እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ተብሎ ሊጠራ የሚችል ሰው ይኖራልን? የአንድን ሰው ታላቅነት የምትመዝኑት በምኑ ነው? በወታደራዊ ስልት አዋቂነቱ ነው? በአካላዊ ጥንካሬው ነው? ወይስ በአእምሮ ችሎታው?
የታሪክ ምሁር የሆኑት ኤች ጂ ዌልስ የአንድ ሰው ታላቅነት ‘ትቷቸው በሚያልፋቸው ነገሮችና በሌሎች ሰዎች አእምሮ ውስጥ በሚያሰርጻቸው ለረጅም ጊዜ ጸንተው የሚኖሩ አዳዲስ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች’ ሊመዘን ይችላል ብለዋል። ምንም እንኳ ዌልስ ክርስቲያን ነኝ የሚሉ ሰው ባይሆኑም “በዚህ መለኪያ ሲመዘን ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው ኢየሱስ ነው” ብለዋል።
ታላቁ እስክንድር፣ ሻርለማኝ (በሕይወት በነበረበት ዘመንም እንኳ “ታላቁ” ተብሎ ለመጠራት የበቃ ሰው ነው) እና ናፖልዮን ቦነፓርት ኃያላን ገዥዎች ነበሩ። አስፈሪ ግርማቸው በሚገዟቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሆኖም ናፖልዮን “ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል መገኘት ሳያስፈልገው ተገዥዎቹን ለማዘዝና ለመግዛት ችሏል” እንዳለ ይነገራል።
ኢየሱስ ከፍተኛ ኃይል ባላቸው ትምህርቶቹና ከእነዚህ ትምህርቶች ጋር በሚጣጣመው አኗኗሩ ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ያህል በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ችሏል። አንድ ደራሲ እንዲህ ሲሉ ነጥቡን ጥሩ አድርገው ገልጸውታል:- “በምድር ላይ የተነሱት የጦር ሠራዊቶችና የባሕር ኃይሎች በሙሉ፣ በምድር ላይ የነገሡ ነገሥታትና ለውይይት የተቀመጡ ምክር ቤቶች በሙሉ በአንድ ላይ ቢጠቃለሉ የኢየሱስን ያህል የሰው ልጆችን ሕይወት አልለወጡም።”
የተረጋገጠ ታሪክ ያለው ሰው
ሆኖም የሚያስገርመው አንዳንዶች ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው አይደለም፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የፈለሰፉት የፈጠራ ሰው ነው ማለታቸው ነው። በብዙዎች ዘንድ የተከበሩት የታሪክ ምሁር ዊል ዱራንት ለእንዲህ ዓይነቱ ጥርጣሬ መልስ ሲሰጡ የሚከተለውን የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርበዋል:- “በአንድ ትውልድ ውስጥ የኖሩ ጥቂት ተራ ሰዎች ይህን የመሰለ ከፍተኛ የመለወጥ ኃይልና ተወዳጅነት ያለው ሰው፣ ይህን የመሰለ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃና ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለመፈልሰፍ ከቻሉ በወንጌሎች ውስጥ ከተጻፉት ተአምራት በሙሉ የበለጠ እምነት የሚጠይቅ ትልቅ ተአምር ይሆናል።”
በሕይወት ኖሮ የማያውቅ ሰው በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ይህን ያህል ታላቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላልን? ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለታሪክ ምሁራን የተዘጋጀ የዓለም ታሪክ (The Historians’ History of the World) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “[ኢየሱስ] ያደረጋቸው ነገሮች በታሪክ ላይ ያስከተሉት ውጤት በዓለማዊ አመለካከት ብቻ እንኳን ሲታይ ማንኛውም ሌላ የታሪክ ሰው ካደረገው እጅግ የሚልቅ ነው። በዓለም ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ በደረሱ አገሮች ዘንድ እውቅና ያገኘ አዲስ ዘመን የጀመረው ከኢየሱስ ልደት ወዲህ ነው።”
አዎን፣ እስቲ ቆም ብለህ አስበው። ሌላው ቀርቶ በዛሬው ጊዜ የዘመናት ቀመር እንኳ ኢየሱስ ተወልዶበታል ተብሎ በሚታሰበው ዓመት ላይ የተመሠረተ ነው። “ከዚያ ዓመት በፊት ያሉት ዓመታት ዓመተ ዓለም ወይም ከክርስቶስ ልደት በፊት ተብለው ይጠራሉ” ሲል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ይገልጻል። “ከዚያ ዓመት በኋላ ያሉት ዓመታት ደግሞ ዓመተ ምሕረት ወይም አኖ ዶሚኒ (በጌታ ዘመን) ተብለው ይጠራሉ።”
ይሁን እንጂ ተቺዎች ስለ ኢየሱስ የሚታወቀው ነገር ሁሉ ተጽፎ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፤ በዚያ ዘመን ስለ እርሱ የተጻፈ ሌላ የታሪክ ማስረጃ የለም ይላሉ። ኤች ጂ ዌልስም እንኳ “የጥንቶቹ የሮማ ታሪክ ጸሐፊዎች ኢየሱስን ፈጽሞ አልጠቀሱትም፤ በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የታሪክ መዛግብት ስለ እሱ አላወሱም” ሲሉ ጽፈዋል። ግን ይህ እውነት ነውን?
