የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 11—1 ነገሥት
ጸሐፊው:- ኤርምያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌምና ይሁዳ
ተጽፎ ያለቀው:- 580 ከዘአበ
የሚሸፍነው ጊዜ:- 1040 ገደማ-911 ከዘአበ
ዳዊት የተቀዳጀው ድል የእስራኤልን ግዛት አምላክ እስከ ሰጣቸው ወሰን ማለትም በሰሜን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንስቶ በደቡብ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ እንዲስፋፋ አድርጓል። (2 ሳሙ. 8:3፤ 1 ነገ. 4:21) ዳዊት ሞቶ ልጁ ሰሎሞን በፋንታው በነገሠበት ወቅት “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።” (1 ነገ. 4:20) ሰሎሞን ሕዝቡን በጥበብ አስተዳድሯል። የእርሱ ጥበብ ከጥንቶቹ ግሪኮች ጥበብ እጅግ የላቀ ነበር። ለይሖዋ ዕጹብ ድንቅ የሆነ ቤተ መቅደስ ገንብቷል። ይሁን እንጂ ሰሎሞንም ራሱ ለሐሰት አማልክት ለሚቀርበው አምልኮ ተንበርክኳል። ሰሎሞን ሲሞት መንግሥቱ ለሁለት ከመከፈሉም በላይ በሁለቱ ተቀናቃኝ መንግሥታት በእስራኤልና በይሁዳ በተከታታይ የነገሡት ክፉ ነገሥታት የተከተሉት የጥፋት ጎዳና ልክ ሳሙኤል አስቀድሞ እንደተነበየው ሕዝቡን ችግር ላይ ጥሎታል። (1 ሳሙ. 8:10-18) የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት ሰሎሞን ከሞተ በኋላ በይሁዳና በእስራኤል ላይ ከነገሡት 14 ነገሥታት መካከል በይሖዋ ፊት ቅን የሆነውን ነገር ያደረጉት 2 ብቻ ናቸው። ታዲያ ይህ ዘገባ “በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” ሊባል ይቻላልን? መጽሐፉ ከሚሰጠው ማሳሰቢያ፣ በውስጡ ከሚገኙት ትንቢቶችና ለመጪው ነገር ጥላ የሚሆኑ ነገሮች እንዲሁም ‘የቅዱስ ጽሑፉ’ ዋነኛ ጭብጥ ከሆነው የአምላክ መንግሥት ጋር ካለው ተዛማጅነት መረዳት እንደምንችለው “በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ” መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።
2 የነገሥት መጽሐፍ መጀመሪያ የተዘጋጀው በአንድ ጥቅልል ወይም ጥራዝ ሲሆን በዕብራይስጥ ሜላኪም (ነገሥት) ተብሎ ይጠራ ነበር። የሰፕቱጀንት ተርጓሚዎች ባሲሎዮን “ንጉሣዊ መንግሥታት” ብለው ይጠሩት የነበረ ሲሆን ለአያያዝ አመቺ እንዲሆን በማሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት ጥቅል ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው። ከጊዜ በኋላም ሦስተኛና አራተኛ ነገሥት ተብለው ይጠሩ ጀመር። የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስያሜ እስከ አሁን ድረስ ይጠቀምበታል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው አንደኛና ሁለተኛ ነገሥት ተብለው ይታወቃሉ። ጸሐፊው እንደ ምንጭ የተጠቀመባቸውን የቀድሞ መዛግብት በስም መጥቀሳቸው የነገሥት መጻሕፍትን ከአንደኛና ከሁለተኛ ሳሙኤል መጻሕፍት የተለዩ ያደርጋቸዋል። ጸሐፊው በሁለቱም መጽሐፍ ውስጥ ‘የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍን’ 15 ጊዜ፣ ‘የእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍን’ 18 ጊዜ የጠቀሰ ሲሆን ‘የሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍንም’ ጠቅሷል። (1 ነገ. 15:7፤ 14:19፤ 11:41) እነዚህ የጥንት መዛግብት በአሁኑ ጊዜ ፈጽሞ የማይገኙ ቢሆንም እንኳ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተዘጋጁት ማለትም ጠቃሚ ታሪክ የያዙት አንደኛና ሁለተኛ ነገሥት እስከ ጊዜያችን ድረስ ተጠብቀው ቆይተዋል።
