በወርቅ ታሪክ ዙሪያ ያለው ምሥጢር
ወርቅ—እምብዛም ጥንካሬ የሌለውና ደመቅ ያለ ቢጫ ቀለም ያለው ብረት ነው። ይህ ብረት ልዩ ባሕርያት ያሉት በመሆኑ ከጥንት ጀምሮ ተፈላጊ ሆኖ ኖሯል። ቀለሙ፣ መብለጭለጩ፣ በተፈለገው ቅርጽ ሊስተካከል የሚችል መሆኑና ዝገትን መቋቋም መቻሉ ከሌሎች የብረት ዓይነቶች ልዩ ያደርገዋል። በፈላጊዎቹ ዘንድ የተሰጠው ከፍተኛ ግምት ከሌሎች ብረቶች ለየት ያለ ታሪክ እንዲኖረው አድርጎታል።
“ወርቅ! እርግጠኛ ነኝ፤ ወርቅ ነው! ወርቅ!” ሰዎች ወርቅ ሲያገኙ ልባቸው በደስታ ይፈነድቃል፤ ምቱ ይጨምራል፤ የሚይዙት የሚጨብጡት ይጠፋቸዋል። በየብስ ላይ፣ በወንዞችና ጅረቶች ውስጥ አልፎ ተርፎም ከምድር ገጽ በታች በሺህ የሚቆጠሩ ሜትሮች ቆፍረው ሲፈልጉት ኖረዋል።
ወርቅ ውድ ጌጥ እንደመሆኑ መጠን ነገሥታትና ንግሥቶች አጊጠውበታል። ዙፋናትና የቤተ መንግሥት ግድግዳዎች አሸብርቀውበታል። በዓሣ፣ በአእዋፍ፣ በእንስሳትና በሌሎችም ነገሮች ምስል የተቀረጹ የወርቅ ጣዖታት እንደ አማልክት ተቆጥረው ተመልከዋል። ሰዎች ወርቅ ለማግኘት ያደረጉት ተጋድሎ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ለሥልጣኔም ያበረከተው ድርሻ እንዲሁ የላቀ ነው።
ወርቅና ታሪክ
የጥንቷ ግብጽ ፈርዖኖች የግብጽ አማልክትና ፈርዖኖች ንብረት ተደርጎ የሚታየውን ወርቅ ፈልገው እንዲያመጡ ነጋዴዎቻቸውንና ሠራዊታቸውን ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች ልከዋል። በ1922 የተገኘው የቱታንካሜን መቃብር እጅግ ከፍተኛ ዋጋ በሚያወጡ የወርቅ ዕቃዎች የተሞላ ነበር። የአስከሬን ሣጥኑ ሳይቀር ከወርቅ የተሠራ ነበር።
እንደ አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች አባባል ከሆነ ታላቁ እስክንድር “በመጀመሪያ ትኩረቱን ወደ እስያ እንዲያዞር ያደረገው ነገር በሰፊው ይነገርለት የነበረው የፋርሳውያኑ የወርቅ ሀብት ነው።” ሠራዊቱ ከፋርስ የዘረፈውን ወርቅ ወደ ግሪክ ለማሸሽ በሺህ የሚቆጠሩ የጭነት እንስሳትን ይጠቀም እንደነበር ሪፖርት ተደርጓል። ከዚህ የተነሣ ግሪክ በወርቅ የበለጸገች ሀገር ሆናለች።
አንድ ታሪክ ጸሐፊ ሪፖርት እንዳደረጉት ከሆነ የሮም “ንጉሠ ነገሥታት ወርቅን በጉርሻ መልክ በመስጠት ባለ ሥልጣኖቻቸው ለእነርሱ ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ባለ ሥልጣናት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይጠቀሙበት ነበር። ከወርቅ በተሠሩ ጌጦቻቸው በሚንጸባረቀው ከፍተኛ ሃብታቸው ሕዝባቸውን ያስደምሙና ብዙውን ጊዜም ያስፈራሩ ነበር።” ሮማውያን ስፔይንን ድል አድርገው በያዙና የስፔይንን የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች ባገኙ ጊዜ ብዙ ወርቅ እንዳፈሱ አንድ ጽሑፍ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ ታሪኩ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ብዙ ደም መፋሰስ የታየበት ታሪክም አለው። ታሪኩ የወረራ፣ የጭካኔ፣ የባርነትና የሞት ታሪክ ነው።
በደም የተጨማለቀ ታሪክ
ሥልጣኔ እየተስፋፋ ሲሄድ ትላልቅና የበለጠ ኃይል ያላቸው መርከቦች አዳዲስ መሬቶችን ማሰስ፣ ነዋሪዎችን ማስፈርና ወርቅ መፈለጉን ተያያዙት። ግንባር ቀደም ባሕረተኛውን ክርስቶፈር ኮለምበስን (1451–1506) ጨምሮ ወርቅ ማግኘት የብዙ አሳሾች የቀን ሕልም ሆነ።