ምንም እንኳ ብዙ ባይሆንም የጥንት ዓለማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጽፈዋል። በብዙዎች ዘንድ የተከበረው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ ኮርኔልየስ ታሲተስ “[ክርስቲያን] የሚለው ስም ገዥው ጴንጤናዊ ጲላጦስ በጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት ካስገደለው ክርስቶስ ከተባለ ሰው የተወሰደ ነው” ሲል ጽፏል። ስዌቶኒየስና ታናሹ ፕሊኒ የተባሉት የዘመኑ የሮማ ታሪክ ጸሐፊዎችም ክርስቶስን ጠቅሰው ጽፈዋል። በተጨማሪም የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁዳውያን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ፍላቪየስ ጆሴፈስ ስለ ያዕቆብ ሲጽፍ “ክርስቶስ የተባለው የኢየሱስ ወንድም” ብሎ ገልጾታል።
በዚህም ምክንያት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይደመድማል:- “በጥንት ዘመናት የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳ ኢየሱስ እርግጠኛ ታሪክ ያለው ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ እነዚህ ገለልተኛ የሆኑ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ሰዎች የኢየሱስን ታሪክ እርግጠኛነት አለበቂ ምክንያት መጠራጠር የጀመሩት በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ፣ በ19ኛው መቶ ዘመንና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።”
እርግጥ፣ ስለ ኢየሱስ የሚታወቁት ነገሮች ሁሉ የተዘገቡት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ተከታዮቹ ነው። የእነዚህ ሰዎች ሪፖርት ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በጻፏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት ወንጌሎች ውስጥ ይገኛል። በእነዚህ ወንጌሎች ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን ይላሉ?
በእርግጥ ኢየሱስ ማን ነበር?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኢየሱስ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችም ይህ ጥያቄ መጥቶባቸው ነበር። ኢየሱስ በነፋስ የተናወጠውን ባሕር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ገስጾ ጸጥ ሲያሰኝ በተመለከቱ ጊዜ በጣም ተደንቀው “ይህ ማን ነው?” ብለው ነበር። ከዚያ ቆየት ብሎም በሌላ ጊዜ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” ሲል ጠይቋቸዋል።— ማርቆስ 4:41፤ ማቴዎስ 16:15
አንተ ይህ ጥያቄ ቢቀርብልህ ምን ብለህ ትመልስ ነበር? ኢየሱስ በእርግጥ እግዚአብሔር ነውን? በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ይላሉ። በዘመኑ የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ግን ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው የሚል እምነት አልነበራቸውም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት ኢየሱስ ላቀረበው ጥያቄ መልስ ሰጥቷል።— ማቴዎስ 16:16
ኢየሱስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አያውቅም፤ ከዚህ ይልቅ ይመጣል ተብሎ የተስፋ ቃል የተሰጠበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ ተናግሯል። በተጨማሪም “የእግዚአብሔር ልጅ” ነኝ አለ እንጂ እግዚአብሔር ነኝ አላለም። (ዮሐንስ 4:25, 26፤ 10:36) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ዓይነት ተራ ሰው ነበር አይልም። ማንኛውም ነገር ከመፈጠሩ በፊት በአምላክ የተፈጠረ በመሆኑ በጣም ልዩ የሆነ ሕያው አካል ነው። (ቆላስይስ 1:15) ኢየሱስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ግዑዛን ነገሮች ከመፈጠራቸው በፊት እንኳን ሳይቀር ለብዙ ቢልዮን ዓመታት መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ ይኖር የነበረ ከመሆኑም በላይ ታላቅ ፈጣሪ ከሆነው ከአባቱ ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አለው።— ምሳሌ 8:22, 27-31
