ሃይማኖት የወጣቶችን ትኩረት የሚስበው ምን ያህል ነው?
በፈረንሳይ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በቦታው ለተሰበሰቡት 750,000 ወጣቶች ይህ ታላቅ የደስታ ምሽት ነበር። ባንዲራዎችን ያውለበልባሉ፣ ይዘምራሉ እንዲሁም ያጨበጭባሉ። ርችቶች ከመተኮሳቸውም በላይ ለየት ያሉ መብራቶች አካባቢውን በሕብረ ቀለማት አድምቀውታል። ሙዚቀኞች ደግሞ ሕዝቡን ይቀሰቅሳሉ። ሁኔታው ከአንድ “ታላቅ የሙዚቃ ዝግጅት” ጋር ይመሳሰላል። በመጨረሻ ሲጠበቁ የነበሩት ሰው ወደ መድረኩ ብቅ ሲሉ አካባቢው በውዳሴ ጩኸት ተደበላለቀ።
ይህ ሁኔታ ዓለምን እየዞረ የሙዚቃ ትርዒት የሚያሳይ የአንድ የሮክ ሙዚቃ ባንድ ዝግጅቱን ማቅረብ መጀመሩን የሚያበስር ነበርን? አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ ዝግጅት የካቶሊክ የዓለም ወጣቶች ሰሞን በሚከበርበት ወቅት በፓሪስ የተካሄደ ብዙ ሕዝብ የተገኘበት ሃይማኖታዊ ስብሰባ ሲሆን ወደ መድረክ ብቅ ያሉትም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል ነበሩ!
ወጣቶች በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሃይማኖታዊ በዓላት መማረካቸው አንዳንዶችን ያስገርማቸው ይሆናል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃን ወጣቶች ለሃይማኖት ያላቸው ስሜት እያንሰራራ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ውጫዊ ገጽታዎች
ከላይ ሲታይ ሃይማኖት እያበበ ያለ ሊመስል ይችላል። 68 በመቶ የሚሆኑት ወጣት አውሮፓውያን ሃይማኖት እንዳላቸው የሚናገሩ ሲሆን በአየርላንድ ይህ አኃዝ ከ90 በመቶ በላይ ሆኖ ተገኝቷል። በአንድ ወቅት ሃይማኖት የጥንት ዘመን ቅርስ ተደርጎ ይታይ በነበረባት በቀድሞዋ የሶቭየት ሪፑብሊክ በአርሜንያ ቀደም ሲል ወና ሆነው የነበሩ አሁን ግን በሰዎች የተሞሉ አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ አንድ ቄስ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሃይማኖት ምን ያህል የወጣቱን ትውልድ ቀልብ እየሳበ እንዳለ ስመለከት በጣም እደነቃለሁ።”
በብዙ አገሮች ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ወጣቶች በኑፋቄዎችና በተዓምራዊ ፈውስ በሚያምኑ ቡድኖች ውስጥ ስለሚያደርጉት ተሳትፎ በሰፊው አትተዋል። መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ሃይማኖታዊ በዓላት በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጆች ናቸው። ይሁን እንጂ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብለን ስንመለከት ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ጉዳዩን ይበልጥ ጠለቅ ብሎ መመልከት
ጉዳዩን ጠለቅ ብለን ስንመለከት በ1967 ከፈረንሳይ ወጣቶች መካከል 81 በመቶ የሚሆኑት በአምላክ ያምኑ ነበር፤ በ1997 ግን ቁጥራቸው በግማሽ ቀንሷል። በመላው አውሮፓ ካሉት ወጣቶች መካከል ሕያው በሆነ አምላክ የሚያምኑት 28 በመቶ ብቻ ናቸው። በመሆኑም በአውሮፓ ካሉ ወጣቶች መካከል አዘውትረው የሚጸልዩት 12 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም። ይህ ሁኔታ ወጣቶች ለሃይማኖት ባላቸው አመለካከት ላይ የተንጸባረቀው እንዴት ነው?
