መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመከላከል ምን ማድረግ ትችላለህ?
ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን በዓለም ላይ እጅግ ተስፋፍተው ከሚገኙ ሰዎች የሚማረሩባቸው ችግሮች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። ይህ ችግር ሐፍረት፣ ጭንቀትና ስጋትን ሊፈጥር ይችላል።
በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ሃልቶሲስ በሚል ስያሜ በስፋት ይታወቃል። ይህ ቃል የመጣው “ትንፋሽ” የሚል ትርጉም ካለው ሃልተስ ከተባለው የላቲን ቃልና መጥፎ ሁኔታን ከሚያመለክተው ኦሲስ ከተባለው ባዕድ መድረሻ ነው። ብዙ ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረን ይሉታል!
መጥፎ የአፍ ጠረን አለህን? ሌሎች ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳላቸው ለማወቅ አስቸጋሪ ባይሆንም የራስህን ሁኔታ ማወቅ ግን ሊያዳግትህ ይችላል። ጃዳ የተባለ አንድ የአሜሪካ የጥርስ ሕክምና ማኅበር መጽሔት ከራሳችን መጥፎ የአፍ ጠረን ጋር እንደምንለማመድና “አፋቸው በጣም የሚሸት ሰዎች እንኳ ችግራቸውን ላያውቁት እንደሚችሉ” ገልጿል። ስለዚህ አብዛኞቻችን መጥፎ የአፍ ጠረን ያለን መሆኑን የምናውቀው አንድ ሰው ስለ ሁኔታው ሲነግረን ነው። ምንኛ ያሳፍራል!
መጥፎ የአፍ ጠረን የብዙ ሰዎች ችግር መሆኑ ብቻ ማጽናኛ ሊሆነን አይችልም። በአጠቃላይ መጥፎ የአፍ ጠረን አስነዋሪና ተቀባይነት የሌለው ነገር ተደርጎ ይታያል። አንዳንድ ጊዜ ከባድ የስሜት መቃወስ ሊያስከትል ይችላል። በእስራኤል ውስጥ የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የአፍ ማይክሮባዮሎጂ ላቦራቶሪ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሜል ሮዘንበርግ እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “መጥፎ የአፍ ጠረን ግምታዊም ሆነ እውነተኛ፣ ከኅብረተሰቡ ለመገለል፣ ከትዳር ጓደኛ ለመፋታትና ራስን ለመግደል ምክንያት ሊሆን ይችላል።”
ስለ መጥፎ የአፍ ጠረን ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
የጤና ባለ ሙያዎች መጥፎ የአፍ ጠረን የጤና ጉድለት መኖሩን ሊጠቁም እንደሚችል ከተገነዘቡ ሰነባብተዋል። በዚህም ምክንያት ሐኪሞች ከጥንት ጀምሮ የሰውን አፍ ጠረን ሲያጠኑ ቆይተዋል።
ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ዝነኛው የፈረንሳይ ኬሚስት አንቶኒ ሎራን ላቫዥየ የሰው ትንፋሽ ምን ነገሮችን እንደያዘ ለማጥናት የሚያስችል የትንፋሽ መመርመሪያ መሣሪያ ፈልስፎ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሳይንቲስቶች የተሻሻሉ ሞዴሎችን ሠርተዋል። በአሁኑ ወቅት በካናዳ፣ በእስራኤል፣ በጃፓንና በኔዘርላንድ የሚገኙ ቤተ ሙከራዎች የአፍን ጠረን መጠን የሚለካውን ሃልሜትር የተባለ መሣሪያ በመጠቀም ላይ ናቸው። በኒው ዚላንድ ውስጥ ሳይንቲስቶች በጥርስ ላይ የሚላከክ ቆሻሻ ማሳደጊያ ጣቢያዎች ሠርተዋል። እነዚህ ጣቢያዎች ሰው ሠራሽ አፎች በመባልም ይታወቃሉ። ጣቢያዎቹ በሰው አፍ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንዲመስሉ ሆነው የተሠሩ ሲሆኑ ምራቅ፣ በጥርስ ላይ የሚላከክ ቆሻሻ፣ ባክቴሪያዎችና መጥፎ የአፍ ጠረን እንኳ ሳይቀር ይገኝባቸዋል።a
ሳይንቲስቶቸ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስለ ትንፋሻችን ብዙ ነገር ለማወቅ ችለዋል። ለምሳሌ ያህል ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት እንደ ተናገረው “ተመራማሪዎች በአሁኑ ጊዜ በሰው ልጅ ትንፋሽ ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉ ወደ ጋዝነት ኦርጋኒክ ውህዶች እንደሚገኙ ደርሰውበታል።” ሆኖም እነዚህ ሁሉ ውህዶች መጥፎ ጠረን የሚያመጡ አይደሉም። አብዛኛውን ጊዜ መጥፎ የአፍ ጠረን የሚያመጡት ሃይድሮጅን ሰልፋይድና ሜትል ሜርካፕታን የሚባሉት ውህዶች ናቸው። እነዚህ ጋዞች ትንፋሻችን ከጥርኝ ጋር በጣም የሚመሳሰል ጠረን እንዲኖረው ያደርጋሉ ተብሏል።
በሰው አፍ ውስጥ ከ300 በላይ የሆኑ የባክቴሪያ ዝርያዎች ሊገኙ ይችላሉ። ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ዳይት ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር “አፋችን ጨለማ፣ ሙቀትና ርጥበት ያለው በመሆኑ መጥፎ ሽታ ለሚፈጥሩ ባክቴሪያዎች በጣም የተመቻቸ የመራቢያ ቦታ ነው” ብሏል። ይሁን እንጂ በተለይ መጥፎ ጠረን የሚፈጥሩት አራት ዝርያዎች ብቻ ናቸው። እነዚህ የባክቴሪያ ዝርያዎች በአፍህ ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም በአብዛኛው እስካሁን ድረስ በስም ላታውቃቸው ትችላለህ። እነርሱም ቬሎኔላ አልካሌሲንስ፣ ፉዞባክቴሪየም ኑክልአተም፣ ባክተሮይድስ ሜላኒኖጂንከስ እና ክሌብሲላ ኒሞኒዬ የተባሉት ናቸው። እነዚህ ባክቴሪያዎች በጥርስ ላይ የሚቀሩ ምግቦችን፣ የሞቱ ሴሎችንና ሌሎች በአፍ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን ይመገባሉ። ይህ የባክቴሪያዎች እንቅስቃሴ ደግሞ መጥፎ ጠረን ያላቸው ጋዞች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ይህ ሂደት ቆሻሻ ሲበሰብስ ከሚፈጠረው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ጀ ፒሪዮዶንቶል የተባለው የጥርስ ሕክምና መጽሔት “በአብዛኞቹ ሁኔታዎች መጥፎ የአፍ ጠረን ማይክሮቦች በሚፈጽሙት የማበስበስ ሂደት ሳቢያ በአፍ ውስጥ ይፈጠራል” በማለት የገለጸው ትክክል ነው። ይህ ሂደት ካልተገታ ጥርስ ሊበሰብስና የድድ በሽታ ሊይዝ ይችላል።
“እንደምን አደርክ! ትንፋሽህ እንዴት ነው?”
