አሁን በሕይወት በመኖሬ ደስ ይለኛል!
“እንደምትሞቺ ታውቂያለሽ፣ አይደል?” ሲል ዶክተሩ ጠየቀኝ። ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ሞቼ ለመገላገል ፈልጌ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን መሞት አልፈለግኩም። ሁኔታውን ልግለጽላችሁ።
ያደግኩት ኒው ዮርክ፣ ከሎንግ አይላንድ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ነው። አባቴ እውቅ መኪና ተወዳዳሪ ነበር። ፉክክር የሚያስደስተውና ከማንኛውም ነገር ፍጽምና የሚጠብቅ ሰው ነበር። በተጨማሪም ግልፍተኛና በቀላሉ የማይደሰት ሰው ነበር። በሌላው በኩል ግን እናቴ በጣም ሰላማዊና ረጋ ያለች በመሆኗ አባዬ ሲወዳደር ማየት እንኳን አትችልም ነበር።
እኔና ወንድሜ አንገታችንን ደፍተን መኖር የተማርነው ገና በሕፃንነታችን ነበር። እማዬም እንዲህ ዓይነቱን ኑሮ ከለመደችው ብዙ ጊዜ ሆኗታል። ጉዳት ማድረሱ ግን አልቀረም። ሁላችንም አባዬን ፈርተን በመንቀጥቀጥ እንኖር ነበር። በዚህም የተነሳ ምንም ነገር በትክክል መሥራት የምችል ሆኖ አይሰማኝም ነበር። ገና በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜዬ አንድ የቤተሰባችን “ወዳጅ” አስገድዶ ካስነወረኝ በኋላ ለራሴ የነበረኝ አክብሮት ፈጽሞ ጠፋ። ስሜቴን መቋቋም ስላልቻልኩ ራሴን ለመግደል ሙከራ አደረግኩ። መሞት ጥሩ መገላገያ እንደሚሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማኝ በዚህ ጊዜ ነበር።
ምንም ዋጋ እንደሌለኝና ማንም ሰው እንደማይወደኝ ስለተሰማኝ ለራሳቸው አክብሮት በሌላቸው ብዙ ወጣት ሴቶች ላይ እንደሚታየው የተዛባ የአመጋገብ ፍላጎት አደረብኝ። ፈንጠዝያን ማሳደድ፣ በተለያዩ ሱሶች መጠመድን፣ ዝሙትና ውርጃን የኑሮዬ ክፍል አደረኩ። የአንድ ዘፈን ስንኝ እንደሚለው “ፍቅርን በማይገኝበት ቦታ መፈለግ” ጀመርኩ። በሞተር ብስክሌትና በመኪና እሽቅድምድም መወዳደር፣ በባሕር ውስጥ ጠለቃ ውድድር መካፈልና በየጊዜው ቁማር ለመጫወት ወደ ላስ ቬጋስ መጓዝ ዋነኛ ተግባሬ ሆነ። በተጨማሪም በመናፍስትነት ሥራዎች መካፈል የሚያስከትለውን ጉዳት ሳልገነዘብ ጠንቋዮችን አማክርና የዕድል ሰንጠረዦችን አነብ ነበር።—ዘዳግም 18:10-12
ይህም አልበቃ ብሎኝ የጀብደኝነት ስሜት እንዲሰማኝ በመፈለግ አደገኛ ዕፆች እንደ መሸጥና በየሱቁ እንደመስረቅ ባሉ ሕገወጥ ድርጊቶች እካፈል ነበር። ፍቅር ለማግኘትና በሌሎች ለመወደድ ያደረግኩት ጥረት ደግሞ በርካታ እጮኛዎችና የወንድ ጓደኞች አፈራልኝ። እነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ አንድ ላይ ተጣምረው ሕይወቴን በጣም አደገኛ ወደሆነ ሁኔታ ውስጥ ከተቱት።
አንድ ቀን ማታ በመኪና መወዳደሪያ ሜዳ አልኮልና አደገኛ ዕፅ ከወሰድኩ በኋላ የወንድ ጓደኛዬ ቤቴ እንዲያደርሰኝ መፍቀዴ ጥበብ የጎደለው ነበር። ፊተኛው ወንበር ላይ እንደተቀመጥኩ ራሴን ሳትኩ። እርሱም ብዙ ሳይቆይ ራሱን ስቶ ኖሮ መኪናው ተጋጨና በድንጋጤ ነቃሁ። በተለያየ የሰውነቴ ክፍል ላይ ጉዳት ደርሶብኝ ስለነበር ሆስፒታል ተኛሁ። ከጊዜ በኋላ በቀኝ ጉልበቴ ላይ ከደረሰው ጉዳት በስተቀር ሙሉ በሙሉ ድኜ ወጣሁ።