በዴንማርክ 90 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ብሔራዊውን ሃይማኖት እንደሚከተሉ ይናገራሉ። አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው የሚሄዱት ግን 3 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። በፈረንሳይ እየታተመ የሚወጣው ላ ክርዋ የተባለው የካቶሊክ ጋዜጣ በ1997 ያካሄደው ጥናት 70 በመቶ የሚሆኑት የፈረንሳይ ወጣቶች ሃይማኖት በሕይወታቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የማያሳድር መሆኑን እንደተናገሩ አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ከሃይማኖታዊ ትምህርት ይልቅ በራስ ልምድ መመራት ይመርጣሉ። በአብዛኞቹ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ውስጥም ያለው ሁኔታ አንድ ዓይነት ነው።
ወጣቶች ከአብያተ ክርስቲያናት እየራቁ ያሉት ለምንድን ነው? ታላላቅ ሃይማኖቶች ለአብዛኞቹ ወጣቶች ውስጣዊ የመተማመን ስሜት አይፈጥሩላቸውም። ለምሳሌ ያህል በፈረንሳይ አብዛኞቹ ወጣቶች በዓለም ላይ ላለው መከፋፈል አንዱ ምክንያት ሃይማኖት እንደሆነ ያስባሉ። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ወጣቶች በስፔይን የምትኖረው ሁዲት የተባለች አንዲት የ15 ዓመት ካቶሊክ ወጣት የተሰማት ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። “ቤተ ክርስቲያኗ ሥነ ምግባርን በተመለከተ በምትሰጠው ትምህርት አልስማማም” ብላለች። በተመሳሳይም በታይዋን የሚኖረው ጆሴፍ የተባለ አንድ የ20 ዓመት ወጣት ሃይማኖት “ኋላ ቀር” ነው የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል። አብዛኞቹ ወጣቶች የራሳቸው ሃይማኖት የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች የማይቀበሉ ከሆነ ታዲያ በምንድን ነው የሚያምኑት?
የሚስማማቸውን ሃይማኖት መምረጥ
በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወጣቶች ሃይማኖታዊ እምነቶችን የሚከተሉት ልክ እንደ ምግብ እያማረጡ ነው። አንድ መጽሔት ሃይማኖትን “እንደ ምግብ ማማረጥ” ሲል ገልጾታል። አንድ የካቶሊክ መጽሔት ደግሞ “ሃይማኖትን እንደ ሸቀጥ ማማረጥ” ሲል ጠርቶታል። ጊዜ አልፎባቸው የነበሩ አስተሳሰቦች አሁን በሰፊው ተቀባይነት ያላቸው ነገሮች ሆነዋል። በመሆኑም በአውሮፓ 33 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በክታብ ያምናሉ፣ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጠንቋዮች ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይ ይችላሉ ብለው የሚያምኑ ሲሆኑ 27 በመቶ የሚሆኑት ኮከቦች በሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ብለው ያምናሉ። በአሁኑ ጊዜ እንደ ሪኢንካርኔሽን ያሉ አስተሳሰቦች የብዙዎቹ አውሮፓውያን ወጣቶች የእምነት ክፍል ሆነዋል።
የተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች ስላሉ ወጣቶች ከፍላጎታቸው ጋር የሚስማሙትን አስተሳሰቦች መርጠው ይይዛሉ። እውነት የሚገኘው በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ብቻ እንደሆነ የሚያምኑት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ወጣቶች ደስ ያላቸውን አስተሳሰብ የሚመርጡ በመሆናቸው በሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው መካከል ያለው ልዩነት እየደበዘዘ ሄዷል። በመሆኑም የማኅበራዊ ጉዳይ አጥኚዎች የተለመዱ እምነቶች “ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ” ወይም “ተጠራርገው እየጠፉ” እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል። ባህላዊዎቹ ሃይማኖቶች ለእንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ምላሽ እየሰጡ ነው?
