የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 65—ይሁዳ
ጸሐፊው:- ይሁዳ
የተጻፈበት ቦታ:- ፍልስጥኤም (?)
ተጽፎ ያለቀው:- በ65 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
በይሁዳ ይኖሩ የነበሩት ወንድሞች አደገኛ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር! ክርስቶስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በነበሩት ዓመታት ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የሚከተሏቸው አንዳንድ ልማዶች ወደ ጉባኤ ሰርገው ገብተው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ከ14 ዓመታት ገደማ በፊት አስጠንቅቆ እንደነበረው እምነትን የሚያዳክመው ጠላት ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ገብቶ ነበር። (2 ተሰ. 2:3) ወንድሞች ንቁ መሆንና ከዚህ አደጋ ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ቀጥተኛ የሆኑና ኃይል ያላቸው ሐሳቦችን ያዘለው የይሁዳ መልእክት ለዚህ ጥያቄ መልሱን ይሰጠናል። ይሁዳ በቁጥር 3 እና 4 ላይ እንደሚከተለው በማለት የራሱን አቋም በግልጽ አስፍሯል:- ‘ፈሪሀ አምላክ የሌላቸው የአምላካችንን ጸጋ በርኩሰት የሚለውጡ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ስለገቡ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።’ ጤናማው ትምህርትና ሥነ ምግባር የተመሠረቱበት መሠረት የመፍረስ አደጋ ተደቅኖበት ነበር። ይሁዳ ወንድሞቹ ብርቱ የእምነት ትግል እንዲያደርጉ ለመርዳት ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ የቀረበለት ያህል ሆኖ ተሰምቶት ነበር።
2 ይሁን እንጂ ይሁዳ ማን ነው? በመክፈቻው ላይ ያለው ሐሳብ እንደሚጠቁመን ደብዳቤውን የጻፈው “የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ” ሲሆን የተጻፈው ደግሞ “ለተጠሩት” ነው። ከመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ 12 ሐዋርያት መካከል ሁለቱ ይሁዳ በሚለው ስም ይጠሩ የነበረ መሆኑ ይሁዳ ሐዋርያ ነበር ለማለት ያስችለናል? (ሉቃስ 6:16) ይሁዳ ሐዋርያ ስለመሆኑ የገለጸው ነገር የለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሐዋርያት በተናገረ ጊዜ “እነርሱ” በማለት መጻፉ ራሱን ከዚያ ውጭ ማድረጉ እንደነበር በግልጽ ያሳያል። (ይሁዳ 17, 18) ከዚህም በላይ ራሱን “የያዕቆብ ወንድም” ብሎ የጠራ ሲሆን ወንድሜ ያለው የያዕቆብን መልእክት የጻፈውንና የኢየሱስ ወንድም የሆነውን ያዕቆብን መሆኑ ግልጽ ነው። (ቁጥር 1) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ለነበረው ጉባኤ እንደ “አዕማድ” የነበረ በመሆኑና በሰፊው ይታወቅ ስለነበር ይሁዳ ከእሱ ጋር ያለውን ዝምድና በመጥቀስ ራሱን አስተዋውቋል። ይህ ማለት ደግሞ ይሁዳ የኢየሱስ ወንድም እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን ይህን የሚያረጋግጡ ሌሎች ዘገባዎችም ይገኛሉ። (ገላ. 1:19፤ 2:9፤ ማቴ. 13:55፤ ማር. 6:3) ይሁን እንጂ ይሁዳ ከፍተኛ ግምት የሰጠው ከኢየሱስ ጋር ለነበረው የሥጋ ዝምድና ሳይሆን ለመንፈሳዊ ዝምድናው ነበር። በመሆኑም “የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ” መሆኑን በትሕትና ተናግሯል።—1 ቆሮ. 7:22፤ 2 ቆሮ. 5:16፤ ማቴ. 20:27
