በሄይቲ የደረሰው የመሬት መናወጥ—እምነትና ፍቅር በሥራ ሲገለጽ
ኤቭሊን ማክሰኞ፣ ጥር 12, 2010 ከቀትር በኋላ 10:53 ላይ አንድ ግዙፍ አውሮፕላን ሲነሳ የሚያሰማው ዓይነት የሚያስገመግም ድምፅ ከመሬት ሲወጣ ሰማች፤ ወዲያውኑም መሬቱ መንቀጥቀጥ ጀመረ። በአቅራቢያው ያሉት ሕንፃዎች ተፈረካክሰው ሲወድቁ ኃይለኛ ድምፅ ያሰሙ ነበር። የመሬት መናወጡ ሲቆም ኤቭሊን ከፍ ወዳለ ቦታ በመውጣት አካባቢውን መቃኘት ጀመረች። በዙሪያዋ የሰዎች ዋይታ ይሰማል። ከፍርስራሹ የሚነሳው አቧራ የሄይቲን ዋና ከተማ ፖርት ኦ ፕራንስን ሸፈናት።
በሴኮንዶች ውስጥ መኖሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት ሕንፃዎች፣ ባንኮች፣ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች ተንኮታኩተው ወደቁ። ሀብታም ድሃ ሳይባል ከ220,000 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን 300,000 የሚያህሉት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሕይወት የተረፉት አብዛኞቹ ሰዎች ከመደንገጣቸው የተነሳ ከፈራረሱት ቤቶቻቸው አጠገብ ፍዝዝ ብለው ተቀምጠዋል። ሌሎች ደግሞ በጭንቀት ስሜት ተውጠው የዘመዶቻቸውንና የጎረቤቶቻቸውን ሕይወት ለማዳን በእጃቸው ፍርስራሹን ይፈነቃቅላሉ። የኤሌክትሪክ ኃይል ስለተቋረጠ ብዙም ሳይቆይ ከተማዋ በጨለማ ተዋጠች፤ በዚህም የተነሳ ነፍስ አድን ሠራተኞቹ በባትሪና በሻማ መሥራት ግድ ሆነባቸው።
በዣክሜል ከተማ የሚኖር ራልፌንዲ የሚባል የ11 ዓመት ልጅ በከፊል ከተደረመሰ አንድ ሕንፃ መውጣት ስላቃተው እዛው ቀርቶ ነበር። የከተማዋ ነፍስ አድን ሠራተኞች ራልፌንዲን ለማውጣት ለሰዓታት ደከሙ። ይሁንና መሰነጣጠቅ የጀመረው የሕንፃው ፎቅ ከዋናው ነውጥ በኋላ በተከሰቱት ተደጋጋሚ ነውጦች ምክንያት እላያቸው ላይ እንዳይደረመስባቸው በመፍራት ጥረታቸውን አቆሙ። የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናዊ የሆነው ፊሊፕ ግን ጥረቱን ለማቆም ፈቃደኛ አልሆነም፤ “ራልፌንዲን እዚያው እንዲሞት ትቶ መሄድ አእምሮዬ ሊቀበለው የሚችለው ነገር አይደለም” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል።
ፊሊፕና ሌሎች ሦስት ሰዎች ከፈረሰው ሕንፃ ሥር ባገኙት ጠባብ ቀዳዳ እንደምንም ብለው ሾልከው ከገቡ በኋላ ራልፌንዲ ወዳለበት ቦታ ቀስ ብለው በጥንቃቄ ሄዱ፤ ጊዜው እኩለ ሌሊት የነበረ ሲሆን ራልፌንዲን ሲያገኙት እግሩ በሕንፃው ፍርስራሽ ተጣብቆ ነበር። ወዲያው ፍርስራሹን በቀስታ ማንሳት ጀመሩ። ትናንሽ ነውጦች በተከሰቱ ቁጥር ከበላያቸው ያለው የኮንክሪት ጣሪያ እያዘመመ ሲሄድና ሲሰነጣጠቅ ይሰማቸው ነበር። ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ ከ12 ሰዓታት በኋላ ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት ሲሆን ራልፌንዲን ጎትተው አወጡት።
የሚያሳዝነው ግን ከተደረጉት እንዲህ ያሉ ጥረቶች ውስጥ ጥሩ ውጤት ያስገኙት ሁሉም አልነበሩም። በነውጡ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ሌኦጋን ከተማ ውስጥ የሚኖረው ሮዤና ትልቁ ልጁ ክሊድ ቤታቸው ላያቸው ላይ ከመደርመሱ በፊት ማምለጥ ችለው ነበር። ክላራንስ የሚባለው ትንሹ ልጁ ግን ሞተ። ክላና የተባለችው የሮዤ ሚስት በሕይወት የነበረች ከመሆኑም በላይ መናገር ትችል ነበር፤ ይሁንና የወደቀው ጣሪያ ጭንቅላቷን አጣብቆ ይዞት ነበር። ሮዤና ጓደኛው እሷን ከፍርስራሹ ክምር ሥር ለማውጣት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ “ፍጠኑ! እየደከምኩ ነው! ትንፋሽ እያጠረኝ ነው!” ትላቸው ነበር። ከሦስት ሰዓት በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች ደረሱላቸው። ይሁን እንጂ ሲያወጧት ሕይወቷ አልፎ ነበር።
ረቡዕ፣ ጥር 13፣ ሁለተኛ ቀን
