የንብ እርባታ “ጣፋጭ” ታሪክ
በግሪክ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ቀላ ያለችው የማለዳ ጀንበር ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች። በማለዳው ቁርና ጭጋግ መሐል አንድ ከኋላው ክፍት የሆነ መኪና በተራራው ግርጌ በሚገኝ መንገድ ላይ በቀስታ ተጉዞ ጥጉን ይዞ ቆመ። ቦት ጫማ፣ ቱታ፣ የእጅ ጓንትና መሸፈኛ ያለው ሠፊ ባርኔጣ ያደረጉ ማንነታቸው የማይለይ ሁለት ሰዎች ከመኪናው ወረዱ። ወደ ሃያ የሚጠጉ የእንጨት ሣጥኖችን በጥንቃቄ እያነሱ መኪናው ላይ ጫኑ። እነዚህ ያገኙትን ንብረት ሠርቀው የሚሸሹ ሰዎች ይሆኑ? የለም፣ በእንክብካቤ የሚጠብቋቸውን የንብ ሠራዊቶች ብዙ የአበባ ወለላ ያላቸው ተክሎች ወደ ሚገኙበት አካባቢ የሚያዛውሩ ንብ አርቢ ባልና ሚስት ናቸው።
ንብ አርቢዎች ልዩ ከሆኑ በራሪ ነፍሳት ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳላቸው በኩራት የሚናገሩ ልዩ ሰዎች ናቸው። በአንደኛው ወገን ምናልባት ከማናቸውም ነፍሳት የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ማርና ሰም የሚያመርቱ፣ እንዲሁም የተለያዩ አዝርዕትን የሚያዳቅሉ ንቦች አሉ። በሌላው ወገን ደግሞ ንቦችን መተዳደሪያቸው ያደረጉና ከእነርሱ አንዱ እንዳለው “የሚያንቀሳቅሳቸው ነገር ምን እንደሆነ በመረዳት” እነዚህን ትናንሽ ፍጥረታት በፍቅር የያዙ ሰዎች አሉ።
“የየቀኑ ተአምራት” ተንከባካቢ
ንብ አርቢ መሆን ማለት ንቦች የሞሉባቸው ቀፎዎች ማዘጋጀት፣ የአበባ ወለላ እንደልብ በሚገኝበት አካባቢ ቀፎዎቹን ማስቀመጥና ከጥቂት ወራት በኋላ ተመልሶ ማር መቁረጥ ብቻ እንደሆነ ሊመስል ይችላል። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ንብ አርቢ መሆን ምን ተግባሮችን እንደሚጠይቅ ለመረዳት በንብ እርባታ የሚተዳደሩትን ጆንን እና ማርያን አነጋግረናል። እነርሱም ስለሚወዱት ሥራቸው በደስታ ነግረውናል።
ጆን ወደ ተከፈተ ቀፎ ጎንበስ ብሎ እየተመለከተ “ንብ አርቢ መሆን በየዕለቱ በሚፈጸም ተአምራዊ ሥራ ተካፋይ መሆን ነው” አለ። “እስካሁን ድረስ የንቦችን የተደራጀ ማህበራዊ ሕይወት፣ የተራቀቀ ሐሳብ ለሐሳብ የመግባባት ችሎታና አስደናቂ የሆነ የሥራ ልማድ አጣርቶ የተረዳ ሰው የለም።”
ጆን የንብ እርባታን አጀማመር ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲነግረን በቀድሞ ዘመን ንብ አርቢዎች ማር የሚቆርጡት ንቦቹ የሚኖሩበትን የተቦረቦሩ የዛፍ ግንዶችንና ሌሎች ክፍት ሥፍራዎችን በማፍረስና ንቦቹን በማባረር እንደነበረ ገለጸልን። በ1851 ግን ሎሬንዞ ሎሬይን ላንግስተሮት የተባለ አሜሪካዊ ንብ አርቢ ንቦች በእያንዳንዱ የሰም እንጀራ መካከል 6 ሚሊ ሜትር የሚያክል ክፍተት እንደሚተው ተገነዘበ። በዚህ መንገድ ሰም በሚጋገርበት ክፈፍ መካከል ተመሳሳይ ክፍተት በመተው በተሠሩ የእንጨት ሣጥኖች መጠቀም እንደሚቻል ታወቀ። ንቦቹ ከቀፎው ውስጥ ሳይባረሩ እያንዳንዱን የንብ እንጀራ ለይቶ በማውጣት ማርና ሰም ማምረት ተቻለ።