3 ይህ መልእክት በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተጻፈው ሙራቶሪያን ፍራግመንት በተባለው ሰነድ ውስጥ ተጠቅሶ መገኘቱ መልእክቱ ትክክለኛ መሆኑን ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ (በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኖረው) የእስክንድርያው ክሌመንት ይህ መልእክት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን አምኖ ተቀብሏል። ኦሪጀን መልእክቱ “በጥቂት መሥመሮች ላይ የሰፈረ ቢሆንም በሰማያዊው ጸጋ ጤናማ ቃል የተሞላ” እንደሆነ ገልጿል።a ተርቱሊያንም ቢሆን መልእክቱ ትክክለኛ መሆኑን ያምን ነበር። የይሁዳ ደብዳቤ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የሌሎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑ ምንም አያጠራጥርም።
4 ይሁዳ መልእክቱን የጻፈው “ለተጠሩት” መሆኑና የትኛውንም ጉባኤ ወይም ግለሰብ ለይቶ አለመጥቀሱ ደብዳቤው ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሠራጭ አጠቃላይ ይዘት ያለው መልእክት እንደሆነ ያሳያል። የተጻፈበት ቦታ ባይጠቀስም በፍልስጥኤም ሳይጻፍ አይቀርም። መቼ እንደተጻፈም በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁን እንጂ መልእክቱ የተጻፈው የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ከብዙ ጊዜ በኋላ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ይሁዳ በጊዜው ለነበሩት ክርስቲያኖች “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን” እንዲያስታውሱ ሲያሳስባቸው 2 ጴጥሮስ 3:3ን እየጠቀሰ ሳይሆን አይቀርም። (ይሁዳ 17, 18) ከዚህም በላይ በይሁዳ መልእክትና በሁለተኛው የጴጥሮስ መልእክት ሁለተኛ ምዕራፍ መካከል ብዙ መመሳሰል ይታያል። ይህም ይሁዳና ጴጥሮስ መልእክቶቻቸውን የጻፉት በተመሳሳይ ጊዜ ላይ እንደሆነና በወቅቱ በጉባኤዎች ላይ አንዣብቦ የነበረው ችግር ሁለቱንም በጣም አሳስቧቸው እንደነበር ይጠቁማል። በመሆኑም የተጻፈው በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ እንደሚሆን ተገምቷል። ይሁዳ፣ በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሴስቲየስ ጋለስ የአይሁዳውያኑን ዓመጽ ለማስቆም ዘመቻ ስለ ማድረጉም ሆነ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌም ስለ መጥፋቷ የተናገረው ነገር አለመኖሩ ይህን ሐሳብ የሚደግፍ ነው። ይሁዳ በኃጢአተኞች ላይ የተወሰዱትን አንዳንድ መለኮታዊ የፍርድ እርምጃዎች በመልእክቱ ላይ የገለጸ ሲሆን በወቅቱ ኢየሩሳሌም ወድቃ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስም ስለዚሁ ሁኔታ አስቀድሞ ተናግሮ ስለነበር ሐሳቡን ለማጠናከር ይህን የፍርድ እርምጃ ምሳሌ አድርጎ ይጠቅስ ነበር።—ይሁዳ 5-7፤ ሉቃስ 19:41-44
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
8 ይሁዳ ራሱ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ወዳጆቹን’ ለማስጠንቀቅ፣ ለመምከር፣ ለማበረታታት፣ ለማስተማርና ለማሳሰብ ጠቃሚ ሆነው አግኝቷቸዋል። ወደ ጉባኤው ሾልከው የገቡ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች የሚፈጽሙትን ከባድ ኃጢአት ለማጋለጥ ሲል ከዳተኞች የነበሩትን እስራኤላውያን፣ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት እንዲሁም የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎችን የመሳሰሉ ምሳሌዎችን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ጠቅሷል። ይሁዳ እንዲህ ባሉ ምሳሌዎች በመጠቀም የብልግና ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ቅጣት እንደሚደርስባቸው አስረድቷል። ብልሹ የሆኑ ሰዎችን፣ አእምሮ ከሌላቸው እንስሳት ጋር ያወዳደራቸው ሲሆን በቃየን መንገድ እንደሚሄዱ፣ የበለዓምን ስህተት ለመድገም እንደሚጣደፉና በዓመጸኛ ንግግራቸው ምክንያት እንደ ቆሬ እንደሚጠፉ ገልጿል። እንዲሁም “በተፈጥሮ መጽሐፍ” ላይ በግልጽ የሚታዩ አንዳንድ ጉዳዮችን ጠቅሷል። ቀጥተኛ ምክሮችን የያዘው የይሁዳ መልእክት ከሌሎቹ ‘ቅዱሳን መጻሕፍት’ መካከል የሚመደብ ነው። ስለሆነም መልእክቱን፣ “በመጨረሻው ዘመን” ልናሳየው የሚገባንን ባሕርይ አስመልክተው ማሳሰቢያ ከሚሰጡን ከሌሎቹ መጻሕፍት ጋር በማመሳከር ልናጠናው ይገባል።—ይሁዳ 17, 18, 5-7, 11-13፤ ዘኁ. 14:35-37፤ ዘፍ. 6:4፤ 18:20, 21፤ 19:4, 5, 24, 25፤ 4:4, 5, 8፤ ዘኁ. 22:2-7, 21፤ 31:8፤ 16:1-7, 31-35
