በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት እና የኋላ ታሪካቸው ጥናት
ጥናት ቁጥር 9—አርኪኦሎጂና በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ
የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ የአርኪኦሎጂ ግኝቶችና ጥንታዊ የሆኑ ዓለማዊ የታሪክ መዛግብት ጥናት።
የመጽሐፍ ቅዱስ አርኪኦሎጂ የሚባለው በመሬት ውስጥ ተቀብረው በሚገኙ ጽሑፎች፣ መገልገያ መሣሪያዎች፣ ሕንፃዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች አማካኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበሩ ሕዝቦችና ክንውኖች የሚደረግ ጥናት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱ ቦታዎች የሚገኙ ጥንታዊ ፍርስራሾችን ወይም ቅርሳ ቅርሶችን ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ፣ ከፍተኛ አሰሳ ማድረግንና በብዙ ሚሊዮኖች ቶን የሚቆጠር አፈር ቆፍሮ ማውጣትን ይጠይቃል። ቅርሳ ቅርስ የሚባሉት በጥንት ዘመን ስለኖሩ ሰዎች እንቅስቃሴና አኗኗር ለማወቅ የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል የሸክላ ዕቃዎች፣ የሕንፃ ፍርስራሾች፣ የሸክላ ጽላቶች፣ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች፣ ሰነዶች፣ ሐውልቶችና በድንጋይ ላይ የተጻፉ ታሪካዊ ዘገባዎች ይገኙበታል።
2 በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ አርኪኦሎጂ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የጥናት መስክ ሆኖ ነበር፤ ተመራማሪዎች በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ሙዚየሞች በሚያደርጉላቸው የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደተጠቀሱ አገሮች ሄደው ምርምር ያደርጉ ነበር። በውጤቱም የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበሩ ነገሮች ለማወቅ የሚያስችሉ በርካታ መረጃዎችን ማግኘት ችለዋል። አንዳንዶቹ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጥቃቅን በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ረገድ ጭምር ትክክል መሆናቸውን በማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መሆኑን አረጋግጠዋል።
አርኪኦሎጂና የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
3 የባቤል ግንብ። መጽሐፍ ቅዱስ የባቤል ግንብ ግዙፍ የግንባታ ሥራ እንደነበር ይገልጻል። (ዘፍ. 11:1-9) የሚገርመው፣ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች አሁን ፍርስራሿ ብቻ በሚገኘው በጥንቷ ባቢሎን ውስጥና በዙሪያዋ በርካታ ዚጉራቶችን ወይም አናታቸው ላይ ቤተ መቅደሶች ያሏቸውና መወጣጫ ደረጃ የተሠራላቸው ፒራሚድ መሰል ሕንጻዎችን አግኝተዋል፤ ከእነዚህ መካከል በባቢሎን ቅጥሮች ውስጥ ይገኝ የነበረው የኢትመናንኪ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ይገኝበታል። እንዲህ ስላሉት ቤተ መቅደሶች የሚናገሩ ጥንታዊ ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ “ጫፉ እስከ ሰማያት ይደርሳል” የሚሉትን ቃላት የያዙ ናቸው። ንጉሥ ናቡከደነፆር “የኢትመናንኪን ጫፍ ሰማይ ጠቀስ አድርጌ ሠርቼዋለሁ” እንዳለ ይነገራል። አንድ የሸክላ ስባሪ ላይ የተገኘ ጽሑፍ እንዲህ ያለውን ዚጉራት አወዳደቅ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የዚህ ቤተ መቅደስ ግንባታ አማልክትን አስቀይሟል። አማልክት የተገነባውን ሁሉ በአንድ ምሽት አፈራረሱት። ሰዎቹን ወደተለያዩ ቦታዎች በታትነው ቋንቋቸውን ደበላለቁት። በዚህ መልኩ ግንባታውን አጨናገፉት።”a