ይህ በአፍ ውስጥ የሚፈጠረው የመበስበስ ሂደት በእንቅልፍ ወቅት ይፋጠናል። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ቀን ቀን አፋችን ብዙ ኦክስጅን በተዋሃደውና አነስተኛ አሲድነት ባለው ምራቅ ሲታጠብ ይውላል። ይህም ባክቴሪያዎችን ያስወግዳል። ሆኖም በእንቅልፍ ወቅት በሰዓት የሚመነጨው ምራቅ በመደበኛው ጊዜ የሚመነጨውን 1/50ኛ ያህል ይሆናል። አንድ መጽሔት እንደገለጸው የደረቀ አፍ “ከ1,600 ቢልዮን ባክቴሪያዎች በላይ የሚኖሩበት የማይንቀሳቀስ ኩሬ ይሆናል።” ይህም በሰፊው የሚታወቀውን መጥፎ ጠረን ያለው “የጠዋት ትንፋሽ” ይፈጥራል።
በተጨማሪም ከእንቅልፍ ሰዓት ውጪ ባለው ጊዜ በጭንቀት ምክንያት የምራቅህ መጠን ሊቀንስ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ተጨንቆ የሚናገር የሕዝብ ተናጋሪ ንግግር በሚሰጥበት ወቅት አፉ ስለሚደርቅ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊኖረው ይችላል። ከዚህም በላይ በዛ ያሉ በሽታዎች ለአፍ መድረቅ ምክንያት ሊሆኑ ወይም ደግሞ የአፍ መድረቅ ራሱ የበሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል።
ሆኖም መጥፎ የአፍ ጠረን ሁልጊዜ በአፍ ውስጥ ከሚገኙ ባክቴሪያዎች እንቅስቃሴ የሚመጣ አይደለም። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ መጥፎ የአፍ ጠረን የተለያዩ ሁኔታዎችና በሽታዎች ምልክት ነው። (በገጽ 22 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) ስለዚህ ባልታወቀ ምክንያት የማያቋርጥ መጥፎ የአፍ ጠረን የሚኖርህ ከሆነ ሐኪም ብታማክር የተሻለ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መጥፎ የአፍ ጠረን ከሆድ ሊመነጭ ይችላል። ሆኖም ብዙዎች እንደሚያምኑት ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነገር አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ አንድ መጥፎ ጠረን ወደ አፍህ የሚመጣው ከሳንባህ ነው። ይህ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? አንዳንድ እንደ ነጭ ሽንኩርት የመሳሰሉ ምግቦች ከተፈጩ በኋላ ወደ ደም ስሮች ይሄዳሉ፤ ከዚያም በደም አማካኝነት ወደ ሳንባዎች ይወሰዳሉ። በዚህ ምክንያት የመጣው ጠረን በመተንፈሻ አካላት አልፎ በአፍህና በአፍንጫህ ይወጣል። ኸልዝ የተባለው መጽሔት በተናገረው መሠረት “ሰዎች የውስጥ እግራቸውን በነጭ ሽንኩርት ፍንካች ቢያሹ ወይም ነጭ ሽንኩርቱን ሳያኝኩ ቢውጡት አፋቸው እንደሚሸት ጥናቶች ያሳያሉ።”
የአልኮል መጠጦችን መጠጣትም ደምህና ሳንባህ በአልኮል ሽታ እንዲሞላ ያደርጋል። ይህ በሚሆንበት ወቅት የተወሰነ ጊዜ ከመጠበቅ በቀር ሁኔታውን ለማሻሻል ማድረግ የምትችለው ነገር የለም። አንዳንድ የምግብ ሽታዎች በሰውነትህ ውስጥ እስከ 72 ሰዓታት ድረስ ይቆያሉ።
መጥፎ የአፍ ጠረንን መከላከል የሚቻልበት መንገድ
መጥፎ የአፍ ጠረን እንደ ማስቲካ ያሉትን ጥሩ ሽታ ያላቸው ነገሮች በመብላት ብቻ ሊጠፋ አይችልም። መጥፎ የአፍ ጠረን ብዙውን ጊዜ የሚመጣው በአፍ ውስጥ ከሚገኙ ባክቴሪያዎች እንደሆነ አስታውስ። ማንኛውም ሰው በአፍ ውስጥ የቀረች በጣም ትንሽ የሆነች በጥርስ ላይ የተላከከች የምግብ ትራፊ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ባክቴሪዎች ጥሩ ግብዣ እንደምትሆን ማስታወስ ይኖርበታል። ስለዚህ መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመከላከል በጣም አስፈላጊ ከሆኑት መንገዶች አንዱ ባክቴሪያዎችን ለመቀነስ የሚያስችለውን የአፍ ንጽሕና መጠበቅ ነው። ዘወትር የምግብ ትርፍራፊዎችንና በጥርስ ላይ የሚላከኩ ቆሻሻዎችን ከጥርስህ ላይ በማስወገድ የአፍህን ንጽሕና ለመጠበቅ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ምግብ ከበላህ በኋላና ልትተኛ ስትል ጥርስህን መፋቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ሆኖም ጥርስ መፋቅ አንድ እርምጃ ብቻ ነው።
