የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተማሪ አድርገን ስንቀበልህ ደስ ይለናል
በምድር ዙሪያ ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በየሳምንቱ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና እየተጠቀሙ ነው። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ አዲሶች ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ለብዙ ዓመታት በትምህርት ቤቱ ሲካፈሉ ቆይተዋል። ይህ ትምህርት ቤት በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ጉባኤዎች ውስጥ ይካሄዳል። በየትኛውም የምድር ክፍል የሥልጠናው ፕሮግራም አንድ ዓይነት ነው። የተለያየ እድሜ፣ ዘር እና የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰዎች ያለ አንዳች ክፍያ ከዚህ ቲኦክራሲያዊ የሥልጠና ፕሮግራም በመጠቀም ላይ ናቸው።
ትምህርት ቤቱ በ1943 ሲጀመር የትምህርት ቤቱን ዓላማ በሚመለከት እንዲህ የሚል ሐሳብ ተሰጥቶ ነበር:- ‘የአምላክን ቃል ሰምተው በዚያ ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳዩትን “የታመኑ ወንዶች” በሙሉ፣ ሌሎችን ለማስተማር የተዘጋጁና ስለ ተስፋቸው ለመስበክ በተሻለ መንገድ የታጠቁ እንዲሆኑ ለመርዳት የታሰበ ነው።’ (የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ኮርስ ገጽ 4) ይህ የትምህርት ቤቱ ዓላማ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም።
አምላክ የሰጠንን አንደበት በመጠቀም ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ መልካም ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (መዝ. 150:6) እንዲህ ስናደርግ የሰማያዊ አባታችንን ልብ ደስ እናሰኛለን። ይህም እርሱ ላሳየን ጥሩነትና ፍቅር አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ክርስቲያኖች “ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” እንዲያቀርቡ መበረታታታቸው ያለ ምክንያት አይደለም። (ዕብ. 13:15) ከአምላክ ያገኘኻቸውን ስጦታዎች ተጠቅመህ በተሻለ ብቃት እርሱን እንድታወድስ ለመርዳት በማሰብ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተማሪ አድርገን ስንቀበልህ ደስ ይለናል።
በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሌሎች የማንበብ ችሎታ እንዲሁም የመናገርና የማስተማር ጥበብ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ነገሮች ቢሆኑም ከዚህ ትምህርት ቤት የምናገኘው ሥልጠና በዚህ ብቻ የተወሰነ ነው ማለት አይደለም። በትምህርት ቤቱ ስትሳተፍ የግል ንባብ፣ የማዳመጥና የማስታወስ፣ የማጥናት፣ ምርምር የማድረግ፣ ነጥቦችን የማጤንና በሥርዓት የማደራጀት፣ ከሰዎች ጋር የመወያየት፣ ለጥያቄዎች መልስ የመስጠት እንዲሁም ሐሳብን በጽሑፍ የመግለጽና የመሳሰሉትን ጠቃሚ ችሎታዎች ማዳበር ትችላለህ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚቀርቡት ክፍሎች በመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት እየቀሰምህ ስትሄድ የእርሱን ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ትጀምራለህ። ይህ ደግሞ በየትኛውም የኑሮ ዘርፍ እጅግ ጠቃሚ ነው! ዊልያም ሊዮን ፌልፕስ የተባሉት የዩኒቨርሲቲ ምሁር የአምላክ ቃል ያለውን ጥቅም በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቆ የሚያውቅ ከሆነ በእርግጥም የተማረ ነው ሊባል ይችላል። . . . የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ከሌለው የኮሌጅ ምሩቅ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቅ የኮሌጅ ትምህርት የሌለው ሰው እንደሚበልጥ አምናለሁ።”
ከሥልጠናው ሙሉ ጥቅም ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
እርግጥ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚቀርበው ሥልጠና ሙሉ ጥቅም ለማግኘት በግልህ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት አጋሩ የነበረውን ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቦታል:- “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር።” (1 ጢሞ. 4:15) አንተ ልታደርጋቸው የሚገቡህ ነገሮች ምንድን ናቸው?