4 በግዮን ምንጭ የነበሩት የውኃ ቦዮች። በ1867 ቻርለስ ዋረን የተባለ ሰው ከግዮን ምንጭ ተነስቶ ወደ ኮረብታው የሚሄድ የውኃ መስመር ኢየሩሳሌም አቅራቢያ አገኘ፤ ውኃው ወደ ላይ ወደ ዳዊት ከተማ የሚወጣበት ቦይ ተሠርቶለት ነበር። የዳዊት ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከተማዋ ዘልቀው የገቡት ይህን መንገድ ተከትለው ይመስላል። (2 ሳሙ. 5:6-10) ከግዮን ምንጭ የሚነሳው የውኃ መስመር ሙሉ በሙሉ በቁፋሮ የወጣው ከ1909-11 ባለው ጊዜ ነበር። በአማካይ 1.8 ሜትር ከፍታ ያለው አንዱ ትልቅ ቦይ የተሠራው ወጥ የሆነ ዓለት በመቦርቦር ሲሆን ርዝመቱ 533 ሜትር ነው። ይህ ቦይ ከግዮን ተነስቶ በታይሮፕያን ሸለቆ (ከተማዋ ውስጥ ያለ ነው) ወደሚገኘው የሰሊሆም ኩሬ የሚደርስ ሲሆን ቦዩን የሠራው ሕዝቅያስ እንደሆነ ይታመናል። ጠባብ በሆነው ቦይ ግድግዳ ላይ በጥንታዊ የዕብራይስጥ ፊደላት የተቀረጸ ጽሑፍ ተገኝቷል። ጽሑፉ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ዓለቱ የተቦረቦረው በዚህ መልኩ ነበር፦ . . . እያንዳንዱ ሰው ወደ ባልንጀራው አቅጣጫ እየቦረቦረ ነበር፤ በመካከላቸው ገና ሦስት ክንድ ርቀት እያለ ባልንጀራውን የሚጠራ ሰው ድምፅ [ተሰማ]። ምክንያቱም በዚያ ቦታ ላይ ዓለቱ በቀኝ [እና በግራ በኩል] የተነባበረ ነበር። ቦዩ ሲሠራ አንደኛው ቆፋሪ በአንድ በኩል ሌላኛው ቆፋሪ ደግሞ በሌላ በኩል (ዓለቱን) እየቆፈረ ወደ መሃል ይመጣ ነበር፤ ከዚያም ውኃው ከምንጩ እየተንዶለዶለ 1,200 ክንድ (533 ሜትር) ርቀት ላይ ወደሚገኘው ማጠራቀሚያ መውረድ ጀመረ። ከቆፋሪዎቹ ራስ በላይ ያለው ዓለት ከፍታው 100 ክንድ (45 ሜትር) ነበር።” ይህ ለዚያ ዘመን እንዴት ያለ አስደናቂ የምሕንድስና ሥራ ነው!b—2 ነገ. 20:20፤ 2 ዜና 32:30
5 የሺሻቅን ድል የሚያወሳ የተቀረጸ ምስል። የግብፅ ንጉሥ የነበረው ሺሻቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰባት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ንጉሥ ሮብዓም የይሖዋን ሕግ ስለተወ ይሖዋ በ993 ዓ.ዓ. ሺሻቅ ይሁዳን እንዲወር የፈቀደ ቢሆንም ከተማዋን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፋ አልፈቀደለትም። (1 ነገ. 14:25-28፤ 2 ዜና 12:1-12) እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ስለዚህ ወረራ የሚናገር ምንም ዘገባ አልተገኘም ነበር። በኋላ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሺሻቅ ብሎ ስለሚጠራው ፈርኦን (ሼሾንቅ ቀዳማዊ) የሚናገር አንድ ትልቅ ሰነድ ተገኘ። ይህ ሰነድ የተገኘው ካርናክ (የጥንቷ ቴብስ) ውስጥ ባለ አንድ ግዙፍ የግብፅ ቤተ መቅደስ ደቡባዊ ግድግዳ ላይ ሲሆን ግድግዳው ሥዕላዊ ጽሑፎችና ምስሎች ተቀርጸውበታል። በዚህ ግዙፍ ግድግዳ ላይ የግብፃውያን አምላክ አሞን በቀኝ እጁ የማጭድ ቅርጽ ያለው ሰይፍ ይዞ ይታያል። ምስሉ አሞን በሰንሰለት እጃቸውን የተጠፈሩ 156 የፓለስቲና እስረኞችን በግራ እጁ በገመድ እየጎተተ ለፈርዖን ሺሻቅ ሲያስረክበው ያሳያል። እያንዳንዱ እስረኛ አንድን ከተማ የሚወክል ሲሆን የከተሞቹ ስም በሥዕላዊ የአጻጻፍ ዘዴ ተጽፏል። በአሁኑ ጊዜ ሊነበቡና ማንነታቸው ሊታወቅ ከቻሉት ስሞች መካከል ራቢት (ኢያሱ 19:20)፤ ታአናክ፣ ቤትሼንና መጊዶ (ኢያሱ 17:11)፤ ሹነም (ኢያሱ 19:18)፤ ሬሆብ (ኢያሱ 19:28)፤ ሃፋራይም (ኢያሱ 19:19)፤ ገባኦን (ኢያሱ 18:25)፤ ቤትሆሮን (ኢያሱ 21:22)፤ አይሎን (ኢያሱ 21:24)፤ ሶኮህ (ኢያሱ 15:35)፤ እና አራድ (ኢያሱ 12:14) ይገኙበታል። በተጨማሪም ሰነዱ “የአብራም እርሻ” የሚል ጽሑፍ ይዟል፤ በግብፃውያን መዛግብት ውስጥ አብርሃም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ሰነድ ላይ ነው።c
