እውነት ሕይወቴን አተረፈልኝ
ከቀድሞ ጓደኞቼ አብዛኞቹ ሕይወታቸው በኤድስ ተቀጥፏል። ከመሞታቸው በፊት ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ አያቸው ነበር። እኔም እውነት ባይደርስልኝ ኖሮ እንደነርሱ ሞቼ ነበር። ሁኔታዬን ልግለጽላችሁ።
የተወለድኩት ታኅሣሥ 11, 1954 ሲሆን የጆንና የዶሮቲ ሆሪ ሁለተኛና የመጨረሻ ልጅ ነኝ። ወላጆቼ ዶሎረስ የሚል ስም ቢያወጡልኝም ስወለድ ትንሽ አሻንጉሊት እመስል ስለ ነበር እማማ ዶሊ ብላ ትጠራኝ ነበር። ይህ የቅጽል ስሜ አብሮኝ ኖረ። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ለእናቴ የብዙ መከራ ምንጭ እንደምሆን የጠረጠረ ሰው አልነበረም።
የምንኖርበት ሕንጻ ረዥምና ጠባብ በመሆኑ የባቡር ሐዲድ አፓርተማ ተብሎ ይጠራ ነበር። ሕንጻው የሚገኘው በኒው ዮርክ ከተማ በ61ኛው ጎዳና ነበር። አፓርተማችን ከአይጦች ጋር ተጋርተን የምንኖርበት በመሆኑ የሚያስደስት ቦታ አልነበረም። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ በአይጥ ከተነከስኩ በኋላ ወዲያው ሕንጻውን ለቅቀን ወጣን።
በ1957 ወደ ደቡብ ማንሃተን ምሥራቃዊ ክፍል ተዛወርን። ይህ መኖሪያችን ቀደም ሲል እንኖርበት ከነበረው ጋር ሲወዳደር በጣም ቆንጆ ቦታ ነበር። ቆንጆ መኝታ ቤቶች ያሉት ከመሆኑም በላይ በመስኮቴ በኩል ሰፊ የሆነ የመናፈሻ ሥፍራና ኢስት የተባለውን ወንዝ ለመመልከት እችል ነበር። ጀልባዎች ሲያልፉና ልጆች ኳስ ሲጫወቱ ማየት እችል ነበር። አዎን፣ ይህ አካባቢ ገነት ሆኖልኝ ነበር። ይሁን እንጂ አስተማማኝ የነበረው ሕይወቴ መፈራረስ ጀመረ።
የአልኮልና የአደገኛ ዕፆች ሱሰኛ መሆን
አባባና እማማ ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቁ ነበር። በመጀመሪያ የሚጨቃጨቁበት ምክንያት አይገባኝም ነበር። በኋላ ግን አባቴ ሁልጊዜ ሰክሮ እንደሚመጣ ተገነዘብኩ። ሥራ ስላላገኘ ሥራ የነበራት እማማ ብቻ ነበረች። ጓደኞቼ አባቴ ሰካራም መሆኑን ሲያውቁ ያወርዱብኝ የነበረው ትችት ሕይወቴ በጣም መራራ እንዲሆን አደረገው።
ሁኔታዎች በጣም እየተባባሱ መጡ። በመጨረሻም አባቴ መደባደብ ስለጀመረ እናቴ ከቤት አስወጣችው። በዚህ ምክንያት በአንድ ወላጅ ብቻ የምንተዳደር ቤተሰቦች ሆንን። ስምንት ወይም ዘጠኝ ዓመት በሆነኝ ጊዜ የቤተሰቤ ሁኔታ በጣም አስመረረኝ። እማማ ኑሮዋን ለማሸነፍ ስትል ብዙ ሰዓት ስለምትሠራ እኔና እህቴ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ጎረቤቶቻችን ቤት እንቆይ ነበር።
ስድስተኛ ክፍል ስደርስ በጣም ዓመፀኛ መሆን ጀመርኩ። ከክፍል እየጠፋሁ በአካባቢያችን ወደ ነበረው የቶምኪንስ አደባባይ መናፈሻ እየሄድኩ ችግሬን ለመርሳት ናላዬ እስኪዞር ድረስ መጠጣት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ከእኔ በዕድሜ ብዙ ከሚበልጡ ልጆች ጋር አብሬ መዋል ጀመርኩ። ገና 11 ዓመቴ ቢሆንም አለ ዕድሜዬ አድጌ ስለ ነበር የ16 ወይም የ17 ዓመት ልጅ መስዬ እታይ ነበር። እነዚህ አዳዲስ ጓደኞቼ ይጠጡ፣ ማሪዋና ያጨሱ፣ ኤል ኤስ ዲ እና ሄሮይን የተባሉትን አደንዛዥ ዕፆች ይወስዱ ነበር። እኔም የእነርሱን ወዳጅነት ለማግኘት ስለፈለግኩ እነዚህን ነገሮች መሞካከር ጀመርኩ። 14 ዓመት ሲሞላኝ አለነዚህ ዕፆች መንቀሳቀስ አቃተኝ።
እናቴ አወቀች
