የሽቶ ቀማሚው ተወዳጅ ፍሬ
ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ሽቶ የረዥም ዘመን ታሪክ አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አቅም ያላቸው ሰዎች ሁሉ ሽቶ ገዝተው በመርጨት ቤታቸው፣ ልብሳቸው፣ አልጋቸውና ገላቸው ጥሩ መዓዛ እንዲኖረው ያደርጉ ነበር። ሽቶ ለመሥራት ከሚያገለግሉት ነገሮች መካከል እሬት፣ የበለሳን ዘይት፣ ቀረፋና ሌሎችም ቅመሞች ይገኛሉ።—ምሳሌ 7:17፤ ማሕልየ መሓልይ 4:10, 14
አሁንም ሽቶ ለመሥራት የሚያገለግሉት መሠረታዊ ነገሮች የሚገኙት ከተክሎች ዘይት ነው። ሽቶ ለመሥራት ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱ ሲመረት ለማየት በጣሊያን ደቡባዊ ጫፍ ወደምትገኘው ካላብሪያ ወደምትባል ባሕረ ገብ መሬት ሄደን ነበር። ምናልባት ቤርጋሞት ሲባል ሰምተህ አታውቅ ይሆናል፤ የሆነ ሆኖ የዚህ ፍሬ መዓዛ ለሴቶች ከሚዘጋጁት ሽቶዎች መካከል በአንድ ሦስተኛው ውስጥ እንዲሁም ለወንዶች ከሚዘጋጁት ግማሽ በሚሆኑት ውስጥ እንደሚገኝ ይገመታል። እስቲ ቤርጋሞት ከሚባለው ከዚህ ፍሬ ጋር እናስተዋውቅህ።
ቤርጋሞት ምንጊዜም ቅጠሉ የማይረግፍ የብርቱካንና የሎሚ ዛፍ ዝርያ ነው። ይህ ዛፍ በፀደይ ወራት ያብብና ለስላሳ ቆዳ ያላቸው ብርቱካን የሚያካክሉ ቢጫ ፍሬዎች ያፈራል። የዚህ ዛፍ ፍሬዎች ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ባሉት የመከር ወራት ደርሰው ይሰበሰባሉ። በመስኩ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች የቤርጋሞት አመጣጥ እምብዛም እንደማይታወቅ ሆኖም የተለያዩ ዛፎች ተዳቅለው የተገኘ ዛፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ቤርጋሞት ወፍ ዘራሽ ተክል አይደለም፤ እንዲሁም በዘር አማካኝነት የሚበቅል አይደለም። ሰዎች ይህን ዛፍ የሚያራቡት አዳዲስ ቅርንጫፎችን ቆርጠው እንደ ሎሚ ወይም ኮምጣጤ በመሳሰሉ ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው ተክሎች ግንድ ላይ በማጣበቅ ነው።
ቤርጋሞት በሽቶ ቀማሚዎች ዘንድ ተወዳጅ ያደረጉት ልዩ ባሕርያት አሉት። ስለዚህ ጉዳይ የሚናገር አንድ መጽሐፍ እንደሚገልጸው ከቤርጋሞት ፍሬዎች ተጨምቆ የሚወጣው ዘይት “ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ የተለያዩ መዓዛዎችን የማስገኘት፣ አንድን ውህድ ልዩ የሚያደርገውን መዓዛ የመፍጠር፣ እንዲሁም ዘይቱ የገባበት እያንዳንዱ ነገር ደስ የሚል ጠረን እንዲኖረው የማድረግ” ችሎታ አለው።a
በካላብሪያ የቤርጋሞት ልማት
ቤርጋሞት ቢያንስ ከ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ በካላብሪያ መብቀል እንደጀመረና የአካባቢው ሰዎች ዘይቱን በዚያ በኩል ለሚያልፉ መንገደኞች ይሸጡ እንደነበረ የታሪክ መጻሕፍት ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ይህን ዛፍ ለገበያ ሲባል ማልማት የተጀመረው የሽቶ ምርት ተቀባይነት ማግኘት ከጀመረ ወዲህ ነው። ከጣሊያን ፈልሶ ጀርመን ውስጥ ይኖር የነበረ ጃን ፓውሎ ፌሚኒስ የተባለ ሰው በ1704 አክዋ አድሚራቢሊስ ወይም “ድንቅ ውኃ” ብሎ የሰየመውን ለስለስ ያለ መዓዛ ያለው ሽቶ ሠራ። ይህን ሽቶ ለመሥራት ከተጠቀመባቸው ንጥረ ነገሮች መካከል ዋነኛው የቤርጋሞት ዘይት ነበር። ሽቶው፣ በተሠራበት ከተማ ስም ተሰይሞ ኦው ደ ኮሎኝ፣ “የኮሎኝ ውኃ” ወይም ደግሞ ኮሎኝ ተብሎ መጠራት ጀመረ።
