የዓለም ፍጻሜ ምን ያህል ቀርቧል?
የሐሰት ማስጠንቀቂያዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?
ስለ አንድ እረኛ የሚነገር ተረት አለ። ይህ እረኛ የመንደሩን በጎች ሰብስቦ ይጠብቃል። ከዕለታት አንድ ቀን የመንደሩን ሰዎች ትንሽ ሊያስደነግጣቸው ይፈልግና “ተኩላ! ተኩላ!” እያለ ይጮኻል። ግን አንድም ተኩላ አልመጣም ነበር። የመንደሩ ሰዎች ተኩላውን ለማባረር ዱላቸውን ይዘው ተሯሩጠው ከወጡ በኋላ ምንም ተኩላ ሳያገኙ ይቀራሉ። እረኛው በቀልዱ በጣም ስለ ተደሰተ ለሁለተኛ ጊዜ ተኩላ መጣ ብሎ ይጮሃል። የመንደሩም ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ ተሯሩጠው ከሄዱ በኋላ ቀልድ እንደሆነ ይመለከታሉ። ከዚያ በኋላ ግን ተኩላ ይመጣል። እረኛውም ልጅ “ተኩላ! ተኩላ!” ብሎ ይጮኻል። የመንደሩ ሰዎች ውሸቱን ነው ብለው ዝም ይሉታል። ከዚህ በፊት የተሞኘነው ይበቃል ብለው ይተውታል።
የዓለም ፍጻሜ ቀርቧል ብለው የተነበዩ ሰዎችም ይህ እረኛ ያደረገውን የሚመስል ነገር አድርገዋል። ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ ባሳለፍናቸው ዘመናት ይፈጸማሉ ተብለው የተነገረላቸው ብዙ ነገሮች ሳይፈጸሙ በመቅረታቸው ብዙ ሰዎች ይፈጸማሉ ስለሚባሉ ትንቢቶች ግድየለሾች ሆነዋል።
ከ590 እስከ 604 እዘአ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ቀዳማዊ ግሪጎሪ ለአንድ የአውሮፓ ንጉሥ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኘው ሁሉን የሚችል አምላክ ቃል በተረዳነው መሠረት የአሁኑ ዓለም ፍጻሜ በጣም እንደቀረበና ፍጻሜ የሌለው የቅዱሳን መንግሥት እንደተቃረበ ግርማዊነትዎ እንዲያውቁ እንፈልጋለን” ብለዋል።
በ16ኛው መቶ ዘመን የሉተራን ቤተክርስቲያን መሥራች የሆነው ማርቲን ሉተር የዓለም ፍጻሜ በጣም ቅርብ አንደሆነ ተንብዮ ነበር። አንድ ማስረጃ እንደሚገልጸው “እኔ በበኩሌ የፍርድ ቀን በደጅ እንደቀረበ እርግጠኛ ነኝ” ብሎ ነበር።
ከመጀመሪያዎቹ የመጥምቃውያን ቡድኖች ስለ አንዱ “በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበሩት መጥምቃውያን የሺው ዓመት ግዛት በ1533 ይጀምራል ብለው ያምኑ ነበር” ተብሏል።
“ከ1519–1588 የዮርክ ሊቀ ጳጳስና የእንግሊዝ ተቀዳሚ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ኤድዊን ሳንዲስ . . . “ይህ የጌታ ምጽአት ቅርብ እንደሆነ እርግጠኛ እንሁን ብለዋል።”
የአድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን መሥራች ናቸው ተብለው የሚታመኑት ዊልያም ሚለር “በአይሁዳውያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ከመጋቢት 21, 1843 እስከ መጋቢት 21, 1844 ባለው ጊዜ ክርስቶስ እንደሚመጣ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ” ብለው እንደ ተናገሩ ተጠቅሷል።
እንደነዚህ ያሉት ትንቢቶች ሳይፈጸሙ መቅረታቸው በዘዳግም 18:20–22 መሠረት እነዚህን ትንቢቶች የተናገሩትን ሰዎች ሐሰተኛ ነቢያት ያሰኛቸዋልን? ይህ ጥቅስ እንዲህ ይነበባል:- “ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፣ እርሱ ይገደል። በልብህም:- እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፣ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፣ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው።”
የሰዎችን ትኩረት ለመሳብና ተከታዮች ለማግኘት ሲሉ ስለ ዓለም ፍጻሜ የሚተነብዩ ሰዎች ቢኖሩም የተናገሩት ቃል እውነት እንደሆነ ከልባቸው የሚያምኑ ሰዎችም አሉ። የተናገሩት ቃል በአንድ ጥቅስ አተረጓጎም ላይ ወይም በአንድ ዓይነት ክስተት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ትንቢታቸው በቀጥታ ከይሖዋ የተገለጠላቸው እንደሆነና በይሖዋ ስም የሚናገሩት ከይሖዋ ስለተገለጠላቸው እንደሆነ አይናገሩም። ስለዚህ የተናገሩት ቃል ሳይፈጸም በሚቀርበት ጊዜ በዘዳግም 18:20–22 እንደተጠቀሱት የሐሰት ነቢያት ሆነው መታየት የለባቸውም። ሊሳሳቱ የሚችሉ ሰዎች በመሆናቸው ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ ተርጉመዋል ማለት ነው።a
