የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ስእለታችንን የግድ መፈጸም አለብንን?
ደስታ የሰፈነበት ትዳር ያላቸው አንድ ባልና ሚስት አስጨናቂ ችግር ተደቀነባቸው። ከዓመታት በፊት በጣም በተወሳሰበና ግራ በሚያጋባ የቤተሰብ ችግር ውስጥ ተዘፍቀው በነበረበት ወቅት ችግሮቻችንን ካቃለልክልን ከምናገኘው ገቢ አንድ አሥረኛውን ለአንተ እንሰጣለን ብለው ለአምላክ ተስለው ነበር። አሁን ግን ዕድሜያቸው ስለገፋና ያልጠበቁት የገንዘብ ችግር ስላጋጠማቸው “የተሳልነውን ስእለት የመፈጸም ግዴታ ይኖርብን ይሆን?” ብለው ያስባሉ።
የገጠማቸው ችግር ጠቢቡ ሰው ለመናገር ችኩል መሆን እንደማይገባ የሰጠውን ምክር አስፈላጊነት የሚያሳይ ነው:- “ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል። ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፣ በመልአክም ፊት:- ስሕተት ነበረ አትበል።”—መክብብ 5:5, 6
ሰንካላ ምክንያት ማቅረብ አይቻልም
ምንም እንኳን በጊዜያችን ባለው ልቅ ኅብረተሰብ በሆነ ባልሆነው መማልና ከአንድ ችግር ለማምለጥ ሲባል ብቻ ቃል መግባት የተለመደ ቢሆንም አምላክ አሳማኝ ያልሆኑ የማታለያ ምክንያቶችን ይቀበላል ብለን መጠበቅ አንችልም። የንግድ ሰዎች እንኳን እንደነዚህ ያሉትን ምክንያቶች አይቀበሉም። ኢንዱስትሪ ዊክ በተባለው የንግድ መጽሔት ላይ የወጣው “በንግድ ጉዳዮች ታማኝ መሆን ሞኝነት ነውን?” የሚለው ርዕስ የሚከተለውን የቅሬታ ሐሳብ አስፍሯል:- “ከእንግዲህ ወዲህ ሰዎች እውነቱን ይነግሩናል ብለን አናምንም፤ ለጥቅማቸው የሚሆነውን እንጂ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ያደርጋሉ ብለን አንጠብቅም፤ የገቡትን ቃል ይጠብቃሉ ብለን አንገምትም።” አበዳሪዎችን “ቼኩን በፖስታ ልኬዋለሁ” ብሎ በመዋሸት ዕዳው የሚከፈልበትን ጊዜ ለማራዘም የሚቻል ቢሆንም መላእክትን ግን ፈጽሞ ማታለል አይቻልም።
ይህ ማለት ግን አምላክ ችግረኛ ተበዳሪዎችን አስጨንቀው ገንዘባቸውን እንደሚቀበሉ ጨካኝ አበዳሪዎች በመላእክቱ አማካኝነት ሰዎች ስእለታቸውን እንዲፈጽሙ ያስገድዳል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ መላእክቱን በፍቅራዊ ሁኔታ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ [ገንቢ በሆነ መንገድ] የሚያገለግሉም መናፍስት” አድርጓቸዋል። (ዕብራውያን 1:14) በዚህ መንገድ መላእክት ለምናቀርባቸው ልባዊ ጸሎቶች መልስ በመስጠት ረገድ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ፣ ያበረክታሉም።
ይሁን እንጂ በምንጸልይበት ጊዜ የማንፈጽመውን ነገር እንደምንፈጽም ቃል በመግባት ከቀጠልን የአምላክን በረከቶች እናገኛለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለንን? ጠቢቡ ሰው:- “እግዚአብሔር በቃልህ ይቆጣ ዘንድ የእጅህንም ሥራ [ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ] ያጠፋ ዘንድ ስለ ምን ትሻለህ?” ብሏል።—መክብብ 5:6
ስለዚህ ሰበብ ከመደርደር ይልቅ ስእለታችንን እንድንፈጽም ሊገፋፋን የሚገባው መላእክት የሚወስዱትን የበቀል እርምጃ መፍራት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረንና በምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ የአምላክ ሞገስ እንዳይለየን ከልብ መፈለግ ይኖርብናል። ከላይ የተጠቀሱት ባልና ሚስት “በአምላክ ፊት ንጹህ ሕሊና እንዲኖረን እንፈልጋለን፤ ከፈቃዱ ጋር ተስማምተን ለመመላለስ እንፈልጋለን” በማለት ጥሩ አድርገው ገልጸውታል።
ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ
ስእለታችንን በመፈጸም ረገድ ንጹህ ሕሊና እንዲኖረን ከፈለግን ለራሳችን ታማኞች መሆን አለብን። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት:- አንድ ሰው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተበድሮሃል እንበል፤ ነገር ግን በአንድ መጥፎ አጋጣሚ ሳቢያ ገንዘቡን መክፈል አልቻለም። ይሁን እንጂ አንተን ደስ የሚያሰኝህ ገንዘቡን ሊከፍልህ አስቦ ዕዳ እንዳለበት እንኳን ቢረሳ ነው ወይስ አቅሙ የቻለውን ያህል በየጊዜው ቢከፍልህ?