ጆን ገለጻውን በመቀጠል “ለተሳካ የንብ እርባታ ለንቦች ከፍተኛ ፍቅር ማዳበር ይገባሃል። ለንቦችህ እንደ አባት መሆን አለብህ። እነርሱም ይህንን የሚገነዘቡና አባትነትህን የሚቀበሉ ይመስለኛል። በተጨማሪም ሐኪማቸው፣ ተንከባካቢያቸው፣ አስቸጋሪ በሆነው የክረምት ወቅት መጋቢያቸውም ነህ” ብሏል።
ማሪያ በማከል እንዲህ ትላለች:- “አንድ ጥሩ ንብ አርቢ ከ8 ሺህ እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ ንቦች ያሉበትን የንብ ቀፎ አንዴ አየት አድርጎ ብቻ ብዙ ነገሮች ማወቅ ይችላል። በቂ ተሞክሮ ያለህ ከሆንክ ቀፎህን ስትከፍት ንቦቹ የሚያሰሙት ድምፅ ቀፎህ ጥሩ እድገት ያለው፣ ምርታማና ‘ደስተኛ’ መሆን አለመሆኑን፣ ንቦችህ ተርበው እንደሆነ፣ ንግሥቲቱ ሞታ ንቦችህ ‘አለ እናት’ ቀርተው እንደሆኑ፣ አንድ የማያስደስት ነገር አስቆጥቷቸው እንደሆነና ሌሎች ብዙ፣ ብዙ ነገሮች ማወቅ ትችላለህ።”
ለተሳካ የንብ እርባታ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች
“አንድ ንብ አርቢ ቀፎዎቹ የሚቀመጡበትን ቦታ በጥንቃቄ መምረጡ ወሳኝ ነው” ይላል ጆን። “ንቦቹ ምግባቸውን እንደልብ ለማግኘት እንዲችሉ አበባ የሚበዛባቸውን መስኮች ለማግኘት እንጥራለን።
“አንድ ንብ አርቢ ንቦቹ ሥራ እንዳይፈቱ አበቦች በብዛት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ይከታተላል። በጸደይና በበጋ ወራት የሚያብቡ የፈረንጅ ጥድና የተለያዩ የጥድ ዛፎች ጥራት ያለውና ቀላ ያለ መልክ ያለው ማር ያስገኛሉ። ንብ አርቢዎች የማር ንጉሥ የሚሉት ከፍተኛ ጥራት ያለው ማር የሚገኘው ከጦስኝ አበባ ነው። በተጨማሪም ንቦች ምግባቸውን ከነጭና ብጫ የማገጥ አበቦች እንዲሁም ከአልፋልፋ አበቦች ይቀስማሉ።”
በተፈጥሮ እውቀት መጠቀም ከፍተኛ ጥቅም አለው። ማርያ እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ቀፎዎቹን የምናስቀምጠው በተራራማ አካባቢ ከሆነ ከተራራው ግርጌ ማስቀመጣችን በጣም ጠቃሚ ነው። ንቦቹ ሽቅብ ከበረሩ በኋላ አበባ ከሞላባቸው ዛፎች የቀሰሙትን የአበባ ወለላ ተሸክመው ሲመለሱ ቁልቁል መውረድ ቀላል ይሆንላቸዋል። ቀፎዎቹ የተቀመጡት ከተራራው አናት ላይ ከዛፎቹ ከፍ ብሎ ከሆነ ንቦቹን ስለሚያደክማቸው ምርታማነታቸውን ይቀንስባቸዋል።”