የጥርስ ብሩሽ የማይደርስባቸው የጥርስ ክፍሎች አሉ። ስለዚህ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ በጥርስና በጥርስ መካከል ዘልቆ በሚገባ ክር ተጥቅሞ ጥርስን ማጽዳት የግድ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ተመራማሪዎች በቀስታ ምላስን መቦረሽ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። ምላስ ባክቴሪያዎች የሚኖሩበትና የሚራቡበት አመቺ ስፍራ ነው። ከዚህም በላይ በየጊዜው መመርመርና ጥርስ ሐኪም ዘንድ ሄዶ በጥርስ ላይ የሚላከከውን ቆሻሻ ማስወገድ አስፈላጊ ነው። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱን ሳያደርጉ መቅረት መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል። ከጊዜ በኋላም ከባድ የጥርስና የድድ በሽታዎችን ያስይዛል።
አፍህ ጥሩ ጠረን እንዲኖረው መውሰድ የምትችላቸው አንዳንድ ጊዜያዊ እርምጃዎች አሉ። ውኃ ጠጣ፣ ስኳር የሌለበት ማስቲካ አኝክ። የምራቅህን መጠን ሊጨምር የሚችል አንድ ነገር አድርግ። ምራቅ ባክቴሪያዎችን የሚያስወግድ የተፈጥሮ የአፍ ንጽሕና መጠበቂያ እንደሆነና ባክቴሪያዎች መኖር የማይችሉበትን አካባቢ እንደሚፈጥር አስታውስ።
በገበያ ላይ የሚገኙ የአፍ መጉመጥመጫዎች ሊጠቅሙ ቢችሉም መጥፎ የአፍ ጠረንን በመከላከል ረገድ ሙሉ በሙሉ ልትተማመንባቸው እንደማትችል በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ አልኮል ባለባቸው መጉመጥመጫዎች መጠቀም የአፍ ድርቀት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ በጣም ውጤታማ ናቸው የሚባሉ የአፍ መጉመጥመጫዎች በጥርስ ላይ የሚላከኩ ቆሻሻዎችን መቀነስ የሚችሉት 28 በመቶ ብቻ ነው። ስለዚህ የምትመርጠውን የአፍ መጉመጥመጪያ ከተጠቀምክ በኋላም ቢሆን በአፍህ ውስጥ ከነበሩት ባክቴሪያዎች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ላይጠፉ ይችላሉ። በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ሙከራዎች መሠረት በአፍ መጉመጥመጪያ ተጠቅሞ ጥርስን ካጸዱ “ከ10 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ባሉት ጊዜያት ውስጥ መጥፎ የአፍ ጠረን እንደሚያገረሽ” ኮንስዩመር ሪፖርትስ የተባለው መጽሔት ገልጿል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ በዶክተር ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ ኃይለኛ የሆኑ የአፍ መጉመጥመጫዎች እንኳ በጥርስ ላይ የሚላከኩ ቆሻሻዎችን መቀነስ የሚችሉት 55 በመቶ ብቻ ነው። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ባክቴሪያዎቹ ወደ ቀድሞው ቁጥራቸው ይመለሳሉ።
በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው መጥፎ የአፍ ጠረንን በመከላከል ረገድ ግዴለሽ መሆን አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ አፍህንና ጥርስህን ዘወትር እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ውድ መሣሪያዎች አድርገህ መያዝ ይኖርብሃል። ኃላፊነት የሚሰማቸው አናጺዎችና መካኒኮች እያንዳንዱን ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ መሣሪያዎቻቸው እንዳይዝጉ፣ እንዳይበሉና ሌላ ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚያደርጉ ጥንቃቄዎችን ይወስዳሉ። ጥርስህና አፍህ ከማናቸውም ሰው ሠራሽ መሣሪያዎች የበለጡ ውድ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የሚገባቸውን እንክብካቤና ጥንቃቄ አድርግላቸው። እንዲህ ካደረግህ መጥፎ የአፍ ጠረንንና በዚሁ ሳቢያ የሚመጣውን ጭንቀትና ሐፍረት ትቀንሳለህ። ከዚህም በላይ አፍህ ይበልጥ ንጹሕና ጤነኛ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥርስ ላይ በሚላከክ ቆሻሻ ውስጥ ጥርስንና ድድን ሊጎዱ የሚችሉ ባክቴሪያዎች ይገኛሉ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤው ምንድን ነው?
ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት መጥፎ የአፍ ጠረን ከሚያመጡ ብዙ ሁኔታዎች፣ በሽታዎችና ልማዶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው:-
ብሮንካይት
ሥር የሰደደ የጨጓራ ሕመም
የስኳር በሽታ
የአልኮል መጠጦችን መጠጣት
የአፍ መድረቅ
ኤምፒየማ
ግሳት
የድድ በሽታ
የሆድ ሄርኒያ
የኩላሊት ችግር
የጉበት በሽታ
የወር አበባ
የአፍ ቁስለት
የሴት እንቁላል ለጽንስ ዝግጁ መሆን
የአፍ ንጽሕና ጉድለት
የሳይነስ በሽታ
ሲጋራ ማጨስ
አንዳንድ የካንሰር በሽታዎች
አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች
የጥርስ መበስበስ
የሳንባ ነቀርሳ
የጥርስ ቀዶ ሕክምና የሚያስከትላቸው ቁስሎች
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምላስህም ትኩረት ይሻል
በቅርብ ወደምታገኘው መስተዋት ሂድና ምላስህን በደንብ ተመልከት። በጣም በርካታ በሆኑ ስንጥቆች የተሸፈነ ነውን? ይህ የምላስ ተፈጥሮ ነው። ሆኖም በምላስህ ላይ ያሉት ስንጥቆች በሚልዮን ለሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች መኖሪያ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች ካልተወገዱ የማያቋርጥ መጥፎ የአፍ ጠረንና ሌሎች በጤንነት ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ሰዎች አፋቸውን ሲያጸዱ ምላሳቸውን ችላ ይላሉ።
የጥርስ ሐኪሞች በለስላሳ የጥርስ ብሩሽ ተጠቅሞ የላይኛውን የምላስ ክፍል ማጽዳት ለመጥፎ የአፍ ጠረን መፍትሔ እንደሆነ ይናገራሉ። አንዳንድ ኤክስፐርቶች የምላስ መፋቂያ መጠቀምን ይመክራሉ። በሕንድ አገር ሰዎች ለበርካታ ትውልዶች መጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ በምላስ መፋቂያዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። በቀድሞዎቹ ዓመታት እነዚህ መፋቂያዎች ከብረት ይሠሩ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የፕላስቲክ መፋቂያዎች በይበልጥ የተለመዱ ሆነዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የምላስ መፋቂያ ለማግኘት የጥርስ ሐኪምህን ማማከር ሊያስፈልግህ ይችላል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የአፍ ንጽሕና በጥርስና በጥርስ መካከል ዘልቆ በሚገባ ክር ተጠቅሞ ጥርስን ማጽዳትንም ሆነ ምላስንና ጥርስን መፋቅን ይጨምራል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
ሕይወት