የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bsi06 ገጽ 11-14
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 18—ኢዮብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 18—ኢዮብ
  • “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 14
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 14
bsi06 ገጽ 11-14

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 18​—ኢዮብ

ጸሐፊው:- ሙሴ

የተጻፈበት ቦታ:- ምድረ በዳ

ተጽፎ ያለቀው:- በ1473 ከክ.ል.በፊት ገደማ

የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ1657 እስከ 1473 ከክ.ል.በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ከ140 የሚበልጡ ዓመታት

በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከተጻፉት እጅግ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል አንዱ ነው! ሰዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጡትና ብዙ ጊዜ የሚጠቅሱት መጽሐፍ ቢሆንም እምብዛም አልተረዱትም። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው ለምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛስ ምን ጥቅም አለው? “የጥላቻ ዒላማ” የሚለው የኢዮብ ስም ትርጉም የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይጠቁመናል። አዎን፣ ይህ መጽሐፍ በንጹሐን ሰዎች ላይ ሥቃይ የሚደርሰው ለምንድን ነው? እንዲሁም አምላክ በምድር ላይ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ለሚሉት ሁለት አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። በኢዮብ ላይ ስለደረሰው ሥቃይና እርሱ ስላሳየው ታላቅ ጽናት የሚገልጸውን ዘገባ በመመርመር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን። ኢዮብ ራሱ እንደተማጸነው ሁሉም ነገር በጽሑፍ ሰፍሯል።—ኢዮብ 19:23, 24

2 ኢዮብ የትዕግሥትና የጽናት ተምሳሌት ነው። ይሁን እንጂ ኢዮብ የሚባል ሰው በሕይወት ኖሮ ያውቃል? ዲያብሎስ እንዲህ ያለውን ግሩም የታማኝነት ምሳሌ ከታሪክ ማኅደር ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም መልሱ ግልጽ ነው። ኢዮብ በእርግጥ በሕይወት የነበረ ሰው ነው! ይሖዋ ምሥክሮቹ ከነበሩት ከኖኅና ከዳንኤል ጋር አብሮ የጠቀሰው ሲሆን እነዚህ ሰዎች በሕይወት የነበሩ መሆናቸውን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስም ተቀብሏል። (ሕዝ. 14:14, 20፤ ከማቴዎስ 24:15, 37 ጋር አወዳድር።) የጥንቱ የዕብራውያን ብሔር ኢዮብ በገሃዱ ዓለም የነበረ ሰው መሆኑን ተቀብሏል። ክርስቲያኑ ጸሐፊ ያዕቆብ የኢዮብን የጽናት ምሳሌ ጠቅሶ ጽፏል። (ያዕ. 5:11) በማንኛውም ሁኔታ ሥር ጽኑ አቋምን ጠብቆ መኖር እንደሚቻል የአምላክ አገልጋዮችን የሚያሳምናቸው ጠንካራ ማስረጃ እውነተኛ ታሪክ እንጂ ልብ ወለድ ሊሆን አይችልም። ከዚህም በላይ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙት ንግግሮች ላይ የተንጸባረቀው ግለትና ስሜት ሁኔታው እውን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

3 የጥንት ዕብራውያን፣ ኢዮብ እስራኤላዊ ባይሆንም እንኳ የኢዮብ መጽሐፍ ምንጊዜም በቅዱሳን ጽሑፎቻቸው ውስጥ እንዲካተት ማድረጋቸው መጽሐፉ ትክክለኛና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ሕዝቅኤልና ያዕቆብ ስለ ኢዮብ ከመናገራቸውም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ከመጽሐፉ ጠቅሶ ጽፏል። (ኢዮብ 5:13 የ1954 ትርጉም፤ 1 ቆሮ. 3:19) መጽሐፉ ትክክለኛነታቸው ከተረጋገጠ ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር በሚያስደንቅ መንገድ መስማማቱ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላ ጠንካራ ማስረጃ ነው። በጥንት ጊዜ የነበሩ ሰዎች የምድርን አቀማመጥ በተመለከተ ለማመን የሚያስቸግሩ የተለያዩ መላ ምቶችን ይሰነዝሩ በነበረበት ዘመን፣ ይሖዋ ‘ምድርን እንዲያው በባዶው ላይ እንዳንጠለጠላት’ እንዴት ሊታወቅ ቻለ? (ኢዮብ 26:7) በጥንት ጊዜ ከነበሩት አመለካከቶች አንዱ ዝሆኖች በአንድ ትልቅ የባሕር ኤሊ ላይ ቆመው ምድርን ተሸክመዋታል የሚል ነው። በኢዮብ መጽሐፍ እንዲህ የመሰለ ትርጉም የለሽ አመለካከት የማይገኘው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሁሉን ነገር የፈጠረው ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እውነቱን ስለገለጠለት ነው። ስለ ምድርና በውስጧ ስላሉት አስደናቂ ነገሮች እንዲሁም አእዋፍና የዱር አራዊት ተፈጥሮ በለገሳቸው መኖሪያ ስለሚገኙበት ሁኔታ የተሰጡት በርካታ መግለጫዎች ፍጹም ትክክለኛ መሆናቸው የኢዮብን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ሊያጽፍ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ መሆኑን ያሳያል።a