6 የሞዓባውያን ጽላት። በ1868 ፍሬድሪክ ክላይን የተባለ ጀርመናዊ ሚስዮናዊ በዚባን (ዲቦን) አንድ አስገራሚ ነገር አገኘ፤ ይህ ግኝት በጽላት ላይ የተቀረጸ ጥንታዊ ጽሑፍ ሲሆን የሞዓባውያን ጽላት በመባል ይታወቃል። በጽሑፉ ላይ ቅርጽ የሚይዝ ነገር በማፍሰስ የፊደላቱን ቅርጽ ማውጣት ተችሎ ነበር፤ ጽላቱ ግን ወደ ሌላ ቦታ ከመዛወሩ በፊት የበድዊን ጎሳ በሆኑ ሰዎች ተሰባብሯል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹን ስብርባሪዎች መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ጽላቱ በሉቨር፣ ፓሪስ ውስጥ ተቀምጧል፤ ቅጂው ደግሞ በለንደን ብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል። ጽላቱ መጀመሪያ የቆመው ሞዓብ ውስጥ በሚገኘው በዲቦን ሲሆን ንጉሥ ሜሻ በእስራኤል ላይ ያስነሳውን ዓመፅ በተመለከተ ከራሱ አንጻር ያሰፈረውን ማብራሪያ ይዟል። (2 ነገ. 1:1፤ 3:4, 5) ጽሑፉ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሜሻ፣ የከሞሽ [ . . . ] ልጅ፣ ዲቦናዊው የሞዓብ ንጉሥ [ነኝ።] . . . ከሞሽ [የሞዓብ አምላክ] በምድሩ ላይ ተቆጥቶ ስለነበር የእስራኤል ንጉሥ ኦምሪ ሞዓብን ለብዙ ዓመታት (ቃል በቃል፣ ቀናት) አዋረዳት። ልጁም የአባቱን ፈለግ በመከተል ‘ሞአብን አዋርዳለሁ’ ብሎ ተነሳ። በእኔ የግዛት ዘመን (ይህን) ተናገረ፤ እኔ ግን በእሱና በቤቱ ላይ ድል የተቀዳጀሁ ሲሆን እስራኤልም ለዘላለም ጠፋች! . . . ደግሞም ከሞሽ ‘ሂድና ነቦን ከእስራኤል ውሰድ!’ አለኝ። ስለዚህ በሌሊት ሄጄ ጎህ ሲቀድ ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን ድረስ በመዋጋት ሁሉንም ገድዬ ነቦን ወሰድኩ። . . . እንዲሁም የያህዌን [ዕቃዎች] በከሞሽ ፊት እየጎተትኩ ከዚያ ወሰድኩ።”d በመጨረሻው ዓረፍተ ነገር ላይ መለኮታዊው ስም እንደተጠቀሰ ልብ በሉ። እዚህ ገጽ ላይ በሚገኘው የሞዓባውያንን ጽላት በሚያሳየው ሥዕል ላይ ይህን መመልከት ይቻላል። መለኮታዊው ስም በሰነዱ በስተቀኝ በ18ኛው መስመር ላይ የይሖዋን ስም በሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኛል።
7 በተጨማሪም የሞዓባውያን ጽላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን የሚከተሉትን ቦታዎች ስም ይዟል፦ አጣሮትና ነቦ (ዘኁ. 32:34, 38)፤ አርኖን፣ አሮዔር፣ መደባና ዲቦን (ኢያሱ 13:9)፤ ባሞትበዓል፣ ቤትበዓልመዖን፣ ያሃጽ እና ቂርያታይም (ኢያሱ 13:17-19)፤ ቤጼር (ኢያሱ 20:8)፤ ሆሮናይም (ኢሳ. 15:5)፤ እንዲሁም ቤትዲብላታይም እና ቀሪዮት (ኤር. 48:22, 24)። በመሆኑም ይህ ጽላት እነዚህ ቦታዎች በጥንት ጊዜ የነበሩ መሆናቸውን ያረጋግጣል።
8 የንጉሥ ሰናክሬም ፕሪዝም። መጽሐፍ ቅዱስ በንጉሥ ሰናክሬም የሚመሩት አሦራውያን በ732 ዓ.ዓ. ስላደረጉት ወረራ በዝርዝር ይናገራል። (2 ነገ. 18:13–19:37፤ 2 ዜና 32:1-22፤ ኢሳ. 36:1–37:38) ከ1847-51 ባሉት ዓመታት እንግሊዛዊው የአርኪኦሎጂ ባለሙያ ኦስተን ሌየርድ የጥንቱ የአሦር ግዛት በነበረው በነነዌ የሚገኘውን ታላቁን የሰናክሬም ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ በቁፋሮ አውጥቷል። ቤተ መንግሥቱ 70 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከ3,000 ሜትር በላይ የሚሆነው ግድግዳው በተቀረጹ ምስሎች ተሸፍኗል። ሰናክሬም በየዓመቱ ያከናወናቸው ክንውኖች በሸክላ ሲሊንደሮች ወይም ፕሪዝሞች ላይ ይመዘገቡ ነበር። ሰናክሬም ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደተጻፈ የሚታመነው የእነዚህ ተከታታይ ዘገባዎች የመጨረሻ ክፍል የቴይለር ፕሪዝም ተብሎ በሚጠራው ቅርጽ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ፕሪዝም በብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል፤ ይሁን እንጂ የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የምሥራቃዊ አገሮች ጥናት ተቋም የአሦር ግዛት ዋና ከተማ የነበረችው የጥንቷ ነነዌ በነበረችበት ስፍራ አቅራቢያ የተገኘ የተሻለ ጥራት ያለው ቅጂ አለው።
