ከዓለም አካባቢ
የጦርነትና ያለመረጋጋት ዘመን
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች 20ኛው መቶ ዘመን ተወዳዳሪ የሌለው ጭካኔና አውሬነት የታየበት ዘመን እንደሆነ ያምናሉ” ብሏል። “ከ1914 እስከ 1989 ያለው ሁለት የዓለም ጦርነቶችና ቀዝቃዛው ጦርነት የተካሄዱበት የ75 ዓመት ዘመን አብዛኛው የዓለም ክፍል ሲዋጋ ወይም ከውጊያ ሲያገግም አለበለዚያም ለውጊያ ሲዘጋጅ ያሳለፈው ዘመን እንደሆነ የሚቆጥሩ የታሪክ ተመራማሪዎች ቁጥር በእጅጉ እየበዛ መጥቷል።” ዘ ዋሽንግተን ፖስት ላይ የወጣ ጽሑፍ ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር እንዲህ ብሏል:- “በ20ኛው መቶ ዘመን የተካሄዱት ጦርነቶች በወታደሮች ላይም ሆነ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥፋት ለማድረስ የታለሙ ‘የጅምላ ጦርነቶች’ ነበሩ። በአይሁዳውያን ላይ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተገደሉትን ጨምሮ በጦርነቱ የተገደሉት ሰዎች በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ናቸው። በቀደሙት መቶ ዘመናት ያልሰለጠኑ ናቸው በሚባሉ ሕዝቦች የተፈጸሙት ጦርነቶች ከእነዚህ ጦርነቶች ጋር ሲወዳደሩ በጣም አነስተኛና ከቁጥር የማይገቡ ናቸው።” ሕዝባዊ ዓመፆችም ለደረሰው እልቂት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በሕዝባዊ ዓመፅ ምክንያት የተገደሉ ሰዎች ምን ያህል ይሆናሉ? “በዝብግንው ብርዥንስኪ ግምት መሠረት ከ1914 ወዲህ የተገደሉት ሰዎች 197 ሚልዮን ይደርሳሉ። ይህ ቁጥር በ1900 የነበረውን ዓለም ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት አንድ አሥረኛ ያክላል ማለት ነው” ሲል ፖስት የተባለው ይኸው ጋዜጣ ገልጿል። ጋዜጣው በመቀጠል “ጭካኔ የተሞላበት ግድያና አሸባሪነት የዚህ የሃያኛው መቶ ዘመን ስር የሰደደ ባሕል መሆኑ የማይታበል ሐቅ ሆኗል። በዚህ መቶ ዘመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ረብሸኞችን ሊያረጋጋና ሊያሳርፍ የቻለ አንድም ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እስካሁን ድረስ አልተገኘም።”
ዘግይቶ የደረሰ ደብዳቤ
በፖስታ አገልግሎት የቅልጥፍና ጉድለት የተማረረ ሰው ካለ በኢጣልያ አገር በቪቼንሳ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ያጋጠማቸው ሁኔታ ሊያጽናናው ይችላል። ኢጣሊያዊው ባል በ1944 በሰሜን አውሮፓ በሚገኝ የናዚዎች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታስሮ እያለ ለሚስቱ “ደብዳቤዬ ቢዘገይብሽ አትጨነቂ” ሲል ይጽፍላታል። ላ ሪፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ “ሰውየው የደብዳቤዋን ዕጣ በደመ ነፍስ ያወቀ ይመስላል” ሲል ገልጿል። ይህ ደብዳቤ ለባለ አድራሻዋ የደረሰው ከ51 ዓመት በኋላ ነው። በአሁኑ ጊዜ በ80 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙት ባልና ሚስት በዚህ ደብዳቤ መድረስ በመደሰታቸውና በመደነቃቸው ለጥቂት ወዳጆቻቸው ግብዣ አዘጋጅተው የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ አድርገዋል። ይህ ፖስታ ይህን ያህል ጊዜ ሊዘገይ የቻለው ወደ የት አቅጣጫ ተጉዞ እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የዓለም ጤና ድርጅት ያደረገው ጥናት