ቤርጋሞት ለመጀመሪያ ጊዜ በብዛት የተተከለው በ1750 በሬጂዮ ዲ ካላብሪዮ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች ከዚያ የሚገኘውን ዘይት ሸጠው ጠቀም ያለ ትርፍ ማግኘታቸው ቤርጋሞትን በስፋት እንዲያለሙ ገፋፍቷቸዋል። ዛፉ ለስለስ ያለ የአየር ንብረትና ከበስተ ሰሜን የሚነፍሰውን ቀዝቃዛ ነፋስ የሚከልለው መከታ ያስፈልገዋል፤ ይሁንና ኃይለኛ ነፋስ፣ ድንገተኛ የሙቀት መለዋወጥና ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ወበቅ አይስማማውም። ትንሽ ለየት ያለ የአየር ጠባይ ያለውና በጣሊያን ደቡባዊ ጠረፍ አቅራቢያ የሚገኘው 5 ኪሎ ሜትር ስፋትና 150 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ኪስ መሬት ይበልጥ ይስማማዋል። ቤርጋሞትን በሌላ ስፍራ ለማልማት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በመላው ዓለም አብዛኛው ምርት የሚገኘው ሬጂዮ ዲ ካላብሪዮ ከሚባለው የጣሊያን ክፍለ ሃገር ነው። ከሬጂዮ ቀጥሎ ከፍተኛ ምርት የምታመርተው ሌላዋ አገር በአፍሪካ የምትገኘው ኮት ዲቩዋር ናት።
የቤርጋሞት ዘይት ወደ አረንጓዴ ያደላ ቢጫ ቀለም ሊኖረው የቻለው በፍሬው ልጣጭ ምክንያት ነው። ከቤርጋሞት ፍሬ በባሕላዊ መንገድ ዘይት የሚወጣው ፍሬውን ለሁለት ቆርጦ ሥጋውን ፈልቅቆ ካወጡ በኋላ በቆዳው የላይኛው ክፍል ላይ ያለውን ፈሳሽ ሰፍነግ ላይ በመጭመቅ ነው። በዚህ መንገድ ወደ ግማሽ ሊትር የሚጠጋ ዘይት ለማግኘት 91 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የቤርጋሞት ፍሬዎች መጭመቅ ያስፈልጋል። በዛሬው ጊዜ የቤርጋሞት ዘይት የማውጣቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ የሚከናወነው ከድፍን ፍሬዎች ላይ ልጣጩን መፈቅፈቅ በሚችሉ ማሽኖች አማካኝነት ነው ለማለት ይቻላል።
እምብዛም የማይታወቅ፣ ሆኖም በሠፊው ጥቅም ላይ የዋለ ፍሬ
ቤርጋሞት ከካላብሪያ ውጪ ብዙም ላይታወቅ ቢችልም አንድ ምንጭ እንደሚናገረው “በባለ ሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ፍሬ ነው።” የዚህ ፍሬ መዓዛ በሽቶዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሳሙናዎች፣ በዲዮድራንቶች፣ በጥርስ ሳሙናዎች፣ በክሬሞችና በመሳሰሉት ምርቶች ውስጥ ሊገኝ ይችላል። እንዲሁም የቤርጋሞት ዘይት ለጥሩ ጣዕም ሲባል በአይስ ክሬም፣ በሻይ፣ በጣፋጭ ምግቦችና በመጠጦች ውስጥ ይገባል። ቆዳን የማጥቆር ባሕርይ ስላለው ቆዳን ከፀሐይ ጨረር ለመከላከል የሚያስችል ቅባት ለመሥራት ከሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል። ጀርሞችንና ባክቴሪያዎችን የመግደል ባሕርይ ያለው መሆኑ በቀዶ ሕክምና ወቅት እንዲሁም ለዓይንና ለቆዳ በሽታዎች የሚያገለግሉ መድኃኒቶችን በሚሠሩ ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ተፈላጊ አድርጎታል። በቤርጋሞት ፍሬ ውስጥ የሚገኘው ፔክቲን የተባለው ንጥረ ነገር የደም መፍሰስንና ተቅማጥን የሚያስቆሙ መድኃኒቶችን ለመሥራት ጥቅም ላይ ይውላል።
በመስኩ የተሰማሩ ተንታኞች የቤርጋሞት ዘይት፣ ልዩ መዓዛና ሌሎች በርካታ ባሕርያት እንዲኖሩት ያደረጉ 350 የሚያህሉ ንጥረ ነገሮችን አግኝተዋል። በአንድ ፍሬ ውስጥ ይህ ሁሉ ንጥረ ነገር የሚገኝ መሆኑ በእርግጥ የሚያስገርም ነው!
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ቤርጋሞት የሚያውቁት ነገር አለ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይከብዳል። ይሁን እንጂ ስለዚህ የብርቱካን ዝርያ ባሕርያትም ሆነ ፈጣሪው ስላለው ጥበብ ለማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መዝሙራዊው ‘የፍሬ ዛፎች ሁሉ ይሖዋን አመስግኑት’ በማለት የተናገራቸውን ቃላት ለማስተጋባት የሚያነሳሳ ምክንያት እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 148:1, 9
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሣር ወይም የአበባ ዱቄት ሲሸታቸው የማይስማማቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ሽቶም የማይስማማቸው ሰዎች አሉ። ንቁ! መጽሔት ይህን ተጠቀሙ ብሎ ማንኛውንም ምርት አያስተዋውቅም።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤርጋሞት ዘይት የሚወጣው ከድፍኑ ፍሬ ላይ ልጣጩን በመፈቅፈቅ ነው
[ምንጭ]
© Danilo Donadoni/Marka/age fotostock