ከዚያም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ አምላክ የልጁን ሕይወት ወደ አንዲት ሴት ማኅፀን አዛወረው። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ በተለመደው መንገድ ከሴት የተወለደ የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ ሆነ። (ገላትያ 4:4) ኢየሱስ በማኅፀን ውስጥ እያደገ በነበረበት ጊዜም ሆነ ከተወለደ በኋላ በነበረው የልጅነት ዘመኑ አምላክ ምድራዊ ወላጆቹ እንዲሆኑ የመረጣቸው ሰዎች ጥገኛ ነበር። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሙሉ ሰው ሆነ፤ ቀደም ሲል በሰማይ ከአምላክ ጋር የነበረውን የቅርብ ግንኙነትም ሙሉ በሙሉ ማስታወስ እንዲችል ተደረገ።— ዮሐንስ 8:23፤ 17:5
ከሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው እንዲሆን ያደረገው ነገር
ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን በሚገባ በመምሰሉ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ለመሆን በቅቷል። ኢየሱስ ታማኝ ልጅ በመሆን ፍጹም በሆነ መንገድ አባቱን በመምሰሉ ለተከታዮቹ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ሊል ችሏል። (ዮሐንስ 14:9, 10) በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው አባቱ በምድር ላይ ቢኖር ኖሮ ሊያደርግ ይችል የነበረውን ነገር ሁሉ አድርጓል። ኢየሱስ “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ . . . ታውቃላችሁ” ሲል ገልጿል። (ዮሐንስ 8:28) ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳለፈውን ሕይወት ስናጠና አምላክ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ግልጽ ግንዛቤ እናገኛለን ማለት ነው።
በመሆኑም ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም” ቢልም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ሲል ሊጽፍ ችሏል። (ዮሐንስ 1:18፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ዮሐንስ እንዲህ ሊል የቻለው የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ በሆነው በኢየሱስ ላይ ባያቸው ነገሮች አማካኝነት የአምላክን ፍቅር ስላወቀ ነበር። ኢየሱስ ርኅሩኅ፣ ደግ፣ ትሑትና በቀላሉ የሚቀረብ ነበር። ደካሞችና የተጨቆኑ ሰዎች ከእሱ ጋር ሲሆኑ መንፈሳቸው ይረጋጋ ነበር። ሁሉም ዓይነት ሰዎች ማለትም ወንዶች፣ ሴቶች፣ ልጆች፣ ሀብታሞች፣ ድሆች፣ ባለሥልጣኖች አልፎ ተርፎም ኃጢአተኞች ከእሱ ጋር ሲሆኑ አይሸማቀቁም ነበር። እሱን የሚጠሉት ክፉ ልብ የነበራቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ።
ኢየሱስ ተከታዮቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱ ማስተማር ብቻ ሳይሆን እንዴት መዋደድ እንዳለባቸው ጭምር ጠቁሟቸዋል። “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:34 የ1980 ትርጉም) ከሐዋርያቱ አንዱ ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ ከእውቀት ሁሉ ይበልጣል’ ሲል ገልጿል። (ኤፌሶን 3:19 NW) አዎን፣ ክርስቶስ ያሳየው ፍቅር ከቀለም ትምህርት እውቀት የላቀ ነው፤ ሌሎች ለዚህ ፍቅር ምላሽ እንዲሰጡ “ግድ” ይላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:14) ስለዚህ ኢየሱስን እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው ያደረገው ዋነኛው ነገር ከሁሉ የላቀ የፍቅር ምሳሌው ነው። ፍቅሩ ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ ነክቷል፤ በሕይወታቸውም ላይ በጎ ተጽእኖ አሳድሯል።