“ወደዚህ ዓለም ያመጣሁሽ እኔ ነኝ፣ እኔው አጠፋሻለሁ።” በአካባቢያችን ያሉ እናቶች ልጆቻቸው በጣም ሲያናድዷቸው ይሉት የነበረ አባባል ነው። አብዛኛውን ጊዜ ረጋ ያለችውና ራስዋን የምትገዛዋ እናቴ የ14 ዓመት ልጅዋ ሄሮይን እንደምትወስድ ስታውቅ የተናገረችኝ ይህንኑ ቃል ነበር።
ወደ መታጠቢያ ቤት ሮጬ ገባሁና በሩን በእግሮቼ ቀርቅሬ ለመያዝ ሞከርኩ። ግን አልሆነልኝም። ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገባሁ! በሕይወቴ እንደዚያ ቀን ተገርፌ አላውቅም። ከእማማ ቁጣ የዳንኩት እህቴና ሄሮይን እንደምወስድ የተናገረችብኝ ሴት መታጠቢያ ቤት ገብተው እናቴን ሲይዙልኝ ሮጬ በማምለጤ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ቤት ተመለስኩና ከዕፅ ሱሰኛነት ለመላቀቅ የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ተስማማሁ።
የባለሙያ እርዳታ ማግኘት
ከጥቂት ወራት በኋላ ለዕፅ ሱሰኞች የተሐድሶ ፕሮግራም ስለሚሰጥ ተቋም የሚገልጽ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን ተመለከትኩ። የዕፅ ሱሰኝነታቸውን ለማሸነፍ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች የሚረዱበት ቦታ ነበር። ስለተመለከትኩት ነገር ለእማማ አዋየኋትና በኒው ዮርክ ከተማ ከሚገኙት የተቋሙ ማዕከሎች ወደ አንዱ ላከችኝ። በዚህ ድርጅት ውስጥ ሰዎች አኗኗራቸውን ለመለወጥ የሚያስፈልጋቸውን ግፊት የሚያስገኝላቸው የቤተሰብ ዓይነት መንፈስ ነበር። በዚያም ሁለት ዓመት ተኩል ያህል ኖርኩ።
የተሰጠኝ እርዳታ ብዙ የጠቀመኝ ቢሆንም በጣም እተማመንባቸውና አከብራቸው የነበሩ የድርጅቱ ሠራተኞች ዕፅ መውሰድን እርግፍ አድርገው ከተዉ በኋላ እንደገና ሲመለሱበት ሳይ በጣም አዘንኩ። እንደተታለልኩና ሞኝ እንደሆንኩ ተሰማኝ። “አንዴ ሱሰኛ የሆነ ምንጊዜም ሱሰኛ እንደሆነ ይኖራል” የሚለው አባባል ስህተት እንደሆነ አስተምረውን ነበር። አሁን ግን ይህ አባባል ስህተት እንዳልሆነ እነዚህ ሰዎች ሕያው ምሥክር ናቸው ብዬ ማመን ጀመርኩ።
ቢሆንም በ17 ዓመቴ ከዕፅ ሱስ ነጻ ሆኜና ሁለተኛ ሄሮይን ላለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። በዚሁ ጊዜ እናቴና እህቴ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀምረው ነበር።
አሁንም የቤተሰቤን ስም ማጥፋቴን ቀጠልኩ
ዕፅ መውሰድ ባቆምም አሁንም የቤተሰቤን ስም እንዳጠፋሁ ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም ማጨስ፣ ፓርቲና ዲስኮ መሄድ የመሳሰሉትን የሚከለክለውን የቤተሰቡን አዲስ ሕግ አክብሬ ለመኖር ዝግጁ ስላልነበርኩ ነው። ጓደኞቼንና ዓለማዊ ዝንባሌዬን ለመተው እምቢተኛ በመሆኔ ብዙም ሳይቆይ እናቴ ከቤት አስወጣችኝ። እንዲህ ማድረጓ በጣም የጠቀመኝ ቢሆንም በጣም ጠላኋት። ፍንክች ሳትል ለጽድቅ ባላት አቋም ጸናች።
በዚህ ምክንያት አዲስና የተሻለ ሕይወት ለመምራት ቤቴን ትቼ ወጣሁ። ትምህርት ቤት ተመልሼ ገባሁና ለኮሌጅ ትምህርት የሚያስፈልገኝን ወጪ የምሸፍንበት ሥራ የሚያስገኝልኝ ሞያ መማር ጀመርኩ። በትምህርቴ ጥሩ ውጤት ስላገኘሁ እንደገና ጠቃሚ የኅብረተሰቡ አባል ሆንኩ። ጥሩ ሥራ ይዤ የራሴን ቤት ተከራየሁ። በዚህ ጊዜ አንድ የቆየ የወንድ ጓደኛዬን አገኘሁና የፍቅር ሕይወት ጀመርኩ። ግንኙነታችንን አድሰን ሁኔታዎችን ካስተካከልን በኋላ ለመጋባት አሰብን።