9 ሰናክሬም፣ ያከናወናቸውን ነገሮች በጻፈባቸው የመጨረሻ ዘገባዎች ላይ በይሁዳ ላይ ስላደረገው ወረራ እንዲህ በማለት በጉራ ተናግሯል፦ “አይሁዳዊው ሕዝቅያስ ሊገዛልኝ ፈቃደኛ ስላልሆነ 46ቱን የጸኑ ከተሞቹን፣ የግንብ ምሽጎቹንና በአካባቢያቸው ያሉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትናንሽ መንደሮች ከብቤ በሚገባ በተጠቀጠቁ (የአፈር) መወጣጫዎች፣ (ቅጥሮቹ) አጠገብ ባቆምናቸው መደርመሻ መሣሪያዎችና እግረኛ ወታደሮች በሚሰነዝሩት ጥቃት አማካኝነት እንዲሁም ጉድጓዶችን በመቆፈር፣ የጦር መሣሪያዎችን በመጠቀምና የከበባ ስልቶችን በመቀየስ ድል አደረግኳቸው። (ከእነዚህ ስፍራዎች) ወጣት አረጋዊ እንዲሁም ወንድ ሴት ሳይል 200,150 ሰዎችን ብሎም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ፈረሶች፣ በቅሎዎች፣ አህዮች፣ ግመሎችና ትልቅም ሆነ ትንሽ የቀንድ ከብቶች ምርኮ አድርጌ ወሰድኩ። እሱንም [ሕዝቅያስን] በጎጆዋ ውስጥ እንዳለች ወፍ ንጉሣዊ መኖሪያው በሆነችው በኢየሩሳሌም እስረኛ አደረግኩት። . . . የበዘበዝኳቸውን ከተሞቹን ከእሱ ወስጄ ለአሽዶድ ንጉሥ ለሚቲንቲ፣ ለኤቅሮን ንጉሥ ለፓዲና ለጋዛ ንጉሥ ለሲሊቤል ሰጠኋቸው። . . . በኋላ ላይ ሕዝቅያስ ራሱ . . . ዙፋኔ ወዳለባት ወደ ነነዌ ከተማ 30 ታላንት ወርቅ፣ 800 ታላንት ብር፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ አንቲሞኒ (የከበረ ድንጋይ ዓይነት)፣ ትላልቅ ቀይ ድንጋዮች፣ በዝሆን ጥርስ (የተሸፈኑ) መቀመጫዎች፣ በዝሆን ጥርስ (የተሸፈኑ) ኒሜዱ ወንበሮች፣ የዝሆን ቆዳዎች፣ ጥቁር እንጨት፣ ቦክስዉድ የተባለ እንጨት (እና) የተለያዩ ውድ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎችን እንዲሁም (የራሱን) ሴት ልጆች፣ ቁባቶች ብሎም ወንድና ሴት ሙዚቀኞች ላከልኝ። ግብሩን ለእኔ እንዲያደርስና እንደ ባሪያ ሆኖ እንዲሰግድልኝ (የግል) መልእክተኛውን ላከው።”* መጽሐፍ ቅዱስ ሰናክሬም በሕዝቅያስ ላይ የጫነበትን ግብር አስመልክቶ ሲናገር ወርቁ 30 ታላንት እንደሆነ ቢናገርም ብሩ ግን 300 ታላንት ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። ከዚህም በላይ ይህ የሆነው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለመክበብ ከመዛቱ በፊት እንደሆነ ይናገራል። ሰናክሬም በአሦራውያን ታሪክ ውስጥ ባሰፈረው የተዛባ ዘገባ ላይ በይሁዳ ያጋጠመውን አስከፊ ሽንፈት ሆን ብሎ ሳይጠቅስ ቀርቷል፤ በይሁዳ አንድ የይሖዋ መልአክ 185,000 የሚያክሉትን የሰናክሬም ወታደሮች የገደለ ሲሆን ሰናክሬምም ኩምሽሽ ብሎ ወደ ነነዌ ሸሽቶ ለመመለስ ተገዷል። የሆነ ሆኖ በሰናክሬም ፕሪዝም ላይ የተመዘገበው ጉራ የተሞላበት ዘገባ አሦራውያን ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት በመሞከራቸው ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ እስኪመልሳቸው ድረስ በይሁዳ ላይ ከባድ ወረራ አድርገው እንደነበር ይጠቁማል።—2 ነገ. 18:14፤ 19:35, 36
10 የለኪሶ ደብዳቤዎች። የተመሸገች ከተማ የሆነችው ዝነኛዋ ለኪሶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ20 ጊዜ በላይ ተጠቅሳለች። ይህች ከተማ ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ ምዕራብ 44 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በነበረችበት ቦታ ላይ ሰፊ ቁፋሮ ተካሂዶ ነበር። በ1935፣ ሁለት በር ባለው የዘቦች ክፍል ውስጥ፣ የተቀረጸ ጽሑፍ ያለባቸው 18 የሸክላ ስብርባሪዎች ተገኝተው ነበር። (በ1938 ሦስት ተጨማሪ ስብርባሪዎች ተገኝተዋል።) እነዚህ ስብርባሪዎች በጥንታዊ የዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፉ ደብዳቤዎች መሆናቸው ተረጋግጧል። ሃያ አንድ የሸክላ ስብርባሪዎችን የያዘው ይህ ስብስብ በአሁኑ ጊዜ የለኪሶ ደብዳቤዎች በመባል ይታወቃል። ለኪሶ የናቡከደነፆርን ጥቃት ከተቋቋሙት የመጨረሻዎቹ የይሁዳ ምሽጎች አንዷ ስትሆን ከ609-607 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ በእሳት ተቃጥላ የአመድ ቁልል ሆናለች። እነዚህ ደብዳቤዎች በወቅቱ የነበረውን አስጨናቂ ሁኔታ ያንጸባርቃሉ። ደብዳቤዎቹ በይሁዳ የጦር ሰፈር ያሉት ከጥፋት የተረፉ ወታደሮች በለኪሶ ላለ ያኦሽ የሚባል የጦር አዛዥ የላኳቸው ይመስላሉ። ከእነዚህ ደብዳቤዎች አንዱ (ቁጥር 4) በከፊል እንዲህ ይላል፦ “የሐወሐ (“ይሖዋ” የሚለው የአምላክ ስም የተጻፈባቸው አራት ፊደላት) አሁንም ለጌታዬ መልካም ዜና ያሰማው። . . . ጌታዬ በሰጣቸው ምልክቶች መሠረት በለኪሶ የእሳት ምልክቶች እስኪታዩ እየጠበቅን ነው፤ ምክንያቱም አዜቃን ልናያት አልቻልንም።” ይህ ጽሑፍ ከይሁዳ ከተሞች መካከል ድል ሳይደረጉ የቀሩት ለኪሶና አዜቃ እንደሆኑ የሚናገረው የኤርምያስ 34:7 ዘገባ ትክክል መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል። ደብዳቤው በዚያ ወቅት አዜቃ በጠላት እጅ እንደወደቀች ይጠቁማል። የአምላክ ስም የሚጻፍባቸው አራት የዕብራይስጥ ፊደላት በደብዳቤው ላይ በተደጋጋሚ መጠቀሳቸው በወቅቱ የነበሩት አይሁዳውያን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ይሖዋ የሚለውን ስም ይጠቀሙበት እንደነበር ያሳያል።
11 ሌላኛው ደብዳቤ (ቁጥር 3) እንደሚከተለው በማለት ይጀምራል፦ “የሐወሐ [ማለትም፣ ይሖዋ] ጌታዬን የሰላም ወሬ ያሰማው! . . . ባሪያህ የሚከተለው መረጃ ደርሶታል፦ የኤልናታን ልጅ የሆነው የጦር አዛዡ ኮንያሁ ወደ ግብፅ ለመሄድ መጥቷል፤ ደግሞም የአኪያህን ልጅ ሆዳውያህን እና ሰዎቹን ከእሱ [የሚያስፈልጉንን ነገሮች] እንዲያመጡ ልኳቸዋል።” ይህ ደብዳቤ አይሁዳውያን የይሖዋን ትእዛዝ በመጣስ እርዳታ ፍለጋ ወደ ግብፅ እንደሄዱና በዚህም ምክንያት ለጥፋት እንደተዳረጉ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚያረጋግጥ ይመስላል። (ኢሳ. 31:1፤ ኤር. 46:25, 26) በተጨማሪም በዚህ ደብዳቤ ሙሉ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሱት ኤልናታንና ሆሻያህ የሚሉት ስሞች በኤርምያስ 36:12 እና በኤርምያስ 42:1 ላይ ይገኛሉ። በደብዳቤዎቹ ላይ የተጠቀሱ ሌሎች ሦስት ስሞችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ። እነሱም ገማርያህ፣ ነሪያህና ያአዛንያህ ናቸው።—ኤር. 32:12፤ 35:3፤ 36:10e
12 የናቦኒደስ ዜና መዋዕል። በ19ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በባግዳድ አቅራቢያ የተደረጉ ቁፋሮዎች በርካታ የሸክላ ጽላቶችንና ሲሊንደሮችን ለማግኘት ያስቻሉ ሲሆን እነዚህ ግኝቶች በጥንቷ ባቢሎን ታሪክ ላይ ደማቅ ብርሃን ፈንጥቀዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ በአሁኑ ጊዜ በብሪትሽ ሙዚየም የሚገኘውና የናቦኒደስ ዜና መዋዕል በመባል የሚታወቀው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰነድ ነው። የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቦኒደስ የእሱ እንደራሴ የሆነው የቤልሻዛር አባት ነው። የቂሮስ ሠራዊት ጥቅምት 5, 539 ዓ.ዓ. ባቢሎንን በተቆጣጠረበት ምሽት ቤልሻዛር የተገደለ ሲሆን አባቱ ናቦኒደስ ግን በሕይወት ሊተርፍ ችሏል። (ዳን. 5:30, 31) ከባቢሎን አወዳደቅ ጋር የተያያዙ ክንውኖችን ከጊዜ አንጻር በሚገባ መዝግቦ የሚገኘው የናቦኒደስ ዜና መዋዕል ባቢሎን የወደቀችበትን ቀን በትክክል ለማወቅ ይረዳል። የናቦኒደስ ዜና መዋዕል በከፊል እንዲህ ይላል፦ “በታሽሪቱ [ቲሽሪ (መስከረም-ጥቅምት)] ወር ቂሮስ፣ ጤግሮስ አካባቢ በሚገኘው በኦፒስ ባለው የአካድ ሠራዊት ላይ ጥቃት በሰነዘረ ጊዜ . . . በ14ኛው ቀን ሲፓር ያላንዳች ውጊያ ተያዘች። ናቦኒደስ ሸሸ። በ16ኛው ቀን [በጁሊያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ጥቅምት 11፣ በግሪጎሪያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ደግሞ ጥቅምት 5, 539 ዓ.ዓ.] የጉቲየም ገዢ የሆነው ጎብሪያስ (ኡግባሩ) እና የቂሮስ ሠራዊት ያላንዳች ውጊያ ወደ ባቢሎን ገቡ። በኋላም ናቦኒደስ ወደ ባቢሎን ሲመለስ (እዚያው) ተያዘ። . . . በአራህሻምኑ ወር [ማርቼስቫን (ጥቅምት-ኅዳር)] በ3ኛው ቀን [በጁሊያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ጥቅምት 28] ቂሮስ ወደ ባቢሎን ገባ፤ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፎች በፊቱ የተነጠፉለት ሲሆን በከተማዋ ላይ ‘ሰላም’ (ሱልሙ) ታወጀ። ቂሮስ ለመላዋ ባቢሎን ሰላምታ ላከ። እሱ የሾመው ገዢ ጎብሪያስ በባቢሎን (የበታች) ገዢዎችን ሾመ።”f
