የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 30—አሞጽ
ጸሐፊው:- አሞጽ
የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ
ተጽፎ ያለቀው:- በ804 ከክ. ል. በፊት ገደማ
አሞጽ፣ ይሖዋ ሲጠራውና በነቢይነት ሲልከው እረኛና የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አልነበረም፤ ሆኖም የራሱ አገር ለሆነው ለይሁዳ ብቻ ሳይሆን በተለይ ለሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ትንቢት እንዲናገር ተላከ። አሞጽ በ2 ነገሥት 17:13, 22, 23 ላይ ከተጠቀሱት ነቢያት አንዱ ነበር። አሞጽ፣ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ከምትገኘውና ከአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ደቡባዊ ድንበር የአንድ ቀን መንገድ ያህል ከምታስኬደው በይሁዳ ከምትገኘው ከቴቁሔ ከተማ የመጣ ሰው ነበር።—አሞጽ 1:1፤ 7:14, 15
2 የትንቢቱ የመክፈቻ ቁጥር እንደሚያመለክተው አሞጽ የነቢይነት ሥራውን የጀመረው በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያንና የእስራኤል ንጉሥ በነበረው በዮአስ ልጅ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመን ሲሆን ይህም በጣም ታላቅ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ማለት ነው። በዚህ መሠረት የአሞጽ ትንቢት የተነገረው ሁለቱ ነገሥታት በተመሳሳይ ወቅት በገዙባቸው ከ829 እስከ 804 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ባሉት 26 ዓመታት ውስጥ ነበር ማለት ነው። ነቢዩ ዘካርያስ በዖዝያን ዘመን ታላቅ የምድር መናወጥ እንደነበረና ሕዝቡም በፍርሃት እንደሸሹ ተናግሯል። (ዘካ. 14:5) የአይሁዳውያን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ፣ ዖዝያን በትዕቢት ተነሳስቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባጠነበት ጊዜ የምድር መናወጥ ተከስቶ እንደነበረ ገልጿል። ይሁን እንጂ አሞጽ የጠቀሰው የምድር መናወጥ የተከሰተው በዖዝያን ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ አካባቢ ይመስላል።
3 አሞጽ የሚለው ስም “ሸክም መሆን” ወይም “ሸክም መሸከም” የሚል ትርጉም አለው። የአሞጽ መልእክት በእስራኤልና በይሁዳ ላይ (እንዲሁም በሌሎች አሕዛብ ብሔራት ላይ) የሚደርሰውን ወዮታ የሚገልጽ ቢሆንም ስለ ይሖዋ ሕዝቦች መልሶ መቋቋም የሚያወሳ የሚያጽናና ሐሳብም ይዟል። በእስራኤል ምድር የወዮታ ሸክም ለመናገር የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበር። በዘመኑ ብልጽግና እንዲሁም የቅንጦት ኑሮ ይታይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ልቅ አኗኗር በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። ሕዝቡ የይሖዋን ሕግ ዘንግቶ ነበር። ከመጠን በላይ እንደ በሰለ ፍሬ መበስበስ እንደጀመሩና ወደ ጥፋት እየተቃረቡ መሆናቸውን እንዳያስተውሉ ብልጽግናቸው አሳውሯቸው ነበር። አሞጽ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአሥሩ ነገዶች መንግሥት ከደማስቆ ወዲያ በግዞት እንደሚወሰድ ተንብዮአል። በዚህ ትንቢቱ የይሖዋን ጻድቅነትና ልዕልና ከፍ ከፍ ያደረገ ሲሆን “ጌታ እግዚአብሔር” ወይም ሉዓላዊ ጌታ የሚለውን መግለጫ 21 ጊዜ ተጠቅሞበታል።—አሞጽ 1:8
