አንዲት ሩሲያዊት ልጃገረድ ያገኘችው ተስፋ
በሩሲያ ከሞስኮ ሰሜናዊ ምሥራቅ 1,200 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘውና ከ100,000 የሚበልጡ ነዋሪዎች ባሏት የኡክታ ከተማ የምትኖር አንዲት የ15 ዓመት ልጃገረድ በምድር ላይ የተሻሉ ሁኔታዎች እንዲሰፍኑ ልባዊ ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጻለች። ይህን የገለጸችው በሩሲያ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በጻፈችው በሚከተለው ደብዳቤ ነው:-
“በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላሳለፈው ሕይወት እንደሚገልጽ ጓደኛዬ ነግራኛለች። ለመጽሐፎቻችሁ፣ ለመጽሔቶቻችሁና ለብሮሹሮቻችሁ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ይህ ፍላጎት ሊያድርብኝ የቻለው እንዴት እንደሆነ ልግለጽላችሁ። የራዲዮና የስልክ ሂሣብ ለመክፈል ወደ ቴሌግራፍ መሥሪያ ቤት ሄጄ በነበረበት ጊዜ ነው። በወለሉ ላይ አንድ ትራክት ወድቆ አገኘሁ። አነሳሁትና በላዩ ላይ የነበረውን አቧራ ካራገፍኩ በኋላ ማንበብ ጀመርኩ። የትራክቱ ርዕስ ሕይወት በችግር የተሞላ የሆነው ለምንድን ነው? የሚል ነበር።
“ሰዎች ስለሚያጋጥሟቸው መከራዎችና ችግሮች አነበብኩ። በትራክቱ ሽፋን ላይ ደግሞ በገነት ውስጥ የሚኖረው አዲስ ሕይወት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ሥዕል አለ። ይህ ሕይወት አንድ ቀን ዕውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ሰዎች ሁሉ ደስተኞች፣ የረኩና ጤነኞች ሆነው የሚኖሩበትን፣ እንዲሁም የሞቱ ዘመዶቼ የሚነሱበትን ጊዜ ለማየት እፈልጋለሁ። . . . ገነት በምትሆነው ምድር ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚኖርብኝ ለማወቅ እፈልጋለሁ። አንዳንድ መጻሕፍት ወይም መረጃዎች እንድትልኩልኝ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። የመጽሐፎቹንም ሆነ የመላኪያውን ዋጋ እከፍላለሁ።”
እርስዎም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ሊረዳዎት የሚችል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ማግኘት ይችላሉ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር አንድ ቅጂ ለማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ ወይም አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርዎትና መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስተምርዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።