13 በዚህ ዜና መዋዕል ላይ ሜዶናዊው ዳርዮስ እንዳልተጠቀሰ መመልከት ይቻላል፤ ደግሞም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ይሄኛው ዳርዮስ ተጠቅሶ የሚገኝበት የተቀረጸ ጽሑፍ ያልተገኘ ከመሆኑም ሌላ ጆሴፈስ (በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረ የታሪክ ምሁር) ከኖረበት ጊዜ በፊት በተጻፈ በየትኛውም ዓለማዊ የታሪክ ሰነድ ላይ ይህ ሰው ተጠቅሶ አይገኝም። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ዳርዮስ፣ ከላይ ባለው ሰነድ ላይ የተጠቀሰው ጎብሪያስ የተባለ ሰው ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ አቅርበዋል። ጎብሪያስን በተመለከተ የተገኘው መረጃ ከዳርዮስ ጋር የሚመሳሰል ቢመስልም ‘ጎብሪያስ፣ ዳርዮስ ነው’ ብሎ ሙሉ በሙሉ መደምደም አይቻልም።g ያም ሆነ ይህ ዓለማዊ ታሪክ ቂሮስ በባቢሎን ላይ ከተገኘው ድል ጋር በተያያዘ ጉልህ ስፍራ ያለው ሰው እንደሆነና ከዚያ በኋላም ንጉሥ ሆኖ በባቢሎን እንደገዛ በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል።
14 የቂሮስ ሲሊንደር። ቂሮስ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነችውን ፋርስን መግዛት ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በ539 ዓ.ዓ. በባቢሎን ላይ የተቀዳጀው ድል በአንድ የሸክላ ሲሊንደር ላይ ተመዝግቧል። ይህ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰነድ በብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል። ጽሑፉ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እኔ ቂሮስ የዓለም ንጉሥ፣ ታላቅ ንጉሥ፣ ሕጋዊ መብት ያለኝ ንጉሥ፣ የባቢሎን ንጉሥ፣ የሱሜርና የአካድ ንጉሥ፣ የአራቱም (የምድር) ማዕዘናት ንጉሥ ነኝ። . . . የአምልኮ ስፍራዎቻቸው ከፈራረሱባቸው ረጅም ዘመናት ላስቆጠሩት በጤግሮስ ማዶ ለሚገኙ [ቀደም ሲል ለተጠቀሱት አንዳንድ] ቅዱስ ከተሞች በዚያ የነበሩትን ዕቃዎቻቸውን መልሼላቸዋለሁ። እንዲሁም ቋሚ የተቀደሱ ቦታዎች እንዲኖራቸው አድርጌያለሁ። (በተጨማሪም የቀድሞ) ነዋሪዎቻቸውን በሙሉ ሰብስቤ ወደ ትውልድ ስፍራቸው መልሻለሁ።”h
15 የቂሮስ ሲሊንደር ንጉሡ ምርኮኞች ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያዝ አዋጅ አውጥቶ እንደነበር ይገልጻል። ከዚህ ድንጋጌ ጋር በሚስማማ መልኩ ቂሮስ አይሁዳውያኑ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና የይሖዋን ቤት መልሰው እንዲገነቡ አዝዞ ነበር። የሚገርመው ነገር፣ ይህ ከመሆኑ ከ200 ዓመት በፊት ይሖዋ ቂሮስን በስም በመጥቀስ ባቢሎንን ድል የሚነሳውና የይሖዋ ሕዝቦች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገው እሱ እንደሆነ በትንቢት ተናግሮ ነበር።—ኢሳ. 44:28፤ 45:1፤ 2 ዜና 36:23
አርኪኦሎጂና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት
16 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ብቻ ሳይሆኑ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትም በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ቅርሳ ቅርሶችን አግኝተዋል።