የዓለም የጤና ድርጅት (ደብልዩ ኤች ኦ) በዓለም ጤና ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ዓመታዊ ጥናት ከዓለም ጠቅላላ ሕዝቦች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት (ከሁለት ቢልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ማለት ነው) ሕመምተኞች ናቸው። አብዛኞቹ በሽታዎችና ሕመሞች ሊወገዱ የሚችሉ ናቸው ይባላል። የበሽታዎቹ ዋነኛ ምክንያት ድህነት ነው። 5.6 ቢልዮን ከሚያክሉት የዓለም ሕዝቦች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጣም መሠረታዊ ናቸው የሚባሉትን መድኃኒቶች ለማግኘት አይችሉም። ከዓለም ሕፃናት መካከል ሲሶ የሚሆኑት በቂ ምግብ አያገኙም። ከዓለም ሕዝቦች መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በሽታቸውን ለመከላከል ወይም ለመታከም አይችሉም። በልብ በሽታ፣ በሳንባ በሽታ፣ በነቀርሳ፣ በወባ፣ በመተንፈሻ አካላት ልክፈት እንዲሁም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በሚያጠቃው የተቅማጥ በሽታና በመሳሰሉት ቀሳፊ በሽታዎች በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ። ሆኖም ሪፖርቱ ባለፉት 25 ዓመታት የሰው ልጅ አማካይ ዕድሜ ከ61 ወደ 65 ከፍ ማለቱን ገልጿል። የዓለም የጤና ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ሂሮሺ ናካጂማ “በሕይወት መቆየት የዕለት ተዕለት ትግል ለሆነባቸው በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ረዥም ዕድሜ ማግኘት እንደ ቅጣት እንጂ እንደ ጥሩ ነገር ሊቆጠር አይችልም” ብለዋል።
ፍሬ ቢስ ሆኖ የቀረ የዓለም መሪዎች ስብሰባ
ከመጋቢት 6-12, 1995 ከመላው ዓለም የተውጣጡ 20,000 የሚያክሉ ልዑካን በዴንማርክ አገር በኮፐንሃገን ከተማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተዘጋጀ “በማኅበራዊ ዕድገት ላይ የሚወያዩ ዓለም አቀፍ የመሪዎች ስብሰባ” የሚል ስያሜ በተሰጠው ላይ ተገኝተው ነበር። የስብሰባው ዓላማ ምን ነበር? በታዳጊ አገሮች ያለውን ድህነት፣ ሥራ አጥነትና መድልኦ ማስወገድ ስለሚቻልበት መንገድ ለመወያየት ነበር። ይሁን እንጂ ለዚህ ዓላማ መሳካት ዋነኛ እንቅፋት የሆነው ምን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ጊዜ አልፈጀም። ዋነኛው ችግር በቂ ገንዘብ አለመኖሩ ነበር። በድህነት የተጠቁት አገሮች ለበለጸጉ አገሮች መክፈል የሚኖርባቸው ዕዳ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ዋናውን ዕዳ ይቅርና ወለዱን እንኳን መክፈል አይችሉም። የስብሰባው አስተናጋጅ የሆነችው ዴንማርክ የበለጸጉ አገሮች የእርስዋን አርዓያ በመከተል በጣም ድሆች በሆኑ አገሮች ላይ ያላቸውን ዕዳ እንዲሰርዙ ሐሳብ አቀረበች። ይሁን እንጂ ይህም የራሱ ችግር ነበረው። ብዙዎቹ ድሀ አገሮች ዕዳ ውስጥ የገቡት የጦር መሣሪያ ለመግዛት ነበር። ስለዚህ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካሪ እንደገለጹት ዕዳው ቢሰረዝላቸው በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመው ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ይገዛሉ።
ብዙ ሰዓት የሚሠሩት ሴቶች ናቸው ወይስ ወንዶች?
