የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 10/8 ገጽ 24-27
  • መሬት ወደ በረሃማነት ሲለወጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መሬት ወደ በረሃማነት ሲለወጥ
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የበረሃዎች ወሰን ይለዋወጣል፤ የሚሰጡትም ፍቺዎች የተለያዩ ናቸው
  • በረሃማነት
  • ዋና መንስኤዎቹና ውጤቶቹ
  • አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ ይገኛል ብሎ ማሰብ አይቻልም
  • ‘በረሃው ሐሴት ያደርጋል’
  • እየተመናመነ የሚገኘው የምድር የተፈጥሮ ሀብት
    ንቁ!—2005
  • ብዙዎች ተስፋ የቆረጡት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2008
  • ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ ነውን?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ንቁ!—1997
g97 10/8 ገጽ 24-27

መሬት ወደ በረሃማነት ሲለወጥ

ወደ 100 በሚጠጉ አገሮች ውስጥ የሚገኝ መሬት ቀስ በቀስ ወደ በረሃማነት እየተለወጠ እንደሆነና ይህም ከ900 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የሚነካ እንዲሁም በዓለም አቀፉ ገቢ ላይ በየዓመቱ 42 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እንደሚያስከትል ይነገራል። በበረሃማነት በእጅጉ እየተጠቁ ያሉት ድሃዎቹ አገሮች (81 የሚያክሉት ታዳጊ አገሮች ናቸው) ቢሆኑም ስጋቱ ያጠላው በእያንዳንዱ አሕጉር በሚገኙት አገሮች ላይ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) በረሃማነትን “በጣም ከባድ ከሆኑት አካባቢያዊ ችግሮች አንዱ” ሲል ሰይሞታል። በአንጻሩ ደግሞ ተመራማሪዎች “በረሃ በመስፋፋት ላይ አይደለም” ይላሉ። እንዲህ ዓይነት የሐሳብ ልዩነት እንዴት ሊኖር ቻለ?

የበረሃዎች ወሰን ይለዋወጣል፤ የሚሰጡትም ፍቺዎች የተለያዩ ናቸው

አፍሪካ ውስጥ በሳህል ክልል ለረጅም ጊዜ ከቆየው ድርቅ በኋላ (1968-73) በረሃ በእርሻ መሬቶች ላይ እየተረማመደ በመገስገስ ላይ ነው የሚለው ሐሳብ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ተቀርጿል። ይሁን እንጂ በኔብራስካ (ዩ ኤስ ኤ) ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የድርቅ መረጃ ማሰባሰቢያ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶናልድ ኤ ዊልሃይት እንዳሉት ከሆነ ሳይንቲስቶች በጊዜው የፈጠሩት “ተስፋ ቢስ የሆነ ሥዕል በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ዓመታት ውስጥ ብቻ በተሰባሰበ አነስተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተና የተዛባ ነበር።”

ባዮማስን (የሕያዋን ነገሮችን ክምችት) የሚያሳዩ ዘመናዊ የሳተላይት ምሥሎች በደረቅና በእርጥብ ወራት የሚኖረው የዕፅዋት መጠን እንደሚዋዥቅ ያሳያሉ። ኤክስፐርቶች እንደሚሉት ይህ ልዩነት “በረሃው እየሰፋ ወይም እየጠበበ ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል።” በመሆኑም የበረሃዎች “ወሰን ይለዋወጣል” ይሁን እንጂ ሁልጊዜ “ይሰፋሉ” ማለት አይደለም። ያም ሆኖ ግን ዶክተር ዊልሃይት “በረሃማነት እየታየ መሆኑን” አስምረውበታል። ይሁን እንጂ ይህ በእርግጥ ምን ማለት ነው?

