የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 8/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አውቶማቲክ መስኮቶች
  • ሙዚቃ ሕፃናትን ይረዳል
  • ቴሌቪዥን በልጆች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ
  • በእግር መሄድ ዕድሜ ሊያስረዝም ይችላል
  • የባሕር ዳርቻዎች ሥነ ምህዳር
  • የምድራችን የምግብ ፍጆታ
  • የአደጋ መከላከያ ቀበቶና በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርስ ሞት
  • ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢል የተባሉ የዓሣ ዝርያዎች
  • ምሥራቅ አፍሪካ በኮሌራ ወረርሽኝ ተመታች
  • የማንበብ ልማድ
  • በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት እንደ ጭስ እየበነነ ነው
    ንቁ!—1999
  • ከሲጋራ ትርቃለህን?
    ንቁ!—1997
  • አገርዎ ዋነኛ ዒላማ ተደርጎ ይሆን?
    ንቁ!—1994
  • የትምባሆ ጠበቆች በሞቃት አየር የተሞሉ ባሉኖቻቸውን መተኮስ ጀምረዋል
    ንቁ!—1999
ንቁ!—1998
g98 8/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

አውቶማቲክ መስኮቶች

አውስትራሊያ በሚገኘው የስድኒ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች ዝቅ ብሎ የሚበር አውሮፕላን ሲቀርብ ራሱ አውቆ የሚዘጋ መስኮት ፈልስፈዋል። ረባሹ ድምፅ ካለፈ በኋላ መስኮቱ ተመልሶ ይከፈታል። ከውጭ በኩል የተገጠመው የድምፅ ማጉያ በመስኮቱ ውስጥ በተገጠመ የኮምፒዩተር ሶፍትዌር በመታገዝ ከከባድ መኪና እንደሚወጡ ያሉ ረባሽ ድምፆች ያላቸውን ፍሪክዌንሲ መለየት ይችላል። እነዚህ መስኮቶች የጫጫታን መጠን እስከ 20 ዲሲብል ድረስ መቀነስ እንደሚችሉና ከእንቅልፍ የሚያባንኑ ድምፆችን እንደሚያስወግዱ በተደረገው ፍተሻ ማረጋገጥ ተችሏል። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ይህ መሣሪያ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ዋነኛው ብዙ ወጪ የሚጠይቅ የሙቀት ማስተካከያ መሣሪያ መግጠም ሳያስፈልግ ሕንጻዎችን በቂ አየር የሚገባባቸውና ከውጭ በሚመጡ ድምፆች እንዳይረበሹ ለማድረግ ማስቻሉ ነው።”

ሙዚቃ ሕፃናትን ይረዳል

የሦስት ወይም የአራት ዓመት ሕፃናትን ሙዚቃ እንዲጫወቱ ማስተማር የማ ሰብና የማመዛዘን ችሎታቸውን እንደሚያዳብር በኧርቪን ከተማ የሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጎርደን ሾው ይናገራሉ። በዚህ ለጋ ዕድሜ የአንጎል ሕዋሳት (ኒውሮን) ትስስር ገና መደራጀታቸው ስለሆነ በቀን ውስጥ ለአሥር ደቂቃ እንኳን ሙዚቃ መለማመድ “አንድ ሕፃን ወደፊት የሚኖረው የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ እንዲሻሻል እንደሚያደርግ” የተለያዩ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። ዘጠኝ ወራት በፈጀ አንድ ጥናት የፒያኖ ትምህርት የተሰጣቸው ሕፃናት የኮምፒዩተር ትምህርት ከተሰጣቸው ወይም ምንም ዓይነት ሌላ ትምህርት ካልተሰጣቸው ሕፃናት ጋር እንዲወዳደሩ ተደርጓል። የፒያኖ የመጫወት ሥልጠና የተሰጣቸው ልጆች በተሰጣቸው የብልህነት ፈተና ውጤት ላይ 35 በመቶ ማሻሻል ሲያሳዩ የተቀሩት ሁለቱ ወገኖች ግን ያሳዩት መሻሻል በጣም አነስተኛ ወይም ምንም ዓይነት መሻሻል እንዳልታየባቸው የለንደኑ ሰንደይ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል።