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ቢሮ እየታተመ የሚወጣው ፖፑሊ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ከሰሜን አሜሪካና ከአውስትራሊያ በስተቀር በሌሎች አገሮች በሙሉ የሚኖሩ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለበርካታ ሰዓቶች ይሠራሉ። ልዩነቱ በጣም ጎልቶ የሚታየው በአፍሪካና በእስያ ፓስፊክ አገሮች ነው። በእነዚህ አገሮች በሥራ ዓለም የተሰማሩ ሴቶች በየሳምንቱ ከ12 ሰዓት በላይ ከወንዶች ይበልጥ ይሠራሉ። መጽሔቱ እንደገለጸው “በብዙ ታዳጊ አገሮች ሴቶች ከአሥር ዓመት በፊት የነበራቸውን አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ ብቻ በየሳምንቱ ከ60 እስከ 90 ሰዓት ይሠራሉ።” በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ግን ወንዶች በቤት ውስጥ ሥራዎች ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል። “ይሁን እንጂ” ይላል ፖፑሊ የተባለው መጽሔት የወንዶች ተሳትፎ እየጨመረ ሊመጣ የቻለው “እንደ ምግብ ማብሰል፣ ቤት ማጽዳትና ልብስ ማጠብ በመሰሉት የተለመዱ የቤት ውስጥ ሥራዎች ከሴቶች እኩል መሥራት በመጀመራቸው ሳይሆን እንደ ሸመታ ባሉት ሥራዎች የሚያጠፉት ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ ነው።”
“የማስታወስ ችሎታ” ያላቸው ዕፀዋት
ብዙ ዕፀዋት አንድ ዓይነት ጥቃት ሲሰነዘርባቸው አጥቂዎቻቸውን የሚያባርርላቸው ኬሚካል ይሠራሉ። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደዘገበው አንዳንድ ዕፀዋት የተሰነዘረባቸውን ጥቃት “የማስታወስ ችሎታ” አላቸው። ይህም በድጋሚ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው በበለጠ ፍጥነት አጥቂውን የሚያባርረውን መርዝ ለመሥራት ያስችላቸዋል። አንድ የትንባሆ ቅጠል በትል ሲበላ ተክሉ ጃስሞኒክ አሲድ የተባለውን መርዝ ይሠራል። ይህ መርዝ ወደ ተክሉ ሥሮች ይወርዳል። ይህም ሥሮቹ ኒኮቲን የተባለውን መርዝ እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። ኒኮቲኑ ወደ ቅጠሉ ይመለስና ቅጠሉ ለበላተኛው የማይጥም እንዲሆን ያደርገዋል። ቀደም ሲል የጃስሞኒክ አሲድ የነካቸው ሥሮች ለሚሠነዘርባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ችለዋል። “ይህም ዕፀዋት በእርግጥም የማስታወስ ችሎታ እንዳላቸው ያመለክታል” በማለት በባፋሎ የኒው ዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ኢያን ባልድዊን ተናግረዋል።
የኤች አይ ቪ ተሸካሚዎች አይነገራቸውም
በጃፓን አገር አንዳንድ ዶክተሮች የኤች አይ ቪ ተሸካሚ የሆኑትን ሰዎች በቫይረሱ መለከፋቸውን አይነግሯቸውም። በዚህም ምክንያት የእነዚህ ሰዎች የትዳር ጓደኞች በቫይረሱ ተለክፈዋል። የጤናና የማኅበራዊ ደህንነት ሚኒስቴር ከአገሪቱ ሆስፒታሎችና የሕክምና ተቋሞች መካከል 363 በሚሆኑት ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ ከተቋሞቹ መካከል ለኤች አይ ቪ በሽተኞች በሙሉ ስለሁኔታቸው የሚገልጹላቸው 43 በመቶ የሚያክሉት ብቻ እንደሆኑ ገልጿል። 28 በመቶ የሚያክሉት ደግሞ የሚናገሩት ለአንዳንድ በሽተኞቻቸው ብቻ ነው። አንዳንድ ሆስፒታሎች ፈጽሞ ለበሽተኞቻቸው እንደማያሳውቁ ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ ጥናቱ ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ ገልጿል። ዶክተሮች ሁኔታውን ከበሽተኞቻቸው ከሚደብቁባቸው ምክንያቶች ዋነኛ ሆኖ የቀረበው የቫይረሱ ተሸካሚዎች “ያላቸው የአእምሮ ሁኔታ በጣም ያልተረጋጋ መሆኑ ነው።”