ጎሕ ሲቀድ አደጋው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በግልጽ ታየ። የፖርት ኦ ፕራንስ አብዛኛው ክፍል የፍርስራሽ ክምር ሆኖ ነበር። የመሬት ነውጡ ያስከተለውን ውድመት የሚገልጸው ዜና ሲሰራጭ በዓለም ዙሪያ ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች ወደ አካባቢው ተንቀሳቀሱ፤ ብዙ ግለሰቦችም ለነፍሳቸው ሳይሳሱ በአደጋው የተጎዱትን ለመርዳት ወደ ቦታው ሄዱ። ወደ 300 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት ላይ በሚገኘው የዶሚኒካን ሪፑብሊክ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግሉት ፈቃደኛ ሠራተኞችም ርዕደ መሬቱ ተሰምቷቸው ነበር። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳበት ቦታ ዘጠኝ ሚሊዮን ከሚሆነው የሄይቲ ሕዝብ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሚኖሩባትና በሕዝብ ብዛት የተጨናነቀችው ፖርት ኦ ፕራንስ አቅራቢያ መሆኑን ሲያውቁ ወዲያውኑ እርዳታ ማሰባሰብ ጀመሩ።
ሄይቲ እንዲህ ያለ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ካጋጠማት 150 ዓመት ሆኗታል። በዚህም የተነሳ የሄይቲ ሕዝብ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚቋቋሙ ሕንፃዎችን ከመገንባት ይልቅ አውሎ ነፋስና ጎርፍ የሚቋቋሙ ሕንፃዎችን ወደ መሥራቱ አዘንብለው ነበር። በመሆኑም አብዛኞቹ ግድግዳዎችና የኮንክሪት ጣሪያዎች በሬክተር መለኪያ 7.0 የሆነውን ርዕደ መሬት ለመቋቋም አቅም አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ በ1987 ተሠርቶ የተጠናቀቀው የሄይቲ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ የተገነባው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመሬት ነውጦችን እንዲቋቋም ተደርጎ ነው። ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው የፖርት ኦ ፕራንስ ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ ቢሆንም ምንም ጉዳት አልደረሰበትም ማለት ይቻላል።
በሄይቲ የሚገኘው ቢሮ በአንድ ምሽት ተለውጦ ከፍተኛ ርብርቦሽ የሚደረግበት የእርዳታ ማዕከል ሆነ። ዓለም አቀፍ የስልክና የኢሜይል ግንኙነት አስተማማኝ ባለመሆኑ የቢሮው አባላት ሪፖርቶችን ለማቀበል ወደ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ድንበር ሁለት ጊዜ በመኪና ሄደዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአደጋው የተጎዱ ሰዎች ወደ ሄይቲ ቢሮ ቅጥር ግቢ ይጎርፉ ነበር፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ነበሩ። ሌሎች ብዙዎች ደግሞ አገልግሎት ወደሚሰጡ ጥቂት ሆስፒታሎች የተወሰዱ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ሆስፒታሎቹ በሰዎች መጨናነቅ ጀመሩ።
ደም የሚፈሳቸውና የሚያቃስቱ የአደጋው ሰለባዎች በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተረፍርፈው ይታያሉ። ከእነዚህም መካከል በተደረመሰ አንድ ሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ ለስምንት ሰዓታት ተቀብራ የቆየችው ማርላ ትገኛለች። እግሮቿ በድን ሆነው ስለነበር ልታንቀሳቅሳቸው አትችልም ነበር። ጎረቤቶቿ ቆፍረው ካወጧት በኋላ ወደ ሆስፒታል ወሰዷት፤ የትኛው ሆስፒታል ይሆን የወሰዷት? ቀደም ሲል ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ የመጣ ኤቫን የሚባል አንድ ዶክተር ስሟን ብቻ ይዞ ሊፈልጋት ተነሳ።