ቆየት ብሎ ግን የወንድ ጓደኛዬ ዕፅ መውሰድ ሲጀምር ሁኔታዎቹ እየተበላሹ ሄዱ። የደረሰብኝን የስሜት ቁስል መቋቋም ስላልቻልኩ እኔም አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ ጀመርኩ። የባለጠጎች መደሰቻ የሚባለውን ኮኬይን መውሰድ ጀመርኩ። በዚያ ጊዜ ኮኬይን ሱስ አያስይዝም ተብሎ ይታመን ስለነበረ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ዕፅ ነበር። ለእኔ ግን ከሄሮይን የከፋ ሆኖብኛል።
በ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ኮኬይን መውሰድ ከጀመርኩ ሦስት ዓመት ሆኖኝ ነበር። በመጨረሻም መያዥያ መጨበጫ ስለጠፋኝ ‘ሕይወት ማለት ይህ ብቻ ነው?’ ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። ሕይወት ማለት ይህ ብቻ ከሆነ መኖር አልፈልግም፣ ሰልችቶኛል ብዬ አሰብኩ። ወደ እማማ ተመለስኩና ሁሉ ነገር ስለ ሰለቸኝ ለዕፅ ሱሰኞች የተሐድሶ ፕሮግራም ወደሚሰጥበት ተቋም መመለሴ ነው አልኳት። በዚያም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ከቆየሁ በኋላ ዳግመኛ ከዕፅ ሱሰኝነት ነጻ ወጣሁ።
እውነትን ወደ ማወቅ ተቃረብኩ
አሁንም እንደገና ጥሩ ሥራ ያዝኩና ጥሩ መኖሪያ ቤት ተከራየሁ። የወንድ ጓደኛም አገኘሁ። ወዲያው ተጫጨን። በዚህ ጊዜ ሁሉ እናቴ አዘውትራ ትጠይቀኝ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትነግረኝና መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ትልክልኝ ነበር። እኔ ግን አንድም ጊዜ አላየኋቸውም። ማግባትና የራሴን ቤተሰብ መመስረት እንዳሰብኩ ለእማማ ነገርኳት። በዚህም ምክንያት በሕይወቴ ላይ ዘላቂ ለውጥ ያስከተለውን የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች አድርገው የተባለውን መጽሐፍ ላከችልኝ።
ይህን መጽሐፍ ሳነብ ስፈልግ የኖርኩት ምን እንደሆነ ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ የምፈልገውን ነገር ላገኝ የሞከርኩት ከተሳሳተ አቅጣጫ ነበር። በመጨረሻ ስሜቴንና በልቤ ውስጥ ያለውን የሚረዳልኝ አገኘሁ። ያን የመሰለ ስሜት የኖረኝ ከሰው ሁሉ የተለየሁ ስለሆንኩ እንዳልሆነ ተረዳሁ። ጤነኛ ሰው ነበርኩ! ይሁን እንጂ ላገባው ያሰብኩት ሰው የቤተሰብ ሕይወት የተባለውን መጽሐፍና መጽሐፍ ቅዱስን ባሳየሁት ጊዜ ሳቀብኝ። ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ለመመስረት የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ከባድ የሆነ ውሳኔ ከፊቴ ተደቀነብኝ። እርሱን ልተው ወይስ አብሬው ልኑር? እርሱን ጥዬ መሄድ እንዳለብኝ ወሰንኩ።
የወንድ ጓደኛዬ በጣም ተቆጣ። አንድ ቀን ወደ ቤቴ ስመለስ ልብሶቼን በሙሉ በምላጭ ብጭቅጭቅ አድርጎ ቀድዶ አገኘሁ። ጫማዎቼ፣ ኮቶቼ፣ የቤት ዕቃዎቼ፣ በጠቅላላው የነበረኝ ንብረት በሙሉ ተቀዳዶ አለበለዚያም ተሽጦ አገኘሁ። የቀረኝ ንብረት የለበስኩት ልብስ ብቻ ነበር። ሞት ተመኘሁ። አንዳንድ ጊዜ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥማችሁ ውጣ ውረድ ያንገሸግሻችኋል። በዚህም ምክንያት ችግሮቼን ለመቋቋም ስል ሳደርግ ወደ ቆየሁት ልማድ፣ ማለትም ራሴን በዕፅ ወደ ማደንዘዝ ለመመለስ ፈለግኩ። ዕፅ መውሰድ ወይም ራሴን መግደል አለብኝ ብዬ አሰብኩ።