ሃይማኖት ወጣቶችን ለመሳብ ያደረገው ጥረት
ሃይማኖቶች ወጣቶችን እንዴት ሊስቡ እንደሚችሉ ግራ ገብቷቸዋል። አንድ የፈረንሳይ ቄስ በፓሪስ በተካሄደው የካቶሊክ የዓለም ወጣቶች ሰሞን በዓል ላይ የተገኙትን እጅግ ብዙ ወጣቶች በተመለከተ የሚከተለውን ጥያቄ አቅርበዋል:- “እነዚህ ሁሉ ወጣቶች ከየት መጡ? በቤተ ክርስቲያኔ አንድም ወጣት አላገኘሁም። ፈጽሞ አይቻቸው አላውቅም።” የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን ለመሳብ ስትል አቀራረቧንና መልኳን እየለወጠች ነው።
“ቤተ ክርስቲያኗ ስልቷን ለውጣለች!” ሲል ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ገልጿል። ቤተ ክርስቲያኗ በፓሪስ የተካሄደውን 12ኛውን የዓለም ወጣቶች ሰሞን ክብረ በዓል አቀራረብ የማደራጀቱን ኃላፊነት የሰጠችው በይበልጥ የሮክ ሙዚቃ ዝግጅቶችን በማቀናበር ልምድ ላላቸው ድርጅቶች ነው። ከ100 ከሚበልጡ አገሮች የመጡትን ወጣቶች ለማዝናናት ከ300 በላይ ትርኢቶች የቀረቡ ሲሆን በአንድ የልብስ ሞድ አውጪም ለቀሳውስት የተዘጋጁ ለየት ያሉ ልብሶችም ለእይታ ቀርበው ነበር።
ብዙዎቹ ሃይማኖቶች በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ወጣቶች ስሜት ሊረዱ ባለመቻላቸውና ካለው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ማስማማት እንዳለባቸው ሆኖ ስለተሰማቸው ሁሉንም የሚያግበሰብሱ ሆነዋል። በፓሪስ የተካሄደውን የዓለም ወጣቶች ሰሞን በዓል ያደራጁት ሚሼል ዱቦ የተባሉ ቄስ የሚከተለውን አስተያየት በመስጠት ይህን መርህ አንጸባርቀዋል:- “እርግጥ የተጠመቁት ሁሉ ለክርስቶስ ታማኝ ቢሆኑ ደስ ይለኛል። ሆኖም ታማኝ ባይሆኑም እንኳ ቤተ ክርስቲያኗ ትቀበላቸዋለች።”
ወጣቶች መልስ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት
አንድ ጋዜጣ ወጣቶች በእርግጥ መልስ ለማግኘት የሚሹ መሆኑን ጎላ አድርጎ በመግለጽ ወጣቶቹ በፓሪስ በተካሄደው ሃይማኖታዊ በዓል ላይ የተገኙት “እምነት ቢያገኙ ብለው እንጂ እምነት ኖሯቸው እንዳልሆነ” አመልክቷል። ታዲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ላለው ጥያቄ ምላሽ ሰጥታለች?
ከትልልቅ ሃይማኖታዊ በዓላት መጋረጃ ጀርባ ስንመለከት ወይም ደግሞ አንድ የካቶሊክ ጋዜጣ “የሚያታልል ውጫዊ መልክ” ብሎ የገለጸውን ሁኔታ ጠለቅ ብለን ስንመረምር የምናገኘው ነገር ምንድን ነው? ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ከላይኛው ገጽታ በታች ስላለው “ትርጉም የለሽ ነገር” አስተያየት ሰጥቷል።
አንድ ምግብ ለዓይን የሚማርክ ብቻ ሳይሆን ገንቢም መሆን አለበት። ወጣቶች የሕይወት ትርጉምን በተመለከተ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በመንፈሳዊ የሚገነቡ መልሶች የሚያሻቸው ናቸው። የሚማርኩ ግን ትርጉም የለሽ የሆኑ መልሶች ወጣቶችን አያጠግቧቸውም።
ትርጉም የለሽ የሆኑት እነዚህ ሃይማኖታዊ ክንውኖች በዛሬው ጊዜ ባሉት ወጣቶች ላይ የሚያመጡት ዘላቂ ለውጥ ይኖራልን? ዳንዬል ኤርቭዩ-ሌዥዬ የተባሉ ፈረንሳዊት የማኅበራዊ ጉዳዮች አጥኚ “እነዚህ ማራኪ ዝግጅቶች ዘላቂ የሆኑ ማኅበራዊ ለውጦች የማምጣት ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ታዲያ ወጣቶች ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልሶች ማግኘት የሚችሉት ከየት ነው?