የተሻለ ነገር ለማግኘት የነበረኝ ፍላጎት
ለራሴ ሕይወት የነበረኝ አክብሮት በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም ስለ ሕፃናትና እንስሳት ደህንነትና መብት እንዲሁም አካባቢን ስለመጠበቅ በጣም አስብ ነበር። የተሻለ ዓለም መጥቶ ለማየት ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረኝ ይህን ዓለም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የበኩሌን እርዳታ ለማበርከት በብዙ ድርጅቶች ውስጥ በንቃት መሳተፍ ጀመርኩ። አንዲት የሥራ ባልደረባዬ የነበረች የይሖዋ ምሥክር ትናገር ወደነበረው ነገር እንድሳብ ያደረገኝ የተሻለ ዓለም ለማየት የነበረኝ ይህ ፍላጎት ነው። ሥራዋ ላይ መጥፎ ነገር ሲያጋጥማት በስጨት በማለት “አይ ይህ ሥርዓት” ትል ነበር። ምን ማለቷ እንደሆነ ስጠይቃት አንድ ቀን፣ በቅርቡ፣ ሕይወት ከሚያስጨንቁ ነገሮች ሁሉ ነጻ እንደሚሆን ገለጸችልኝ። በጣም የማከብራት ሴት ስለሆነች በጉጉት አዳመጥኳት።
ከዚያ በኋላ ለመገናኘት ባንችልም የተናገረቻቸውን ነገሮች አልረሳሁም። አምላክን ለማስደሰት ከፈለግኩ አንድ ቀን በአኗኗሬ ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብኝ ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ ለዚህ ለውጥ ዝግጁ አልነበርኩም። ቢሆንም ለጋብቻ ለሚጠይቁኝ ሁሉ አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክር መሆኔ ስለማይቀር ይህን ካልወደዱ አሁኑኑ መለያየት እንደሚኖርብን እነግራቸው ነበር።
በመጨረሻ ያገኘሁት ወንድ ጓደኛዬ ስለተማርኩት ነገር የበለጠ ለማወቅ ፈለገና እኔ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩኝ እርሱም እንደሚሆን ነገረኝ። ስለዚህም የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመርን። ይሁን እንጂ እነርሱ ራሳቸው ቤታችን ድረስ ስለመጡ ቀድመው አገኙን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ይሁን እንጂ የወንድ ጓደኛዬ ከጊዜ በኋላ ጥናቱን አቆመና ወደ ቀድሞ ሚስቱ ለመመለስ መረጠ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ብዙ ጊዜ ይቋረጥ ነበር። ይሖዋ ስለ ደም ቅድስና ያለውን አመለካከት ለመገንዘብ ረዥም ጊዜ ወስዶብኛል። አስተሳሰቤን ወዲያው ካስተካከልኩ በኋላ ከአውሮፕላን ላይ መዝለልና ሲጋራ ማጨስ መተው እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ሕይወት ውድ መሆኑን እየተገነዘብኩ ስሄድ የተረጋጋ ኑሮ ለመምራትና ሕይወትን አደጋ ላይ ከሚጥሉ እንቅስቃሴዎች ለመራቅ ተዘጋጀሁ። ጥቅምት 18 ቀን 1985 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ወዲያው ሕይወቴን ትልቅ አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ አጋጠመኝ።
