ነጎድጓዳማ ውሽንፍር አስፈሪው የደመናት ንጉሥ
አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ብዙ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ በደመናት ሲደነቁ ኖረዋል። የ80 ዓመት አዛውንት የሆኑ አንድ ሰው በልጅነታቸው ሣር ላይ ተኝተው “የሰማይ ላይ ሰልፈኞች” ብለው የገለጿቸውን ደመናት እንዴት ይመለከቱ እንደነበረ ያስታውሳሉ። ደመናት የተሠሩት ከምን ይሆን እያሉ በተደጋጋሚ ራሳቸውን ይጠይቁ እንደነበረ ይናገራሉ። ከጥጥ ይሆን? እያንዳንዳቸው የተለያየ ቅርጽ ይዘው የሚታዩት ለምንድን ነው? ይሄኛው መርከብ ይመስላል፤ ያኛው ደግሞ የሚጋልብ ፈረስ ይመስላል። እየመጣ ያለው ደመና ደግሞ ግንብ ይመስላል። ያለማቋረጥ በሚለዋወጥ ቅርጽና መጠን በሰማይ ላይ ሲንሳፈፉ የልጅ አእምሯቸውን ደስ ያሰኙት ነበር። አሁንም ድረስ ደመናትን እየተመለከቱ በሰማይ ላይ “የሚሠሩትን ቅርጽ ለመገመት መሞከር” እንደሚያስደስታቸው ተናግረዋል። ምናልባት አንተም እንዲህ ማድረጉ ያስደስትህ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ከሁሉም ይበልጥ አስደናቂና አስፈሪ የሆኑት ደመናዎች “መናገር” የሚችሉት ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ደመናት ዝናብ ደመና በመባል ይታወቃሉ። ጥቁርና አስፈሪ የሆኑት እነዚህ ደመናት 16 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ከፍታ ሊኖራቸው የሚችል ከመሆኑም በላይ ነጎድጓዳማ ውሽፍንር የሚያመጡት እነዚሁ ደመናት ናቸው። ውሽንፍር የሚፈጥሩ ደመናዎች በሰማይ ላይ እየተከማቹ ሲሄዱ መብረቅ ሊያስከትሉና የማስጠንቀቂያ ጉርምርምታ ድምፅ ሊያሰሙ ይችላሉ። በምሽት ማንኛውንም ሰው ሠራሽ ርችት የሚያስንቅ አስገራሚ ድምፅና ብርሃን ሊያወጡ ይችላሉ። ዝናባቸውንና በረዷቸውን ካወረዱና ካዘነቡ በኋላ ክው ብሎ ደርቆ የቆየውን መሬት አርጥበው ንጹሕና ቀዝቃዛ ጠረን ትተው ይሄዳሉ።
ነጓድጓዳማ ውሽንፍር የሚፈጠርበት መንገድ
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰው ልጅ ከጠፈር ላይ ሆኖ ፕላኔቷን ምድር መመልከት ችሏል። አብዛኛውን የምድር ገጽ የሸፈነ ደመና እንዳለ ተመልክቷል። ደራሲው ፍሬድ ሃፕጉድ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በማንኛውም ወቅት ቢሆን ግማሽ ያህሉ ማለትም 250 ሚልዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆነው የምድር ገጽ [በደመናዎች] የተሸፈነ ነው። እነዚህ ደመናዎች ንጣፍ፣ ቁልል፣ ንብር፣ ሸንተረር፣ ንድፍ፣ ባዘቶ፣ ብርሃን የሚያንባርቁና የማያንጸባርቁ ሲሆኑ እየተከማቹ፣ እየተበተኑ፣ እየተንሳፈፉና ቀስ በቀስ እየደበዘዙ ሄደው በመጨረሻ ይጠፋሉ።” ከዚህ የደመና መጠነቁስ መካከል ግማሽ ያህሉ ነጎድጓዳማ ውሽፍንር ነው። እንዲያውም በየዓመቱ በምድር ዙሪያ 15,000,000 ነጎድጓዳማ ውሽንፍሮች የሚከሰቱ ሲሆን በማንኛውም ወቅት ወደ 2,000 የሚጠጉ ነጎድጓዳማ ውሽንፍሮች ይገኛሉ።
ነጎድጓዳማ ውሽንፍር የሚፈጠረው ጥቅጥቅ ያለ ቀዝቃዛ አየር ሳሳ ባለ እርጥበት አዘል አየር ላይ በሚያርፍበት ጊዜ ነው። እንደ ፀሐይ ሙቀት፣ ግምባር የአየር ጠባይ (frontal weather) ወይም ደግሞ ከፍተኛ ቦታዎች ያሉ አፀግብሮቱን የሚቀሰቅሱ ነገሮች ሞቃታማው እርጥበት አዘል አየር በቀዝቃዛው አየር ውስጥ ወደ ላይ መውጣት እንዲጀምር ያደርጉታል። የአየር ሞገድ ይፈጠርና የሙቀት ኃይል አየሩ ውስጥ ይከማቻል። ተኑ ደግሞ ወደ ንፋስና የኤሌክትሪክ ኃይል ይለወጣል።