4 ይህም ሆነ ሌሎቹ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው የአሞጽ ትንቢት ትክክለኛ መሆኑን ይመሰክራል። በተጨማሪም ነቢዩ በእስራኤል ዙሪያ የነበሩት ጠላት ብሔራት ማለትም ሶርያውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣ ጢሮሳውያን፣ ኤዶማውያን፣ አሞናውያንና ሞዓባውያን በጥፋት እሳት እንደሚበሉ ተንብዮአል። እነዚህ ጠላት ብሔራት በየተራ መውደቃቸው በታሪክ የተመዘገበ ሐቅ ነው። የይሁዳና የእስራኤል አካሄድ ደግሞ ከእነዚህ ብሔራትም የከፋ ነበር። ምክንያቱም የይሖዋን አምልኮ ትተው የሐሰት አምልኮ መከተል ጀምረው ነበር። የእስራኤል የመጨረሻ ጠንካራ ምሽግ የሆነው የሰማርያ ከተማ በስልምናሶር አምስተኛ ይመራ በነበረው የአሦራውያን ሠራዊት ከተከበበ በኋላ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦር እጅ ወደቀ። (2 ነገ. 17:1-6) ይሁዳ እህት ብሔር በሆነችው በእስራኤል መንግሥት ላይ ከደረሰው ቅጣት ሳትማር በመቅረቷ እርስዋም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጠፋች።
5 አሞጽ እስራኤላውያንን በቅንጦት ስለተሞላ አኗኗራቸው አውግዟቸዋል። ባለጠጎቹ የተትረፈረፈ ምግብ የሚበሉባቸውና የወይን ጠጅ የሚጠጡባቸው “በዝሆን ጥርስ ያጌጡ ቤቶች” ለመሥራት ሲሉ ድሆችን ያታልሉና ይዘርፉ ነበር። (አሞጽ 3:15፤ 5:11, 12፤ 6:4-7) አርኪኦሎጂስቶች በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ብልጽግና እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ አግኝተዋል። በሰማርያ በተደረገ ቁፋሮ በዝሆን ጥርስ የተሠሩ በርካታ ዕቃዎች ወጥተዋል። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አርኪኦሎጂካል ኤክስካቬሽንስ ኢን ዘ ሆሊ ላንድ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ሁለት ዋና ዋና ክፍሎችን መለየት ይቻላል። 1. በሐውልቱ ላይ በደንብ ጉብ ብለው እንዲታዩ ተደርገው የተቀረጹ ጽላቶችና . . . 2. በትንሹ ብቻ ጉብ ብሎ በሚታይ መንገድ ተቀርጸው በፈርጦችና በባለ ቀለም መስተዋቶች ያጌጡ እንዲሁም በወርቅ የተለበጡ ጽላቶች አሉ። . . . የዝሆን ጥርሶቹ የፊንቃውያን የሥነ ጥበብ ውጤት እንደሆኑ የሚታመን ሲሆን የእስራኤል ነገሥታት ይገለገሉባቸው ለነበሩት የቤተ መቅደስ ዕቃዎች መለበጫ ሆነው ያገለገሉ ሳይሆኑ አይቀሩም። መጽሐፍ ቅዱስ አክዓብ ‘ከዝሆን ጥርስ ስለሠራው ቤት’ ከመናገሩም በላይ (1 ነገ. 22:39 የ1954 ትርጉም) አሞጽ በተናገረው የተግሣጽ ቃል ውስጥ የተገለጸው ‘ከዝሆን ጥርስ የተሠራ አልጋ’ በሰማርያ የነበረውን የቅንጦት ኑሮ ያመለክታል (6:4)።”a
6 የአሞጽ መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ መሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖር አይችልም። እስጢፋኖስ በሐዋርያት ሥራ 7:42, 43 ላይ ከአሞጽ ትንቢት ሦስት ቁጥሮችን ጠቅሶ በራሱ አባባል የተናገረው ሐሳብ እንዲሁም ያዕቆብ በሐዋርያት ሥራ 15:15-18 ላይ ከዚህ መጽሐፍ መጥቀሱ የአሞጽ መጽሐፍ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑን ያረጋግጣሉ።—አሞጽ 5:25-27፤ 9:11, 12
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
13 የዘመናችን መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን አሞጽ ለእስራኤል፣ ለይሁዳና ለአጎራባች አገሮች የማስጠንቀቂያ መልእክት ያወጀበትን ምክንያት በማስተዋል ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። የይሖዋን ሕግ የሚያቃልሉ፣ ድሆችን የሚያታልሉና የሚጨቁኑ፣ ስግብግቦች የሆኑና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗር የሚከተሉ እንዲሁም ጣዖት የሚያመልኩ ሁሉ የይሖዋን ሞገስ አያገኙም። ቢሆንም ይሖዋ እንደዚህ ካለው አካሄድ ተመልሰው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ይቅር ይላል፤ ምሕረቱንም ያሳያቸዋል። በዚህ ክፉ ዓለም ካለው አቋማችንን የሚያበላሽ ወዳጅነት መራቃችንና “እኔን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ” የሚለውን የይሖዋ ማሳሰቢያ መከተላችን ጥበብ ይሆናል።—5:4, 6, 14