እንደገና ሞትን መመኘት
ከጥቂት ወራት በኋላ መጋቢት 22 ቀን 1986 ምሽት ላይ ቤቴ አጠገብ ቆሜ ከላውንድሪ ያመጣሁትን ልብስ ከመኪናዬ ሳወጣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚበር መኪና ገጨኝና 30 ሜትር የሚያክል ርቀት ላይ ጎትቶ ጣለኝ! መኪናው ግን ሳያቆም በዚያው አመለጠ። ጭንቅላቴ ቢመታም ራሴን አልሳትኩም ነበር።
በጨለማ መሐል መንገድ ላይ በግንባሬ ተደፍቼ እንዳለሁ ያሳስበኝ የነበረው ሌላ መኪና ቢገጨኝስ የሚለው ፍርሃት ነበር። ይሰማኝ የነበረው ሕመም ልቋቋመው ከምችለው በላይ ነበር። ስለዚህም እንድሞት ይሖዋን ለመንኩት። (ኢዮብ 14:13) አንዲት ነርስ የሆነች ሴት መጣች። እግሮቼ ተከታትፈው ስለነበረ እንድታስተካክላቸው ጠየቅኳት። አስተካከለችልኝና ከአንዱ እግሬ ይፈስ የነበረውን ደም ለማቆም ልብሷን ቀድዳ አሰረችልኝ። ጫማዎቼ በደም ተሞልተው ከአንድ ሕንጻ ባሻገር ወድቀው ተገኙ!
መንገድ አላፊዎች የተገጨሁት በእግሬ እንደቆምኩ መሆኑን ስላላወቁ መኪናዬ የት እንደሆነ ደጋግመው ይጠይቁኝ ነበር። ምን ያህል ርቀት እንደተጎተትኩ ስላልታወቀኝ አሁንም መኪናዬ አጠገብ ያለሁ መስሎኝ ነበር። የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ሲደርሱ ወዲያው የምሞት መሰላቸው። ስለዚህ በመኪና ሰው መግደል ከባድ ወንጀል ስለሆነ መርማሪ ፖሊሶች ጠሩ። የገጨኝ የመኪና አሽከርካሪ ብዙ ሳይቆይ ተያዘ። በአካባቢው ወንጀል እንደተፈጸመበት ያክል አካባቢውን ወረሩት። መኪናዬም በኤግዚብትነት ተያዘች። በአንድ ጎን በኩል ያሉት ሁለቱም በሮች ተገነጣጥለዋል።
የደረሰብኝን ችግር መጋፈጥ
ከዚያም የኦክሲጅን ጭንብል ተደርጎልኝ በአካባቢዬ ወደሚገኘው የድንገተኛ አደጋ ማዕከል ስደርስ “ደም አልወስድም፣ ደም አልወስድም፣ እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ!” እያልኩ እወተውት ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ የማስታውሰው በጀርባዬ በኩል ያለው ልብስ በትልቅ መቀስ ሲቀደድና የድንገተኛ አደጋ ሐኪሞች በጥድፊያ ስሜት እየተጯጯሁ ሲነጋገሩ ነው።
ነቅቼ ራሴን ሳውቅ አሁንም በሕይወት ያለሁ መሆኔ አስደነቀኝ። በተደጋጋሚ ራሴን እስት ነበር። በነቃሁ ቁጥር ቤተሰቦቼ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑኝ የነበሩትን ባልና ሚስት እንዲጠሩልኝ እጠይቅ ነበር። ቤተሰቦቼ የይሖዋ ምሥክር መሆኔ አስከፍቷቸው ስለነበር ሊነግሯቸው አልፈለጉም። ይሁን እንጂ ሳላቋርጥ ጨቀጨቅኳቸው። ዓይኔን በከፈትኩ ቁጥር የምናገረው ይህንኑ ብቻ ነበር። በመጨረሻ ሳላቋርጥ መጨቅጨቄ ፍሬ አስገኘልኝና አንድ ቀን ስነቃ አጠገቤ ቆመው አገኘኋቸው። እፎይ! አልኩ። የይሖዋ ሕዝቦች የት እንዳለሁ አወቁ ማለት ነው።
ይሁን እንጂ የደሜ መጠን በጣም መቀነስ በመጀመሩ ደስታዬ ለብዙ ጊዜ አልቆየም። ከፍተኛ ትኩሳትም ያዘኝ። ተመርዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ አጥንቶች ከወጡልኝ በኋላ በጉልበቶቼ ውስጥ አራት ብረቶች ገቡልኝ። ብዙ ሳይቆይ ትኩሳቱ አገረሸብኝ፣ እግሮቼም ጥቀርሻ መሰሉ። ጋንግሬን ስለጀመረኝ ሕይወቴን ለማትረፍ እግሬን መቁረጥ ግዴታ ሆነ።
