የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 54—1 ጢሞቴዎስ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- መቄዶንያ
ተጽፎ ያለቀው:- ከ61–64 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ሉቃስ፣ ስለ ጳውሎስ ሕይወት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ያሰፈረው ዘገባ የሚደመደመው ጳውሎስ ለቄሣር ይግባኝ ካለ በኋላ በሮም ሆኖ መልሱን ሲጠብቅ ነው። ዘገባው፣ ጳውሎስ በተከራየው ቤት ውስጥ እንደሚኖርና ወደ እሱ ለሚመጡት ሁሉ “ማንም ሳይከለክለው . . . በፍጹም ግልጽነት” ስለ አምላክ መንግሥት እንደሚያስተምር ይገልጻል። (ሥራ 28:30, 31) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ “እንደ ወንጀለኛ እስከ መታሰር ድረስ መከራን እየተቀበልሁ ነው” በማለት የጻፈ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ እንደሚገደል ተናግሯል። (2 ጢሞ. 2:9፤ 4:6-8) እንዴት የሚያስገርም ለውጥ ነው! በመጀመሪያው ዘገባ ላይ እንደ ተከበረ እስረኛ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን በሁለተኛው ላይ ግን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሯል። ጳውሎስ በሮም ሁለት ዓመት ካሳለፈ በኋላ በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስለነበረበት ሁኔታ በሚገልጸው በሉቃስ ዘገባና ጳውሎስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ስለ ራሱ ሁኔታ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ምን ተከስቶ ነበር?
2 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች፣ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና ለቲቶ የጻፋቸው ደብዳቤዎች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከሸፈነው ጊዜ ጋር አለመጣጣማቸው ጳውሎስ ለቄሣር ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ተፈትቶ ይሆናል ወደሚል መደምደሚያ አድርሷቸዋል። ዘ ኒው ዌስትሚንስተር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል:- “የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመዝጊያ ጥቅስ፣ ሐዋርያው ታስሮ በነበረበት ጊዜ ተፈርዶበት ሞቷል ከሚለው ግምታዊ ሐሳብ ይልቅ ከዚህኛው አመለካከት [ጳውሎስ ሁለት ዓመት ከታሰረ በኋላ ተለቋል ከሚለው] ጋር ይበልጥ ይስማማል። ሉቃስ፣ ሐዋርያው ማንም ሳይከለክለው ሥራውን ያከናውን እንደነበር ማጉላቱ የጳውሎስ አገልግሎት ወደ ማብቂያው እየተቃረበ እንዳልነበር እንድናስብ ያደርገናል።”a እንግዲያው አንደኛ ጢሞቴዎስ የተጻፈው ከ61-64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ማለትም ጳውሎስ ከመጀመሪያው የሮም እስር በተፈታበትና ለመጨረሻ ጊዜ መልሶ በታሰረበት ጊዜ መካከል ይመስላል።
3 ጳውሎስ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ከጢሞቴዎስና ከቲቶ ጋር በመሆን የሚስዮናዊነት አገልግሎቱን እንደቀጠለ ምንም አያጠራጥርም። አንዳንዶች እንደሚገምቱት ጳውሎስ ስፔን ስለ መድረሱ በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም። ጳውሎስ “በስተ ምዕራብ እስካለው ጠረፍ ድረስ” መሄዱን የሮሙ ክሌመንት (በ95 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) የጻፈ ሲሆን ይህ ደግሞ ስፔንን ይጨምር ይሆናል።b
4 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የላከውን የመጀመሪያ ደብዳቤ የጻፈው የት ሆኖ ነበር? አንደኛ ጢሞቴዎስ 1:3 እንደሚገልጸው ጳውሎስ ወደ መቄዶንያ ሲሄድ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን አንዳንድ የጉባኤ ጉዳዮችን እንዲከታተል ዝግጅት አድርጎ ነበር። ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ መቄዶንያ እያለ ኤፌሶን ለሚገኘው ለጢሞቴዎስ ደብዳቤ የጻፈለት ይመስላል።
