መለወጥ ማየት ማመን ነው?
በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ጠንቋዩ ሞቷል። በቤቱ ዙሪያ ለተሰበሰበው ብዙ ሕዝብ ግን ወደ ሌላ አካል ተለውጧል። ጠንቋዩ በሞተበት ወቅት አንድ ግዙፍ ዘንዶ እየተሳበ ከቤቱ ውስጥ ሲወጣ ተመልክተዋል! ለአንዳንዶች ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነገር ነው። ለሌሎች ግን ጠንቋዩ ወደ ዘንዶነት መለወጡን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው!
በብዙ የአፍሪካ አገሮች ሰው ወደ እንስሳ ሊለወጥ ይችላል ወይም ይለወጣል የሚለው አስተሳሰብ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ነው። ብዙውን ጊዜ አስማተኞች የነብርና የዘንዶ አካል የመልበስ ኃይል አላቸው ተብሎ ይታመናል። በተጨማሪም አንድ አስማተኛ ሌሎች ሰዎችን ወደ እንስሳነት ሊለውጥ ይችላል የሚለው ፍርሃትም በሰፊው የተስፋፋ ነው። በምዕራብ አፍሪካ ጠንቋዮች በሌሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲፈልጉ የሰዎችን መንፈስ በወፎችና በሌሎች እንስሳት አማካኝነት ይልካሉ ተብሎ ይታመናል። በመካከለኛው አፍሪካ አንዳንዶች በሞት የተለያቸው ዘመዳቸው ወደ እንስሳነት ተለውጦ ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ እንደ ዝሆን ወይም እባብ ያሉ እንስሳትን አይገድሉም።
እንደነዚህ ያሉ እምነቶች አንዳንድ አንባብያንን ሊያስገርሙ የሚችሉ ቢሆኑም ብዙ አፍሪካውያን እንዲህ ዓይነቱ ተአምራዊ ለውጥ በዓይን ምሥክሮች የተረጋገጠ እንደሆነ ይናገራሉ። አስተዋይ በሆኑ ሰዎች የሚነገሩት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ታሪኮች ሁሉ በአጋጣሚ የተከሰቱ ሊሆኑ አይችሉም ብለው ይከራከራሉ።
ይህን የመሰሉ እምነቶች በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል በጃፓን ሰዎች ተለውጠው ቀበሮዎች፣ ውሾችና ሽኮኮዎች ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል። በተመሳሳይም በአውሮፓ ሌሊት ሌሊት ወደ አደገኛ ተኩላነት ስለሚለወጡ ሰዎች የሚነገሩ ተረቶች አሉ። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ደግሞ አንዴ የሰው አንዴ ደግሞ የእንስሳ አካል ስለሚለብሱ ነብሮች፣ ከርከሮዎች፣ አዞዎችና አልፎ ተርፎም ድመቶች የሚነገሩ አፈ ታሪኮች አሉ።
ቅዱሳን ጽሑፎች ይደግፉታል?
አንዳንዶች ይህን በተአምራዊ ሁኔታ የሚደረገውን ለውጥ ቅዱሳን ጽሑፎችም ይደግፉታል ብለው ይናገራሉ። ብዙውን ጊዜ ለዚህ በማስረጃነት የሚጠቀሱት አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ናቸው። የመጀመሪያው ኢየሱስ ከሁለት ሰዎች አጋንንት እንዲወጡ ካደረገ በኋላ አጋንንቱ በእርያ መንጋ ውስጥ መግባታቸውን የሚገልጸው ነው። (ማቴዎስ 8:28-33) ሁለተኛው ዘኁልቁ 22:26-35 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሲሆን የበለዓም አህያ አፍ አውጥታ መናገሯን ይገልጻል። ሦስተኛውና ምናልባትም ደግሞ ከእነዚህ ታሪኮች ሁሉ ይበልጥ በስፋት የሚታወቀው በኤደን የአትክልት ሥፍራ አንድ እባብ ሔዋንን እንዳነጋገራት የሚገልጸው ነው።—ዘፍጥረት 3:1-5
እነዚህን ታሪኮች ጠለቅ ብለን ስንመረምር ግን መለወጥን የሚያመለክቱ ምሳሌዎች አለመሆናቸውን እንረዳለን። አጋንንት የገቡባቸውን እርያዎች ሁኔታ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ እርያዎች ወደ እንስሳነት የተለወጡ ሰዎች ናቸው ብሎ አይናገርም። ታሪኩ እንደሚገልጸው አጋንንቱ ወደ እነርሱ ከመግባታቸው በፊት ‘ብዙ የእርያ መንጋ ተሰማርቶ ነበር’ ይላል። (ማቴዎስ 8:30) እርያዎቹ ውስጥ የገቡት የሰይጣን አጋንንት እንጂ የሰዎች መናፍስት አይደሉም።