4 ኢዮብ የኖረው ዖፅ በሚባል አገር ሲሆን አንዳንድ የጂኦግራፊ ምሁራን እንደሚሉት ቦታው የሚገኘው በሰሜናዊ አረብ ኤዶማውያን ይኖሩበት ከነበረው ቦታ አቅራቢያና ለአብርሃም ዘሮች ቃል ከተገባላቸው ምድር በስተ ምሥራቅ ነበር። ከዖፅ በስተ ደቡብ ሳባውያን፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ ከለዳውያን ይኖሩ ነበር። (1:1, 3, 15, 17) ኢዮብ መከራ የደረሰበት ከአብርሃም ዘመን ረጅም ጊዜ ቆይቶ ነው። ይህ ጊዜ “በምድር ላይ እንደ [ኢዮብ] ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን . . . ሰው የለም” የተባለበት ዘመን ነው። (1:8) ይህም ድንቅ እምነት ያሳየው ዮሴፍ በሞተበት (1657 ከክርስቶስ ልደት በፊት) እና ሙሴ በታማኝነት መመላለስ በጀመረበት ጊዜ መካከል ያለው ዘመን ሳይሆን አይቀርም። እስራኤላውያን በግብፃውያን የአጋንንት አምልኮ ተበክለው በነበረበት በዚህ ወቅት ኢዮብ ንጹሑን አምልኮ በመከተል ልቆ ታይቷል። ከዚህም በላይ በኢዮብ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙት ልማዶች እንዲሁም አምላክ ኢዮብን እንደ እውነተኛ አምላኪው አድርጎ መቀበሉ፣ በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አምላክ በሕጉ አማካኝነት ከእስራኤላውያን ጋር ብቻ ግንኙነት ከመሠረተበት ጊዜ በፊት ወደ ነበረው የፓትሪያርኮች ዘመን ይመልሰናል። (አሞጽ 3:2፤ ኤፌ. 2:12) በዚህም መሠረት ኢዮብ የኖረበትን ረጅም ዓመት ግምት ውስጥ በማስገባት መጽሐፉ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1657 አንስቶ ሙሴ እስከ ሞተበት ዓመት እስከ 1473 ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ይመስላል። ሙሴ መጽሐፉን ጽፎ ያጠናቀቀው ኢዮብ ከሞተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ይጓዙ በነበሩበት ወቅት ነው።—ኢዮብ 1:8፤ 42:16, 17

5 ጸሐፊው ሙሴ ነው የምንለው ለምንድን ነው? እንዲህ ሊባል የሚችለው በአይሁዳውያንም ሆነ በጥንት የክርስትና ምሁራን ዘንድ የነበረውን ጥንታዊ ወግ መሠረት በማድረግ ነው። በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የተሠራበት በጣም ገላጭ የሆነ ጥንታዊ የዕብራይስጥ የግጥም አጻጻፍ ስልት፣ መጽሐፉ በመጀመሪያ የተጻፈው ሙሴ ይናገር በነበረው በዕብራይስጥ ቋንቋ እንደሆነ ያረጋግጣል። እንደ አረብኛ ካለ ከሌላ ቋንቋ የተተረጎመ ሊሆን አይችልም። እንዲሁም በስድ ንባብ መልክ የተጻፈው የመጽሐፉ ክፍል ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይልቅ ከፔንታቱች ጋር በጣም ይመሳሰላል። “የእግዚአብሔር ቃል በዐደራ የተሰጠው” ለአይሁዳውያን እንደመሆኑ መጠን ጸሐፊው እንደ ሙሴ ያለ እስራኤላዊ መሆን አለበት። (ሮሜ 3:1, 2) ሙሴ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ለ40 ዓመታት የኖረው ከዖፅ ብዙም በማትርቀው በምድያም ምድር በመሆኑ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ዝርዝር መረጃዎች ሊያገኝ ይችል ነበር። ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት በተጓዙበት ወቅት በኢዮብ የትውልድ አገር አቅራቢያ ሲያልፉ ሙሴ በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ የሚገኙትን መረጃዎች ሊያገኝና ሊጽፍ ይችላል።