በረሃማነት

ብዙውን ጊዜ በ“በረሃማነት” እንዲሁም በበረሃዎች መስፋፋትና መጥበብ መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን እንደገለጸው በረሃማነት የሚያመለክተው ሌላ ክስተትን ነው። የበረሃ መስፋፋትም ሆነ መጥበብ የሚታየው በበረሃዎች ዳርቻ ላይ ሲሆን በረሃማነት ግን በጣም ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚታይ ሁኔታ ነው፤ ምናልባትም እነዚህ ቦታዎች ከበረሃ ርቀው የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። ከምድር የየብስ ገጽ 35 በመቶውን ከሚሸፍነው ከዚህ ስፋት ያለው ደረቅ የእርሻ መሬት መካከል አብዛኛው ቀስ በቀስ ወደ በረሃነት እየተለወጠ ነው። ዛሬ በረሃማነት በመባል የሚታወቀው ይህ ክስተት ነው።

በረሃማነት የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በሚመለከት ያለው አመለካከት ይህን ያህል ሰፊ ይሁን እንጂ ሁለቱን ክስተቶች በሚመለከት አሁንም ግራ መጋባቱ አልተወገደም። ለምን? መቀመጫውን ለንደን ያደረገውና በልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ፓኖስ የተባለው የመረጃ ድርጅት ይህ ግራ መጋባት እንዲፈጠር ያደረገውን አንደኛውን ምክንያት ጠቁሟል። አንዳንድ ጊዜ የፖሊሲ ንድፍ አውጭዎች በረሃዎች እየተስፋፉ ነው የሚለው ሐሳብ እንዳይጠፋ የሚፈልጉት የፖለቲካዊ ወገኖችን ድጋፍ ለማሰባሰብ “ስለ ‘በረሃማነት’ ውስብስብ ሂደት ከማስረዳት ይልቅ ይህን ቀላል ሆኖ ስለሚያገኙት ነው።”

ፓኖስ እንደጠቆመው “የግንዛቤው መለዋወጥ በእርግጥ ‘በረሃማነት’ ምንድን ነው በሚለው ጉዳይ ላይ የጦፈ ክርክር እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።” ክርክሩ ምንድን ነው? ተጠያቂው ሰው ነው ወይስ የአየር ጠባዩ የሚል ነው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለበረሃማነት የሚከተለው ፍቺ እንዲሰጥ ሐሳብ አቅርቦ ነበር:- “የሰው ልጅ በሚፈጽመው ጥፋት ምክንያት በሐሩር፣ በከፊል ሐሩርና በእርጥበት አዘል ደረቅ አካባቢዎች ላይ የሚከሰት ፍርስረሳ (ዲግሬዴሽን) ነው።” (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) አካባቢና ልማት በተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የድራይላንድ ፕሮጄክት ዳይሬክተር የሆኑት ካሚላ ቱልሚን እንዳሉት ይህ ፍቺ ለበረሃማነት ተጠያቂ የሚያደርገው ሰውን በመሆኑ ብዙዎቹን አገሮች አስከፍቷል። በመሆኑም በቅርቡ የፍቺው የመጀመሪያ ክፍል “ከአየር ንብረት መለዋወጥና ከሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች የተነሣ” ተብሎ ተስተካክሏል። (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ይህ አዲስ ፍቺ ሰዎችና የአየር ንብረቱ በጋራ ለበረሃማነት ተጠያቂ እንደሆኑ ይገልጻል፤ ይሁን እንጂ ክርክሩ በዚህ አልተቋጨም። ለምን?

ፓኖስ እንደሚለው “ለበረሃማነት የሚሰጡት ፍቺዎች እንዲህ እንደ አሸን መፍላታቸውና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ውዝግብ ችግሩ ስጋት ላይ ለጣላቸው ብዙ አገሮች ተጨማሪ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ የሚሰማቸው አንዳንድ ኤክስፐርቶች አሉ።” ውዝግቡ የማያባራ ከመሆኑ የተነሣ “ቃሉ ትርጉም የለሽ እየሆነ ሄዷል።” “በረሃማነት” የሚለው ቃል ጭራሽ ሊቀር ይገባል የሚሉ ወገኖችም አሉ። ይሁንና ቃሉን መቀየር ለችግሩ እልባት አይሆንም ወይም የችግሩን መንስኤ አያስወግድም። ለበረሃማነት ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?