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ አንድ ሰው ሳያስብበት በችኮላ ሙሉ ጊዜውን ወይም ንብረቱን ለክርስቲያናዊ ሥራዎች ለማዋል ቃል ገብቶ ሊፈጽም ግን አልቻለም እንበል። በወቅቱ ያለው ሁኔታ በፈቀደለት መጠን የተሳለውን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ሆኖ ሊሰማው አይገባምን? ሊያደርግ የሚችለው ነገር ይነስም ይብዛ ጳውሎስ “ለመስጠት መልካም ፈቃድ ካለ . . . ተቀባይነት” አለው ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 8:12 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ትክክለኛ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እውቀት ከማግኘቱ በፊት ስለገባቸው ስእለቶች ምን ማለት ይቻላል?
ትክክለኛ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ስእለቶች
የተሳልነው ስእለት መጥፎ ወይም ከሥነ ምግባር ውጪ እንደሆነ ካወቅን ስእለቱን እንደሚፋጅ ፍም ወዲያውኑ እርግፍ አድርገን ልንጥለው ይገባል! (2 ቆሮንቶስ 6:16–18) የሚከተሉት የመጥፎ ስእለት ምሳሌዎች ናቸው:-
◻ ለተባእት ወይም እንስት የሐሰት አማልክት መሳል፣ የባቢሎናውያንን “የሰማይ ንግሥት” እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።—ኤርምያስ 44:23, 25
◻ ሕጋዊ ያልሆኑ ስእለቶች፣ ሐዋርያው ጳውሎስን እስኪገድሉ ምንም ምግብ ላይቀምሱ እንደተማማሉት 40 ሰዎች ዓይነት ማለት ነው።—ሥራ 23:13, 14
◻ የክህደት ስእለት፣ “በውሸተኞች . . . የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት” ይከተላሉ፤ “መጋባትን ይከለክላሉ፣ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 4:1–3
ስለዚህ ቀደም ሲል የገባናቸውን አንዳንድ ስእለቶች ማፍረስ እንደሚኖርብን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆነ ትምህርት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውን ስእለቶች ላለመፈጸም ሰበብ የምንፈላልግበት ምን ምክንያት አለ? በአሁኑ ጊዜ ያገኘነው ትክክለኛ እውቀት ከዚህ በፊት ለገባናቸው ስእለቶች ከምንጊዜም የበለጠ አክብሮት እንድናሳይ ሊያደርገን አይገባምን?
ስለ ቀድሞዎቹና ስለ ወደፊቶቹ ስእለቶችህ አስብ
ለወደፊቱም ቢሆን በአምልኮታችን ላይ ሌላ ስእለት ከመጨመራችን በፊት በጥሞና ማሰብ ይኖርብናል። ስእለቶች አንድ ሰው አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ሲል ለምሳሌ ያህል በክርስቲያናዊ አምልኮ የሚያሳልፈውን ጊዜ ለማሳደግ ወይም ከሚገባው በላይ ከመብላት ለመቆጠብ ሲል ብቻ መሳል የለበትም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሁሉንም ዓይነት መሐላ አልተቃወመም። በሕጋዊ ፍርድ ቤት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የሚፈጸመውን መሐላ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይሁን እንጂ “ደግሞ ለቀደሙት:- በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ” ተብሏል። “እኔ ግን እላችኋለሁ:- ከቶ አትማሉ” ብሎ በማስጠንቀቅ ያልታሰበበት የችኮላ መሐላ ትክክል አለመሆኑን በግልጽ አመልክቷል። (ማቴዎስ 5:33, 34) ይህን አቋም የወሰደው ለምንድን ነው? መሐላ ተገቢ መሆኑ ቀርቷልን?
በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ ሰዎች ያደረጓቸው መሐላዎች ብዙውን ጊዜ እንዲፈጸሙላቸው ከሚፈልጓቸው ነገሮች ጋር የተዛመዱ ነበሩ። ‘ይህን ችግር እንድወጣው ከረዳኸኝ ለአንተ እንዲህ አደርግልሃለሁ’ ብለው በጸሎት ለይሖዋ ይሳሉ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ:- “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” ብሏል። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ይህን ብታደርግልኝ እንዲህ አደርግልሃለሁ ብለው ከመሳል ይልቅ “እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ . . . ለምኑ ትቀበሉማላችሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።—ዮሐንስ 16:23, 24
በኢየሱስ ስም ወይም በእርሱ ሥልጣን የተገኘው ይህ ትምክህት “ሳያስብ በከንፈሩ” ለአምላክ የገባውን ቃል የተቻለውን ጥረት ሁሉ ቢያደርግም መፈጸም ባለመቻሉ ምክንያት ሕሊናው የሚወቅሰውን ሰው እንኳን ሊያፅናና ይገባል። (ዘሌዋውያን 5:4–6) ስለዚህ ቀደም ሲል የፈጸምናቸውን ስእለቶች አቅልለን ባንመለከትም በአሁኑ ጊዜ በኢየሱስ ስም መጸለይ ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን አምላክን መጠየቅ እንችላለን። በኢየሱስ ስም በደላችንን ይቅር እንዲለን መለመን እንችላለን። በዚህ መንገድ “ከክፉ ኅሊና እንድንነጻ ልባችንን ተረጭተን . . . እውነተኛ እምነት” ልናገኝ እንችላለን።—ዕብራውያን 10:21, 22 የ1980 ትርጉም
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
Priests taking vows at Montmartre