6 ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዳለው ከሆነ የኢዮብ መጽሐፍ ብዙውን ጊዜ “በዓለም ላይ ድንቅ ከሚባሉት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል የሚቆጠር” ነው።b ይሁን እንጂ መጽሐፉ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ከመሆንም ያልፋል። መጽሐፈ ኢዮብ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት መካከል የይሖዋን ኃይል፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር በመግለጽ ረገድ ልቆ የሚታይ መጽሐፍ ነው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የተነሳውን ዋነኛ ግድድር ግልጽ አድርጎ ያሳያል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በተለይ ደግሞ በዘፍጥረት፣ በዘፀአት፣ በመክብብ፣ በሉቃስ፣ በሮሜ እና በራእይ መጻሕፍት ውስጥ የተነገሩት ነገሮች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑልን ያደርጋል። (ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7ን ከዘፍጥረት 3:15፤ ከዘፀአት 9:16፤ ከሉቃስ 22:31, 32፤ ከሮሜ 9:16-19 እና ከራእይ 12:9 ጋር አወዳድር፤ እንዲሁም ኢዮብ 1:21፤ 24:15፤ 21:23-26፤ 28:28ን ከመክብብ 5:15፤ 8:11፤ 9:2, 3፤ 12:13 ጋር በቅደም ተከተል አወዳድር።) በሕይወት ውስጥ ለሚነሱ ለብዙዎቹ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። በእርግጥም የኢዮብ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል ከመሆኑም በላይ ቅዱሳን ጽሑፎችን መረዳት እንድንችል እገዛ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

39 የኢዮብ መጽሐፍ ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን እጅግ ጥልቅ ለሆነው ጥበቡና ኃይሉ ማስረጃ ያቀርባል። (12:12, 13፤ 37:23) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ አምላክ ሁሉን ቻይ እንደሆነ 31 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን ይህም በተቀሩት የቅዱሳን ጽሑፍ ክፍሎች ውስጥ በአጠቃላይ ከሰፈረው የሚበልጥ ነው። ዘገባው የአምላክን ዘላለማዊነትና ከፍ ያለ ቦታ (10:5፤ 36:4, 22, 26፤ 40:2፤ 42:2) እንዲሁም ፍትሑን፣ በጎነቱን ወይም ፍቅራዊ ደግነቱንና ምሕረቱን (36:5-7፤ 10:12፤ 42:12) ያወድሳል። የይሖዋ ስም መቀደስ ከሰዎች መዳን የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። (33:12፤ 34:10, 12፤ 35:2፤ 36:24፤ 40:8) የእስራኤል አምላክ የሆነው ይሖዋ የኢዮብም አምላክ እንደሆነ ተገልጿል።

40 በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዘገባ የአምላክን የፍጥረት ሥራ ያጎላል እንዲሁም ያብራራል። (38:4 እስከ 39:30፤ 40:15, 19፤ 41:1፤ 35:10) ሰው ከአፈር እንደተሠራና ወደ አፈር እንደሚመለስ ከሚገልጸው ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይስማማል። (ኢዮብ 10:8, 9፤ ዘፍ. 2:7፤ 3:19) መጽሐፉ ‘የሚቤዥ፣’ “ቤዛ” እና ‘ተመልሶ በሕይወት መኖር’ የሚሉትን መግለጫዎች የሚጠቀም ሲሆን ይህም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ዋነኛ ትምህርቶች በተመለከተ ፍንጭ ይሰጣል። (ኢዮብ 19:25፤ 33:24፤ 14:13, 14) ነቢያትና ክርስቲያን ጸሐፊዎች በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ በርካታ መግለጫዎችን ጠቅሰው ወይም ከዚያ ጋር የሚመሳሰሉ መግለጫዎችን ተጠቅመው ጽፈዋል። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን አወዳድር:- ኢዮብ 7:17—መዝሙር 8:4፤ ኢዮብ 9:24—1 ዮሐንስ 5:19፤ ኢዮብ 10:8—መዝሙር 119:73፤ ኢዮብ 12:25—ዘዳግም 28:29፤ ኢዮብ 24:23—ምሳሌ 15:3፤ ኢዮብ 26:8—ምሳሌ 30:4፤ ኢዮብ 28:12, 13, 15-19—ምሳሌ 3:13-15፤ ኢዮብ 39:30—ማቴዎስ 24:28።c