ዋና መንስኤዎቹና ውጤቶቹ

በአለን ግሬንገር የተዘጋጀው በረሃማነት (ዴዘርቲፊኬሽን) የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ለበረሃማነት ዋና መንስኤዎች ሳያፈራርቁ ማረስ፣ ከልክ በላይ ለግጦሽ መሬትነት መጠቀም፣ የደን ምንጠራና ደካማ የመስኖ ዘዴዎች ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ መንስኤዎች መካከል ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት በአንድ ላይ ሲከሰቱ በረሃማነት ያስከትላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሕዝብ ብዛት፣ በአየር ጠባይ እንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ረገድ የሚታዩት ለውጦች ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

በረሃማነት የሚያስከትለው አንዱ በግልጽ የሚታየው ውጤት የደረቁን ምድር ምግብ የማብቀል ችሎታ ማምከን ነው። ይህ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ በመከሰት ላይ ያለ ነገር ቢሆንም በተለይ 66 በመቶ የሚሆነው የአሕጉሪቱ ክፍል በረሃ ወይም ደረቅ ምድር በሆነባት በአፍሪካ ጉልህ ሆኖ ይታያል። ይሁን እንጂ በረሃማነት ከዚህም የከፋ ውጤት አለው። ወደ ጦርነት ይመራል። ግሪንዎር—ኢንቫይርመንት ኤንድ ኮንፍሊክት የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው “ለማኅበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲሁም ለደም መፋሰስና ጦርነት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መሃል የአካባቢ ፍርስረሳ የሚጫወተው ሚና እያደር እየጨመረ መጥቷል።”

ሌላው ቀርቶ ጦርነትን ለመከላከል የሚደረጉት ጥረቶች እንኳ የአካባቢ ውድመትን የሚያስከትሉና ድህነትን የሚያባብሱ ሆነዋል። እንዴት? ፓኖስ እንዲህ በማለት ያስረዳል:- “መንግሥታት ከመሬት ፍርስረሳ የተነሣ እየተመናመኑ በመጡት የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ በሚደረገው ሽኩቻ ሳቢያ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲገጥማቸው ብዙውን ጊዜ ዓመፁን ለማዳፈን የሚመርጡት በጠመንጃ አፈሙዝ ነው። በዚህ መንገድ መንግሥታት ገንዘባቸውን ድህነትን ለማቃለል ሳይሆን ለወታደራዊ ወጪዎች ያውሉታል።” ይሁን እንጂ የበረሃማነትን ውጤቶች ከመታገል ይልቅ መንስኤዎቹን ለመዋጋት ምን ሊደረግ ይችላል?

አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ ይገኛል ብሎ ማሰብ አይቻልም

ከ100 ከሚበልጡ አገሮች የተውጣጡ ተወካዮች በዚህ ጥያቄ ላይ ለ13 ወራት ሲመክሩ ከቆዩ በኋላ “በረሃማነትን ለመዋጋት የተነደፈውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነት” ተቀብለዋል፤ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባባል ከሆነ ይህ ስምምነት በረሃማነትን ለመዋጋት ለሚደረገው ትግል አንድ እርምጃ ነው። ስምምነቱ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ በረሃማነትን ለመከላከል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ከአደጉት አገሮች ወደ ታዳጊ አገሮች መላክን የሚጠይቅ ሲሆን የምርምርና የሥልጠና መርኃ ግብሮች መዘርጋትን በተለይም በየአገሩ ያለውን የሰው ኃይል በተሻለ መንገድ መጠቀምን የሚያካትት ነበር። (ዩ ኤን ክሮኒክል) ይህ አዲስ ስምምነት የደረቅ ምድርን ፍርስረሳ ይገታ ይሆን?

ፓኖስ እንዳለው ለውጥ ለማምጣት ከቃላት በተጨማሪ ተጨባጭ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋል። ከጉባኤው አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት ሃማ አርባ ደያሎ ከ1977 እስከ 1988 ባሉት ዓመታት ውስጥ በረሃማነትን ለመከላከል በተወሰዱት እርምጃዎች በዓመት እስከ አንድ ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ድረስ ወጪ ተደርጓል። ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እንደሚለው ጉልህ መሻሻል እንዲታይ ካስፈለገ ታዳጊዎቹ አገሮች ከዚህ የገንዘብ መጠን ከአራት እስከ ስምንት ጊዜ ድረስ እጥፍ ወጪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ይሁን እንጂ ይህንን ወጪ መሸፈን የሚችል ማን ይኖራል? ፓኖስ “በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገሮች በረሃማነትን ለመግታት ከቀድሞው ወጪያቸው የተለየ ነገር አያደርጉም” በማለት ካስጠነቀቀ በኋላ በመቀጠል “በበረሃማነት የሚሰቃዩት ድሃ አገሮች ከዚህ ጉባኤ ስምምነት ቀላል የሆነ ወይም ቅጽበታዊ መፍትሔ ይገኛል ብለው መጠበቃቸው እውነታውን መሸሽ ይሆናል” ብሏል። የሆነ ሆኖ ፓኖስ በረሃማነት እንዲህ በዓለም አቀፍ መድረክ መወያያ ርዕስ መሆኑ ችግሩ ፈጦ እንዲታይ የሚያደርግ በመሆኑ “ይህ በራሱ አንድ ድል ነው” ሲል ገንቢ አስተያየት በመስጠት ደምድሟል።

