ጥናት 16
አዎንታዊና የሚያበረታታ
ኢዮብ 16:5
ፍሬ ሐሳብ፦ በችግሮች ላይ ሳይሆን በመፍትሔያቸው ላይ ትኩረት አድርግ፤ አድማጮችህን ለተግባር የሚያነሳሱ ነጥቦችን ጥቀስ።
ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ስለ አድማጮችህ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ወንድሞችህና እህቶችህ ይሖዋን ማስደሰት እንደሚፈልጉ እምነት ሊኖርህ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ምክር መስጠት ሊያስፈልግህ ይችላል፤ ያም ሆኖ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ፣ ምክር ከመስጠትህ በፊት አመስግናቸው።
ብዙ ችግር አታውራ። አንድን ችግር የምትጠቅሰው ለንግግርህ ጠቃሚ ሆኖ ካገኘኸው ብቻ ሊሆን ይገባል። የንግግርህ አጠቃላይ መንፈስ የሚያበረታታ መሆን ይኖርበታል።
የአምላክን ቃል በሚገባ ተጠቀምበት። ይሖዋ ለሰው ልጆች ያደረገውን፣ አሁን እያደረገ ያለውንና ወደፊት የሚያደርገውን ነገር አበክረህ ግለጽ። ንግግርህ አድማጮችህን የሚያበረታታና ተስፋ የሚፈነጥቅላቸው ሊሆን ይገባል።