ኮለምበስ ወርቅ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ለአገሬው ሰዎች ሕይወት ቅንጣት ታክል አዘኔታ አልነበረውም። ወጪዎቹን ይሸፍኑለት ለነበሩት የስፔይን ንጉሥና ንግሥት በአንድ ደሴት ላይ ስላጋጠመው ነገር ሲዘክር በውሎ ማስታወሻው ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህን አካባቢ ለመግዛት የሚያስፈልገው እዚህ ሰፍሮ በአገሬው ላይ ሥልጣን ማወጅ ብቻ ነው፤ የታዘዙትን ሁሉ የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው። . . . ሕንዳውያኑ . . . እርቃናቸውን የሚሄዱና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ በመሆናቸው ትእዛዝ ተቀብለው በተግባር ለማዋል የተዘጋጁ ናቸው።” ኮለምበስ የአምላክን በረከት እንዳገኘ ይሰማው ነበር። የወርቅ ክምችቱ ስፔይን የምታደርጋቸውን ቅዱስ ጦርነቶች በገንዘብ ለመደገፍ የሚረዳ ነበር። በአንድ ወቅት የወርቅ ጭምብል በስጦታ ካገኘ በኋላ ‘አምላክ በምሕረቱ ወርቅ እንዳገኝ ይርዳኝ’ ብሏል።
የኮለምበስን ዱካ በመከተል የባሕር ጉዞ የጀመሩት የስፔይን ባለ ድሎች ከስፔይኑ ንጉሥ ፈርዲናንድ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል:- “ወርቅ አምጡልኝ! የሚቻል ከሆነ በሰላም። እንዴትም ቢሆን ብቻ ወርቁን አምጡልኝ።” ምሕረት የለሾቹ አሳሾች በሜክሲኮ እንዲሁም በማዕከላዊና ደቡባዊ አሜሪካ ያገኟቸውን በሺህ የሚቆጠሩ የአገሬውን ተወላጆች ደም አፍስሰዋል። ወደ ስፔይን የተጫነው ወርቅ ደም የተነከረ ነበር ለማለት ይቻላል።
ከዚያም የየትኛውንም ብሔር ባንዲራ የማያውለበልቡ የባሕር ወንበዴዎች ብቅ አሉ። በጋራ የባሕር ክልሎች ላይ እየጠበቁ ወርቅና ሌሎች ውድ ንብረቶች የጫኑትን የስፔይን የንግድ መርከቦች ዘርፈዋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ የንግድ መርከቦች ራሳቸውን ለመከላከል የነበራቸው የጦር መሣሪያም ሆነ የሰው ኃይል በሚገባ ከታጠቁት የባሕር ወንበዴዎች ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ነበር። በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን የባሕር ላይ ውንብድና በተለይ በዌስት ኢንዲስና በአሜሪካ ድንበር አካባቢ የባሕር ላይ መቅሰፍት ሆኖ ነበር።
የ19ኛው መቶ ዘመን የወርቅ ሽሚያ
በ1848 በካሊፎርኒያ ሳክራሜንቶ ሸለቆ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ተገኝቶ ነበር። ወሬው ወዲያው ስለተሰማ ድርሻቸውን ለማግኘት የፈለጉ ብዙ ሰዎች ወደዚያው ይነጉዱ ጀመር። በሚቀጥለው ዓመት ካሊፎርኒያ “ፎርቲ ናይነርስ” በሚባሉ ከዓለም ዙሪያ በመጡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሀብት ፈላጊዎች ተጥለቀለቀች። በ1848 ሃያ ስድስት ሺህ ገደማ የነበረው የካሊፎርኒያ ነዋሪዎች ቁጥር በ1860 ወደ 380,000 ደርሶ ነበር። በወርቅ እንጀራቸውን ለማውጣት ሲሉ ገበሬዎች መሬታቸውን ትተው ሄደዋል፣ መርከበኞች ሥራቸውን ትተዋል፣ ወታደሮችም ሠራዊቱን ጥለው ወጥተዋል። አንዳንዶቹም “ደም የተጠሙ ወስላቶች” የሚል ስያሜ አትርፈዋል። ከተለያየ ሕብረተሰብ የተሰበሰቡ ሰዎች በሚገኙበት በዚህ ቦታ ወንጀልና ዓመፅ ተስፋፍቶ ነበር። ወርቁ ያማለላቸው፣ ግን ድካሙን የጠሉ ሰዎች ወርቅ ተጭነው የሚመጡ ጋሪዎችንና ባቡሮችን መዝረፍ ጀመሩ።