14 እስጢፋኖስ በሰማዕትነት በሞተበት ጊዜ ከአሞጽ ትንቢት በመጥቀስ ተናግሮ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በግዞት የተወሰዱት እንደ ሞሎክና ሬምፉም የመሰሉትን ባዕድ አማልክት በማምለካቸው እንደሆነ ለአይሁዳውያኑ አሳሰባቸው። ታዲያ እነዚህ አይሁዶች አሞጽ የተናገራቸውን ቃላት በድጋሚ በመስማታቸው ተጠቅመዋል? የለም አልተጠቀሙም! በጣም ተቆጥተው እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው በመግደል በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰውን ጥፋት በራሳቸው ላይ አምጥተዋል።—አሞጽ 5:25-27፤ ሥራ 7:42, 43
15 በእስራኤል፣ በይሁዳና በሌሎች ብሔራት ላይ በደረሰው ቅጣት ፍጻሜያቸውን ያገኙትን ትንቢቶች ብቻ ሳይሆን ስለ መታደስ ዘመን የተነገሩትን የአሞጽ ትንቢቶች አፈጻጸም ብንመረምር እንጠቀማለን። ይሖዋ በአሞጽ በኩል በተናገረው ቃል መሠረት የእስራኤል ግዞተኞች በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባድማ ሆነው የቆዩትን ከተሞቻቸውን መልሰው ለመሥራትና በዚያ ለመኖር እንዲሁም ወይናቸውንና አትክልቶቻቸውን ለማልማት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።—አሞጽ 9:14፤ ዕዝራ 3:1
16 ይሁን እንጂ በሐዋርያት ዘመንም የአሞጽ ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን ይህም አጽናንቷቸዋል። ያዕቆብ፣ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ስለመሰብሰባቸው በመንፈስ ተነሳስቶ ሲናገር ይህ ሁኔታ በአሞጽ 9:11, 12 ላይ የተተነበየ መሆኑን ገልጿል። ‘የፈረሰው የዳዊት ቤት ስለመገንባቱ’ የተነገረው ትንቢት ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን እንዳገኘና “ይኸውም የቀሩት ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉ፣ ስሜን የተሸከሙ አሕዛብም እንዲሹኝ ነው” ብሎ ይሖዋ እንደተናገረ ገልጿል። በእርግጥም ስምዖን ጴጥሮስ ለተረከው አዲስ ክስተት፣ ማለትም አምላክ “ለስሙ የሚሆን ወገን” ከአሕዛብ እየወሰደ ለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሆን ጥቅስ ነው።—ሥራ 15:13-19
17 የዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “የአባቱን የዳዊትን ዙፋን” የሚወርስና ለዘላለም የሚነግሥ “የዳዊት ልጅ” መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላም ቦታ ተገልጿል። (ሉቃስ 1:32, 33፤ 3:31) ስለዚህ የአሞጽ ትንቢት ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን የሚፈጸምበትን ሁኔታ ያመለክታል። የአሞጽ የመደምደሚያ ቃላት ‘የዳዊት ድንኳን’ በሚነሳበት ጊዜ የሚኖረውን ብልጽግና አስደናቂ በሆነ መንገድ ከመግለጻቸውም በላይ የአምላክን መንግሥት ዘላለማዊነት አበክረው ይናገራሉ:- “‘በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤ ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛ አይነቀሉም’ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።” ይሖዋ “የዳዊትን ድንኳን” ሙሉ በሙሉ በሚያድስበት ጊዜ ምድር በዘላለማዊ በረከት ትሞላለች!—አሞጽ 9:13-15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a 1978 ጀሩሳሌም፣ ገጽ 1046