ስለ በለዓም አህያና ስለ ኤደኑ እባብስ ምን ለማለት ይቻላል? የበለዓምን አህያ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ አህያዋ ትናገር ዘንድ “እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዘኁልቁ 22:28) ወደ አህያነት የተለወጠች ሰው አልነበረችም። የኤደኑን እባብ በተመለከተም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ የሚባለውን ክፉ መንፈስ “የቀደመው እባብ” በማለት ይጠራዋል። (ራእይ 12:9) በእባቡ ተጠቅሞ የተናገረውና ‘በተንኮሉ ሔዋንን ያሳታት’ ሰይጣን ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:3) አዎን፣ የበለዓም አህያም ሆነች እባቡ ከመናገራቸው በፊት፣ በተናገሩበት ጊዜም ሆነ ከተናገሩ በኋላ እንስሶች ነበሩ።
ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሰው አራተኛ ታሪክ ደግሞ ዕብሪተኛውን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርን የሚመለከት ነው። አምላክ ናቡከደነፆርን እንዳዋረደው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። “ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ . . . እስኪያውቅ ድረስ . . . ልቡም እንደ አውሬ ሆነ፣ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፣ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።” (ዳንኤል 5:21) አእምሮው ተነክቶ በነበረባቸው ሰባት ዓመታት ናቡከደነፆር መልኩም ሆነ ባሕርይው እንደ አውሬ ሆኖ ነበር። ዳንኤል 4:33 እንደሚገልጸው ‘ጠጉሩም እንደ ንስር፣ ጥፍሩም እንደ ወፎች ረዝሞ’ ነበር። ሆኖም ንጉሡ ላባም ሆነ የእንስሳ ጥፍር አላበቀለም። በዚያን ጊዜም ቢሆን ሰው ነበር!
የተአምራዊ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በቀጥታ የሚቃረን ነው። አንደኛ ነገር፣ ሰው ወደ እንስሳነት ተለውጣ ልትኖር የምትችል የተለየች ነፍስ እንደሌለችው መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ከዚህ ይልቅ ሰው ራሱ “ሕይወት ያለበት ነፍስ” ነው! (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም) በተጨማሪም ይህ ዓይነቱ የመለወጥ ሂደት ይሖዋ አምላክ ካቋቋመው ተፈጥሯዊ ሥርዓት ጋር ይጋጫል። እንስሳት የተፈጠሩት ‘እንደየወገናቸው’ እንዲባዙ ነው። (ዘፍጥረት 1:24, 25) አምላክ በፈጠረው በራሂያዊ ገደብ ምክንያት ዓይነታቸው ወይም ወገናቸው ፈጽሞ የተለያየ እንስሳት ሊዋለዱና ሊባዙ አይችሉም። ‘በአምላክ መልክ’ በተፈጠረው ሰውና በእንስሳት መካከል ደግሞ በጣም ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አለ። (ዘፍጥረት 1:26) አምላክ የሰው ልጆች ተለውጠው የማሰብ ችሎታ የሌላቸው እንስሳት መሆን የሚችሉበት ኃይል እንዲኖራቸው በማድረግ ከራሱ ሕጎች ጋር የሚጻረር ተግባር አይፈጽምም።
እርግጥ ነው፣ በተፈጥሮ የሚታይ ልውጠተ ቅርጽ አለ። አባጨጓሬዎች ወደ ቢራቢሮነት፣ እንቁሪዎች (tadpoles) ደግሞ ወደ እንቁራሪትነት ይለወጣሉ። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ ጥልቅ ምርምሮች እነዚህ የልውጠተ ቅርጽ ምሳሌዎች በተለያዩ “ወገኖች” መካከል የሚካሄዱ የለውጥ ሂደቶች ሳይሆኑ በአንድ “ወገን” ውስጥ የሚታዩ የእድገት ደረጃዎች እንደሆኑ አመልክተዋል። ወደተሟላ የእድገት ደረጃቸው ላይ በሚደርሱበት ጊዜ ‘እንደየወገናቸው’ ይባዛሉ።
ማየት ማመን ነው የሚለው አባባል ሁልጊዜ አይሠራም
ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ተአምራዊ ለውጥ በዓይናችን አይተናል ለሚሉት ሰዎች ሁኔታውን አሳማኝ በሆነ መንገድ ግልጽ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ “ለሚጠፉ . . . በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው” ከተባሉት ነገሮች አንዱ ነው።—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10
ደካማ የሆኑትን የሚያጠቁ ጉልበተኛ ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ አጋንንትም ሰዎች ኃይላቸውን ከልክ በላይ አጋንነው እንዲመለከቱላቸው ማድረግ ይፈልጋሉ። ሌቦችና አጭበርባሪዎች ከሚፈጽሙት የማጭበርበር ድርጊት ብዙም የማይለዩ አሳማኝ ‘ምልክቶች’ ይፈጽማሉ።