3 የነገሥትን መጽሐፍ የጻፈው ማን ነው? መጻሕፍቱ ነቢያት ባከናወኑት ሥራ በተለይ ደግሞ ኤልያስና ኤልሳዕ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ጸሐፊው የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ያመለክታል። የቋንቋው፣ የተቀናበረበት መንገድና የአጻጻፍ ስልቱ ከኤርምያስ መጽሐፍ ጋር መመሳሰል ጸሐፊያቸው አንድ እንደሆነ ያመለክታል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ የማይገኙ በነገሥትና በኤርምያስ ውስጥ ብቻ የሚገኙ በርካታ የዕብራይስጥ ቃላትና መግለጫዎች አሉ። ይሁን እንጂ የነገሥትን መጽሐፍ የጻፈው ኤርምያስ ከሆነ ስለ እርሱ ያልጠቀሰው ለምንድን ነው? ያከናወናቸው ሥራዎቹ በስሙ በሚጠራው መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሰው የነበረ በመሆናቸው በነገሥት መጽሐፍ ውስጥ ማስፈሩ አስፈላጊ አልነበረም። ከዚህም በላይ የነገሥት መጽሐፍ የተጻፈው ይሖዋንና አምልኮቱን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንጂ የኤርምያስን ዝና ለማጋነን አልነበረም። እርግጥ ነው፣ በአብዛኛው የነገሥት መጻሕፍትና ኤርምያስ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ ሲሆን በአንዱ ውስጥ የማይገኝ ነገር በሌላው ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ተመሳሳይ ዘገባዎች እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል 2 ነገሥት 24:18–25:30ን እና ኤርምያስ 39:1-10ን፤ 40:7–41:10፤ 52:1-34ን መመልከት እንችላለን። ኤርምያስ አንደኛና ሁለተኛ ነገሥትን እንደጻፈ የአይሁድ ወግም ያረጋግጣል። ሁለቱንም መጻሕፍት ማዘጋጀት የጀመረው በኢየሩሳሌም እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ሁለተኛው መጽሐፍ ደግሞ በ580 ከዘአበ አካባቢ በግብፅ ተጽፎ ያለቀ ይመስላል። ምክንያቱም በዘገባው መደምደሚያ ላይ በዚህ ዓመት የተፈጸሙ ክንውኖች ተጠቅሰዋል። (2 ነገ. 25:27) የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ የእስራኤልን ታሪክ የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ካቆመበት አንስቶ ኢዮሣፍጥ እስከ ሞተበት እስከ 911 ከዘአበ ድረስ ያለውን ክንውን ይተርካል።—1 ነገ. 22:50
4 አንደኛ ነገሥት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በትክክለኛው ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል። ከዚህም በላይ በአንደኛ ነገሥት ውስጥ የሰፈሩት ክንውኖች በግብፅ እና በአሦር ታሪኮች ውስጥም ተረጋግጠዋል። አርኪኦሎጂም በመጽሐፉ ውስጥ ለሚገኙት በርካታ አባባሎች ድጋፍ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል ኪራም ለሰሎሞን ቤተ መቅደስ መሥሪያ የናሱን ቅርጽ ያስያዘው “በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጸርታን መካከል” እንደሆነ በ1 ነገሥት 7:45, 46 ላይ እናነባለን። አርኪኦሎጂስቶች በጥንቷ ሱኮት አካባቢ ባደረጉት ቁፋሮ በዚህ ቦታ የማቅለጥ ሥራ ይሠራ እንደነበረ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን አግኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የግብፁ ንጉሥ ሼሾንክ (ሺሻቅ) በይሁዳ ላይ ያደረገውን ወረራ በኩራት የሚዘክር ውቅር ምስል በካርናክ (በጥንቷ ቲቤስ) ቤተ መቅደስ ግድግዳ ላይ ይታያል። ይህ ወረራ በ1 ነገሥት 14:25, 26 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል።