በዚህ ጊዜ ርዕደ መሬቱ ከደረሰ 24 ሰዓታት ያለፉ ከመሆኑም ሌላ ጨልሞ ነበር። ኤቫን በአንድ ሆስፒታል ደጅ ላይ በተረፈረፉት ሬሳዎች ላይ እየተረማመደ ፍለጋውን ጀመረ፤ በልቡ ከጸለየ በኋላ “ማርላ” እያለ መጣራቱን ቀጠለ። በመጨረሻ “አቤት!” የሚል ድምፅ ሰማ። ማርላ ኤቫንን ስታየው ፊቷ በፈገግታ ፈካ። ኤቫን በመገረም ፈገግ ያለችው ለምን እንደሆነ ጠየቃት። እሷም “ምክንያቱም አሁን መንፈሳዊ ወንድሜን አግኝቻለሁ” በማለት መለሰችለት። በዚህ ጊዜ ኤቫን እንባውን መቆጣጠር አቃተው።
ሐሙስ፣ ጥር 14፣ ሦስተኛ ቀን
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ከማርቲኒክ፣ ከካናዳ፣ ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ፣ ከጀርመን፣ ከጉዋዴሎፕ፣ ከፈረንሳይና ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር በመተባበር ያለውን ቁሳቁስ፣ ገንዘብና የሰው ኃይል እንዲሁም መጓጓዣዎችንና የመገናኛ መሥመሮችን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም እንዲቻል በአደጋ የተጎዱትን የመርዳቱን ሂደት አቀናጀ። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ 78 የሕክምና ባለሙያዎች ከሌሎች ብዙ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር በመሆን ወደ ሄይቲ አቀኑ። የመጀመሪያው ጭነት መኪና 6,804 ኪሎ ግራም የሚመዝን ምግብ፣ ውኃ፣ መድኃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭኖ ከሌሊቱ 8:30 ላይ ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ ቢሮ ወደ ሄይቲ ጉዞ ጀመረ።
ጭነቱ ጠዋት ላይ ሲደርስ የሄይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ አባላት እርዳታውን ለማከፋፈል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ። ሌቦች ምግቡን ሰርቀው ሊሸጡት ስለሚችሉ የእርዳታ ሠራተኞቹ ጭነቱን ሌላ ነገር ለማስመሰል ሞከሩ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ የመጣውን እርዳታ በቤተሰብና በግለሰብ ደረጃ ለማከፋፈል እንዲያመች ምግቡንና ሌሎች ቁሳቁሶችን እየቀናነሱ በትናንሽ ከረጢቶች በመቋጠር ሌት ተቀን ይደክሙ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ከ400,000 በላይ የሚሆኑ የታሸጉ ምግቦችን ጨምሮ ከ450,000 ኪሎ ግራም የሚበልጥ የእርዳታ ቁሳቁስ በነፃ አከፋፍለዋል።
ዓርብ፣ ጥር 15፣ አራተኛ ቀን
እኩለ ቀን ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ 19 ዶክተሮች፣ ነርሶችና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ከዶሚኒካን ሪፑብሊክና ከጓዴሎፕ ተነስተው ወደ ሄይቲ መጡ። እነሱም በፍጥነት የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሚሰጥበት ክሊኒክ አቋቋሙ። በክሊኒኩ ከታከሙት መካከል ከሕፃናት ማሳደጊያ የመጡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታ ወላጅ አልባ ሕፃናት ይገኙበታል። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሠራተኞች ለሕፃናት ማሳደጊያው ምግብና ለመጠለያነት የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ሸራዎችን ሰጥተዋል። የሕፃናት ማሳደጊያው ዳይሬክተር የሆኑት ኤትየን “የይሖዋ ምሥክሮችን በጣም አመሰግናቸዋለሁ። እነሱ ባይኖሩ ኖሮ ምን እንደሚውጠን አላውቅም” ብለዋል።
ጠፍታ ተገኘች
የሰባት ዓመት ልጅ የሆነችው ኢስላንድ፣ የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት ጊዜ ከቤቷ ሆና ወደ ውጭ ስትመለከት የኤሌክትሪክ ሽቦዎቹ ሲንጣጡና የእሳት ፍንጣቂዎችን ሲያዘንቡ አየች። ከዚያም የቤቱ ግድግዳ ተፈረካክሶ ወደቀ፤ በዚህ ጊዜ ፍርስራሹ እግሯን ስለሰበራት ክፉኛ ተጎዳች። ሰዎች ከፍርስራሹ ውስጥ ካወጧት በኋላ አባቷ ጃኒ ከዶሚኒካን ድንበር አለፍ ብሎ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል በመኪና ወሰዳት። ከዚያም የዶሚኒካን ዋና ከተማ በሆነችው ሳንቶ ዶሚንጎ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተወሰደች። በኋላ ላይ ጃኒ ስለ ኢስላንድ ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታሉ ሲደውል አጣት።