ዕፅ ወደ መውሰድ ብመለስም እማማ ተስፋ ቆርጣ አልተወችኝም። በየጊዜው ትጎበኘኝና መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ታመጣልኝ ነበር። አንድ ቀን ምሽት ላይ ልትጠይቀኝ ስትመጣ እንዴት እንደሚሰማኝ ነገርኳት። ያደረግኩት ሙከራ ሁሉ እንዳሰለቸኝና ተስፋ እንደቆረጥኩ ገለጽኩላት። እርሷ ግን “ሁሉን ነገር ሞክረሻል፣ ይሖዋን ደግሞ ለምን አትሞክሪም?” አለችኝ።
እውነት አዳነኝ
ለበርካታ ዓመታት አጥብቃ ስትመክረኝ የቆየችውን ነገር ለማድረግ የተስማማሁት በ1982 ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ኮስተር ብዬ ማጥናት ጀመርኩ። ወዲያው በምማራቸው ነገሮች መመሰጥ ጀመርኩ። የእኔ ሕይወት በይሖዋ ፊት በጣም ውድ እንደሆነና ሕይወት እውነተኛ ዓላማ እንዳለው ማስተዋል ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ይሖዋን ለማገልገል ከፈለግኩ ብዙ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብኝና ይህንንም ለማድረግ ስሜታዊም ሆነ መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ስለዚህም እማማን ወደ ቤትዋ ተመልሼ መኖር እችል እንደሆነ ጠየቅኳት።
እማማ ብዙ ጊዜ አሳዝኜአት ስለ ነበረ አመነታች። ወደ ቤትዋ ተመልሼ አብሬያት እንድኖር ስላቀረብኩላት ጥያቄ ከአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ጋር ተማከረች። በዚህ ጊዜ በእርግጥ ልለወጥ እንደምችል እናቴ እንደተሰማት ስለ ተገነዘበ “እስቲ አንድ ዕድል ስጪያት” ሲል መከራት።
በዚህ ጊዜ ግን አላሳዘንኳትም። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩ። በይሖዋ እርዳታ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ ቻልኩ። የአምላክ የእውነት ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም አስችሎኛል። (ዮሐንስ 17:17) ከሄሮይንና ከኮኬይን ሱስ ይበልጥ አስቸጋሪ የሆነብኝን የትንባሆ ሱስ እንኳን ለማሸነፍ ቻልኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሕይወት መኖር አስደሰተኝ።
ከጥቂት ወራት በኋላ ታኅሣሥ 24, 1983 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ። በሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ሆንኩ። ይህም አገልግሎቴን ከፍ ለማድረግ አስችሎኛል። መጀመሪያ ላይ የቀድሞ ጓደኞቼ በአገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርቼ ሲያዩኝ ይቀልዱብኝና ይሳለቁብኝ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ቀደም ብሎ እንዳስጠነቀቀው “በዚህም ነገር ወደዚያ መዳራት ብዛት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ።”— 1 ጴጥሮስ 4:4
በመስከረም ወር 1984 የዘወትር አቅኚ ሆንኩና ብዙም ሳልቆይ በየሳምንቱ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ቻልኩ። ከእነዚህ ጥናቶች አንዳንዶቹ አገልግሎት በጀመርኩበት ጊዜ ከተሳለቁብኝ ሰዎች መካከል ነበሩ። በርካታ ወጣቶች እውነትን እንዲቀበሉ ለመርዳት ስለቻልኩ በሕይወቴ ውስጥ እንደዚህ ደስተኛ የሆንኩበት ጊዜ የለም። ሁልጊዜም እናት የመሆን ፍላጎት ስለነበረኝ አሁን የመንፈሳዊ ልጆች እናት ለመሆን መቻሌ ዘወትር ያስደስተኛል።— ከ1 ቆሮንቶስ 4:15 ጋር አወዳድር።