ነጎድጓዳማ ውሽንፍሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉት የከባቢ አየር ሁኔታዎች በታችኛዎቹ ኬክሮሶች በብዛት ይገኛሉ። ይህ ደቡብ አሜሪካና አፍሪካ ለነጎድጓዳማ ውሽንፍር ይበልጥ የተጋለጡ ሊሆኑ የቻሉበትን ምክንያትና መካከለኛው አፍሪካና ኢንዶኔዥያ ከረጅም ጊዜ አንስቶ በዓለማችን በከፍተኛ ሁኔታ የነጎድጓዳማ ውሽንፍር እንቅስቃሴ የሚታይባቸው አገሮች ተደርገው ሊቆጠሩ የቻሉት ለምን እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ተቀባይነት ያገኘው አኃዝ እንደሚያሳየው በኡጋንዳ ካምፓላ ውስጥ በየዓመቱ ነጎድጓዳማ ውሽንፍር የሚከሰትባቸው 242 ቀናት ይመዘገባሉ። በሌሎች ብዙ የምድር ክፍሎችም ነጎድጓዳማ ውሽንፍር ይከሰታል።
የሰማይ ላይ ርችቶች
ለሁሉም ሰው ግልጽ የሆኑት ሁለቱ የነጎድጓዳማ ውሽንፍር ገጽታዎች ነጎድጓድና መብረቅ ናቸው። ይሁን እንጂ ለእነዚህ አስደናቂና ብዙውን ጊዜም አስፈሪ የሆኑ ክስተቶች መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው? መብረቅ የሚታየው በሁለት ቦታዎች ያሉ የኤሌክትሪክ ሙሌት ልዩነቶች የአየሩን የመክላት ኃይል (insulating effect) መቋቋም የሚችሉ ሆነው ሲገኙ ነው። ይህ ሁኔታ በአንድ ደመና ውስጥ፣ በደመናዎች መካከል ወይም በደመናዎችና በምድር መካከል ሊከሰት ይችላል። መብረቅ አየሩ ለተወሰነ ጊዜ የሙቀት መጠኑ በሚያስገርም ሁኔታ እንዲጨምር ያደርገዋል። የኤሌክትሪክ ሙሌቱ በሚወጣበት ጊዜ የአየሩ ሙቀት መጠን እስከ 30,000 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል።
መብረቅ ጭረተ-ቀለም መብረቅ፣ መንሽ መብረቅ ወይም ደግሞ ንጣፍ መብረቅ ተብሎ ሊከፈል ይችላል። የሚወጣው ብርሃን እንደ አንድ መሥመር ሆኖ የሚታይ ከሆነ ጭረተ-ቀለም መብረቅ ነው። መሥመሩ የተከፋፈሉ ቅርንጫፎች ካሉት መንሽ መብረቅ ነው። ብልጭታው በደመናው ውስጥ ብትንትን ብሎ የሚታይ ከሆነ ደግሞ ንጣፍ መብረቅ ይባላል። አብዛኛውን ጊዜ የምናየው መብረቅ ከደመና ወደ ምድር የሚወርድ መብረቅ እንደሆነ ጠበብት ይናገራሉ።
መብረቅ ሕያዋን በሆኑ ነገሮች ላይ ጉዳት ያስከትላል። እንዲያውም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሞትና የአካል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በባሕር ዳርቻዎችና በተንጣለሉ ሜዳዎች እንዲሁም በገጠራማ ቦታዎች ከቤት ውጪ ያሉ ሰዎች ከኤሌክትሪክ ሙሌቱ የተጠበቁ ባለመሆናቸው ለአደጋው በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው።—ገጽ 13 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
በመብረቅ ከሚመቱት ሰዎች መካከል የሚሞቱት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሲሆኑ ወዲያውኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ ማግኘት የቻሉ ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጉዳት አይደርስባቸውም። ይሁን እንጂ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት አፈ ታሪክ ከሚለው በተለየ መልኩ መብረቅ በአንድ ቦታ ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ ሊወድቅ ይችላል፣ ይወድቃልም!