5 ለጢሞቴዎስ የተላኩት ሁለቱን ደብዳቤዎች ጳውሎስ እንደጻፋቸውና የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንደሆኑ ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ተቀባይነት አግኝቷል። እንደ ፖሊካርፕ፣ ኢግናቲየስና የሮሙ ክሌመንት የመሳሰሉትን ጨምሮ ቀደምት ክርስቲያን ጸሐፊዎች በሙሉ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፤ እንዲሁም ደብዳቤዎቹ የጳውሎስ መልእክቶች እንደሆኑ ተቆጥረው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት መቶ ዓመታት በነበሩት ዝርዝሮች ውስጥ ተጠቃለዋል። አንድ ባለ ሥልጣን፣ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ስለላካቸው ደብዳቤዎች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[የእነዚህን ደብዳቤዎች ያህል] እውነተኛ ስለመሆናቸው ጠንካራ ማስረጃ ያላቸው [የአዲስ ኪዳን] መጻሕፍት ጥቂት ናቸው፤ . . . በመሆኑም በሐቀኝነታቸው ላይ የሚሰነዘር ተቃውሞ፣ የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበውን ጠንካራ ማስረጃ የሚቃረን ዘመናዊ ሐሳብ እንደሆነ ተደርጎ መታየት አለበት።”c
6 ጳውሎስ ይህን የመጀመሪያ ደብዳቤ ለጢሞቴዎስ የጻፈው በጉባኤ ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን አንዳንድ ድርጅታዊ አሠራሮችን በግልጽ ለማስቀመጥ ነበር። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ከሐሰት ትምህርቶች ራሱን እንዲጠብቅ እንዲሁም ወንድሞች እንዲህ ያለውን ‘የውሸት ዕውቀት’ እንዳይቀበሉ እንዲያጠናክራቸው ማሳሰቢያ መስጠት ያስፈልግ ነበር። (1 ጢሞ. 6:20) የንግድ ማዕከል በነበረችው የኤፌሶን ከተማ፣ ቁሳዊ ሀብት የማሳደድና ‘በገንዘብ ፍቅር’ የመጠመድ ፈተና ስለነበር ጳውሎስ በዚህ ረገድም ምክር መለገሱ ወቅታዊ ነበር። (6:10) ጢሞቴዎስ ለዚህ ሥራ የሚጠቅመው ግሩም ተሞክሮ እንደነበረውና ሥልጠና እንዳገኘ ምንም ጥርጥር የለውም። አባቱ ግሪካዊ ሲሆን እናቱ ደግሞ አምላክን የምትፈራ አይሁዳዊት ነበረች። ጢሞቴዎስ ስለ ክርስትና ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው መቼ እንደሆነ በትክክል አይታወቅም። በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ ወይም በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጀመሪያ አካባቢ ጳውሎስ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ላይ ልስጥራንን በጎበኘበት ወቅት ጢሞቴዎስ (ምናልባት ዕድሜው በአሥራዎቹ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይሆናል) “በልስጥራንና በኢቆንዮን በነበሩት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት ነበረው።” በዚህም ምክንያት ጳውሎስ፣ እሱና ሲላስ በሚያደርጉት ጉዞ ጢሞቴዎስም አብሯቸው እንዲሄድ ዝግጅት አደረገ። (ሥራ 16:1-3) ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ ከጻፋቸው 14 ደብዳቤዎች ውስጥ በ11ዱ ላይ እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በስም ተጠቅሷል። ጳውሎስ፣ ምንጊዜም ለጢሞቴዎስ እንደ አባት ያስብለት የነበረ ሲሆን በርከት ላሉ ጊዜያትም የተለያዩ ጉባኤዎችን እንዲጎበኝና እንዲያገለግል ልኮት ነበር፤ ይህም ጢሞቴዎስ በሚስዮናዊነት መስክ ጥሩ ሥራ እንዳከናወነና ከባድ ኃላፊነቶችን ለመሸከም ብቁ እንደነበረ የሚያረጋግጥ ነው።—1 ጢሞ. 1:2፤ 5:23፤ 1 ተሰ. 3:2፤ ፊልጵ. 2:19
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
15 ይህ ደብዳቤ ከንቱ በሆኑ ግምታዊ አስተሳሰቦችና በፍልስፍና ላይ በተመሠረቱ ንትርኮች ውስጥ ለሚገቡ ሁሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ‘ስለ ቃላት መከራከር’ ከኩራት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንዲህ ካለው ነገር መራቅ አለብን፤ ጳውሎስ እንደተናገረው “እነዚህ ነገሮች በእምነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሥራ ይልቅ ክርክርን” ስለሚያነሳሱ ለክርስቲያናዊ እድገት እንቅፋት ናቸው። (6:3-6፤ 1:4) እንደዚህ ያሉት ክርክሮችና የሥጋ ሥራዎች ‘ከቡሩክ እግዚአብሔር የክብር ወንጌል ጋር የሚስማማውን ጤናማ የሆነውን ትምህርት ይጻረራሉ።’—1:10, 11