አጥጋቢ መልሶች
በ1997 ለ ፕዋን የተባለ አንድ የፈረንሳይ መጽሔት ወጣቶች የገጠሟቸውን ችግሮች በተመለከተ አንድ ርዕስ አውጥቶ ነበር። አብዛኞቹ ወጣቶች የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ ዘወትር ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ ወጣቶች ከወንጀልና ከዓመፅ ድርጊቶች የመላቀቅ ችግር አለባቸው። ይህን ችግር መወጣት ይቻል ይሆን? መጽሔቱ ያወጣው ርዕስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ዴቪድ 30 ዓመት ሲሞላው አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፆችና የዓመፅ ድርጊቶች በሰውነቱ ላይ እያስከተሉ ያሉት ጉዳት ያሳስበው ጀመር። የይሖዋ ምሥክሮች እቤቱ መጥተው አነጋገሩትና ከዚህ ሁሉ መንጻት የሚችልበትን መንገድ ጠቆሙት። ጥናት ጀመረና ተለወጠ። ያለበትን የቁማር ዕዳ ሁሉ ከመክፈሉም በላይ አጭበርብሮ ገንዘብ እንደወሰደባቸው ለማያውቁት ሰዎች እንኳ ሳይቀር ገንዘባቸውን መለሰላቸው። ማጨስ፣ መጠጣትም ሆነ መደባደብ አቁሟል።”
ይኸው ርዕስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ስላጠኑ ሌሎች ወጣቶች ሲናገር “ለጥያቄዎቻቸው ሁሉ መልስ አግኝተዋል” ብሏል። አንድ ወጣት ምሥክር ሁኔታውን እንዲህ ሲል በአጭሩ ገልጾታል:- “መጽሐፍ ቅዱስ ለሁለት ሺህ ዓመታት እውነትን ሲናገር ቆይቷል፤ ታዲያ ከሌላ አቅጣጫ መመሪያ ለማግኘት የምጥርበት ምን ምክንያት አለ?”
የአምላክ ቃል ለወጣቶች የሚሆን መልእክት ይዟል። ተግባራዊ ምክሩ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ችግሮች እንዲቋቋሙ የሚረዳቸው ከመሆኑም በላይ ወደፊት ሰላምና የወንድማማችነት መንፈስ የሚሰፍንበት ጊዜ ይመጣል ብለው እንዲያምኑ የሚያደርግ ጠንካራ ማስረጃ ያቀርባል። ዘወትር ተለዋዋጭ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው የሚያረጋጋና የሚያጽናና ተስፋ “ለሕይወታችን እንደማይነቃነቅ አስተማማኝ መልሕቅ ነው።” (ዕብራውያን 6:19 የ1980 ትርጉም) በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው ሕይወታቸው እውነተኛ ትርጉም ያለው ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ውስጣዊ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል በራሳቸው ተሞክሮ አይተውታል። ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን መልሶች በመቀበላቸው እውነተኛ እምነት ለማግኘት ያደረጉት ጥረት እንደተካሰ ተገንዝበዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃይማኖታዊ በዓል በፓሪስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ይስባል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፓሪስ የተከበረው የዓለም ወጣቶች ሰሞን በዓል በእርግጥ ሃይማኖት እንዳንሰራራ የሚያሳይ ነው?