መብረቅ እሳት ያስነሳል። ይህ ደግሞ ሰፋፊ መሬቶችን ሊያወድም ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚከሰተው የደን ቃጠሎ መካከል 10 በመቶ የሚሆነው መነሾው መብረቅ እንደሆነ ይገመታል። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ካለው ደንና ዱር ከ35 በመቶ በላይ የሚሆነው በእሳት ይወድማል።
ሆኖም መብረቅ መውደቁ ጥቅምም አለው። ለምሳሌ ያህል ደኖች መብረቅ በሚወድቅበት ጊዜ በብዙ መልኩ ይጠቀማሉ። በመብረቅ የሚነሣ እሳት አነስተኛ መጠን ያለው በሚሆንበት ጊዜ በጫካው ውስጥ የሚገኙትን ትንንሽ ተክሎች ያመናምናቸዋል። ይህ ደግሞ ዛፎቹ ጫፍ ድረስ ሊደርስ የሚችል ከባድ ሰደድ እሳት ሊነሳ የሚችልበትን አጋጣሚ ሊቀንስ ይችላል። በተጨማሪም መብረቅ ለዕፅዋት ጥቅም የማይሰጠውን የናይትሮጅንን ጋዝ ጥቅም ሊሰጥ ወደሚችልበት ሁኔታ ይለውጠዋል። መብረቅ በሚወርድበት ጊዜ ይህንን ጋዝ ወደ ናይትሮጅን ውሁድነት ይለውጠዋል። ይህ ደግሞ ለእንስሳት ሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ፕሮቲኖች ለሚያስገኙት የዕፅዋት ህብረህዋሳትና ዘሮች ዕድገት በጣም ወሳኝ ነው። በዝናብ ውስጥ ከሚገኘት ናይትሮጅን ኦክሳይዶች ውስጥ ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው በመብረቅ አማካኝነት የሚፈጠር እንደሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በዚህ መንገድ 30 ሚልዮን ቶን የናይትሮጅን ውሁድ እንደሚፈጠር ይገመታል።
ነጎድጓዳማ ውሽንፍር የሚያስገኘው ከፍተኛ ጥቅም
ነጎድጓዳማ ውሽንፍር ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ እንዲዘንብ ሊያደርግ ይችላል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚዘንብበት ዋነኛው ምክንያት አየሩ ከፍተኛ መጠን ያለውን ውኃ ወደ ላይ ገፍቶ ይዞ ስለሚቆይና በድንገት ስለሚለቀው ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ በሰዓት 203 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ዝናብ ይመዘገባል። እርግጥ፣ እንዲህ ዓይነቱ ከባድ ዝናብ መጥፎ ጎንም ሊኖረው ይችላል።
ነጎድጓዳማ ውሽንፍር በዝግታ በሚጓዝበት ጊዜ አብዛኛው ዝናብ የሚወርደው በአንጻራዊ ሁኔታ በተወሰነ አካባቢ ላይ በመሆኑ ድንገተኛ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል። በእንዲህ ዓይነቱ ነጎድጓዳማ ውሽንፍር ወቅት የሚፈጠረው ድንገተኛ ጎርፍ ወንዞችና ጅረቶች ከአፍ እስከ ገደፍ እንዲሞሉ ያደርጋቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ጎርፍ ከሚያስከትለው ጉዳት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው በነጎድጓዳማ ውሽንፍር በሚመጣ ድንገተኛ ጎርፍ ሳቢያ የሚከሰት እንደሆነ ይገመታል።
ይሁን እንጂ በነጎድጓዳማ ውሽንፍር ወቅት የሚዘንበው ዝናብ ብዙ ጥቅሞች አሉት። አፈሩ የሚያገኘውም ሆነ ወደ ውኃ ማጠራቀሚያዎችና ግድቦች የሚገባው ውኃ መጠን በእጅጉ ይጨምራል። በአንዳንድ ቦታዎች ከሚዘንበው የዝናብ መጠን ውስጥ ከ50 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው በነጎድጓዳማ ውሽንፍር የሚመጣ ነው። በመሆኑም በእነዚህ ቦታዎች የነጎድጓዳማ ውሽንፍር ዝናብ ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ስለ በረዶስ ምን ማለት ይቻላል?
