በመዝናኛ ረገድ መራጮች ሁኑ
መዝናኛ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? ለ30 ዓመታት ያክል የልጆች አስተማሪና ሐኪም ሆነው የሠሩት አልቪን ፖሴይንት የጾታ ብልግናና የዓመፅ ድርጊቶች የሚታዩባቸውን ፊልሞች መመልከት ወጣቶች እነዚህ ድርጊቶች ምንም ስህተት እንዳልሆኑ አድርገው እንዲያስቡ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል። ሌላም አደጋ እንዳለው ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ልጆች እንዲህ ዓይነት ፊልሞችን አይተው እቤት ሲመለሱ ከፍተኛ ፍርሃት እንደሚሰማቸው ወይም ደግሞ በጣም ጠበኞች እንደሚሆኑ ተረድቻለሁ። ሌሎቹ ደግሞ በፍርሃት ስሜት ሰው ላይ ልጥፍ ይላሉ፣ አውራ ጣታቸውን ይጠባሉ ወይም ደግሞ አልጋ ላይ ይሸናሉ።” እኚሁ ዶክተር እንደገለጹት አካላዊ ድብደባ፣ በጾታ ማስነወር ወይም ደግሞ በጦርነት ቀጠና ውስጥ መኖር የመሳሰሉ ሁኔታዎች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አንዳንድ ጠበብት በጥናት ደርሰውበታል። “ማንኛችንም ብንሆን ልጃችን እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዲደርሱበት አንፈቅድም” ካሉ በኋላ “ነገር ግን በፊልሞች ላይ ስናያቸው የሚሰቀጥጡንን ነገሮች ልጆቻችን እንዳያዩ ምንም የምንወስደው እርምጃ የለም” ብለዋል።
ክርስቲያኖች የሚመርጡት መዝናኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያስጥሳቸው እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረጋቸው ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 11:5 “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” ይላል። በተጨማሪም ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ በምድር ያሉትን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም . . . መጎምጀት ነው፤ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ።”—ቆላስይስ 3:5, 8
ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸውም ሆነ ለራሳቸው የሚመርጡት መዝናኛ “የሥጋ ሥራ” የሚያስፋፋ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። (ገላትያ 5:19–21) የመዝናኛውን ጥራትም ሆነ መጠን በሚመዝኑበት ጊዜ መራጮች መሆን አለባቸው።—ኤፌሶን 5:15–17