17 የጢባርዮስ ምስል የተቀረጸበት ዲናር። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው በጢባርዮስ ቄሳር የግዛት ዘመን እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። አንዳንድ ተቃዋሚዎች ለቄሳር ግብር ከመክፈል ጋር የተያያዘ ጥያቄ በማንሳት ኢየሱስን ሊያጠምዱት ሞክረው ነበር። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ ‘ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡና አሳዩኝ’ አላቸው። እነሱም አመጡለት፤ እሱም ‘ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?’ አላቸው። እነሱም ‘የቄሳር’ አሉት። ከዚያም ኢየሱስ ‘የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ’ አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ።” (ማር. 12:15-17) የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የጢባርዮስ ቄሳርን ከአንገት በላይ ምስል የሚያሳይ የብር ዲናር አግኝተዋል! ይህ ዲናር አገልግሎት ላይ መዋል የጀመረው በ15 ዓ.ም. ገደማ ነበር። ይህም ጢባርዮስ በ14 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት ሆኖ መግዛት እንደጀመረ ከሚታወቀው እውነታ ጋር ይስማማል፤ እንዲሁም አጥማቂው ዮሐንስ አገልግሎቱን በጢባርዮስ የግዛት ዘመን 15ኛ ዓመት ላይ ወይም በ29 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት እንደጀመረ ለሚናገረው ዘገባ ተጨማሪ ድጋፍ ይሰጣል።—ሉቃስ 3:1, 2
18 ስለ ጳንጥዮስ ጲላጦስ የሚናገር የተቀረጸ ጽሑፍ። ስለ ጳንጥዮስ ጲላጦስ የሚናገረው የመጀመሪያው የአርኪኦሎጂ ግኝት በቁፋሮ የወጣው በ1961 ነበር። በቂሳርያ የተገኘው ይህ ጠፍጣፋ ድንጋይ የጳንጥዮስ ጲላጦስን ስም በላቲን ይዟል።
19 አርዮስፋጎስ። ጳውሎስ በጽሑፍ ከሠፈሩት ዝነኛ ንግግሮቹ መካከል አንዱን ያቀረበው በ50 ዓ.ም. አቴንስ፣ ግሪክ ውስጥ ነበር። (ሥራ 17:16-34) ይህን ንግግር ያቀረበው አንዳንድ የአቴንስ ሰዎች ወደ አርዮስፋጎስ ይዘውት በሄዱ ወቅት ነበር። አርዮስፋጎስ ወይም የአሬስ ኮረብታ (የማርስ ኮረብታ) ተብሎ የሚጠራው ቦታ፣ በአቴንሷ አክሮፖሊስ ሰሜናዊ ምዕራብ የሚገኝ 113 ሜትር ከፍታ ያለው ገላጣና ዓለታማ ኮረብታ ነው። ዓለቱን በመፈልፈል የተሠሩት ደረጃዎች ወደ ኮረብታው ጫፍ የሚወስዱ ሲሆን በኮረብታው ጫፍ ላይ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ከዓለት ተጠርበው የተሠሩ መቀመጫዎች አሉ፤ እነዚህን መቀመጫዎች አሁንም ድረስ ማየት ይቻላል። አርዮስፋጎስን ዛሬም ቢሆን ማየት የሚቻል መሆኑ ጳውሎስ ታሪካዊ ንግግሩን በዚያ እንዳቀረበ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል።
20 የቲቶ ቅስት። በቲቶ የሚመራው የሮማውያን ሠራዊት በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አጠፋ። በቀጣዩ ዓመት ቲቶ ከአባቱ ከንጉሠ ነገሥት ቨስፔዥያን ጋር ሮም ውስጥ ድሉን አከበረ። በድል ሰልፉ ላይ 700 የተመረጡ አይሁዳውያን እስረኞች በሰልፍ እንዲያልፉ ተደረገ። በተጨማሪም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች እንዲሁም በጦርነቱ የተገኙ በርካታ ምርኮዎች በሰልፉ ላይ ለእይታ ቀርበው ነበር። ቲቶ ራሱ ከ79 እስከ 81 ዓ.ም. ድረስ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ የገዛ ሲሆን ከእሱ ሞት በኋላ የቲቶ ቅስት የተባለ ትልቅ ሐውልት ቆሞለታል፤ ይህ ሐውልት ዲቮ ቲቶ (አምላክ የተደረገው ቲቶ) ተብሎ በቲቶ ስም ተሰይሟል። በቅስቱ መተላለፊያ የውስጠኛ ክፍል ጎንና ጎን ላይ የድል ሰልፉን የሚያሳይ ምስል ተቀርጿል። በአንደኛው ጎን፣ ጫፍ የሌለው ጦር የያዙና ከላውሮ ቅጠል የተሠራ አክሊል የደፉ የሮም ወታደሮች ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የተወሰዱ የተቀደሱ ዕቃዎችን ተሸክመው ይታያል። ከእነዚህ መካከል ሰባት ቅርንጫፍ ያለው መቅረዝና የተቀደሱ መለከቶች የተደገፉበት የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ ይገኙበታል። በመተላለፊያው ሌላኛው ጎን ላይ ደግሞ ድል አድራጊው ቲቶ አራት ፈረሶች በሚጎትቱትና የሮም ከተማን የምትወክል ሴት ከፊት ከፊት በምትመራው ሠረገላ ላይ ቆሞ ይታያል።