ጆን አንዲት ወጣት ንግሥት ተመቻችታ የተቀመጠችበትን የማር እንጀራ በጥንቃቄ እንደያዘ “ማንኛውም ንብ አርቢ ንግሥቲቱ በቀፎው ውስጥ ያሉት ንቦች ደህንነትና ምርታማነት ረገድ የሚኖራትን ከፍተኛ ድርሻ ይረዳል” አለ። “ቀፎው አነስተኛ እጭና ማር የሚያመርት ከሆነ ንግሥቲቱ መገደልና በሌላ ንግሥት መተካት ይኖርባታል። ወጣት ንግሥት ያላቸው ቀፎዎች ከፍተኛ ማር ያመርታሉ። በተጨማሪም አዲስ ቀፎ ለመጀመር በምንፈልግበት ጊዜ ጤናማና ብዙ ንቦች ያሉትን ድርብ ቀፎ እንወስድና የሣጥኑን የላይኛውንና የታችኛውን ክፍል እንለያየዋለን። ንግሥቲቱ በአንደኛው ደርብ ውስጥ ስለምትኖር በሌላኛው ደርብ ውስጥ ሌላ የተጠቃች ወጣት ንግሥት እናስገባለን። አበቦች መፈንዳት ሲጀምሩ አዲሲቱ ንግሥት እንቁላል መጣል ስለምትጀምር ቀፎው በወጣት ሠራተኛ ንቦች መሞላት ይጀምራል።”
አንድ ንብ ምን ያህል ዕድሜ ይኖራል? የአንድ ሠራተኛ ንብ ዕድሜ የሚወሰነው በሚሠራው ሥራ መጠን እንደሆነ ተነግሮናል። አንድ ንብ በቀን 15 ሰዓት ለሚያክል ጊዜ አበቦችን በሚቀስምበትና በሰዓት 21 ኪሎ ሜትር በሚያክል ፍጥነት በሚበርበት የበጋ ወራት ዕድሜው ከስድስት ሳምንት አያልፍም። በክረምቱ ወቅት ንቦች በቀን የሚሠሩት ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት ብቻ በመሆኑና ይህም ብዙ የሚያደክማቸው ስላልሆነ ለበርካታ ወራት ሊኖሩ ይችላሉ።
የተለያዩ ምርቶች
ስለ ንብ እርባታ በምንናገርበት ጊዜ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው የመጀመሪያ ነገር ማር እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። ይህን ወፍራምና ጣፋጭ ፈሳሽ ከአበቦች ወለላ የሚያዘጋጁት ሠራተኛ ንቦች ናቸው። አንድ ቀፎ በአማካይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 29 ኪሎ ማር ያመርታል። ሌላው የንቦች እንቅስቃሴ ተረፈ ምርት ደግሞ ሰም ነው። አንድ ማር እንጀራ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ለሚያክል ጊዜ አገልግሎት ይሰጣል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን በተለያዩ ሚክሮቦችና ጥገኛ ተውሳኮች ምክንያት ቀለሙ ስለሚጠቁር መቀየር ይኖርበታል። የሚቀየረው ማር እንጀራ ሰም ይሆናል። ከአሥር ኩንታል ማር በሚመረትበት ጊዜ ውስጥ የሚመረተው ሰም መጠን ከ9 እስከ 18 ኪሎ ግራም ይደርሳል።
ለንግሥቲቱ፣ ለሠራተኛ ንቦችና ለድንጉላ ንቦች እድገት አስፈላጊ የሆኑት ፕሮቲኖች፣ ቪታሚኖችና ስብ ዋነኛ ምንጭ የሆነው ፖለን ለብዙ አካላዊ ሕመሞች የሚጠቅም ጥሩ የተፈጥሮ መድኃኒት እንደሆነ በአንዳንድ ሰዎች ይነገራል። አንድ ቀፎ በአንድ ዓመት እስከ 5 ኪሎ ግራም የሚደርስ ፖለን ይሰጣል። ፕሮፖሊስ ንቦች ቀፎአቸውን ለመለሰንና ከቀፎአቸው ውስጥ ተሸክመው ለማውጣት ያልቻሉትን እንግዳ ነገር ጠቅልለው ለማስቀመጥ የሚጠቀሙበት ንጥረ ነገር ነው።