‘በረሃው ሐሴት ያደርጋል’

እርግጥ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ብዙ ወንዶችና ሴቶች በረሃማነት በዚሁ ከቀጠለ የሚያስከትለውን እልቂት የሰው ልጅ እንዲገነዘብ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። “ደን ከሰው በፊት ነበር፤ በረሃ ግን የመጣው ከሰው በኋላ ነው” እንደሚለው ያሉት አባባሎች ሰዎች ለውጥ ለማምጣት እንዲጣጣሩ አነሳስተዋቸዋል።

ይሁንና አስተዋይ የሆኑ ሰዎች የበረሃማነት ችግር እጅግ ውስብስብ እንደሆነ ይገነዘባሉ። የሰው ልጅ ምንም ያህል በቅን ልቦና ተነሳስቶ ቢሠራ ዛሬ ምድር አቀፍ ለሆኑት ችግሮች መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በሚመለከት ሊያደርገው የሚችለው ነገር ውስን እንደሆነ ይገነዘባሉ።

ይሁን እንጂ በአንጻሩ የምድር ፈጣሪ ይህንንም ሆነ ሌሎቹን አካባቢያዊ ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እንደሚያስወግዳቸው ማወቅ ስለ ምድር የወደፊት ዕጣ ለሚጨነቁ ሰዎች የሚያጽናና ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ የቀሩበት ጊዜ ባለመኖሩ ነቢዩ ኢሳይያስ በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት በረሃዎችንና ፍርስረሳ የደረሰበትን መሬት በሚመለከት የጻፈውን ትንቢት ፍጻሜም በጉጉት መጠባበቃችን እውነትነት አለው:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። . . . በምድረ በዳ ውኃ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፣ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች።” (ኢሳይያስ 35:1-7፤ 42:8, 9፤ 46:8-10) በቅርቡ በረሃማነት ተገቶ ሁኔታው ሲለወጥ የዓይን ምሥክር መሆን መቻል እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በረሃ ወይም ደረቅ መሬት የሆነው ምድር በመቶኛ

አፍሪካ 66%

እስያ 46%

አውስትራሊያ 75%

አውሮፓ 32%

ሰሜን አሜሪካ 34%

ደቡብ አሜሪካ 31%

ዓለም 41%

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በመስኖ መጠቀም መሬት ወደ በረሃነት እንዲለወጥ ያደርጋልን?

መስኖ መሬትን ውኃ ማጠጣት ሆኖ ሳለ ወደ በረሃማነት ሊለውጥ ይችላልን? አዎን የተሳሳተ የመስኖ አጠቃቀም እንደዚያ ያደርጋል። ይህ የሚሆነው በመስኖ የሚለማው መሬት ውኃውን በሚገባ የማያሰርገው ከሆነ ነው። በመጀመሪያ አፈሩ ውኃ ያቁራል፤ ከዚያም ወደ ጨዋማነት ይለወጣል፤ በመጨረሻም ከሥር የጨው ቅራፎ ይፈጥራል። ፓኖስ እንዳስገነዘበው “አዳዲስ የመስኖ እርሻዎች የመጀመራቸውን ያህል፣ የተሳሳቱ የመስኖ አጠቃቀሞች መሬቱን በፍጥነት ወደ በረሃማነት በመለወጥ ላይ ናቸው።”

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ካርታ]

በረሃ

የሚያሰጋቸው ቦታዎች

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1995 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእርሻ መሬት የነበረው ቦታ ቀስ በቀስ ወደ በረሃነት ሲለወጥ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