9 ከውጭ የሚመጣው ተቃውሞና ተጽዕኖ የክርስትናን እድገት ሊገታው አልቻለም፤ ይሁን እንጂ ወንድሞች በመካከላቸው ባሉ ምግባረ ብልሹ ግለሰቦች የተነሳ ስጋት ላይ ወደቁ። ይህ፣ በባሕር ውስጥ ያለ ስውር አለት ለመርከብ አደገኛ እንደሆነ ሁሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው እነዚህ ሰዎች መላውን ጉባኤ አደጋ ላይ ጥለው ነበር። ይሁዳ ሁኔታው ከዚህ የበለጠ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ስለተገነዘበ ‘ስለ እምነት መጋደል’ አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ተናግሯል። የይሁዳ ደብዳቤ በዚያን ወቅት እጅግ አስፈላጊ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ጉልህ ጠቀሜታ አለው። በአሁኑ ጊዜም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ያስፈልገናል። ዛሬም እምነታችንን ከአደጋ ልንጠብቀውና ልንጋደልለት ይገባል፤ ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ድርጊቶች ማስወገድም ይኖርብናል። የሚቻል ከሆነ ደግሞ፣ ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎችን በምሕረት ዓይን በመመልከት ልንረዳቸውና ‘ከእሳት ነጥቀን ልናወጣቸው’ ይገባል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ፣ መንፈሳዊነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንዲሁም ለእውነተኛ አምልኮ ለመቆም ሲሉ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነት ላይ መገንባታቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። ትክክለኛ የሆኑትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሙሉ ልብ መደገፍና በጸሎት ወደ አምላክ መቅረብ ይገባቸዋል። ‘ለሥልጣን’ ተገቢ አመለካከት በመያዝ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለውን ከአምላክ የተሰጠ ሥልጣን ማክበር ያስፈልጋቸዋል።—ይሁዳ 3, 23, 8
10 “በደመ ነፍስ የሚነዱ መንፈስ የሌላቸው” ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት ፈጽሞ የማይገቡ ከመሆኑም ሌላ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ ያሉትንም አደጋ ላይ ይጥላሉ። (ይሁዳ 19፤ ገላ. 5:19-21) ጉባኤው እነዚህን ሰዎች በሚመለከት ለወድሞችና እህቶች ማስጠንቀቂያ መስጠትና እንዲወገዱ ማድረግ ይኖርበታል! እንዲህ ከሆነ፣ ወዳጆች ለሆኑት “ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር” ይበዛላቸዋል። እነሱም ‘ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳቸውን የጌታቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ሲጠባበቁ ሳለ’ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር ይጠነቀቃሉ። አዳኝ የሆነው አምላክ የመንግሥቱን ወራሾች ‘በክብሩ ፊት ነውር የሌለባቸው አድርጎ በደስታ’ ያቆማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ከይሁዳ ጋር በመተባበር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል “ክብር፣ ግርማ፣ ኀይልና ሥልጣን” ለአምላክ ይሁን እንደሚሉ ምንም ጥርጥር የለውም።—ይሁዳ 2, 21, 24, 25
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በቢ. ኤም. ሜትዝገር የተዘጋጀው ዘ ካነን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት፣ 1987, ገጽ 138