ጃኒ ለሁለት ቀናት ያህል ኢስላንድን በየቦታው ቢያፈላልጋትም አጣት። እሷ ግን ወደ ሌላ ሆስፒታል ተወስዳ ነበር፤ በዚያም አንዲት የሆስፒታሉ ፈቃደኛ ሠራተኛ ኢስላንድ ወደ ይሖዋ ስትጸልይ ሰማቻት። (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) “ይሖዋን ትወጂዋለሽ?” በማለት ፈቃደኛ ሠራተኛዋ ጠየቀቻት። ኢስላንድም ዓይኖቿ እንባ አቅርረው “አዎ” አለቻት። ሴትየዋም “እንግዲያው አትጨነቂ፤ ይሖዋ ይረዳሻል” በማለት አበረታታቻት።
ጃኒ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ ኢስላንድን በማፈላለግ እንዲረዳው ጠየቀ። ሜላኒ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ኢስላንድን በማፈላለግ ልትረዳው ፈቃደኛ ሆነች። ሜላኒ አንድ ሆስፒታል ሄዳ ስታጠያይቅ ኢስላንድን ስትጸልይ አይታት የነበረችው ፈቃደኛ ሠራተኛ ድንገት ሰማችና ልጅቷ ያለችበትን ቦታ ጠቆመቻት። ወዲያውም ኢስላንድ ከቤተሰቧ ጋር ተቀላቀለች።
የቀዶ ሕክምና ክሊኒኮችና የማገገሚያ ጣቢያዎች
ከቆሰሉት መካከል ብዙዎቹ በሄይቲ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ ውስጥ ወደተቋቋመው ክሊኒክ ከመድረሳቸው በፊት የተደረገላቸው ሕክምና አጥጋቢ አልነበረም ወይም ጨርሶ ሕክምና አላገኙም፤ በዚህም የተነሳ የቆሰሉት እግሮቻቸውና እጆቻቸው ወደ ጋንግሪን ተቀይረውባቸው ነበር። የበሽተኞቹን ሕይወት ለማትረፍ የተሻለው አማራጭ የተበላሸውን የሰውነት ክፍል መቁረጥ ነበር። የመሬት መንቀጥቀጡ በደረሰ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመድኃኒቶችና የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች ሌላው ቀርቶ የማደንዘዣ መድኃኒቶች እጥረት አጋጥሞ ነበር። ሁኔታው ለሐኪሞችም እንኳ ከፍተኛ ጭንቀት የሚፈጥር ነበር። አንድ ዶክተር “ያየኋቸውና የሰማኋቸው ነገሮች ከአእምሮዬ አልጠፋ ብለዋል፤ አምላክ እነዚህን ትዝታዎች ከአእምሮዬ እንዲፍቅልኝ እመኛለሁ” ብሏል።
የመሬት መናወጡ ከደረሰ ከሁለት ሳምንት በኋላ ውስብስብና አጣዳፊ ቀዶ ሕክምናዎችን ለማድረግ የሚረዱ መሣሪያዎችን የያዙ ልምድ ያላቸው የይሖዋ ምሥክር ዶክተሮች ከአውሮፓ መምጣት ጀመሩ። የሕክምና ቡድኑ 53 ቀዶ ሕክምናዎችን ያደረገ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሕክምናዎችንም ሰጥቷል። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው የ23 ዓመቷ ዊደሊን ወደ ፖርት ኦ ፕራንስ የመጣችው የመሬት መናወጡ ከመድረሱ ከአንድ ቀን በፊት ነበር። ርዕደ መሬቱ ሲከሰት ቀኝ እጇ ስለተጨፈለቀ በአካባቢው ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተወስዳ እጇን መቆረጥ ነበረባት። በኋላ ላይ ዘመዶቿ በፖርት ደ ፔ ካለው ቤታቸው የሰባት ሰዓት መንገድ ርቆ ወደሚገኘው ሆስፒታል ወሰዷት። ይሁን እንጂ የዊደሊን ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ የሆስፒታሉ ሠራተኞች እንደማትተርፍ ስለተሰማቸው እሷን መርዳታቸውን አቆሙ።
አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና ቡድን ዊደሊን ስላለችበት አስከፊ ሁኔታ ሲሰማ እሷን ለማከምና ፖርት ኦ ፕራንስ መጥታ ተጨማሪ እንክብካቤ እንድታገኝ ለማድረግ እሷ ወዳለችበት ቦታ ሄደ። ሌሎቹ ታካሚዎች የዊደሊን መንፈሳዊ ወንድሞች እንደመጡላት ሲመለከቱ የተሰማቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገለጹ። ዊደሊን በቤተሰቧና በጉባኤው እርዳታ አሁን ከአዲሱ ሁኔታዋ ጋር በጥሩ ሁኔታ እየተላመደች ትገኛለች።
በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ከሄይቲ ለሚመጡ ታካሚዎች የማገገሚያ ጣቢያዎች በመሆን የሚያገለግሉ ቤቶችን ተከራዩ። በማገገሚያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የይሖዋ ምሥክር ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ወጌሾች እንዲሁም ለበሽተኞች እንክብካቤ የሚሰጡ ሌሎች ሰዎች በፈረቃ ይሠሩ ነበር። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ታካሚዎቹ አገግመው ከጣቢያው እስኪወጡ ድረስ በደስታ ይንከባከቧቸው ነበር።
እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ሲገለጽ
በርዕደ መሬቱ ቀጠና ውስጥ ከሚገኙት 56 የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾች መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 6ቱ ብቻ ነበሩ። በመሬት መናወጡ ምክንያት ከተፈናቀሉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ ያረፉት ጉዳት ባልደረሰባቸው አዳራሾች ውስጥ ወይም ገላጣ በሆኑ ሌሎች ሥፍራዎች ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ ቀድሞውኑም አንድ ላይ የመሰብሰብ ልማድ ስለነበራቸው ልክ ለትላልቅ ስብሰባዎች እንደሚያደርጉት ራሳቸውን አደራጁ።
“ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን የተረጋጋ መንፈስ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው የጉባኤው የዘወትር መንፈሳዊ ፕሮግራም እንደወትሮው እንዲቀጥል አደረግን” በማለት ዣን ክሎድ የሚባል የአካባቢው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ ተመልካች ገልጿል። በዚህስ ምን ውጤት ተገኘ? “የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም እየዞሩ ሲሰብኩ ሳያቸው በጣም ደስ አለኝ” በማለት አንድ ሰው ተናግሯል። “እናንተን ባናይ ኖሮ ሁኔታው በጣም የከፋ እንደሆነ አድርገን እናስብ ነበር።”
የይሖዋ ምሥክሮች ለሕዝቡ የመጽናናት ምንጭ ሆነውላቸው ነበር። “ያገኘነው ሰው ሁሉ ለማለት ይቻላል፣ የመሬት መናወጡ ከአምላክ የመጣ ቅጣት እንደሆነ ያምናል” በማለት አንድ የይሖዋ ምሥክር ገልጿል። “እኛም የመሬት መናወጡ የተፈጥሮ አደጋ እንጂ አምላክ ያመጣው እንዳልሆነ አስረዳናቸው። ዘፍጥረት 18:25ን አነበብንላቸው። በዚህ ጥቅስ ላይ አብርሃም፣ አምላክ ጥሩ ሰዎችን ከክፉዎች ጋር ማጥፋቱ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ተናግሯል። በተጨማሪም ሉቃስ 21:11ን አነበብንላቸው። በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ በዘመናችን ታላላቅ የመሬት ነውጦች እንደሚከሰቱ ትንቢት የተናገረ ሲሆን በቅርቡ ኢየሱስ በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች እንደሚያስነሳ ብሎም መከራን በሙሉ እንደሚያስወግድ ገለጽንላቸው። ብዙ ሰዎች ይህን እውቀት ስላካፈልናቸው ምስጋናቸውን ገልጸዋል።”a
እንደዚያም ሆኖ መፍትሔ የሚያሻቸው ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ነበሩ። “የመጀመሪያው አደጋ ማለትም የመሬት መናወጡ አልፏል። አሁን ደግሞ አደጋው ያመጣቸውን ጣጣዎች መጋፈጥ አለብን” በማለት ዣን ኤማኑዌል የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ዶክተር ገልጿል። “በሕዝብ በተጨናነቁና ንጽሕና በጎደላቸው እንዲሁም በዝናብ በጨቀዩ ሠፈሮች ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉት የተለያዩ በሽታዎች ከሚፈጥሩት ስጋት በተጨማሪ ታምቀው የቀሩ ስሜቶች የሚፈጥሩት የአእምሮ ቀውስም አለ።”