ነጎድጓዳማ ውሽንፍር ካሉት በጣም ጎጂ ገጽታዎች አንዱ ብዙውን ጊዜ ከባድ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ የሚያስከትል መሆኑ ነው። በረዶ የሚፈጠረው የዝናብ ጠብታዎች በሚረጉበት ጊዜ ሲሆን አየሩ እነዚህን የረጉ የዝናብ ጠብታዎች ወደ ላይና ወደ ታች በመግፋት በሚያካሂደው ዑደት መጠናቸው እየጨመረ ይሄዳል። አስገራሚ የሆነ መጠንና ክብደት ስላላቸው የበረዶ ድንጋዮች የሚናገሩ አንዳንድ ዘገባዎች አሉ። በ1925 ጀርመን ውስጥ 26 ሴንቲ ሜትር በ14 ሴንቲ ሜትርና በ12 ሴንቲ ሜትር መጠን ያለው የበረዶ ድንጋይ ወድቆ እንደነበረ ይነገራል። ክብደቱ ከ2 ኪሎ ግራም በላይ እንደነበረ ይገመታል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከተመዘገቡት ትልልቅ የበረዶ ድንጋዮች መካከል በ1970 በካንሳስ ግዛት የወደቀው የበረዶ ድንጋይ ይገኝበታል። ይህ የበረዶ ድንጋይ ረጅሙ ዙሮሽ (circumference) ሲለካ 44 ሴንቲ ሜትር ሲሆን 776 ግራም ይመዝናል። ከላይ ከደመናት የተወረወረ ይህን ያህል መጠን ያለው የበረዶ ድንጋይ ሰውን ሊገድል ይችላል።
ደግነቱ፣ በጥቅሉ ሲታይ በረዶ መጠኑ ከዚህ በጣም ያነሰ ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ አንዳንድ ችግሮች ከመፍጠር በቀር ሞት አያስከትልም። በተጨማሪም በረዶ በሚያስከትሉ ነጎድጓዳማ ውሽንፍሮች ጠባይ የተነሳ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል በረዶ የሚዘንብባቸው ቦታዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ናቸው። ይሁን እንጂ በበረዶ ሳቢያ በዓለም የእርሻ ሰብሎች ላይ የሚደርሰው ውድመት ሲሰላ በየዓመቱ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።
ኀብላይ ነፋስና ነጎድጓዳማ ውሽንፍር
ነጎድጓዳማ ውሽንፍር ከሚያስከትላቸው ነገሮች ሁሉ ይበልጥ አደገኛው ኀብላይ ነፋስ (tornado) ሳይሆን አይቀርም። በመሠረቱ ማንኛውም ኀብላይ ነፋስ ከነጎድጓዳማ ውሽንፍር ጋር ዝምድና አለው ማለት ይቻላል። ሆኖም ሁሉም ነጎድጓዳማ ውሽንፍሮች ኀብላይ ነፋስ የቀላቀሉ አይደሉም። ኀብላይ ነፋስ በኃይል የሚሽከረከር ጠባብ የአየር አምድ ሲሆን ከነጎድጓዳማ ደመና አንስቶ እስከ ምድር ድረስ የሚደርስ በብዙ መቶ ሜትር የሚቆጠር ዲያሜትር ያለው ነፋስ ነው። በጣም ኃይለኛ ኀብላይ ነፋስ በሚኖርበት ጊዜ የነፋሱ ፍጥነት በሰዓት ከ400 ወይም ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ሊደርስ ይችላል። የሚሽከረከሩት ኃይለኛ ነፋሳትና መሀል ላይ አየሩ ወደ ላይ የሚፈጥረው ግፊት ጥምረት ሕንፃዎችን ሊያፈራርስና ፍርስራሹን እያነሳ በመወርወር ሕይወት ሊያጠፋ ይችላል። ኀብላይ ነፋስ በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች ይከሰታል።
ወደ ታች ኃይለኛ ግፊት ከሚያሳድር አየርና ማይክሮበርስት ከተባለው ኃይለኛ አየር ጋር ዝምድና ያላቸው በቀጥታ መስመር የሚጓዙ ነፋሳትም የኀብላይ ነፋስን ያህል ባይሆንም እንኳ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው። ወደ ታች ኃይለኛ ግፊት የሚያሳድረው አየር በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ የሚችል አደገኛ ነፋስ በምድር ላይ ወይም በምድር አቅራቢያ ሊያስከትል ይችላል። ማይክሮበርስት ይበልጥ ኃይለኛ ሲሆን በሰዓት ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ሊጓዝ ይችላል።