16 የገንዘብ ፍቅር በተጠናወታት የኤፌሶን ከተማ የሚኖሩት ክርስቲያኖች ፍቅረ ንዋይንና ማዘናጊያዎቹን እንዲዋጉ ምክር ያስፈልጋቸው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስም እንዲህ ዓይነት ምክር ሰጥቷቸዋል። “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው” የሚለው የጳውሎስ ምክር ባለንበት ዓለም ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ቢሆንም ይህን ምክር ሰምተው በሥራ የሚያውሉት ጥቂቶች ናቸው! ከዚህ በተቃራኒ ግን ክርስቲያኖች ይህን ምክር ምንጊዜም ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው የሕይወት ጉዳይ ነው። ጎጂ ከሆነው የፍቅረ ንዋይ ወጥመድ መሸሽ አለባቸው፤ እንዲሁም “ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ” ማድረግ አይኖርባቸውም።—6:6-12, 17-19
17 የጳውሎስ ደብዳቤ እንደሚያሳየው ጢሞቴዎስ ለወጣት ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ ነበር። በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ በዕድሜ ወጣት ቢሆንም በመንፈሳዊ ጎልምሶ ነበር። የበላይ ተመልካች ለመሆን ይጣጣር የነበረ ሲሆን ብዙ መብቶችን በማግኘትም ተባርኳል። ያም ቢሆን በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ቀናተኛ ወጣት አገልጋዮች ሁሉ እሱም እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮርና እነሱንም በትጋት መፈጸም ነበረበት። ክርስቲያናዊ እድገት በማድረግ ደስተኛ ሆነው ለመቀጠል ለሚፈልጉ ሁሉ “ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህና” የሚለው የጳውሎስ ምክር ወቅታዊ ነው።—4:15, 16
18 ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ደብዳቤ ሥርዓት ላለው የአምላክ ዝግጅት አድናቆት እንዲያድርብን ያደርጋል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ በጉባኤ ውስጥ ቲኦክራሲያዊ አንድነት እንዲኖር ድርሻቸውን መወጣት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። (2:8-15) ከዚያም የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን ይዘረዝራል። ልዩ ኃላፊነት ይዘው የሚያገለግሉ ሁሉ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን መንፈስ ቅዱስ በዚህ መንገድ ገልጾልናል። በተጨማሪም ደብዳቤው ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮች በሙሉ እነዚህን መሥፈርቶች እንዲያሟሉ ሲያበረታታ “ማንም ኤጲስቆጶስነትን ቢፈልግ፣ መልካም ሥራን ይመኛል” ይላል። (3:1-13) በዚህ ደብዳቤ ላይ፣ የበላይ ተመልካቹ የተለያየ ዕድሜና ፆታ ላላቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው እንደሚገባ እንዲሁም በኃጢአት የተከሰሱ ሰዎችን ጉዳይ በምሥክሮች ፊት ማየትን በሚመለከት ማብራሪያ ተሰጥቷል። ጳውሎስ፣ በመስበክና በማስተማር የሚተጉ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር እንደሚገባቸው ለማጉላት ሁለት ጊዜ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደ ባለ ሥልጣን አድርጎ በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መጽሐፍም፣ ‘እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሠር፤’ ደግሞም፣ ‘ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል’ ይላልና።”—1 ጢሞ. 5:1-3, 9, 10, 19-21, 17, 18፤ ዘዳ. 25:4፤ ዘሌ. 19:13
19 ጳውሎስ ይህን ሁሉ ግሩም ምክር ከሰጠ በኋላ ‘ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶችም ጌታ ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ’ ትእዛዙን ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጨምሮ ገልጿል። ደብዳቤው፣ ክርስቲያኖች ይህን የመንግሥት ተስፋ መሠረት በማድረግ “መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ . . . እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው” እንዲያከማቹ ጥብቅ ምክር በመስጠት ይደመድማል። (1 ጢሞ. 6:14, 15, 18, 19) በእርግጥም በአንደኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ የሚገኙት ግሩም መመሪያዎች በሙሉ እጅግ ጠቃሚ ናቸው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a 1970፣ በኤች ኤስ ጌማን የተዘጋጀ ገጽ 721
c ኒው ባይብል ዲክሽነሪ፣ ሁለተኛ እትም፣ 1986 በጄ ዲ ዳግላስ የተዘጋጀ ገጽ 1203