አምላክ ያስብልናልን?
መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?
ይህ ሁኔታ አንድ ቀን ያቆም ይሆን?
የሚያመራምሩ ጥያቄዎች ናቸው፤ አይደሉም? እነዚህ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀ አንድ ብሮሹር ሽፋን ላይ የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው። ብሮሹሩን አንብበውታል? ብሮሹሩ እስካሁን ለብዙ ሰዎች ማጽናኛና ተስፋ አስገኝቷል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፔንሲልቫንያ ክፍለ ሀገር በፊላደልፊያ ከተማ የምትኖር አንዲት ሴት ስለዚህ ብሮሹር እንዲህ በማለት ጽፋለች:–
“ቃላትን እንዲህ አሳምሮና ልብን በሚነካ መንገድ አቀነባብሮ መጻፍ የሚቻል አይመስለኝም ነበር። ልክ በአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ሳለሁ አንድ ሰው በድንገት መብራት እንዳበራልኝ ያህል ነው የተሰማኝ። ‘አምላክ እንደሚያስብልን ’ ተገንዝቤአለሁ!
“ሳይንስ ነክ የሆኑ ነገሮች ደስ ይሉኛል። ስለዚህ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ ሳይንሳዊ የሆኑ ንግግሮች፣ ጽሑፎች ወይም ፊልሞች መንፈሴን ያድሱልኛል። ይህ ብሮሹር ግን መንፈሴን ማደስ ብቻ ሳይሆን ለስለስ ባለና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ነክቶኛል።
“በመጀመሪያ ዓይን የሚማርከው ሽፋኑ ነው። ዓይን የሚስብ የሆነው ስዕሉ ላይ ያሉት ሰዎች እውነተኛ በመሆናቸው ነው። በጥቁር ቀለም በትልልቅ ፊደላት የተጻፈው ‘አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?’ የሚለው ጥያቄ ያሳሰባቸው መሆኑን በያንዳንዳቸው ፊት ላይ መመልከት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ ሁሉ ሰው የሚሰማውን ስሜት ፊታቸው እንደ መስታወት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
“ትምህርቱ በቀላሉ የሚገባ ነው። ቀላልና ነጥቡን በቀጥታ የሚገልጽ እንዲሁም አሳማኝ ነው። የሚያቀርበው ሐሳብ ምክንያታዊ ነው። በጣም ደስ የሚልና ለማንበብ የሚቀልል ከመሆኑ የተነሣ አንዴ ማንበብ ከጀመራችሁ አቁሙ አቁሙ አይላችሁም።”
ተጨማሪ ማብራሪያ ብንሰጥዎ ደስ የሚልዎት ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።
[በገጽ 32ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?
ታዲያ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?
ይህ ሁኔታ አንድ ቀን ያቆም ይሆን?