ይህ በብዙ የአፍሪካ የገበያ ቦታዎች በካርታ ጨዋታ የሚያጭበረብሩትን ሰዎች እንድናስታውስ ያደርገናል። ያላንዳች ሃፍረት አንዳንድ የቤት እመቤቶችን በካርታ ጨዋታ በማማለል ጥረው ግረው ያገኙትን ገንዘብ አራግፈው ባዶ እጃቸውን እንዲመለሱ ያደርጓቸዋል። ለሴትየዋ ሁለት ቀይና አንድ ጥቁር ካርታ ያሳዩአትና ጥቁሩን ካርታ መለየት ከቻለች የገንዘቧን እጥፍ እንደምታገኝ ይነግሯታል። ለመጫወት ታመነታ የነበረችው ይህች ሴት ሌላ ሰው ለይስሙላ ተጫውቶ ሲበላ ስታይ ወዲያው ለመጫወት ትነሳሳለች። ገንዘቡን የበላው ሰውም ከአጭበርባሪዎቹ አንዱ መሆኑን አታውቅም። ገንዘቧን ታስይዝና አጫዋቹ ካርታዎቹን ወዲያና ወዲህ ሲያዟዙር ጥቁሩን ካርታ በዓይኗ ትከተላለች። ያመለከተችው ካርታ ቀይ መሆኑን ስትረዳ ድንጋጤና ሀፍረት ይውጣታል። ለቤተሰቧ እህል የምትሸምትበትን ገንዘብ በሙሉ ትበላለች። የራሷ ስግብግብነትና አጭበርባሪው የተጠቀመበት የማታለያ ዘዴ ጠልፈው ይጥሏታል! ማየት ማመን ነው የሚለው አባባል ሁልጊዜ እንደማይሠራ የምትረዳው ሁሉ ነገር ካለፈ በኋላ ነው።
በተመሳሳይም ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን በማታለል የሰው ልጆች ወደ እንስሳነት መለወጥ ይችላሉ ብለው እንዲያምኑ ማድረግ ያስደስታቸዋል። ሰይጣን ቀንደኛ አታላይ ነው። እንዲያውም ሔዋንን “ሞትን አትሞቱም፤ . . . እንደ እግዚአብሔርም [ትሆናላችሁ]” በማለት የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው እሱ ነው። (ዘፍጥረት 3:4, 5) ነፍስ አትሞትም፣ እሳታማ ሲኦልና ሰው በተአምራዊ ሁኔታ ይለወጣል የሚሉትን የመሳሰሉ ሰዎች በፍርሃት ተውጠው እንዲኖሩ የሚያደርጉ ትምህርቶች የመነጩት ከዚህ ውሸት ነው። በመሆኑም በአፍሪካ ውስጥ ሰዎች ወደ እንስሳነት እንዳንለወጥ ይጠብቀናል ብለው የሚያምኑበትን “ክትባት” ለመከተብ ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ። እውነታው እንደሚያሳየው ግን እነዚህ ሰዎች ‘በአጋንንት ትምህርት’ የተጠላለፉ ከመሆናቸውም በላይ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 4:1፤ ያዕቆብ 4:7
እውነተኛ ለውጥ
ምናልባት አንተም በተአምራዊ ለውጥ የምታምንና አልፎ ተርፎም ይህ ሁኔታ ይደርስብኝ ይሆናል ብለህ የምትፈራ ልትሆን ትችላለህ። እንዲህ ዓይነት እምነት ያለህ ከሆንክ በሮሜ 12:2 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ልብ በል። እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው የመጀመሪያው ግሪክኛ ቃል ሜታሞርፎ የተባለው ነው። እንዲህ እናነባለን:- “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ [ሜታሞርፎስቴ]።” ይህ ሊሆን የሚችልን የተሟላ የባሕርይ ለውጥ የሚያመለክት ነው!
መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ጥብቅ ምክር የሚሰጥ በመሆኑ አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ማድረግ አለባቸው:- ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁ የፈጠረውን ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱ።’—ቆላስይስ 3:9, 10
መለወጥ የምትችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ነው። ይህ እውቀት ከፍ አድርገህ ትመለከታቸው የነበሩ አስተሳሰቦችንና ጽንሰ ሐሳቦችን እርግፍ አድርገህ እንድትተው ሊያደርግህ ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ እንዳለው ‘እውነትን ታውቃለህ፤ እውነትም ነፃ ያወጣሃል።’ (ዮሐንስ 8:32) አዎን፣ በተአምራዊ ሁኔታ ስለመለወጥ ከሚነገሩት ተረቶችና እነዚህ ተረቶች ከሚፈጥሩብህ ፍርሃት ነፃ መውጣት ትችላለህ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓይናችን “የሚያየው” ነገር ሁሉ እውነት ነው ማለት አይደለም
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ጠንቋይ:- Courtesy Africana Museum, Johannesburg