አንዳንዶች ከዚህ ቀደም ሳይፈጸሙ የቀሩት ትንቢቶች ተስፋ ሳያስቆርጧቸው በ2000 ዓመት መቅረብ በመገፋፋት የዓለም ፍጻሜ ስለሚሆንበት ጊዜ ሌሎች ተጨማሪ ትንቢቶችን ተናግረዋል። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በታኅሣሥ 5, 1989 እትሙ ላይ “የሺህ ዓመት ግዛት ትኩሳት፣ ፍጻሜው ቀርቧል የሚሉ ነቢያት እንደ አሸን ፈልተዋል” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። 2000 ዓመት እየቀረበ ስለመጣ ብዙ ወንጌላውያን ኢየሱስ በመምጣት ላይ እንዳለና የ1990ዎቹ ዓመታት “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የመከራ ዓመታት” እንደሚሆኑ በመተንበይ ላይ ናቸው። ይህ ጽሑፍ ለተጻፈበት ጊዜ በጣም ቅርብ የሆነው ትንቢት የተነገረው በኮሪያ ሪፑብሊክ ነው። የመጪዎቹ ቀናት ሚስዮን የተባለው ድርጅት ክርስቶስ ጥቅምት 28 ቀን 1992 እኩለ ሌሊት ላይ መጥቶ አማኞችን ወደ ሰማይ እንደሚወስድ ተንብዮ ነበር። ሌሎች ብዙ የጥፋት ቀን ነቢያት ተመሳሳይ ትንቢት ተናግረዋል።
የሐሰት ማስጠንቀቂያዎች ይህን ያህል መብዛታቸው የሚያሳዝን ነገር ነው። እረኛው ልጅ ተኩላ ተኩላ ሲል እንዳሰማው ጩኸት ሆነዋል። ሰዎች እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች በቸልታ ስለሚመለከቱአቸው እውነተኛ ማስጠንቀቂያ በሚሰጥበት ጊዜም ቸልተኞች ይሆናሉ።
ይሁን እንጂ ካለፉት መቶ ዘመናት ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው የውሸት ማስጠንቀቂያ የማሰማት አዝማሚያ የተስፋፋው ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 24:23–26) ኢየሱስ ለመምጣቱ ምልክት ስለሚሆኑ የተለያዩ ነገሮች ለተከታዮቹ ከተናገረ በኋላ በማቴዎስ 24:36–42 ላይ እንደምናነበው እንዲህ ብሏቸዋል:- “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። . . . ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”
ነቅተውና ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ብቻ ሳይሆን በናፍቆት እንዲጠብቁ ተነግሯቸው ነበር። ሮሜ 8:19 እንዲህ ይላል:- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና።” የሰው ልጅ ተፈጥሮ አንድን ነገር ሲናፍቅና በጉጉት ተስፋ ሲያደርግ በቂ መረጃ ባይኖርም እንኳን በደጅ እንደቀረበ አድርጎ ለመመልከት ይፈልጋል። በጣም በመጓጓታችን የተነሣ የሐሰት ማስጠንቀቂያዎች ተነግረው ሊሆን ይችላል።
ታዲያ እውነተኛውን ማስጠንቀቂያ ከሐሰተኛው ማስጠንቀቂያ እንዴት መለየት ይቻላል? መልሱን ለማግኘት የሚቀጥለውን ጽሑፍ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ዳግም ምጽአት በጣም በመናፈቃቸው ምክንያት ኢየሱስ ስለሚመጣበት ጊዜ ስህተት ሆነው የተገኙ ቀኖችን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ሐሰተኛ ነቢያት ናቸው ይሏቸዋል። ይሁን እንጂ አንድም ጊዜ ቢሆን የተነበይነው ‘በይሖዋ ስም’ ነው ብለው አያውቁም። ‘ይህ የይሖዋ ቃል ነው’ ብለው አያውቁም። የይሖዋ ምሥክሮች ኦፊሴላዊ መጽሔት የሆነው መጠበቂያ ግንብ “ትንቢት የመናገር ስጦታ የለንም።” (ጥር 1883 ገጽ 425) “ጽሑፎቻችንም ቅዱስ ናቸው ወይም ስህተት ሊኖርባቸው አይችልም አንልም” ብሎ ነበር። (ታኅሣሥ 15, 1896 ገጽ 306) በተጨማሪም መጠበቂያ ግንብ አንዳንዶች የይሖዋ መንፈስ ያላቸው በመሆናቸው “በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሁሉ በመንፈስ ተነድተው ይናገራሉ ማለት አይደለም። በዚህ በመጠበቂያ ግንብ የሚወጡት ጽሑፎች በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ፣ ስህተት የሌለባቸውና ስህተትም ሊገኝባቸው የማይችሉ አይደሉም” ብሏል። (ግንቦት 15, 1947 ገጽ 157) “መጠበቂያ ግንብ የሚያወጣቸው ጽሑፎች በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው ወይም ቀኖና ናቸው አይልም።” (ነሐሴ 15, 1950 ገጽ 263) “እነዚህን ጽሑፎች የሚያዘጋጁት ወንድሞች የማይሳሳቱ አይደሉም። ጽሑፎቻቸውም እንደ ጳውሎስና እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈስ የተጻፉ አይደሉም። (2 ጢሞ. 3:16) ስለዚህ ይበልጥ ግልጽ የሆነ ማስተዋል በተገኘ ቁጥር አንዳንድ አመለካከቶችን ማስተካከል አስፈላጊ ሆኗል። (ምሳሌ 4:18)”—የካቲት 15, 1981 ገጽ 19