ሆኖም አንዳንዶች ‘የመስቀል ጦርነቶች፣ ኢንኩዊዝሽን (የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን የምትላቸውን ለመደምሰስ ያካሄደችው አረመኔያዊ ምንጠራ) እንዲሁም ክርስቲያን ነን እያሉ በተለያዩ ጎራዎች ተሰልፈው እርስ በርስ በሚገዳደሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተካሄዱት ጦርነቶች በክርስቶስ ስም የተፈጸሙ አይደሉምን?’ የሚል ተቃውሞ ሊያስነሱ ይችላሉ። ሆኖም እነሱ የኢየሱስ ተከታዮች ነን ይበሉ እንጂ እውነታው አለመሆናቸውን የሚያሳይ ነው። የኢየሱስ ትምህርትና አኗኗር የእነሱን ድርጊቶች የሚጻረር ነው። ሌላው ቀርቶ የሂንዱ እምነት ተከታይ የነበሩት ሞሃንዳስ ጋንዲ እንኳን “ክርስቶስን እወደዋለሁ፤ ክርስቲያኖች ግን የክርስቶስን አኗኗር ስለማይከተሉ እጠላቸዋለሁ” ብለው ለመናገር ተገደዋል።
ስለ እሱ በመማር የሚገኝ ጥቅም
በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና አገልግሎት ከማጥናት የበለጠ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል ጥናት አይኖርም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኢየሱስን . . . በትኩረት ተመልከቱ” ሲል አጥብቆ መክሯል። “[ስለ እርሱ] በአንክሮ አስቡ።” አምላክ ራሱም ስለ ልጁ በተናገረ ጊዜ “እርሱን ስሙት” ሲል አዟል። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው ይህ መጽሐፍ ይህን ማድረግ እንድትችሉ ይረዳችኋል።— ዕብራውያን 12:2, 3 NW፤ ማቴዎስ 17:5፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
ኢየሱስ የሰጣቸውን ንግግሮች፣ ምሳሌዎችና ያደረጋቸውን ተአምራት ጨምሮ በአራቱ ወንጌሎች ውስጥ የሰፈረውን በምድራዊ ሕይወቱ ወቅት የተከናወነውን እያንዳንዱን ነገር ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል። በተቻለ መጠን እያንዳንዱን ነገር በተፈጸመበት የጊዜ ቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ተሞክሯል። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ ምዕራፉ የተመሠረተባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይገኛሉ። እነዚህን ጥቅሶች እንድታነብና ለቀረቡት የክለሳ ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጥ እናበረታታሃለን።
የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑ አንድ ምሁር በቅርቡ እንዲህ ብለዋል:- “ባለፉት ሀያ ዓመታት ስለ ኢየሱስ የተጻፈው ጽሑፍ ቀደም ሲል በነበሩት ሁለት ሺህ ዓመታት ከተጻፈው ይበልጣል።” ሆኖም የወንጌል ዘገባዎችን በግለሰብ ደረጃ መመርመሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ምክንያቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በአሁኑ ጊዜ የኢየሱስን ታሪክ የሚያጠና ሰው ስለ ኢየሱስና ስለ ወንጌሎች በሚናገሩ እርስ በርሳቸው በሚጋጩ ብዙ ጽንሰ ሐሳቦች ስለተዋከበ እነዚህን መሠረታዊ ምንጮች ማለትም ወንጌሎችን የማጥናቱን ጉዳይ ቸል ብሎታል።”
ያለ ምንም አድሎአዊ ጥላቻ የወንጌል ታሪኮችን በጥልቀት ከመረመርክ በኋላ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የላቁ ክንውኖች የተፈጸሙት የናዝሬቱ ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ ለመስጠት ወደዚች ምድር በመጣበት በሮማው አውግስጦስ ቄሣር የግዛት ዘመን እንደነበር ማስረጃዎቹ ያሳምኑሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።