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በ1851 በአውስትራሊያ ከፍተኛ ክምችት ያለው ወርቅ ተገኘ። ሪፖርቱ እንደገለጸው “ምርቱ በእርግጥም ድንቅ ነበር።” ለአጭር ጊዜም ቢሆን አውስትራሊያ በዓለም ከፍተኛ የወርቅ አገር አምራች ሆና ነበር። ወደ ካሊፎርኒያ ከሄዱት መካከል አንዳንዶቹ ሻንጣቸውን ጭነው ወደ ታችኛዋ አገር አቅንተዋል። የአውስትራሊያ ነዋሪዎች ቁጥር በ1850 ከነበረበት ከ400,000 ተነስቶ በ1860 ወደ 1,100,000 ከፍ ብሏል። አብዛኛዎቹ ሰዎች የተረባረቡት ወርቅ በመዛቅ እንጀራቸውን ለማውጣት ስለ ነበር ግብርናውና ሌሎቹም ሥራዎች ዕድገታቸው ባለበት ተገትቶ ነበር።
በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ እነዚህ ወርቅ የማግኘት ምኞት ያሰከራቸው ሰዎች በዩኮንና አላስካ ወርቅ ሲገኝ ወደዚያም ተጉዘዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በወርቅ በበለጸገ አገር በመኖር የድርሻቸውን ለመሰብሰብ ራቅ ወዳለው ሰሜናዊ ክፍል ማለትም ወደ ክሎንዳይክና አላስካ ሄደዋል።
ባሕር ውስጥ የሰጠመ ሀብት
በባሕር ውስጥ ጠልቆ የመዋኘት ችሎታ በዳበረበት በ20ኛው መቶ ዘመን ወርቅ ፈላጊዎች በባሕር ውስጥም ማሰስ ጀምረዋል። እንደ ወርቅ ያሉ ውድ ማዕድኖችንና ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የተሠሩ ሰው ሠራሽ ጌጦችን ፍለጋ የሰጠሙ መርከቦችን ማሰሱን ተያይዘውታል።
መስከረም 20, 1638 ኮንሴፕሲዮን የተባለችው የስፔይን የንግድ መርከብ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ እየተገፋች ከአለቶች ጋር በመላተሟ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ከሳይፓን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ሰጥማ ነበር። የጫነቻቸው ወርቅና ሌሎች ውድ ነገሮች ዛሬ ባለው ተመን በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያወጣ ነበር። ተሳፍረው ከነበሩት 400 ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሞተዋል። ጠላቂ ዋናተኞች እያንዳንዳቸው 1.5 ሜትር ርዝማኔ ያላቸውና ብዙ ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 32 የወርቅ ሰንሰለቶችን ማውጣት ችለዋል። በአጠቃላይ ጠላቂ ዋናተኞቹ 1,300 የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦች ማለትም ሰንሰለቶች፣ መስቀሎች፣ አርማዎች፣ የደረት ጌጦች፣ ቀለበቶችና ዘለበቶች አግኝተዋል።
ሌሎች የሰጠሙ መርከቦችም ተገኝተዋል። በ1980 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፍሎሪዳ የባሕር ዳርቻ የሚገኙ ጠላቂ ዋናተኞች በ17ኛው መቶ ዘመን የሰጠመችውን ሳንታ ማርጋሪታ የተባለች የስፔይን የንግድ መርከብ አግኝተዋል። እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ድረስ ጠላቂ ዋናተኞቹ ከ44 ኪሎ ግራም የሚበልጥ ጥፍጥፍ ወርቅና ሌሎችም ከወርቅ የተሠሩ ነገሮችን ማውጣት ችለዋል።
በጦርነት የተገኘ ወርቅ