41 ይሖዋ ያወጣቸው ለሕይወት መመሪያ የሚሆኑ የጽድቅ መሥፈርቶች በተለያዩ ምዕራፎች ውስጥ ሰፍረዋል። መጽሐፉ ፍቅረ ነዋይን (ኢዮብ 31:24, 25)፣ ጣዖት አምልኮን (31:26-28)፣ ምንዝርን (31:9-12)፣ በሌላው ውድቀት መደሰትን (31:29)፣ የፍትሕ መጓደልንና መድልዎን (31:13፤ 32:21)፣ ራስ ወዳድነትን (31:16-21) እንዲሁም እምነት ማጉደልንና መዋሸትን (31:5) አጥብቆ የሚያወግዝ ሲሆን እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጽም ማንኛውም ሰው የአምላክን ሞገስም ሆነ የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ እንደማይችል ይጠቁማል። ኤሊሁ ደፋርነትንና አምላክን ከፍ ከፍ ማድረግን ጨምሮ ጥልቅ አክብሮት በማሳየት እንዲሁም ልክን በማወቅ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። (32:2, 6, 7, 9, 10, 18-20፤ 33:6, 33) ኢዮብ የራስነት ሥልጣኑን የተጠቀመበት መንገድ፣ ለቤተሰቡ የነበረው አሳቢነትና እንግዳ ተቀባይ መሆኑ ግሩም ትምህርት ይዟል። (1:5፤ 2:9, 10፤ 31:32) ይሁን እንጂ ኢዮብ ከሁሉ ይበልጥ የሚታወሰው ታማኝነቱን በመጠበቁና በትዕግሥት በመጽናቱ ሲሆን ባለፉት ዘመናት ለነበሩትና በተለይ ደግሞ እምነት በሚፈታተነው በአሁኑ ዘመን ለሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ እምነት የሚያጠነክር ትልቅ ምሳሌ ሆኗል። “ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።”—ያዕ. 5:11

42 ኢዮብ የመንግሥቱ ተስፋ ከተሰጣቸው የአብርሃም ዘሮች አንዱ ባይሆንም የአቋም ጽናቱን አስመልክቶ የሰፈረው ዘገባ ስለ ይሖዋ መንግሥት ዓላማዎች ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። የኢዮብ መጽሐፍ፣ የሰው ልጅ ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጎን በታማኝነት የመቆሙን ጉዳይ የሚያካትተውን በአምላክና በሰይጣን መካከል የተነሳውን መሠረታዊ ውዝግብ የሚገልጽ በመሆኑ ወሳኝ ድርሻ ያለው የመለኮታዊ ዘገባ ክፍል ነው። ምድርና የሰው ልጅ ከመፈጠራቸው በፊት ይኖሩ የነበሩት መላእክትም ይህንን ጉዳይ እንደሚመለከቱ፣ በምድር ላይ የሚከናወነው ነገር ትኩረታቸውን እንደሚስበው እንዲሁም የተነሳውን አከራካሪ ጥያቄ የመጨረሻ ውጤት ለማወቅ እንደሚጓጉ ያሳያል። (ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-5፤ 38:6, 7) መጽሐፉ አከራካሪው ጥያቄ የተነሳው ከኢዮብ ዘመን በፊት እንደሆነና ሰይጣን መንፈሳዊ ፍጡር መሆኑን ያመለክታል። የኢዮብን መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ ከሆነ ሃስሳታን የሚለው መግለጫ በዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፍሮ የሚገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሲሆን ይህም “የጥንቱ እባብ” ማን እንደሆነ የሚጠቁም ተጨማሪ መግለጫ ይሰጣል። (ኢዮብ 1:6፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ ራእይ 12:9) መጽሐፉ በሰው ልጆች ላይ ሥቃይ፣ ሕመምና ሞት ያመጣው አምላክ እንዳልሆነ ከማረጋገጡም በላይ ይሖዋ በአንድ በኩል ጻድቃን መከራ እንዲደርስባቸው በሌላ በኩል ደግሞ ክፉዎች እንዲኖሩና ክፋት እንዲስፋፋ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ያስረዳል። ይሖዋ ይህ አከራካሪ ጥያቄ መልስ አግኝቶ ማየት እንደሚፈልግም ይጠቁማል።

43 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር መኖር የሚፈልጉ ሁሉ የጽናት ጎዳና በመከተል “ከሳሽ” ለሆነው ለሰይጣን መልስ የሚሰጡበት ጊዜ አሁን ነው። (ራእይ 12:10, 11) የአቋም ጽናታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ሁሉ ‘የሚያስደንቅ መከራ’ ቢደርስባቸውም የአምላክ ስም እንዲቀደስና የአምላክ መንግሥት መጥቶ ሰይጣንንና ዘሮቹን በሙሉ እንዲደመስስ ሳያሰልሱ መጸለይ ይገባቸዋል። ይህ ወቅት የአምላክ ‘የጦርነትና የውጊያ ቀን’ ሲሆን ከዚያ በኋላ ኢዮብ ተስፋ ያደረገው የእረፍትና የበረከት ጊዜ ይከተላል።—1 ጴጥ. 4:12፤ ማቴ. 6:9, 10፤ ኢዮብ 38:23፤ 14:13-15

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 280-281, 663, 668, 1166፤ ጥራዝ 2 ገጽ 562-563

b 1987፣ ጥራዝ 6 ገጽ 562

c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 83

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