባሕርይ ለሦስት ዓመታት ካጠኑ በኋላ ሁለት ምክንያቶችን አግኝተዋል። ልጆች ቴሌቪዥን በብዛት ሲመለከቱ ከንባብ የሚያገኙትን ደስታ ያጣሉ እንዲሁም የማተኮር ችሎታቸው ይቀንሳል። በኔዘርላንድ ከሚገኘው ሌዲን ዩኒቨርሲቲ ዜና እንደተሰማው ቀስ በቀስ የሚያነቡትን ነገር መጨበጥና አእምሮአቸው ከፊት ለፊታችው ባለው ገጽ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይከብዳቸዋል። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፋቸውን ይጥሉና ሪሞት ኮንትሮል ይፈልጋሉ። ተመራማሪው የፕሮግራሙ ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣም ደርሶበታል። ልጆቹ ብዙ አስቂኝ ትርዒቶችን፣ የልጆች ፕሮግራሞችን፣ ድራማዎችን ወይም እውቀት ሰጪ ፕሮግራሞችን ይመልከቱ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው:- “የንባብ መቀነስ።”

አማራጭ ሃይማኖት ለማግኘት የሚደረግ ፍልሰት

የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ቀሳውስት እየፈለሱባት ነው። ለምን? “መንስኤው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሴት ቀሳውስትን ለመሾም ያደረገው አከራከሪ ውሳኔ ይመስላል” ሲል ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ስታር “ከ130 የሚበልጡ የአንግሊካን ቀሳውስት ኮብልለዋል። አሁንም ሌሎች በብዛት የሚኮበልሉ ይመስላል። 7 የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና 700 ቀሳውስት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን አጋጣሚ እየፈለጉ ነው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ለእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ድጋፍ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል። በእንግሊዝ ውስጥ የተጠመቅን አንግሊካን ነን ከሚሉት 20 ሚልዮን ሰዎች ውስጥ እሑድ ቅዳሴ ላይ የሚገኙት አንድ ሚልዮን ብቻ ናቸው። አስቸጋሪ ጊዜያት ይጠብቋቸዋል። ከቤተ ክርስቲያኑ መፍለስ የሚቀጥል ይመስላል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንስሐ ልትገባ?

ለካቶሊክ ካርዲናሎች በተላከ ደብዳቤ ላይ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያኒቱ “አባሎቿ በስሟ” የፈጸሟቸውን ስሕተቶች እንድትቀበልና ንስሐ እንድትገባ አጥብቀው አሳስበዋል። ጳጳሱ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተጠቀመችባቸው “ሰብአዊ መብቶችን የሚገፉ የማስገደጃ ዘዴዎች በ20ኛው መቶ ዘመን አምባገነን ፖለቲከኞች እንደተሠራባቸው አምነዋል” ሲል የሮሙ ላ ሪፓብሊካ ገልጿል። ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንስሐ የምትገባው ከምንድን ነው? የቫቲካን ዘጋቢ ማርኮ ፖሊቲ “ከብዙ ነገሮች” ሲል አምኗል። “ጠንቋዮችን እያሳደደች ከማደን፣ መናፍቆች በእንጨት ላይ በእሳት እንዲቃጠሉ ከመላክ፣ ሳይንቲስቶችንና በሃይማኖት ረገድ የራሳቸው አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ከማሠቃየት፣ ፋሽስት መንግሥታትን ከመደገፍ፣ በመስቀል ስም በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ስለተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች” እንዲሁም “ራሷን ሕሊናን በተመለከተ ሙሉ ሥልጣን በአደራ ሊሰጣት የሚገባ ፍጹም ኅብረተሰብ አድርጋ መቁጠሯንና በአንድ የታሪክ ወቅት ጳጳሱ የክርስቶስ ወኪል ነው ብላ ከማመኗ (ካደረሳቸው ሃይማኖታዊ ስድብ) ንስሐ መግባት አለባት” ብሏል።

እግር ኳስን ከልክ በላይ ማፍቀር

በኢንግላንድ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ለኳስ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ እንዲህ ያለ ያልተለመደ ነገር ሲያደርጉ ይታያሉ:- ሲሞቱ አስከሬናቸው ተቃጥሎ አመዱ የሚደግፉት ቡድን በሚጫወትበት ሜዳ ላይ እንዲበተን ይጠይቃሉ። አንድ ዝነኛ ቡድን በየዓመቱ 25 የሚጠጉ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ይቀበላል። ይህ ድርጊት በጣም እየተስፋፋ ስለመጣ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር እንደዚህ ያሉት የሰው አስክሬኖች እንዴት መቀበር እንዳለባቸው የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ለእግር ኳስ ክለቦች ለማውጣት ተገዷል። ዘ ሜዲካል ፖስት እንዳለው ከሆነ መመሪያቸው የሚከተለውን ሐሳብ ይጨምራል:- “አመዱን በሙሉ መበተን አያስፈልግም። ትንሽ ቆንጠር አድርጋችሁ ልትበትኑ ትችላላችሁ። አመዱን መቆለል ግን ሳሩ እንዲደርቅ ያደርጋል። . . . አመዱ በስሱ እንዲበተን በመጥረጊያ ጥረጉት።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