ከምንመገባቸው ምግቦች አንድ አራተኛ የሚሆነው ምርት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ንቦች አዝርዕትን ለማራባት ባላቸው ችሎታ ላይ የተመካ ነው። ፖም፣ አልመንድ፣ ከርቡሽ፣ ፕሩኝ፣ ሸክኒት፣ ኪያርና ሌሎች አትክልቶች ሊያፈሩ የሚችሉት በንቦች አማካኝነት ነው። እንደ ካሮት፣ ሽንኩርትና ሱፍ የመሰሉት እንኳን ሳይቀር የሚራቡት በንብ ነው። ለከብቶች መኖነት የሚያገለግለው አልፋልፋም የሚራባው በንቦች ስለሆነ በሥጋና በወተት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ።
“የተፈጥሮ ጥበብ”
“አብዛኞቹ ንብ አርቢዎች በአምላክ የሚያምኑ ይመስለኛል” ትላለች ማርያ። ይህም ንቦች በጣም ረቂቅ ማህበራዊ ሥርዓታቸውን፣ አስደናቂና ውስብስብ የሆነውን የኅብረት አኗኗራቸውን፣ በጣም የተራቀቀውን አቅጣጫ የማግኘትና እርስበርስ መረጃ የመለዋወጥ ችሎታቸውን ከየት አገኙት የሚለውን ጥያቄ መልስ ልናገኝለት አለመቻላችንን ያስገነዝበናል። የንቦችን አኗኗር የሚያጠኑና ለንቦች እንክብካቤ የሚያደርጉ በርካታ ሰዎች ንቦች “የተፈጥሮ እውቀት” ስላላቸው ነው ይላሉ። ይህን የተፈጥሮ እውቀት በለጋስነት የሰጣቸው ታላቁ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ነው።—ከምሳሌ 30:24 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአበባ እስከ ገበታ
1 ንቢቱ አበባ ትቃኝና የአበባ ወለላ ትሰበስባለች
ንቦች ከአበባ ወደ አበባ እየተዘዋወሩ የቀሰሙትን ወለላ የጉሮሯቸው ቅጥያ በሆነ ከረጢት ውስጥ ያጠራቅማሉ። አንዲት ንብ ይህን ከረጢት ለመሙላት የተለያዩ አበቦችን ከ1,000 እስከ 1,500 ጊዜ ያህል ትጎበኛለች
2 ወደ ቀፎዋ ትመለሳለቸ፣ የአበባው ወለላ በቀፎው ውስጥ በሚገኘው ማር እንጀራ ውስጥ ይቀመጣል
ንቢቱ ወደ ቀፎዋ ትመለስና በማር ከረጢትዋ ውስጥ ያጠራቀመችውን የአበባ ወለላ በወጣት ሠራተኛ ንብ አፍ ውስጥ ትተፋዋለች። ከዚያም ሠራተኛዋ ንብ የአበባ ወለላውን በእንቆራ ውስጥ ከጨመረች በኋላ ወደ ማርነት ለመለወጥ የሚያስፈልገውን ተግባር ትፈጽማለች
3 ንብ አርቢው ማሩን ይቆርጣል
ንብ አርቢው በእያንዳንዱ ክፈፍ ላይ የሚገኙትን እንቆራዎች የሸፈነውን ሰም በጋለ ስለት ፍቆ ያነሳል። ከዚያም እንጀራዎቹን የማሩን ወለላ ለይቶ በሚያወጣ ተሽከርካሪ መሣሪያ ውስጥ ይጨምራል
4 ማሩ በትልልቅ ወይም በትንንሽ ዕቃዎች ውስጥ ይጨመራል
በማር ማስቀመጫዎች ላይ የሚለጠፈው ጽሑፍ ንቦቹ ከምን ዓይነት ዕጸዋት የቀሰሙት እንደሆነ ይናገራል። ማስቀመጫው ብርሃን የሚያስተላልፍ ከሆነ የማሩን ቀለም በመመልከት ጥራቱን ማወቅ ትችላለህ
5 ማር ለጤንነት ጠቃሚ ነው!
ማር በቀላሉ ከሰውነት ጋር የሚዋሃድና በፍጥነት ወደ ኃይልነት የሚለወጥ ነው። ረፖርቶች እንደሚያመለክቱት በቃጠሎ የሚፈጠሩ ቁስሎችንና የተለያየ ዓይነት ቁስል ለማከም ሊያገለግል ይችላል