በጉዞ ምክንያት የሚሰማ ሕመም
በጉዞ ምክንያት ታመህ ታውቃለህ? ከሆነ ይህ ዓይነቱ ችግር ያለብህ አንተ ብቻ አይደለህም። መጠኑ ይለያይ እንጂ ከአሥር ሰዎች መካከል ዘጠኙ በጉዞ ምክንያት እንደሚታመሙ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን ዘግቧል። ውሾች፣ በተለይም ቡችሎች ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል። ሌላው ቀርቶ ዓሦች እንኳን ሞገድ ባለበት ባሕር ላይ በጀልባ ተጭነው ሲወሰዱ እንዲህ ዓይነት ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል! ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች በአብዛኞቹ መድኃኒት ቤቶች የሚሸጡ መድኃኒቶችን ይወስዳሉ። ሊረዱ የሚችሉ ተጨማሪ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል:- በተሽከርካሪ ስትጓዝ አታንብብ። ብዙ በማይወዘውዝ ቦታ ላይ ተቀመጥ፤ ለምሳሌ ያህል በመኪና ውስጥ በፊት ወንበሮች፣ በአውሮፕላን ውስጥ ደግሞ በክንፎች አካባቢ ልትቀመጥ ትችላለህ። እንደ አድማስ ያሉትን ራቅ ያሉ ነገሮች ተመልከት። ሩቅ ለመመልከት ካልፈለግህ ዓይንህን ጨፍን።
“ኃይል የሚያስገኝ ሽልብታ”
ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው “ሽልብታ ጠባይ፣ ንቃትና የሥራ ጥራት ያሻሽላል።” ጥሩ ሽልብታ ሰውነት የማደስ ችሎታ ያለው መሆኑን በመገንዘብ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ሠራተኞቻቸው በመደበኛው የሥራ ሰዓት ማሸለብ የሚችሉበት መንገድ በማፈላለግ ላይ ናቸው። በተለይ የዚህ አስፈላጊነት ግልጽ ሆኖ የሚታየው ንቃትና ደህንነት በጣም በሚዛመዱባቸው እንደ ከባድ መኪና ማሽከርከር፣ አውሮፕላን መንዳትና የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እንደመቆጣጠር ባሉ ሥራዎች ነው። ስለ እንቅልፍ ብዙ ጥናት ያደረጉት ክላውዲዮ ስታምፒ “በ15 ደቂቃ ሽልብታ ለበርካታ ሰዓቶች የሚቆይ ንቃት ማግኘት እንደሚቻል ተገንዝበናል” ብለዋል። ይሁን እንጂ በመደበኛ የሥራ ሰዓት ማሸለብ በብዙ አሠሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ገና ብዙ ይቀረዋል። ጆርናል የተባለው ጋዜጣ እንደሚለው “የሽልብታ ደጋፊዎች ልማዱ በሥራ ቦታዎች ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ‘ኃይል የሚያስገኝ ሽልብታ’ ብለው መጥራት ጀምረዋል።”
ጫጫታውን አቁሙልን
ዘ ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ ባወጣው ርዕስ “እባካችሁ ጫጫታውን አቁሙልን” ሲል ተማጽኗል። ከሣር መከርከሚያ መሣሪያዎች፣ ከረገፉ ቅጠላቅጠል ማጽጃዎች፣ ከመኪና ጥሩንባዎች፣ ከአደጋ ማስጠንቀቂያዎች፣ ከውሾች ጩኸት፣ ከሕፃናት ልቅሶና ከእኩለ ሌሊት በኋላ ከሚደረጉ ድግሶች የሚወጣው የማያባራ ጫጫታ ፀረ ጫጫታ እንቅስቃሴዎች ለሰላምና ለፀጥታ ጠንከር ያለ ዘመቻ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል። ስታር የተባለው ጋዜጣ እንደሚለው እንደነዚህ ላሉት ጫጫታዎች ረዘም ላለ ጊዜ መጋለጥ “ድካምና ጭንቀት ሊያባብስ ይችላል።” በማከልም “የሕክምና ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የደም ግፊት ሊጨምር፣ የልብ ምት ፍጥነት ሊለወጥ እንዲሁም ሰውነት በደም ሥሮች ላይ ተጽእኖ ያላቸውን እንደ አድሬናሊን ያሉትን ሆርሞኖች ሊያመነጭ ይችላል” ብሏል። የጤና ጠበብት እንደሚሉት እንደ ሣር ማጨጃ መኪና ወይም እንደ ሞተር ብስክሌት ካሉት መሣሪያዎች ለሚወጡት ከ85 ዴሲብል የሚበልጡ ድምፆች ከስምንት ሰዓት በላይ መጋለጥ ለመስማት ችሎታችን በጣም አደገኛ ነው።