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በቤታችን አካባቢ ባሉ ጎዳናዎች ላይ አብሬያቸው ዕፅ እወስድ የነበሩ ጓደኞቼን እመለከታለሁ። እነዚህ ጓደኞቼ በኤድስ የተለከፉ ሰዎች በተጠቀሙባቸው መርፌዎች በመጠቀማቸው ምክንያት ኤድስ ስለያዛቸው በጣም አስፈሪ ቁመና አላቸው። ከዚያ ወዲህ ብዙዎቹ ሞተዋል። እኔም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ባልማር ኖሮ እንደነርሱ እሞት እንደነበረ አውቃለሁ። እውነት ሕይወቴን አትርፎልኛል ለማለት እችላለሁ።
ራሳችሁን ከሥቃይ አድኑ
ገና ሕፃን ሳለሁ እውነትን ባውቅ ኖሮ ይህ ሁሉ ሥቃይና መከራ በሕይወቴ ላይ አይደርስም ነበር ብዬ አስባለሁ። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ የወጣትነት ዕድሜዬን በከንቱ በማባከኔ የሚሰማኝን ጸጸትና ምሬት እንድቋቋም እየረዳኝ ቢሆንም የደረሰብኝ የስሜት ቁስል ሙሉ በሙሉ እንዲፈወስ አዲሱን ሥርዓት መጠበቅ ይኖርብኛል። (ራእይ 21:3, 4) በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ይሖዋን በማወቃቸውና ይሖዋ የሚያስተምራቸውን ነገሮች ሥራ ላይ እንዲያውሉ የሚረዳቸው ድርጅት በማግኘታቸው ምን ያህል የተባረኩ እንደሆኑ ልነግራቸው ከልብ እጥራለሁ።
ይህ ዓለም በጣም የሚያስደስትና የሚያጓጓ መስሎ ሊታይ ይችላል። በተጨማሪም ምንም ችግር ሳይደርስባችሁ ራሱ ያስደስታሉ በሚላቸው ድርጊቶች ልትካፈሉ እንደምትችሉ ሊያሳምናችሁ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ዓለም ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞባችሁ ሲበቃው ይወረውራችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ዓለም ገዥ፣ እንዲያውም የዚህ ዓለም አምላክ ዲያብሎስ እንደሆነና ዓለምንም ሆነ በዓለም ያሉትን መውደድ እንደማይገባን የሚናገረው በእርግጥ ትክክል ነው። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17፤ 5:19) የዓለም ሰዎች የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ስለሚኖሩ ከእነርሱ ጋር መወዳጀት እውነተኛ ደስታ ሊያመጣላችሁ አይችልም።— 2 ጴጥሮስ 2:19
ስለ ግል ሕይወቴ የተናገርኳቸው እነዚህ ነገሮች ሊደክሙለት የሚገባው ሕይወት “እውነተኛው ሕይወት” ማለትም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኘው የዘላለም ሕይወት ብቻ እንደሆነ ሰዎች እንዲገነዘቡ እንደሚረዳቸው ተስፋ አደርጋለሁ። በእውነት ውስጥ በምንመላለስበት ጊዜ ምንም ያህል ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን ከአጥሩ በስተ ማዶ ባለው የሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚገኘው መስክ በምንም መንገድ ካለንበት የተሻለ አይደለም። የተሻለ ሆኖ እንዲታየን የሚሞክረው ሰይጣን ነው። ከክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ሆኜ ዐይኖቼ በእውነተኛው ሕይወት፣ አዎን፣ በገነቲቱ ምድር በሚገኘው እውነተኛ ሕይወት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ እጸልያለሁ። (1 ጢሞቴዎስ 6:19)—ተራኪዋ ዶሊ ሆሪ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከእናቴ ጋር ሆኜ በቶምኪንስ አደባባይ መናፈሻ ስመሰክር