የቪክቶሪያ ሐይቅ ተጫዋች ወፍ
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ጀልባችን ጸጥ ባለው የቪክቶሪያ ሐይቅ ባሕር ላይ ስትቀዝፍ ከቆየች በኋላ ዓይናችን በድንገት አንድ ነገር ላይ አረፈ። በሐይቁ ዳርቻ በሚገኝ አንድ ያረጀ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ግዙፍ የሆነ የወፍ ጎጆ አየን። የጎጆው ስፋት 1.8 ሜትር ያህል ሲሆን አንድ ግዙፍ ፍጥረት ማስጠለል የሚችል ነው።
ይህን ጎጆ ከቅርብ ለማየት ስለ ቆረጥን ጀልባችንን በትልቁ ዛፍ ግርጌ በሚገኝ አንድ ቋጥኝ ላይ ካሰርን በኋላ ጎጆው ወደሚገኝበት ቅርንጫፍ ላይ መውጣት ጀመርን። ከጀልባችን ነጂ በስተቀር የቀረ ሰው አልነበረም። በሐይቁ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ወደዚህ ወፍ ፈጽሞ አይቀርቡም። ስሙ የወንዝ ዓመቴ ይባላል።
ወደ ጎጆው ቀረብ ስንል ከዚህ በፊት ካየናቸው የወፍ ጎጆዎች በሙሉ ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ተመለከትን። ወንዱና ሴቷ የወንዝ ዓመቴዎች የቤታቸውን “መሠረት” ለመጣል ብቻ የሦስትና የአራት ቀን ከባድ ልፋት ይጠይቅባቸዋል። መሠረቱ ዘርዘር ያለ ይሆንና የወጭት መልክ ይዞ ይወጣል። ከቄጠማ፣ ከጭራሮና ከገለባ የተሠራ ነው። ይኸኛው የግንባታ ደረጃ ሲጠናቀቅ ዙሪያውን ግድግዳ ከሠሩ በኋላ ከበስተጀርባ ጀምረው ጣሪያውን ይሠራሉ። ጣሪያው በግማሽ ሲጠናቀቅ ሴቷ ከጎጆዋ መውጣት ታቆማለች። ወንዱ ተጨማሪ የግንባታ ዕቃዎችን ለማሰባሰብ ሲማስን እርሷ አርፋ ትቀመጣለች።
የፊቱ በረንዳ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ውጭውንና የውስጠኛውን ክፍል በጭቃ ይለስኑታል። ከዚያ በኋላ ጎጆው ውኃ የማያስገባና የሚሞቅ እንዲሆን የተለያዩ ነገሮች በጣሪያውና በግድግዳው ላይ ይደርባሉ። በመጨረሻም ቤታቸው በተለያዩ ነገሮች “ያጌጣል።” የቆርቆሮ ጣሳዎች፣ የእባብ ቆዳዎች፣ የጨርቅ ቁርጥራጮችን በአጠቃላይ ወንዴው ወፍ ያገኘውን ማንኛውንም ነገር በጎጆው አናት ላይ ይከምራል። ጠቅላላው የግንባታ ፕሮጀክት በአምስት ወይም በስድስት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል።
ጎጆውን በትኩረት ከመረመርን በኋላ ወደ ጀልባችን ተመልሰን መጠባበቅ ጀመርን። የዚያ ግዙፍ ጎጆ ባለቤት የሆነው የወንዝ ዓመቴ በታላቅ ግርማ መጥቶ በጎጆው ጣሪያ ላይ የሚያርፍበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ይሁን እንጂ የመጣው ወፍ እንዳሰብነው ግዙፍ አልነበረም። ቁመቱ ከ56 ሳንቲ ሜትር የማይበልጥ ቡናማ መልክ ያለው ተራ ወፍ ነበር። ከአናቱ በስተቀር ምንም ልዩ ነገር አይታይበትም። አፉ ወፈር ያለና ከበስተኋላው ትልቅና ችምችም ያለ ጉትዬ ስላለው ከመዶሻ ጋር የሚመሳሰል መልክ አለው።
የወንዝ ዓመቴው ወዲያው ተጫዋቹ ወፍ የሚል ስም ያተረፈለትን እንቅስቃሴ ጀመረ። ጮክና ቀጠን ባለ ድምፅ ካስካካ በኋላ መጨፈር ጀመረ። ወዲያው ሚስቲቱ ብቅ አለችና ጀርባው ላይ ከተፈናጠጠች በኋላ አስቂኝ ጭፈራቸውን ተያያዙት። የዚህ ወፍ እንቅስቃሴ በዚህ አያበቃም። በሐይቁ ዳርቻ ከተሠራ ቪላ ቤቱ ቁልቁል ይወርድና እንቅልፍ በተኛ አንድ ጉማሬ ጀርባ ላይ ያርፋል። ጉማሬው ሲንቀሳቀስ ከሥሩ ያለው ውኃ በጭቃ ይደፈርሳል። በዚህ የተደናገጡ እንቁራሪቶች እየዋኙ ወደ ላይ ሲወጡ የወንዝ ዓመቴው ይለቃቅማቸዋል። የወንዝ ዓመቴ ከሚመገባቸው እንስሳት መካከል ትናንሽ ዓሣዎች፣ ትላትሎችና ክረስቴሻዎች ይገኙበታል።
የወንዝ ዓመቴን ተጫዋችም በሉት ጎበዝ አናጢ በእርግጥ በጣም አስደናቂና የፈጣሪያችን ገደብ የለሽ ጥበብ የተንጸባረቀበት ወፍ ነው።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የወንዝ ዓመቴና ጎጆው