የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 1/8 ገጽ 10-11
  • ደጃፋችን ላይ የሚገኘው ዶልፊን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ደጃፋችን ላይ የሚገኘው ዶልፊን
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እምብዛም የማይታዩት ለምንድን ነው?
  • በእርግጥ ዶልፊኖች ናቸው?
  • ስለ ኢርዋዲዎች የምናውቃቸው ጥቂት ነገሮች
  • ወደፊት የመኖር ተስፋ ይኖረው ይሆን?
  • በኒው ዚላንድ ዶልፊኖችን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
    ንቁ!—2002
  • ዶልፊኖች አካባቢያቸውን ለማወቅ የሚጠቀሙበት ዘዴ
    ንድፍ አውጪ አለው?
  • ሻርክ ቤይ—አስደናቂ የባሕር ወሽመጥ
    ንቁ!—2007
  • በጥልቅ ባሕር ውስጥ የሚኖሩ ግዙፍ ፍጥረታት
    ንቁ!—2009
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 1/8 ገጽ 10-11

ደጃፋችን ላይ የሚገኘው ዶልፊን

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ጥልቀት የሌላቸውን የሐሩር አካባቢ ሞቃታማ ባሕሮች ይወድዳል። ከዚህ ሌላ ባሕሩ ጨዋማ ሆነ አልሆነ፣ ድፍርስ ሆነ የጠራ ግድ የለውም። የሚኖረው ከሕንድ የቤንጋል ባሕር ሰርጥ ጀምሮ በሰሜናዊ አውስትራሊያ እስከሚገኙት የማለይ ደሴቶች በሚገኘው ቀጣና ነው።

ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች፣ በተለይ እነዚህ እንስሳት ከማንኛውም የዓለም ክፍል በብዛት በሚገኙበት በአውስትራሊያ ሰሜናዊ ጫፍ የሚኖሩ ሰዎች ስለ ኢርዋዲ ዶልፊን ሰምተውም ሆነ ዓይተው አያውቁም። አያስገርምም? ሊያስገርምም ላያስገርምም ይችላል።

በ19ኛው መቶ ዘመን ጆን አንደርሰን የተባለው ዙዎሎጂስት እነዚህ ወደ ሰማያዊነት የሚያደላ ግራጫ መልክ ያላቸው ባለ ክብ ጭንቅላት ዶልፊኖች ብዙ ሆነው በምያንማር (በዚያ ጊዜ በርማ ትባል በነበረችው) በሚገኘው የኢርዋዲ ወንዝ ሲዋኙ ተመለከተ። በዚህ ምክንያት የኢርዋዲ ዶልፊን የሚል ስም አወጣላቸው።

እምብዛም የማይታዩት ለምንድን ነው?

ኢርዋዲዎች ለኑሮ የሚመቻቸው ሙቀትና እርጥበት በሚበዛባቸው የባሕር ዳርቻዎች የሚገኙ ባሕሮችና ወንዞች ናቸው። ብዙውን ጊዜ የሚኖሩት ጭቃማ በሆኑ፣ ትንኞችና አንዳንድ ጊዜም ዓዞዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ነው። እነዚህ ቦታዎች ሰዎች አዘውትረው የሚሄዱባቸው አይደሉም።

በተጨማሪም እንደነዚህ ባሉት አካባቢዎች የሚኖረው ውኃ አብዛኛውን ጊዜ ድፍርስና ጭቃማ ስለሚሆን ዶልፊኖቹን ማየት የሚቻለው አየር ለመተንፈስ ራሳቸውን ብቅ በሚያደርጉበት አጭር ጊዜ ብቻ ነው። በዚህም ጊዜ ቢሆን ብቅ የሚለው በጣም ትንሽ የሆነ የሰውነቱ ክፍል ብቻ ስለሆነ ብዙ ማየት አይቻልም። ጀርባውን በትንሹ ማየት ሲቻል በጀርባው ላይ ያለው ክንፍ ከሌሎች ዶልፊኖች ጋር ሲወዳደር አነስ ያለ ነው።

ይሁን እንጂ የኢርዋዲ ዶልፊኖችን እንደ ልብ ማየት የሚቻልባቸው አንዳንድ አካባቢዎች አሉ። በምያንማር በሚገኘው የኢርዋዲ ወንዝና በእስያ የዶልፊኖች ቀጣና በሚገኙ ሌሎች ባሕሮች የሚሠሩ ዓሣ አጥማጆችና ጀልባ ነጂዎች ወጣ ብለው ሲያድኑና ሲቦርቁ እንዲሁም ልክ እንደ ፏፏቴ ያለ ውኃ ከአፋቸው እየረጩ ሲጫወቱ ተመልክተዋል።