በተቻለ መጠን በየሳምንቱ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ጥረት አድርግ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለውን ይህን መማሪያ መጽሐፍ በሚገባ ተጠቀምበት። በመጀመሪያው ገጽ ላይ በሚገኘው “የተማሪው ስም” በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ስምህን ጻፍ። በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ ስትገኝ መጽሐፉ አይለይህ። ይህ መማሪያ መጽሐፍ ልታሻሽል የምትፈልጋቸውን ነጥቦች የምትጽፍበት ክፍት ቦታም አለው። ልትሠራባቸው የሚገቡ ጠቃሚ ነጥቦች ስታገኝ አስምርባቸው። ከትምህርት ቤቱ የምታገኛቸውን ጠቃሚ ነጥቦች ሰፋ ባሉት ኅዳጎች ላይ መጻፍ ትችላለህ።
የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ለብቻው ተዘጋጅቶ ይሰጥሃል። ይህ ፕሮግራም ትምህርት ቤቱ እንዴት እንደሚካሄድ የሚገልጽ ዝርዝር ማብራሪያም ይኖረዋል። ፕሮግራሙን በቀላሉ ማግኘት እንድትችል መጽሐፉ ውስጥ ብታስቀምጠው የተሻለ ይሆናል።
ለሳምንታዊው የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ስትዘጋጅ ዋነኛው የመማሪያ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን አትዘንጋ። ለሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቅድሚያ ስጥ። ሌሎቹንም በትምህርት ቤቱ የሚቀርቡ ክፍሎች ቀደም ብሎ ማንበቡ ጠቃሚ ይሆናል።
የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም በሚካሄድበት ወቅት አድማጮች የሚሳተፉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። እነዚህን አጋጣሚዎች በሚገባ ተጠቀምባቸው። እንዲህ ያለው ተሳትፎ የሰማሃቸውን ነገሮች በማስታወስና በሕይወትህ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።
ሁሉም ተማሪዎች ለጉባኤው ንግግር ወይም ሠርቶ ማሳያ የማቅረብ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። እንዲህ ያለውን እያንዳንዱን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀምበት። በተመደበልህ የንግግር ባሕርይ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ ከልብህ ጥረት አድርግ። የሚሰጡህ ምክሮች ቀጣይ የሆነ እድገት እንድታደርግ የሚረዱ ናቸው። እነዚህን ምክሮች በደስታ ተቀበል። ልታሻሽላቸው የሚገቡ ነጥቦች ካሉና ምን ማድረግ እንዳለብህ ምክር ከተሰጠህ መጽሐፍህ ላይ ማስታወሻ ያዝ። አንድ ሰው የራሱ ድክመቶች ለራሱ ጉልህ ሆነው ስለማይታዩት የሚሰጥህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ፍቅራዊ ምክርና ሐሳብ ለእድገትህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ለብዙ ዓመታት በትምህርት ቤቱ ስትካፈል የቆየህ ቢሆንም እንኳ የምታገኘው ምክር በዚህ ረገድ እንደሚጠቅምህ የታወቀ ነው።—ምሳሌ 1:5
የምታደርገው እድገት ይበልጥ ፈጣን እንዲሆን ትፈልጋለህ? የግል ጥረትህ ከታከለበት እድገትህ ሊፋጠን ይችላል። እያንዳንዱን የተማሪ ክፍል አስቀድመህ አጥና። ክፍል የወሰደውን ሰው ተክቶ የሚያቀርብ ፈቃደኛ በሚጠየቅበት ጊዜ ክፍሉን የማቅረብ አጋጣሚ ይኖርሃል። ይህ ደግሞ ተሞክሮህን እያዳበርህ እንድትሄድ ይረዳሃል። ሌሎች ክፍል በሚያቀርቡበት ጊዜ እንዴት አድርገው እንደሚያቀርቡት በጥሞና ተከታተል። አንዳችን ከሌላው ትምህርት እናገኛለን።
ከዚህም በተጨማሪ ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ይህን የመማሪያ መጽሐፍ አስቀድመህ በግል በማጥናት እድገትህን ይበልጥ ማፋጠን ትችላለህ። በሚቀጥሉት 15 ጥናቶች ውስጥ ያሉትን ነጥቦች በሚገባ ከተረዳህ በኋላ ከገጽ 78 ጀምሮ ያለውን “የንግግርና የማስተማር ችሎታን ለማዳበር የሚረዳ ፕሮግራም” የሚለውን ክፍል ማጥናትህን ቀጥል። እያንዳንዱን ትምህርት ካጠናህ በኋላ መልመጃዎቹን ሥራ። ያገኘኸውን ትምህርት በአገልግሎትህ ተጠቀምበት። ይህም የአምላክን ቃል የመናገርና የማስተማር ችሎታህን በእጅጉ ሊያዳብርልህ ይችላል።
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምታገኘው ሥልጠና በሕይወትህ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ልትሰጠው ለሚገባ ነገር እንድትዘጋጅ ይረዳሃል። በሕይወት ልንኖር የቻልነው በአምላክ ፈቃድ በመሆኑ እርሱን ማወደሳችን የተፈጠርንበትን ዓላማ እንደተገነዘብን ያሳያል። ለይሖዋ አምላክ የሚቀርበው ውዳሴ ጥራት ያለው ሊሆን ይገባል። (ራእይ 4:11) በትምህርት ቤቱ ውስጥ የምናገኘው ሥልጠና ነገሮች ግልጽ ሆነው እንዲታዩን፣ በጥበብ እንድንመላለስ እንዲሁም አምላክ በመንፈሱ ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ድንቅ እውነት ለሌሎች በሚማርክ መንገድ እንድናካፍል በመርዳት ለይሖዋ የምናቀርበው ውዳሴ ጥራት ያለው እንዲሆን ያግዛናል።