ቴሌቪዥን በልጆች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ

ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው የሜክሲኮ ጋዜጣ ሪፖርት እንዳደረገው “ከ6 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ጠባይ በአብዛኛው የሚቀረጸው በትምህርት ቤታቸው ሳይሆን በካርቱን ፊልሞችና በቪዲዮ ጨዋታዎች ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ልጆች ቴሌቪዥን በማየት የሚያሳልፉት ጊዜ በሳምንት 38 ሰዓት ሲሆን በትምህርት ክፍል ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ ግን በሳምንት 23 ሰዓት ብቻ ነው።” ኦማር ቶርብላካ የተባሉት ተመራማሪ ቴሌቪዥን ልጆች ጥሩ ይሁን መጥፎ ሳይታወቃቸው በተለያዩ ሁኔታዎች የትኛውን ዝንባሌ ማዳበር እንደሚኖርባቸው እንደሚያስተምራቸው ተገንዝበዋል። እንዲህ በማለት ይገልጻሉ:- “ሕፃኑ አንድ ገጸ ባሕርይ በመታሠሩ ምክንያት የተሳካ ውጤት እንደተገኘ የሚያሳይ ካርቱን ወይም ፊልም ቢመለከት እርሱም ይህንኑ ድርጊት ለመኮረጅ መፈለጉ አይቀርም።” “ልጆች ትምህርት ቤትን እንደ ግዴታ ስለሚመለከቱ በዕለታዊ ኑሯቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት በትምህርት ቤት የሚማሩትን ነገር ሳይሆን በየቀኑ ከቴሌቪዥን የሚያዩትን እንደሆነ” የቶርብላካ ምርምር አረጋግጧል።

በእግር መሄድ ዕድሜ ሊያስረዝም ይችላል

በየቀኑ በእግር መሄድ ዕድሜ ሊያስረዝም እንደሚችል ኤዥያዊክ ገልጿል። ዕድሜያቸው ከ61 እስከ 81 በሆነና በእግር መሄድ በሚችሉ 707 በሚያክሉ ትንባሆ በማያጨሱ ወንዶች ላይ 12 ዓመት የፈጀ ጥናት ተደርጎ ነበር። የጥናቱ ሪፖርት “ዘና ብለው በየቀኑ 3.2 ኪሎ ሜትር በእግር የሄዱት ሞትን በሚያስከትሉ በሁሉም ምክንያቶች የመሞት አጋጣሚያቸው በግማሽ ቀንሶ እንደተገኘ” ገልጿል። በእግር የማይሄዱት ቢያንስ በየቀኑ 3.2 ኪሎ ሜትር ይሄዱ ከነበሩት በሁሉም የካንሰር ዓይነቶች የመያዝ አጋጣሚያቸው 2.5 ጊዜ ከፍ ብሎ ተገኝቷል። ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን ላይ ታትሞ የወጣው ይህ ጥናት በቀን 800 ሜትር ያህል እንኳን በእግር መሄድ የመሞትን አጋጣሚ እንደሚቀንስ አረጋግጧል። ከዚህ በፊት የአካላዊ ብቃት ጠበብት እንዲህ ያለው አድካሚ ያልሆነ ቀላል እንቅስቃሴ ብዙም ጥቅም ያለው አይመስላቸውም ነበር። አሁን ግን ይህ አዲስ ጥናት “አረጋውያን በእግር እንዲሄዱ ማበረታታት ለጤንነታቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።

የባሕር ዳርቻዎች ሥነ ምህዳር

አንድ የባሕር ዳርቻ በጣም ንጹሕ እንዲሆን በማድረግ ሕልውናውን ማጥፋት ይቻላል? በዌልስ አገር በስዋንሲ ባሕር ዳርቻ ላይ የተደረገ አንድ ጥናት አዎን ይቻላል ይላል። ለአንድ የባሕር ዳርቻ ጤናማ መሆን ቁልፉ በቀን ሁለት ጊዜ የባሕሩ ሞገድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የሚተፋው የቆሻሻ ክምር መኖሩ ነው። ይህ ቆሻሻ በባሕር ውስጥ የሚበቅሉ ዕፀዋትን ጨምሮ ዛፎችን፣ ጉማጅ እንጨቶችን፣ አልጌዎችን፣ ሣሮችንና የሞቱ እንስሳትን ሬሳ ሳይቀር ሊጨምር ይችላል። ይህ የቆሻሻ ጥርቅም የዕፀዋቱን ብስባሽ ለሚያብላሉ ጥቃቅን ነፍሳት መቀፍቀፊያ ይሆናል። በእነዚህ ነፍሳት የተብላላው ብስባሽ በነፋስና በባሕር ሞገድ ኃይል ይበተንና ለአሸዋ መጋገር ምክንያት ይሆናል። በተጨማሪም የባሕሩ ጠረፍ ለአእዋፍና እንደ አይጥ፣ ጥንቸልና ቀበሮ ላሉት እንስሳት ምግብ ያስገኛል። የባሕር ዳርቻዎችን ሙልጭ አድርጎ ማጽዳት በጣም ውስብስብ በሆነው የሥነ ምህዳር ሚዛን ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ሊታወቅ የቻለው በባሕር ጠረፎች አካባቢ ምግባቸውን ይለቃቅሙ የነበሩ አእዋፍ እየጠፉ መሄዳቸው ነበር። ብዙ የባሕር ዳርቻ አፍቃሪዎች ከልክ በላይ ንጽሕ የሆነ የባሕር ዳርቻ ይፈልጋሉ። እንዲያውም አንድ ጎብኚ ከአሸዋ ውስጥ ጠጠሮች ተለቅመው እንዲወገዱ እንደጠየቀ የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል።