በአውስትራሊያ ኢርዋዲዎች የሚሰማሩት በምዕራባዊው የባሕር ጠረፍ፣ በአኅጉሪቱ አናትና በምሥራቃዊው የባሕር ጠረፍ አካባቢዎች ነው። አንዳንድ ጊዜ እስከ 15 የሚደርሱ አንድ ላይ ሆነው የሚታዩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የሚታዩት ግን ከስድስት ያነሰ ቁጥር ያላቸው ኢርዋዲዎች አንድ ላይ ሆነው ነው። የአውስትራሊያዎቹ ኢርዋዲዎች እንደ እስያዎቹ ወገኖቻቸው ውኃ ከአፋቸው ሽቅብ እየረጩ ሲጫወቱ ታይተው አያውቁም።

በእርግጥ ዶልፊኖች ናቸው?

ኢርዋዲዎች የሚኖሩት በመሬት አካባቢ ሲሆን በጠራ ባሕር ከሚኖሩት ዓሣ ነባሪዎችና ዶልፊኖች ጋር ሲወዳደሩ ፈጣን ዋናተኞች አይደሉም። ቢሆንም ሳይንቲስቶች እነዚህን እንስሳት ለማጥናት ብዙ ተቸግረዋል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የሚኖሩበት አካባቢ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ በጃካርታ፣ ኢንዶኔዥያ በሚገኘው የጃይ አኮል የባሕር አራዊት መኖሪያ በሕይወት የሚንቀሳቀሱ ኢርዋዲዎች ተጠንተዋል።

ስለ ኢርዋዲዎች ብዙ የታወቀ ነገር ባለመኖሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባዮሎጂስቶች ኢርዋዲዎች የዓሣ ነባሪ ወገን ይሁኑ የዶልፊን ወገን በእርግጠኝነት ለመናገር ተቸግረው ነበር። ከዶልፊኖች ጋር ብዙ ተመሳሳይነት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ቢሆንም በቀለማቸው ይለዩ እንጂ (ወደ ግራጫነት የሚያደላ ሰማያዊ ቀለም አላቸው) በቅርጻቸው ከአርክቲክ ቤሉጋ ዓሣ ነባሪዎች ወይም ከነጭ ዓሣ ነባሪዎች ጋር በጣም ይመሳሰላሉ። ወደፈለገው አቅጣጫ ለመጠማዘዝ የሚችለው አንገታቸው እንኳን ከቤሉጋ ዓሣ ነባሪዎች አንገት ጋር በጣም ይመሳሰላል። ታዲያ ምንድን ናቸው? እውነተኛ ዶልፊን ናቸው ወይስ የሐሩር አካባቢ ቤሉጋ ዓሣ ነባሪዎች?

ይህን ለማወቅ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ የሁለቱን አናቶሚያዊና ጀነቲካዊ ባሕርይ አስተያይቶ መረጃዎቹ ወደየትኛው ወገን እንደሚያዘነብሉ መመልከት ነው። በዚህ ዓይነት የተገኘው ማስረጃ ይበልጥ የሚያጋድለው ወደ ዶልፊኖች ነው።

ስለ ኢርዋዲዎች የምናውቃቸው ጥቂት ነገሮች

የኢርዋዲ ግልገሎች በሚወለዱበት ጊዜ ከአንድ ሜትር ትንሽ የሚያንስ ቁመትና 12 ኪሎ ግራም ክብደት ይኖራቸዋል። ወንዶቹ አድገው አካለ መጠን ሲደርሱ የ2.75 ሜትር ቁመት ሲኖራቸው ሴቶቹ ከዚህ ትንሽ አነስ ያሉ ይሆናሉ። እስከ 28 ዓመት ሊኖሩ ይችላሉ።

ከሞቱ ኢርዋዲዎች ሆድ ውስጥ ከተወሰዱ ናሙናዎች ለማወቅ እንደተቻለው ስክዊዶችን፣ ሽሪምፖችን፣ ፕራውኖችንና በተለይ በባሕር ወለሎች የሚኖሩ ዓሦችን ይመገባሉ። የእስያ ዶልፊኖች ውኃ ከአፋቸው የሚተፉት በድፍርስ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ ዓሦችን ለማደን እንዲረዳቸው እንደሆነ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ይገምታሉ።