ደም እንድወስድ የተደረገብኝ ግፊት
የደሜ መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ በመሄዱ ደም ካልወሰድኩ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል ነገር እንደሆነ ታሰበ። ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ቤተሰቦቼና የቆዩ ወዳጆቼ ተሰብስበው ደም እንድወስድ ይገፋፉኝ ጀመር። ከዚያም በሩ አጠገብ የሹክሹክታ ድምፅ ሰማሁ። ዶክተሮች አንድ ነገር ለማድረግ እንዳሰቡ ገባኝ፤ ሆኖም ምን ነገር እንዳሰቡ በትክክል አልገባኝም። ደግነቱ አንዲት ልትጠይቀኝ የመጣች የይሖዋ ምሥክር ሰምታቸው ኖሮ አስገድደው ደም ሊሰጡኝ እንዳሰቡ አወቀች። ወዲያው በአካባቢው ላሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ነገረቻቸውና እነርሱም ሊረዱኝ መጡ።
የአእምሮዬን ሁኔታ የሚገመግም የሥነ አእምሮ ሐኪም ተቀጥሮ መጣ። ዋና ዓላማቸው ለራሷ ለመወሰን የአእምሮ ብቃት የላትም ብለው ያለ ውዴታዬ እርምጃ ለመውሰድ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህ እቅዳቸው አልተሳካላቸውም። ከዚህ በኋላ ራሱ ደም ወስዶ የነበረ አንድ ቄስ ደም መውሰድ ምንም ስህተት እንደሌለው እንዲያሳምነኝ አመጡ። በመጨረሻ ቤተሰቦቼ በግድ ደም እንድወስድ ለማድረግ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት አመለከቱ።
ከሌሊቱ በስምንት ሰዓት አንድ የዶክተሮች ቡድን፣ አንድ የፍርድ ቤት ጸሐፊ፣ አንድ የችሎት ሥርዓት አስከባሪ፣ ሆስፒታሉን የሚወክሉ ጠበቆችና አንድ ዳኛ ወደ ክፍሌ እየተጣደፉ ገቡ። ችሎቱ ተሰየመ። በቅድሚያ የተሰጠኝ ማስጠንቀቂያም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የሕግ አማካሪ አልነበረኝም። ከዚህም በላይ በወሰድኩት የስቃይ ማሥታገሻ መድኃኒት ደንዝዤ ነበር። የችሎቱ ውሳኔ ምን ሆነ? ዳኛው የይሖዋ ምሥክሮች ስላላቸው የአቋም ጽናት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተደነቁ መሆናቸውን ገልጸው የፍርድ ቤት ትእዛዝ ሊሰጥ እንደማይችል ወሰኑ።
በካምዴን፣ ኒው ጀርሲ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተቀብሎ ሊያክመኝ ተስማማ። የኒው ዮርኩ ሆስፒታል አስተዳደር በጣም ተቆጥቶ ስለነበረ የሥቃይ ማስታገሻ መድኃኒትን ጨምሮ ምንም ዓይነት የሕክምና እርዳታ ለመስጠት እምቢተኛ ሆነ። በተጨማሪም ወደ ኒው ጀርሲ የሚወስደኝ ሄሊኮፕተር እንዳያርፍ ከለከለ። ቢሆንም በአምቡላንስ ለመጓዝ ቻልኩ። ወዲያው እንደደረስኩ በዚህ ታሪክ መግቢያ ላይ የጠቀስኳቸውን “እንደምትሞቺ ታውቂያለሽ፣ አይደል?” የሚሉትን ቃላት ሰማሁ።
የተሳካ ቀዶ ሕክምና