i እስከዛሬ ድረስ በሮም የሚገኘው የቲቶ ቅስት፣ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢትና ይሖዋ በዓመፀኛዋ ኢየሩሳሌም ላይ ያስተላለፈው አስፈሪ ፍርድ መፈጸሙን የሚያሳይ ድምፅ አልባ ምሥክር ነው፤ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን የድል ቅስት ለማየት ወደ ሮም ይጎርፋሉ።—ማቴ. 23:37–24:2፤ ሉቃስ 19:43, 44፤ 21:20-24
21 በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ያልተበረዘውን የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መልሶ ለማስገባት እንዳስቻሉ ሁሉ በቁፋሮ የተገኙት አብዛኞቹ ቅርሳ ቅርሶችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው እያንዳንዱ ዝርዝር ነገር ከታሪክ፣ ከጊዜና ከቦታ አንጻር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ አስችለዋል። ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂ ሙሉ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል ብሎ መደምደም ስህተት ነው። የአርኪኦሎጂ መረጃዎች ትክክል ሆነው የሚገኙት ሁልጊዜ እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል። በአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ላይ ትንታኔ የሚሰጡት ሰዎች ሲሆኑ እነዚህ ትንታኔዎች ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለወጡ እንደሚችሉ ታይቷል። የአርኪኦሎጂ ዓላማ የአምላክን ቃል ትክክለኛነት ማረጋገጥ ባይሆንም እግረ መንገዱን እንዲህ ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ። ከዚህም በላይ ለበርካታ ዓመታት የብሪትሽ ሙዚየም ዳይሬክተርና የቤተ መጻሕፍቱ ዋና ኃላፊ የነበሩት ሟቹ ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንደተናገሩት አርኪኦሎጂ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ “የኋላ ታሪክና መቼት የተሟላ መረጃ በመስጠት [መጽሐፉ] ይበልጥ ለመረዳት ቀላል” እንዲሆን አድርጓል።j ሆኖም ለእምነታችን መሠረት ሊሆን የሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ አርኪኦሎጂ አይደለም።—ሮም 10:9፤ ዕብ. 11:6
22 በቀጣዩ ጥናት ላይ እንደምንመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሕያውና ጸንቶ የሚኖር የአምላክ ቃል’ እንደሆነ የሚያረጋግጥ አስተማማኝ ማስረጃ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል።—1 ጴጥ. 1:23
[የግርጌ ማስታወሻ]
a Bible and Spade, 1938, S. L. Caiger, page 29
b Ancient Near Eastern Texts, 1974, J. B. Pritchard, page 321; Insight on the Scriptures, Vol. 1, pages 941-2, 1104
c Light From the Ancient Past, 1959, J. Finegan, pages 91, 126
d Ancient Near Eastern Texts, page 320
e Ancient Near Eastern Texts, page 288
f Insight on the Scriptures, Vol. 1, pages 151-2; Light From the Ancient Past, pages 192-5
g Ancient Near Eastern Texts, page 306
i Ancient Near Eastern Texts, page 316
j Light From the Ancient Past, page 329.
The Bible and Archaeology, 1940, page 279