ነጎድጓዳማ ውሽንፍሮች ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ከመሆናቸውም በላይ የሚያስከትሉትን አደጋ ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል። ነጎድጓዳማ ውሽንፍር ገና ብዙ ትምህርት ከምንቀስምባቸው በርካታ የፍጥረት ሥራ ገጽታዎች አንዱ ብቻ ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከመብረቅ ራስን ለመከላከል ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
የአውስትራሊያ የድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ መምሪያ ነጎድጓዳማ ውሽንፍር በሚኖርበት ጊዜ የሚከተሉትን ቅደመ ጥንቃቄዎች መውሰድ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጿል።
ከቤት ውጪ ስትሆን
◼ ድፍን ጣራ ባለው ተሽከርካሪ ወይም በቤት ውስጥ ተጠለል። በትንንሽ መጠለያዎች፣ በጨርቅ ድንኳኖችና ነጠል ባሉ ወይም ብዛት በሌላቸው ዛፎች አጠገብ አትጠለል።
◼ ምንም መጠለያ በሌለበት ቦታ ላይ ከሆንክ ቢቻል ጎድጓዳ በሆነ ሥፍራ ላይ (ብቻህን) እግሮችህን አንድ ላይ ሰብስበህ ቁጢጥ በል። ከጭንቅላትህም ሆነ ከሰውነትህ ላይ ብረት ነክ የሆኑ ነገሮችን አስወግድ። መተኛት ባይኖርብህም በአካባቢህ ካሉት ነገሮች ዝቅ ማለት አለብህ።
◼ ፀጉርህ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆም ከሆነ ወይም ደግሞ በአካባቢህ ያሉ እንደ ዓለትና አጥር ያሉ ነገሮች ጥዝ የሚል ድምፅ ካሰሙ ወዲያውኑ ቦታህን ቀይር።
◼ መቆጣጠሪያ ሽቦ ያላቸውን መጫወቻ አውሮፕላኖች አታብርር።
◼ እንደ መንጠቆ፣ ጃንጥላና የጎልፍ መጫወቻ ዘንጎች ያሉ ረጃጅም ወይም ብረት ነክ ነገሮች አትያዝ።
◼ የብረት መዋቅሮችን፣ የሽቦ አጥሮችን ወይም የልብስ ማስጫ ሽቦዎችን አትያዝ ወይም ወደነዚህ ነገሮች አትቅረብ።
◼ ፈረስ አትጋልብ፤ ወይም ደግሞ ብስክሌት ወይም ከላይ ክፍት የሆኑ መኪናዎች አትንዳ።
◼ እያሽከረከርክ ከሆነ በዝግታ ንዳ፤ ወይም እንደ ዛፍና የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ካሉ ረጃጅም ነገሮች ርቀህ አቁም። ድፍን ጣራ ባላቸው ተሽከርካሪዎች ወይም ተሳቢዎች ውስጥ ተቀመጥ። ሆኖም ብረት ነክ የሆነውን የመኪናውን አካል መንካትም ሆነ መደገፍ የለብህም።
◼ እየዋኘህ ከሆነ ወዲያውኑ ከውኃው ውስጥ ወጥተህ መጠለያ ፈልግ።
◼ በጀልባ እየሄድክ ከሆነ በፍጥነት ወደ ባሕሩ ዳርቻ ውጣ። እንዲህ ማድረጉ አደገኛ ከሆነ እንደ ድልድይ ወይም ጀልባ ማቆሚያ ባለ ትልቅ መዋቅር ሥር ተጠለል። የጀልባው ምሰሶና የሽቦ ገመድ በሚገባ ውኃው ውስጥ መቀበር አለባቸው።
ቤት ውስጥ ስትሆን
◼ ከመስኮቶች፣ ከኤሌክትሪክ መሣሪያዎች፣ ከቧንቧዎችና ከሌሎች ብረት ነክ ዕቃዎች ራቅ።
◼ ስልክ አትጠቀም። አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ መደወል ካስፈለገ በተቻለ መጠን በአጭሩ ለመቋጨት ሞክር።
◼ ውሽንፍሩ ከመምጣቱ በፊት ከራዲዮና ከቴሌቪዥን ጋር የተገናኙ የውጪ አንቴናና የኤሌክትሪክ መስመሮችን ንቀል። የኮምፒዩተር ሞደሞችንና ሶኬቶችን ንቀል። ከዚያም ከኤሌክትሪክ መሣሪያዎች ራቅ።
[ምንጭ]
ሲቪየር ስቶርምስ:- ፋክትስ፣ ዋርኒንግስ ኤንድ ፕሮቴክሽን ከተባለው ጽሑፍ የተወሰደ።