በጣም ደክሜ ስለነበር ቀዶ ሕክምና እንዲደረግልኝ መስማማቴን በሚገልጸው ቅጽ ላይ የኤክስ ምልክት ለማድረግ እንኳን የነርሷ እርዳታ አስፈልጎኝ ነበር። ቀኝ እግሬ ከጉልበቴ በላይ መቆረጥ ነበረበት። ከዚህ በኋላ የነበረኝ የሄሞግሎቢን መጠን ከሁለት በታች በመውረዱ ዶክተሮች በአንጎሌ ላይ ከባድ ጉዳት ሳይደርስ እንደማይቀር ተጠራጠሩ። ይህ ጥርጣሬ ሊያድርባቸው የቻለው በሕክምና ካርዴ ላይ የሰፈረውን ስሜን አይተው “ቨርጅንያ፣ ቨርጅንያ” እያሉ ቢጣሩ ምንም ምላሽ ባለመስጠቴ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ጂንጀር፣ ጂንጀር” የሚል ለስለስ ያለ ድምፅ ስሰማ ዓይኖቼን ከፈትኩና ከዚህ በፊት አይቼ የማላውቀው ሰው አየሁ።
ቢል ቱርፒን በኒው ጀርሲ ከሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የመጣ ሰው ነበር። ዕድሜዬን በሙሉ ስጠራበት የቆየሁትን ጂንጀር የተባለውን የቅጽል ስሜን ያወቀው ኒው ዮርክ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ነበር። የመተንፈሻ መሣሪያ ተደርጎልኝ ስለነበረና ፈጽሞ መናገር ስለማልችል ዓይኖቼን በማርገብገብ ብቻ ለመመለስ የምችላቸው ጥያቄዎች አቀረበልኝ። “እየተመላለስኩ እንድጠይቅሽና ስለ ሁኔታሽ ኒው ዮርክ ለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች እንድነግርልሽ ትፈልጊያለሽ?” ብሎ ጠየቀኝ። የተሰማኝ ደስታ በዓይን ብቻ ሊገለጽ የሚችል አልነበረም። ቤተሰቦቼ አንድም የይሖዋ ምሥክር እንዳይጠይቀኝ ትእዛዝ ሰጥተው ስለነበረ ወንድም ቱርፒን የገባው ተደብቆ ነበር።
ለስድስት ወራት ያህል ሆስፒታል ከቆየሁ በኋላ ምግብ እንደመጉረስና ጥርሴን እንደመቦረሽ ከመሰሉት መሠረታዊ እንቅስቃሴዎች የበለጠ ነገር ማድረግ አልችልም ነበር። ከጊዜ በኋላ ሰው ሠራሽ እግር ተደረገልኝና ምርኩዝ ይዤ ትንሽ መንቀሳቀስ ቻልኩ። በመስከረም 1986 ከሆስፒታል ወጣሁና ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ያህል የምትረዳኝ አስታማሚ አብራኝ ከረመች።
ከወንድማማች ማኅበር ያገኘሁት እርዳታ
ወደ ቤት ከመመለሴ በፊትም ቢሆን የክርስቲያን ወንድማማቾች ማኅበር አባል መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ችዬ ነበር። (ማርቆስ 10:29, 30) ወንድሞችና እህቶች በፍቅር ተነሳስተው ሥጋዊ ፍላጎቶቼ ብቻ ሳይሆኑ መንፈሳዊ ፍላጎቶቼም ጭምር መሟላታቸውን ይከታተሉ ነበር። በሰጡኝ ፍቅራዊ እርዳታ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ ውሎ አድሮም ረዳት አቅኚነት በሚባለው የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል ችዬ ነበር።
አደጋ ባደረሰብኝ አሽከርካሪ ላይ የተመሠረተው ክስ በተለመደው አሠራር የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለማስያዝ ብቻ ቢያንስ አምስት ዓመት የሚፈጅ ቢሆንም በወራት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ አገኘ። ይህም የራሴን ጠበቃ ሳይቀር አስገርሞታል። ፍርድ ቤት በወሰነልኝ የጉዳት ካሣ ይበልጥ አመቺ ወደሆነ መኖሪያ ለመዛወር ቻልኩ። በተጨማሪም ጋሪ ማንሻ ያለውና በእጅ ብቻ የሚነዳ መኪና ገዛሁ። በዚህ መንገድ በ1988 በዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ተሰማርቼ በየዓመቱ ቢያንስ 1,000 ሰዓት በስብከት ሥራ ማሳለፍ ጀመርኩ። ባለፉት ዓመታት በኖርዝ ዳኮታ፣ አላባማና ኬንታኪ ክፍለ አገሮች በሚገኙ የአገልግሎት ክልሎች በመሥራት ብዙ ደስታ አግኝቻለሁ። በመኪናዬ ሆኜ 150,000 ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት የተጓዝኩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን የተጓዝኩት ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ነበር።
በባለ ሦስት ጎማዋ ሞተር ብስክሌቴ በምጓዝባቸው ጊዜያት ብዙ አስቂኝ ሁኔታዎች ገጥመውኛል። ከተጓዥ የበላይ ተመልካች ሚስቶች ጋር እያገለገልኩ እንዳለሁ ሁለት ጊዜ ተገልብጫለሁ። አንድ ጊዜ በአላባማ ይህች ብስክሌት አንዲት ትንሽ ጅረት ልታሻግረኝ የምትችል መስሎኝ ገባሁባትና መሬት ላይ ወድቄ በጭቃ ተለወስኩ። ቢሆንም ሁሉንም እንደ ዋዛ በመመልከቴና ስለ ራሴ ብዙ የማልጨነቅ በመሆኔ አዎንታዊ አመለካከት ይዤ እንድቀጥል ረድቶኛል።
ያለኝ ጠንካራ ተስፋ አበርትቶኛል
የጤንነት ችግሮች ፍጹም ከአቅም በላይ የሚሆኑባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሌላው እግሬ መቆረጥ የሚያስፈልገው መስሎ በመታየቱ ምክንያት ሁለት ጊዜ አቅኚነቴን ለማቋረጥ ተገድጃለሁ። አሁንም አንዱን እግሬን አጣ ይሆናል የሚለው ስጋት አልተወገደልኝም። ባለፉት አምስት ዓመታት ከጋሪዬ ወርጄ መንቀሳቀስ አቅቶኛል። በ1994 ክንዴ ተሰበረ። በዚህ ምክንያት ገላዬን የሚያጥበኝ፣ ልብስ የሚያለብሰኝ፣ ምግብ የሚያዘጋጅልኝ፣ ቤት የሚያጸዳልኝና ከቦታ ቦታ የሚያጓጉዘኝ ሰው አስፈልጎኛል። ቢሆንም ወንድሞች በሚያደርጉልኝ ድጋፍ እነዚህን ሁሉ እክሎች ተቋቁሜ በአቅኚነቴ ለመቀጠል አስችሎኛል።
ዕድሜዬን በሙሉ ከፍተኛ ደስታ ያስገኛሉ የሚባሉ ነገሮችን ሳሳድድ ኖሬያለሁ። አሁን ግን ከፍተኛ ደስታ የሚገኘው ገና ወደፊት እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ። በዚህ በአሁኑ ዘመን በሕይወት ለመኖር በመቻሌ የምደሰተው አምላክ ወደ እኛ እየገሰገሰ በሚገኘው አዲስ ዓለም ውስጥ ማንኛውንም የአካል ጉድለት እንደሚያስወግድ ጠንካራ እምነት ስላለኝ ነው። (ኢሳይያስ 35:4-6) በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ከዓሣ ነባሪዎችና ከዶልፊኖች ጋር ስዋኝ፣ አንበሳና የአንበሳ ግልገሎች አጅበውኝ ተራራ ስወጣ፣ በባሕር ዳርቻዎች በእግር ስንሸራሸር ይታየኛል። ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ እንድንደሰትባቸው አምላክ የፈጠረልንን እነዚህን ነገሮች በሙሉ በዓይነ ሕሊናዬ መመልከት በጣም ያስደስተኛል።—ጂንጀር ክላውስ እንደተናገረችው
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቁማር የሕይወቴ ክፍል በነበረበት ጊዜ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የሰጠው ተስፋ ድጋፍ ሆኖልኛል