ከዓለም አካባቢ
መቀመጫውን ቱኒዝያ ያደረገው አረብ ሮድ ሴፍቲ ኦርጋናይዜሽን የተባለው ድርጅት ያወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚጠቁመው በአረቡ ዓለም ከ500,000 የሚበልጡ የመኪና አደጋዎች በየዓመቱ ይደርሳሉ። በዚህም ምክንያት 36,000 ሰዎች ይሞታሉ።—ሮይተርስ ዜና አገልግሎት፣ ቱኒዝያ
“አንድ ጥናት እንዳመለከተው በትምህርት ቤቶችም ሆነ በቤት ውስጥ የሚሰጠው የፆታ ትምህርት በቂ ባለመሆኑ የቻይናውያን ወጣቶች ዋነኛ የፆታ መረጃ ምንጭ ኢንተርኔት ነው።”—ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና
ኮምፒውተር ላይ የሚገጠሙ ቪድዮ ካሜራዎችን (ዌብካም) ተጠቅሞ የሰውን ገመና ማየት
በቅርቡ የጀርመን ፖሊሶች፣ የራሳቸውን ዌብካም ተጠቅሞ የበርካታ ሴቶችን ክፍሎች በመቃኘቱ ክስ የተመሠረተበት አንድ ሰው ይዘዋል። በሌሎች ኮምፒውተሮች ውስጥ ያለውን መረጃ ሳይፈቀድለት የሚያየው ይህ ሰው ቀላል ሆኖ ያገኘውን የአንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚ የይለፍ ቃል ካወቀ በኋላ ከዚሁ ተጠቃሚ የበርካታ ሰዎችን መረጃ አግኝቷል። ከፖሊስ የተገኘው ሪፖርት እንደሚያሳየው ይህ ሰው ጠልፎ ባገኘው አድራሻ በመጠቀም የጥቃቱ ዒላማ ለሆነው ሰው፣ ሴቶች ጓደኞች በስክሪን ሴቨር ሽፋን የሚላኩ ቫይረሶችን ይልካል። ይህን ማድረጉ የሴቶቹን ኮምፒውተርና ዌብካም በፈለገው ጊዜ በርቀት ለመቆጣጠር ያስችለዋል። መርማሪዎች ቤቱን በፈተሹበት ጊዜ ሦስት ሚሊዮን የሚያክሉ ፎቶግራፎችን ያገኙ ሲሆን “ሴቶቹ ሳያውቁ 80 ከሚያክሉት ሴቶች ኮምፒውተር ጋር የቀጥታ ግንኙነት ያደርግ እንደነበር” አኸነር ጻይቱንግ ገልጿል።
ለሳይንስ አዲስ የሆኑ ቋንቋዎች
የቡታንና የቻይና አዋሳኝ በሆነችው፣ በሕንድ ሰሜናዊ ምሥራቅ በምትገኘው በአሩናቻል ፕራዴሽ የሚነገሩትን ብዙም የማይታወቁ የአካ እና የሚጂ ቋንቋዎች የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ኮሮ የሚባል ሌላ ሦስተኛ ቋንቋ አግኝተዋል። ሊቪንግ ታንግስ ኢንስቲትዩት ፎር ኢንዴንጀርድ ላንጉጅስ የተባለው ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ግሪጎሪ አንደርሰን “ይህ ቋንቋ ተመዝግቦ የማያውቅና ጨርሶ የማይታወቅ ነው” ብለዋል። ኮሮ እስካሁን ድረስ ሳይታወቅ የቀረው 800 በሚያክሉ ሰዎች ብቻ የሚነገር መሆኑና ወደ አካባቢው መድረስ እጅግ አዳጋች ስለሆነ ነው። ከዚህ በፊት አንድ ቋንቋ ብቻ እንዳለ ሪፖርት በተደረገበት በቻይና ውስጥ በሚገኝ አንድ አካባቢ በ2009፣ ሃያ አራት ቋንቋዎች እንዳሉ ታውቋል።
በራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች የተበከሉ የዱር አሳማዎች
ሽፒገል ኦንላይን “[በጀርመን፣] የዱር አሳማዎች በራዲዮአክቲቭ በመበከላቸው ምክንያት ኪሣራ ላይ ለወደቁ አዳኞች መንግሥት የሚሰጠው ካሣ ከ2007 ወዲህ በአራት እጥፍ እንዳደገ” ዘግቧል። ብዙ አዳኞች ለሰው ቀለብ የሚሆን የዱር አሳማ ሥጋ ለሽያጭ የሚያቀርቡ ቢሆንም መንግሥት ከ25 ዓመት በፊት በቸርኖብል በደረሰው ፍንዳታ ምክንያት የተሠራጨው ሲዝየም-137 የተባለ ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር በብዛት ያለባቸው የዱር አሳማዎች ሥጋ እንዳይሸጥ የሚያግድ ደንብ አውጥቷል። የዱር አሳማዎቹ ለዚህ ብክለት ሊጋለጡ የቻሉት “ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮችን ስቦ የማቆየት ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውን የእንጉዳይ ዝርያዎች መብላት” ስለሚወዱ እንደሆነ ሽፒገል ገልጿል። አክሎም “እርግጥ የካሳ ክፍያው ሊያሻቅብ የቻለበት ምክንያት የራዲዮአክቲቭ ብክለት ስለጨመረ ሳይሆን በጀርመን የዱር አሳማዎች ቁጥር እጅግ ስላደገ ነው” ብሏል። ተመራማሪዎች የጨረሩ ችግር ሌላ 50 ዓመት ሳይቆይ እንደማይቀር ይናገራሉ።