የመሬት መናወጡ ከደረሰ ከሳምንታት በኋላ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ክሊኒኩ በመምጣት በማያቋርጥ ራስ ምታትና በእንቅልፍ እጦት እየተሠቃየ መሆኑን ተናገረ፤ እነዚህ ችግሮች ከአደጋ በኋላ የሚያጋጥሙ የተለመዱ ምልክቶች ናቸው። “ጭንቅላትህን የመታህ ነገር አለ እንዴ?” በማለት አንዲት የይሖዋ ምሥክር ነርስ ጠየቀችው። “አይ፣ የለም” በማለት ከመለሰ በኋላ ስሜቱን ዋጥ አድርጎ “ለ17 ዓመት የትዳር አጋሬ የነበረችው ሚስቴ በአደጋው ሞታለች። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉ ነገሮች እንደሚደርሱ የምንጠብቀው ነገር ነው። ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች እንደሚከሰቱ ተናግሯል” አላት።
ነርሷም የሕመሙ መንስኤ ይህ ሊሆን እንደሚችል በማስተዋል “ግን እኮ በሞት ያጣኸው የሕይወት አጋርህን ነው። የደረሰብህ ነገር በጣም ከባድ ነው! ብታዝንና ብታለቅስ ምንም አይደለም። ኢየሱስም ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ አልቅሷል” አለችው። ስሜቱን በማፈኑ ይሠቃይ የነበረው ይህ ሰው ወዲያው እንባውን ያጎርፈው ጀመር።
አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ከሚኖሩት ከ10,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 154ቱ በመሬት መናወጡ ሳቢያ ሞተዋል። ከፖርት ኦ ፕራንስ ነዋሪዎች መካከል ከ92 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአደጋው ምክንያት አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሞት እንደተነጠቁ ይገመታል። የይሖዋ ምሥክሮች አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት በማሰብ ተመላልሰው ይጠይቋቸው ነበር፤ ይህ ደግሞ ሐዘንተኞቹ እምነት ሊጥሉበት ለሚችሉት ሰው ስሜታቸውን አውጥተው የመናገር አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ትንሣኤና ገነት ስለምትሆነው ምድር የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ቀደም ብለው የሚያውቁ ቢሆንም እነሱም የሐዘናቸው ተካፋይ ለሆኑ የእምነት አጋሮቻቸው ስሜታቸውን መግለጽና ርኅራኄ የሚንጸባረቅባቸውን አጽናኝ ቃላት መስማት ያስፈልጋቸው ነበር።
የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ጊዜ መጋፈጥ
ሐዋርያው ጳውሎስ “እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ እንዳሉ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:13) እነዚህ ባሕርያት ብዙ የሄይቲ የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ የደረሰባቸውን መከራ ችለው እንዲኖሩ፣ ሌሎችን እንዲያበረታቱና የወደፊቱን ጊዜ ያላንዳች ፍርሃት እንዲጠብቁ አስችለዋቸዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ የተጎዱትን ለመርዳት ያነሳሳቸው ያላቸው እምነት፣ አንድነትና ፍቅር ነው። “ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ የፍቅር መግለጫ አይቼ አላውቅም” በማለት ፔትራ የምትባል ለእርዳታ ከጀርመን የመጣች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ዶክተር ተናግራለች። “በጣም አልቅሻለሁ፤ ሆኖም ብዙ ያስለቀሰኝ ደስታው እንጂ ሐዘኑ አልነበረም።”
ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በ2010 በሄይቲ የደረሰውን የመሬት መናወጥ፣ “በአንዳንድ መሥፈርቶች ሲታይ በአንድ አገር ውስጥ ከደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ እጅግ አስከፊው” በማለት ጠርቶታል። ሆኖም ይህ አደጋ ከደረሰ ወዲህ ዓለማችን ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የሆኑ ሌሎች አሳዛኝ አደጋዎችን አስተናግዳለች። ታዲያ እነዚህ አደጋዎች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? በሄይቲም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አምላክ በቅርቡ እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት አላቸው፦ “እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ “አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 11ን ተመልከት።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ራልፌንዲን እዚያው እንዲሞት ትቶ መሄድ አእምሮዬ ሊቀበለው የሚችለው ነገር አይደለም”
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም እየዞሩ ሲሰብኩ ሳያቸው በጣም ደስ አለኝ”
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለአደጋው ሰለባዎች ቤት መሥራት
ርዕደ መሬቱ በደረሰ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ መሐንዲሶች፣ ሰዎች ተመልሰው ቢኖሩባቸው ስጋት የማይፈጥሩት ቤቶች የትኞቹ እንደሆኑ ማጣራት ጀመሩ። ቤቶቻቸው ከፈረሱባቸው መካከል ብዙዎቹ ቋሚ መኖሪያ እስኪያገኙ ድረስ ጊዜያዊ መጠለያ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር።
“ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ባላቸው ተሞክሮ ላይ በመንተራስ አብዛኞቹ ሰዎች ይኖሩባቸው ከነበሩት ቤቶች ጋር ተመሳሳይ ስፋት ያላቸውና በቀላሉ ሊገጣጠሙ የሚችሉ ቤቶችን በርካሽ ዋጋ ለመሥራት ንድፍ አወጣን” በማለት በሄይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠራው ጆን ገልጿል። “የሚሠራው ቤት ከዝናብና ከነፋስ ከለላ ከመሆን ባለፈ የመሬት መናወጥ ተከስቶ ቢደረመስ እንኳ በሰዎች ላይ ጉዳት የማያደርስ ነው።” የመሬት ነውጡ ከተከሰተ ገና ሦስት ሳምንታት ብቻ እንዳለፉ ከሄይቲ የተውጣጡ የግንባታ ቡድኖችና ዓለም አቀፍ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጊዜያዊ ቤቶቹን መገንባት ጀመሩ።
የቤቶቹን ተገጣጣሚ ክፍሎች የጫኑት መኪኖች መንገድ ላይ ሲያልፉ ሰዎች ደስታቸውን ይገልጹ ነበር። አንድ የሄይቲ ጉምሩክ ባለሥልጣን ለግንባታ የሚሆኑት ቁሳቁሶች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ፈቃድ በሚሰጡበት ጊዜ “የይሖዋ ምሥክሮች ድንበር በማቋረጥ ለሕዝቡ እርዳታ ለመስጠት የመጀመሪያ ከሆኑት መካከል ናቸው። እነሱ እርዳታ ስለመስጠት የሚያወሩ ብቻ ሳይሆኑ የተግባር ሰዎች ናቸው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከነውጡ በኋላ ባሉት ጥቂት ወራት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያቸውን ላጡ ሰዎች 1,500 የሚሆኑ ቤቶችን ሠርተዋል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሄይቲ
ፖርት ኦ ፕራንስ
ሌኦጋን
የርዕደ መሬቱ መነሻ
ዣክሜል
ዶሚኒካን ሪፑብሊክ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርላ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢስላንድ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዊደሊን
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሄይቲ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን የአደጋውን ሰለባዎች ለማጽናናት ሲሰማራ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ባቋቋሙት ክሊኒክ ውስጥ አንድ ዶክተር አንድን ልጅ ሲያክም