የጀርመን መንግሥት በ1945 እጁን ከሰጠ በኋላ የሕብረ ብሔሩ ኃይል በጀርመን ቱሪንጂ ባለው በካይዜሮደ የጨው ማምረቻ አስገራሚ ነገር አግኝቷል። ዘ አትላንታ ጆርናል እንዳለው ከሆነ “በቁፋሮው ቦታ 2.1 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ጥፍጥፍ ወርቅ፣ የጌጣጌጥ ሥራዎች፣ ጥሬ ገንዘብና የአክሲዮን ባለቤትነት ዋስትና” ተገኝተዋል። በተጨማሪም ናዚ ባካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ ካለቁት ሰዎች የተሰበሰቡ የወርቅና የብር የጥርስ ሥራዎች የተቀመጡባቸው ከረጢቶች ተገኝተዋል። ይህ የተደበቀ ወርቅ የናዚ የጦር አዛዦች ረጅም ጊዜ የፈጀውን ጦርነት በገንዘብ ለመደገፍ አስችሏቸዋል። ጆርናሉ ሪፖርት እንዳደረገው ከሆነ 2.5 ቢልዮን ዶላር እንደሚያወጣ የተገመተ ወርቅ በአንድ ወቅት በጀርመን ተይዘው ለነበሩት አሥር የሚያክሉ አገሮች ተመልሶላቸዋል። ናዚ የደበቀው ገና ያልተገኘ ወርቅ አለ የሚል እምነት ስላለ ፍለጋው ቀጥሏል።
ወርቅ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ወርቅ እንደ ሌሎቹ ቁሳዊ ንብረቶች ሁሉ ለሚጓጉለት ሰዎች ሕይወትን ሊሰጥ እንደማይችል ይናገራል። (መዝሙር 49:6–8፤ ሶፎንያስ 1:18) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል” ይላል። (ምሳሌ 16:16) የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ሲሆን ይህ ጥበብ የሚገኘው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። እንዲህ ያለውን ጥበብ የሚፈልጉ ሰዎች የአምላክን ቃል በማጥናት የአምላክን ሕግጋት፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምክር ሊማሩና በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። በዚህ መንገድ የሚገኘው ጥበብ የሰው ልጅ እስከዛሬ ድረስ ቆፍሮ ያወጣውን ወርቅ ሁሉ የሚያስንቅ ነው። ይህ ዓይነቱ ጥበብ ዛሬ የተሻለ ሕይወት ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝልን ይችላል።—ምሳሌ 3:13–18
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ወርቅ ጥቂት ለማለት ያህል
• ወርቅ ከማንኛውም ብረት ይበልጥ በቀላሉ የተፈለገው ቅርጽ ሊሰጠው ይችላል። ወርቅን 0.1 ማይክሮሜትር እስከሚያክል ድረስ ማሳሳት ይቻላል። 28 ግራም የሚመዝነውን ወርቅ በመጠፍጠፍ 17 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሸፍን ማድረግ ይቻላል። 28 ግራም ወርቅ በቀጭኑ እየተጎተተ 70 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊረዝም ይችላል።
• ንጹሕ ወርቅ ጥንካሬ ስለሚጎድለው ከሌሎች የብረት ዓይነቶች ጋር ተቀላቅሎ እንዲጠነክር ይደረግና ጌጣጌጦችና ሌሎች ነገሮች ይሠሩበታል። የወርቁ መጠን የሚገለጸው በአንድ 24ኛ መለኪያ ሲሆን ይህም ካራት ይባላል። በመሆኑም 12 ካራት ወርቅ ማለት 50 በመቶ ወርቅ ነው ማለት ነው። 18 ካራት ደግሞ 75 በመቶው ወርቅ ነው። 24 ካራት ከሆነ ንጹህ ወርቅ ነው ማለት ነው።
• ግንባር ቀደም የወርቅ አምራች አገሮች ደቡብ አፍሪካና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።
[ምንጭ]
ታላቁ እስክንድር:- The Walters Art Gallery, Baltimore
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶፈር ኮለምበስ ወርቅ ፍለጋ በ1942 ወደ ባሕማስ ሲገባ የሚያሳይ ስዕል
[ምንጭ]
Courtesy of the Museo Naval, Madrid (Spain), and with the kind permission of Don Manuel González López