የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bsi08-2 ገጽ 24-25
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 63—2 ዮሐንስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 63—2 ዮሐንስ
  • “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 17
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 17
bsi08-2 ገጽ 24-25

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 63​—⁠2 ዮሐንስ

ጸሐፊው:- ሐዋርያው ዮሐንስ

የተጻፈበት ቦታ:- በኤፌሶን ወይም በአቅራቢያው

ተጽፎ ያለቀው:- በ98 ከክ.ል.በኋላ ገደማ

ሁለተኛው የዮሐንስ መልእክት አጭር ከመሆኑ የተነሳ በአንድ ገጽ ፓፒረስ ላይ ሊጻፍ ይችላል። ያም ሆኖ ይህ ደብዳቤ ብዙ ቁም ነገሮችን ይዟል። ደብዳቤው የተላከው “ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ” ነው። በዚያ ዘመን “ኪሪያ” (በግሪክኛ “እመቤት” ማለት ነው) የሚለው ቃል፣ መጠሪያ ስም ሆኖ ያገለግል ስለነበር አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ደብዳቤው የተጻፈው በዚህ ስም ትጠራ ለነበረች ግለሰብ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች ‘ለተመረጠች እመቤት’ ብሎ የጻፈው ለአንድ የክርስቲያን ጉባኤ እንደሆነ ያስባሉ። ምናልባት ይህን ያደረገው አሳዳጆች በቀላሉ እንዳይረዱት አስቦ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ከሆነ፣ በመጨረሻው ቁጥር ላይ የተጠቀሰው፣ “የእኅትሽ ልጆች” ሰላምታ ያቀርቡልሻል የሚለው ሐሳብ ከሌላ ጉባኤ የተላከ ሰላምታን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ሁለተኛው መልእክት ለአንድ ግለሰብ ወይም ጉባኤ የተላከ ስለሚሆን እንደ መጀመሪያው ደብዳቤ አጠቃላይ ይዘት ያለው መልእክት እንዲያስተላልፍ የታቀደ አይደለም።—ቁጥር 1

2 የዚህ መልእክት ጸሐፊ ዮሐንስ ስለመሆኑ የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። ጸሐፊው ራሱን “ሽማግሌው” ሲል ጠርቷል። ይህ መግለጫ ከዮሐንስ ሁኔታ ጋር ይስማማል የምንለው በዕድሜ ስለገፋ ብቻ ሳይሆን እንደ “አዕማድ” (ገላ. 2:9) ከሚቆጠሩት መካከል አንዱ መሆኑና ከሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ በሕይወት ያለው እሱ መሆኑ በእርግጥም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ “ሽማግሌ” ነበር ሊያስብለው ስለሚችል ጭምር ነው። ዮሐንስ በሰፊው ይታወቅ ስለነበር ለአንባቢዎቹ እሱን በተመለከተ ሌላ ተጨማሪ መግለጫ መስጠት አላስፈለገውም። የዚህ መልእክት አጻጻፍ ከመጀመሪያው የዮሐንስ መልእክትና ከዮሐንስ ወንጌል ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ የመልእክቱ ጸሐፊ እሱ መሆኑን ይጠቁማል። ልክ እንደ መጀመሪያው መልእክት ሁለተኛውም የተጻፈው በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ፣ በኤፌሶን ወይም በዚያ አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛና ሦስተኛ የዮሐንስ መልእክቶችን በሚመለከት የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “በጥቅሉ ሲታይ ካላቸው የመመሳሰል ሁኔታ አንጻር ሁለቱ መልእክቶች የመጀመሪያው መልእክት ከተጻፈ ብዙም ሳይቆይ በኤፌሶን ተጽፈዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ሁለተኛውና ሦስተኛው መልእክቶች በአንደኛ ዮሐንስ ውስጥ በዝርዝር በተቀመጡ የተለያዩ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በመንተራስ አንድን ዓይነት ምግባር በተመለከተ የተጻፉ ናቸው።”a በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረው ኢራኒየስ ከሁለተኛው የዮሐንስ ደብዳቤ መጥቀሱና በተመሳሳይ ዘመን የኖረው የእስክንድርያው ክሌመንት ይህንን መልእክት የተቀበለው መሆኑ ለትክክለኛነቱ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው።b የዮሐንስ መልእክቶች በሙራቶሪያን ፍራግመንት ላይ ተጠቅሰዋል።

3 እንደ መጀመሪያው መልእክት ሁሉ ዮሐንስ ይህን ደብዳቤ እንዲጽፍ ምክንያት የሆነው ሐሰተኛ አስተማሪዎች በክርስትና እምነት ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት ነበር። ዮሐንስ አንባቢዎቹ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ለይተው በማወቅ ከእነሱ እንዲርቁ አስጠንቅቋቸዋል፤ እንዲሁም እርስ በርስ በመዋደድ በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

5 በዘመናችን እንደሚታየው ሁሉ በዮሐንስ ጊዜም ግልጽና ያልተወሳሰበ የሆነውን የኢየሱስን ትምህርት ተከትለው መኖር አልዋጥ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች የነበሩ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን የሚያረካላቸውን፣ በሌሎች ዘንድ ውዳሴ የሚያስገኝላቸውንና ከዓለማዊ ፈላስፎች ተርታ የሚያስመድባቸውን ነገር ማግኘት ይፈልጉ ነበር። ስለሆነም የራስ ወዳድነት ስሜታቸውን ለማርካት ሲሉ የክርስቲያን ጉባኤን ከመበከልና ከመከፋፈል ወደኋላ አላሉም። ዮሐንስ፣ በፍቅር ላይ እንዲሁም ከአብና ከወልድ ፈቃድ ጋር በሚስማማው ትክክለኛ እውቀት ላይ ለተመሠረተው የክርስቲያን ጉባኤ የአንድነት መንፈስ ከፍተኛ ግምት ይሰጥ ነበር። ዛሬም፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሰፈረው ውጪ የራሳቸውን ትምህርት በማስተማር ክህደት ከሚያስፋፉ ጋር ባልንጀርነት ባለመመሥረትና እነዚህን ሰዎች ሰላም ባለማለት የጉባኤውን አንድነት መጠበቅ ይኖርብናል። የአምላክን ትእዛዛት ጠብቀን መጓዛችንን ከቀጠልንና በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ኅብረት ከሚገኘው ሙሉ ደስታ ከተቋደስን “ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ [የሚገኘው] ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር” እንደሚሆን ልንተማመን እንችላለን። (ቁጥር 3) በእርግጥም ሁለተኛው የዮሐንስ መልእክት ክርስቲያናዊ አንድነት የሚያስገኘውን በረከት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በ1981 በድጋሚ የታተመው፣ ጥራዝ 4 ገጽ 955

b በጄ. ዲ. ዳግላስ የተዘጋጀው ኒው ባይብል ዲክሽነሪ ሁለተኛ እትም፣ 1986 ገጽ 605

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