5 ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ከመጽሐፉ መጥቀሳቸውና ፍጻሜ ያገኙት ትንቢቶቹ አንደኛ ነገሥት ትክክለኛ መሆኑን የሚደግፉ ናቸው። ኢየሱስ በኤልያስ ዘመን የነበረው ክንውንና በሰራፕታ የነበረች መበለት ሁኔታ በትክክል የተፈጸመ መሆኑን ተናግሯል። (ሉቃስ 4:24-26) ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስን በማስመልከት ሲናገር “ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው” ብሏል። (ማቴ. 11:13, 14) እዚህ ላይም ኢየሱስ ሚልክያስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከተናገረበት የትንቢት መጽሐፍ ጠቅሶ መናገሩ ነበር:- “እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።” (ሚል. 4:5) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ስለ ሰሎሞን እና ስለ ደቡቧ ንግሥት የሚናገረውን ታሪክ በመጥቀስ ይህ መጽሐፍ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ማቴ. 6:29፤ 12:42፤ ከ1 ነገሥት 10:1-9 ጋር አወዳድር።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
23 በአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ ከሚገኘው መለኮታዊ መመሪያ ከፍተኛ ጥቅም ይገኛል። በመጀመሪያ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ ይዞ የሚገኘውን የጸሎትን ሁኔታ ተመልከት። ሰሎሞን በእስራኤል ንጉሥ መሆን የሚያስከትልበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ባሰበ ጊዜ ልክ እንደ ሕፃን በትሕትና ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ማስተዋልና ታዛዥ ልብ እንዲያገኝ ጸልዮአል፤ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ጥበብ ከማግኘቱም በላይ ይሖዋ ብልጥግናና ክብር ሰጥቶታል። (3:7-9, 12-14) ዛሬም ቢሆን በይሖዋ አገልግሎት ጥበብና መመሪያ ለማግኘት በትሕትና የምናቀርበው ጸሎት በእርግጥም ሰሚ እንደሚያገኝ ሙሉ እምነት ይኑረን! (ያዕ. 1:5) ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ ለአምላክ አገልግሎት ሲወሰን እንዳደረገው ለይሖዋ ጥሩነት የጠለቀ አድናቆት በማሳየት አዘውትረን ከልባችን የምንጸልይ እንሁን! (1 ነገ. 8:22-53) ኤልያስ ፈተና በገጠመው ጊዜና አጋንንት አምላኪ ከሆነ ብሔር ጋር ፊት ለፊት በተጋፈጠ ጊዜ እንዳቀረበው ዓይነት ጸሎት እኛም የምናቀርበው ጸሎት በይሖዋ ላይ ፍጹም እምነትና ትምክህት ያለን መሆኑን በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጥ ይሁን! ይሖዋ በጸሎት ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ በልግስና ይሰጣል።—1 ነገ. 17:20-22፤ 18:36-40፤ 1 ዮሐ. 5:14
24 በተጨማሪም በይሖዋ ፊት ራሳቸውን ለማዋረድ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የደረሰባቸው ነገር ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይገባል። አዎን፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል”! (1 ጴጥ. 5:5) በቲኦክራሲያዊ መንገድ ይሖዋ የሚሰጠውን ሹመት መጋፋት እንደሚችል ሆኖ የተሰማው አዶንያስ (1 ነገ. 1:5፤ 2:24, 25)፤ የተወሰነለትን ክልል ጥሶ ቢሄድም መመለስ እንደሚችል ሆኖ የተሰማው ሳሚ (2:37, 41-46)፤ በእርጅናው ዘመን ታዛዥ ሳይሆን በመቅረቱ ምክንያት ከይሖዋ ቁጣ የመጣበት ሰሎሞን (11:9-14, 23-26) እንዲሁም የተከተሉት የሃሰት ሃይማኖት ወጥመድ የሆነባቸው የእስራኤል ነገሥታት ተጠቅሰዋል። (13:33, 34፤ 14:7-11፤ 16:1-4) ከዚህም