የምድራችን የምግብ ፍጆታ

የዓለማችን ሕዝብ በየቀኑ ምን ያህል ቀለብ እንደሚፈጅ አስበህ ታውቃለህ? ቶ ቪማ የተባለው የግሪክ ጋዜጣ ይህን በሚመለከት አስገራሚ የሆኑ አሐዛዊ መረጃዎችን አውጥቷል። በመላው ዓለም በቀን ሁለት ቢልዮን የሚያክሉ እንቁላሎች ተመርተው ይበላሉ። ይህም የቆጵሮስ ደሴትን ስፋት የሚያክል ኦመሌት ለመሥራት የሚበቃ እንቁላል በየቀኑ ይበላል ማለት ነው! የዓለም ሕዝብ 16 ሚልዮን ኩንታል የሚያክል በቆሎ በየቀኑ የሚቀለብ ሲሆን ምግባችንን ለማጣፈጥ 5,000,000 ኩንታል ጨው እንፈጃለን። በተጨማሪም ድንች በብዙዎች የሚዘወተር ምግብ ሲሆን 7,270,000 ኩንታል ድንች ይበላል! ሩዝን ዋነኛ ምግባቸው ያደረጉ ሕዝቦች በጣም ብዙ ሲሆኑ በየቀኑ 15 ሚልዮን ኩንታል ሩዝ ይመረታል። ከዚህ ውስጥ 3,650,000 ኩንታል የሚሆነውን የሚቀለቡት ቻይናውያን ናቸው። 70,000 ኩንታል የሚያክል የሻይ ቅጠል እየተፈላ ሦስት ቢልዮን ኩባያ የሚያክል ሻይ ይጠጣል። ባለጠጎቹ 27 ኩንታል የሚያክል ካቪያር የተባለ ከዓሣ የሚሠራ ምግብ ይመገባሉ። በምዕራቡ ዓለም የሚኖር አንድ ሙሉ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው በቀን 4,000 ካሎሪ ይመገባል። ሊቃውንት አንድ ሰው በቀን 2,500 ካሎሪ ቢመገብ ጥሩ እንደሚሆን ሲናገሩ በአፍሪካ የሚኖሩ ሕዝቦች በአማካይ የሚመገቡት በቀን 1,800 ካሎሪ ብቻ ነው።

የአደጋ መከላከያ ቀበቶና በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርስ ሞት

የኮስታ ሪካ ሕገ መንግሥታዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመኪና አሽከርካሪዎች የአደጋ መከላከያ ቀበቶ እንዲያደርጉ የሚያስገድደውን ሕግ የግለሰቦችን ነጻነት የሚገድብ ሕግ ነው በማለት እንደሻረው የሳን ጆሴ፣ ኮስታ ሪካ ዘ ቲኮ ታይምስ ዘግቧል። ይህ ውሳኔ ከተሰጠ ወዲህ በአደጋ መከላከያ ቀበቶ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ቁጥር ከ87 በመቶ ወደ 44 በመቶ ያሽቆለቆለ ሲሆን ለሞት የሚያደርሱ አደጋዎች ደግሞ በብዛት ጨምረዋል። የኮስታ ሪካ የአውራ ጎዳና ደህንነት ጉባኤ የሚደርሰውን ጉዳት መጠን ለመቀነስ አፋጣኝ እርምጃዎች ቢወስድም መንገደኞች የአደጋ መከላከያ ቀበቶ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ጥረቱ በሙሉ ከንቱ እንደሆነበት ሪፖርቱ ገልጿል። የዚህ ጉባኤ ተወካይ የሆኑት ማንፍረት ሰርቫንተስ እንዲህ ብለዋል:- “ሰዎች ኃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎች በመሆን ራሳቸውንም ሆነ ሕይወታቸውን ከጉዳት ሊጠብቁ እንደሚችሉ ለማስረዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው።”

ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢል የተባሉ የዓሣ ዝርያዎች

ኢሎች በጃፓን በውኃ ጥራት ቁጥጥር ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ ሪፖርት አድርጓል። የሂሮሺማ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ኬንጂ ናምባ ኢሎች የውኃ ጥራት በትንሹ እንኳን ሲጓደል የባሕርይ ለውጥ እንደሚያሳዩ የተገነዘቡት ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። እንደ ካድሚየም ወይም ሳያናይድ ያሉት ጎጂ ንጥረ ነገሮች የኢል ልብ ትርታ ዝግ እንዲል ሲያደርጉ ካንሰር አምጪ የሆኑት እንደ ትራይክሎሮኤትሊን የመሰሉት ኬሚካሎች ደግሞ የልባቸው ትርታ በጣም እንዲፈጥን ያደርጋሉ። በአሁኑ ጊዜ ይህን የኢሎች ልዩ ባሕርይ ተግባራዊ ጠቀሜታ ላይ የሚያውል መሣሪያ ገበያ ላይ ውሏል። አንድ ኢል በዚህ መሣሪያ ውስጥ በሚገኝ ከአክርሊክ የተሠራ ቱቦ ውስጥ እንዲተኛ ይደረጋል። ውኃው በዚህ ቱቦ ውስጥ በሚያልፍበት ጊዜ በቱቦው ላይ የተገጠሙ ኤሌክትሮዶች የኢሉን የልብ ምት እየለኩ የተገኘውን ለውጥ መሣሪያውን ለሚቆጣጠር ቴክኒሽያን ይልካሉ። ለዚህ ሥራ የሚመረጡት ኢሎች በጣም ንጹሕ ከሆኑ ውኃዎች የተገኙ ናቸው። የሚያስተላልፉት መረጃ የተዛባ እንዳይሆን በየወሩ ይቀየራሉ።

ምሥራቅ አፍሪካ በኮሌራ ወረርሽኝ ተመታች

“በምሥራቅ አፍሪካ ኮሌራ ከፍተኛ ወረርሽኝ ሆኗል” ይላል ከናይሮቢ ኬንያ የተላከ የአሶሲዬትድ ፕሬስ ዜና ዘገባ። ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥ የሚያስከትል ተላላፊ የአንጀት መታወክ ሲሆን ተገቢ ሕክምና ካልተደረገ ለሞት ያደርሳል። የዓለም ጤና ድርጅት በሰጠው ሪፖርት መሠረት በ1997 በምሥራቅ አፍሪካ በበሽታው የተለከፉ ሰዎች ቁጥር ከ61,000 በላይ ሲሆን 2,687 ሰዎች እንደሞቱ ሪፖርት ተደርጓል። የአካባቢ ንጽሕና በተጓደለባቸውና በቂ የሕክምና ክትትል በማይደረግባቸው አካባቢዎች ለኮሌራ መከሰት ምቹ ቦታዎች ናቸው። በየወቅቱ የሚዘንብ ዝናብ ከሰዎች የሚወገዱ እጣቢዎችን ለመጠጥነት ወደሚያገለግሉ ውኃዎች በሚጨምርበት ጊዜ ሁኔታው ይባባሳል። የዓለም ጤና ድርጅት የኮሌራ ግብረ ኃይል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ማርያ ኔይራ በሽታው በሚገኝባቸው አካባቢዎች በሙሉ የቆሻሻ ማስወገጃዎችና የንጹሕ ውኃ አቅርቦት እስከሌለ ድረስ ይህ አካባቢ ከኮሌራ ሊጸዳ አይችልም ብለዋል።

የማንበብ ልማድ

ብራዚልያውያን በአማካይ በዓመት 2.3 መጻሕፍት እንደሚያነቡ ጆርናል ዳ ታርዴ ዘግቧል። አብዛኞቹ ብራዚልያውያን ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከመጻሕፍት ጋር ፈጽመው ይቆራረጣሉ። የባሕል ሚኒስቴር ጸሐፊ የሆኑት ኦታቪያኖ ደ ፊዮሬ “ዋናው ችግር በብራዚል ከሚነበቡት መጻሕፍት መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በትምህርት ላይ የሚገኙ ልጆች ተገድደው የሚያነቧቸው መሆናቸው ነው” ብለዋል። “የቀሩት 40 በመቶ የሚሆኑ መጻሕፍት በአብዛኛው ሃይማኖታዊና ተራ ሰው ሊያነባቸው የማይችሉ፣ በወሲብ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ወይም ራስ አገዝ መጻሕፍት ናቸው” ይላል ጋዜጣው። ደ ፊዮሬ ስለ ንባብ ልማድ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ልጆች ሰብሰብ ብለው የሚጫወቱት በቤተሰብ ውስጥ ወይም በትምህርት ቤት ወይም በቴሌቪዥን ዙሪያ ነው። በቤተሰብ ውስጥ ማንበብ የሚያዘወትር ሰው ከሌለ የማንበብ ፍላጎት ጨርሶ አያድርባቸውም።” ጨምሮም “የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የማንበብ ልማድ እንዲዳብር የሚገፋፉ አይደሉም” ብሏል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