ኢርዋዲዎች እንደ ሌሎቹ ዶልፊኖች ሁሉ ልዩ የሆነ ድምፅ ያሰማሉ። የትሮፒካል ክዊንስላንድ ሙዚየም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፒተር አርኖልድ “በጃይ አኮል ኦሽናርየም በተደረገ ጥናት እንደታወቀው ኢርዋዲ ዶልፊኖች ይህ የሚያሰሙት ድምፅ አስተጋብቶ ሲመለስ የሚታደነው እንስሳ የሚገኝበትን ቦታ ይጠቁማቸዋል። ሌሎች ዶልፊኖችም እንዲሁ ያደርጋሉ” በማለት ለንቁ! ገልጸዋል።

ወደፊት የመኖር ተስፋ ይኖረው ይሆን?

በዓለም ዙሪያ ምን ያህል ኢርዋዲዎች እንዳሉ ሳይንቲስቶች አስረግጠው አያውቁም። ቢሆንም ሞተው ያልቁ ይሆናል የሚለው ስጋት እየጨመረ መጥቷል። በአንዳንድ የደቡባዊ ምሥራቅ የእስያ ክፍሎች ቁጥራቸው በጣም እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ፈጽሞ ሊታዩ ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል።

እንዲህ ሊሆን የቻለው ደኖች በመጨፍጨፋቸውና በዚህም ምክንያት የአካባቢ ብክለትና የወንዞች ደለል እየጨመረ መሄዱ ነው። በአውስትራሊያ የኢርዋዲዎቹ መኖሪያ አካባቢዎች በአብዛኛው ገና ሰው ያልደረሰባቸው ናቸው። በምሥራቃዊው የባሕር ጠረፍ ግን የከተሞችና የቱሪዝም መስፋፋት ብዙ ጉዳት አድርሷል። አንዳንድ ኢርዋዲዎች ዋናተኞችን ለመጠበቅ በተጠመዱ የሻርክና የዓሣ ማጥመጃ መረቦች ውስጥ ይወድቃሉ። በተጨማሪም ኢርዋዲዎች የሚመገቧቸው ዓሣዎች በዓሣ አጥማጆች ተጠምደው ስላለቁ በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው የምግብ እጥረት ለቁጥራቸው መመናመን ምክንያት ሆኗል።

ከሁሉ በላይ የሚያሰጋው አደጋ ግን ወደ ወንዞችና ውቅያኖሶች እየተጠራረገ የሚገባው ቆሻሻ በጣም እየጨመረ መምጣቱ ሊሆን ይችላል። በጣም አሳሳቢ ከሆኑት ቆሻሻዎች መካከል እንደ ፖሊክሎሪኔትድ ባይፌኒል (ፒ ሲ ቢ) ያሉት ሰው ሠራሽ ኦርጋኒክ ውህዶች ይገኛሉ። ፒሲቢዎች ለኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች፣ ለቀለሞች፣ ለቅባቶች፣ ለእንጨትና ለብረታ ብረት ቅብና ለሌሎች ዕቃዎች መሥሪያ ሆነው ያገለግላሉ።

በአዎንታዊ ጎኑ ደግሞ የአውስትራሊያ የተፈጥሮ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ዚ አክሽን ፕላን ፎር አውስትራሊያን ሴታሲያንስ በተባለው ሰነዱ “በክዊንስላንድ የሚገኘው የኢርዋዲዎች መሰማሪያ በአብዛኛው በታላቁ ባርየር ሪፍ ማራይን ፓርክ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በክዊንስላንድ ባሕሮች ውስጥ ተገቢውን እንክብካቤ የመስጠት ጥሩ አጋጣሚ አለ” ብሏል።

ይኸው መሥሪያ ቤት የተሻለ እንክብካቤ ለማድረግ እንዲቻል ኢርዋዲ እንደ ሃምባክ ዓሣ ነባሪ፣ እንደ ደቡባዊው ራይት ዓሣ ነባሪና እንደ ባለ ጠርሙሱ አፍንጫ ዓሣ ነባሪ ለሕዝብ በሚሠራጨው ትምህርት ረገድ ዋነኛ ትኩረት የሚደረግበት ዝርያ እንዲሆን ሐሳብ አቅርቧል። ይህ እርምጃ ለኢርዋዲ ዶልፊኖችም ሆነ ለእኛ የሚበጅ ይሆናል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶ:- Courtesy Dr. Tony Preen

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