በላይ ከአካብ ዙፋን በስተጀርባ ከፍተኛ ግፊት ታሳድር የነበረችው ክፉ የመጎምጀት ስሜት የተጠናወታት ኤልዛቤልም አለች። መጥፎ ምሳሌነቷ ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ በትያጥሮን የሚገኘውን ጉባኤ ለማስጠንቀቅ ተጠቅሷል። “ዳሩ ግን:- ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ።” (ራእይ 2:20) የበላይ ተመልካቾች የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅና እንደ ኤልዛቤል ያሉ ተጽዕኖዎችን ማጽዳት አለባቸው!—ከሥራ 20:28-30 ጋር አወዳድር።
25 በአንደኛ ነገሥት ውስጥ የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው የይሖዋን ትንቢት የመናገር ችሎታ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል ኢዮርብዓም በቤቴል የገነባውን መሠዊያ የሚያፈራርሰው ኢዮስያስ እንደሚሆን 300 ከሚበልጡ ዓመታት ቀደም ብሎ የተነገረ አንድ አስደናቂ ትንቢት አለ። ልክ እንደተባለውም ኢዮስያስ ትንቢቱን ፈጽሟል! (1 ነገ. 13:1-3፤ 2 ነገ. 23:15) ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ሰሎሞን ከሠራው ከይሖዋ ቤት ጋር በተያያዘ የተነገሩት ትንቢቶች ናቸው። ይሖዋ ወደ ሃሰት አማልክት ዞር ካሉ እስራኤላውያንን ከምድር እንደሚያጠፋቸውና ለስሙ የቀደሰውንም ቤት እንደሚተወው ለሰሎሞን ነግሮታል። (1 ነገ. 9:7, 8) ይህ ትንቢት ምንም ዝንፍ ሳይል ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ማግኘቱን 2 ዜና መዋዕል 36:17-21 ላይ እናነባለን። ከዚህም በላይ ታላቁ ሄሮድስ በዚያው ቦታ ላይ የሠራው ኋለኛው ቤተ መቅደስ በተመሳሳይ ምክንያት ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚገጥመው ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:6) ይህም ቢሆን ፍጻሜውን አግኝቷል! እነዚህን መቅሰፍቶችና መቅሰፍቶቹ የደረሱበትን ምክንያት ማስታወስ ይኖርብናል። በእውነተኛው አምላክ መንገዶችም ሁልጊዜ መጓዝ እንዳለብን ሊያስታውሱን ይገባል።
26 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፣ የሕዝቡን ብልጥግናና ዕጹብ ድንቅ የሆነውን የይሖዋን ቤት ጨምሮ የመንግሥቱን ክብር ለማየት ስትል ከምትኖርበት ከሩቅ አገር መጥታለች። ሆኖም ሰሎሞን “ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!” በማለት ለይሖዋ ሐቁን ተናግሯል። (1 ነገ. 8:27፤ 10:4-9) ይሁን እንጂ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ክርስቶስ ኢየሱስ በተለይ በታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ተመልሶ ከሚቋቋመው እውነተኛ አምልኮ ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ የግንባታ ሥራ ለማከናወን መጣ። (ዕብ. 8:1-5፤ 9:2-10, 23) ከሰሎሞን ለሚበልጠው ለክርስቶስ “የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ” በማለት ይሖዋ የተናገረው ተስፋ ተፈጽሞለታል። (1 ነገ. 9:5፤ ማቴ. 1:1, 6, 7, 16፤ 12:42፤ ሉቃስ 1:32) የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ መንፈሳዊው የይሖዋ ቤተ መቅደስ የተጎናጸፈውን ክብር እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሚመራው የይሖዋ መንግሥት ጥበብ በሞላበት አስተዳደር ሥር ራሳቸውን የሚያስገዙ ሁሉ የሚያገኙትን ብልጽግና፣ ደስታና ሐሴት ከወዲሁ ይጠቁማል። ለእውነተኛው አምልኮ አስፈላጊነትና በዘሩ ለሚተዳደረው ድንቅ ለሆነው የአምላክ መንግሥት ዝግጅት ያለን አድናቆት እያደገ ይሂድ!