የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es21 ገጽ 7-17
  • ጥር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ ጥር 1
  • ቅዳሜ፣ ጥር 2
  • እሁድ፣ ጥር 3
  • ሰኞ፣ ጥር 4
  • ማክሰኞ፣ ጥር 5
  • ረቡዕ፣ ጥር 6
  • ሐሙስ፣ ጥር 7
  • ዓርብ፣ ጥር 8
  • ቅዳሜ፣ ጥር 9
  • እሁድ፣ ጥር 10
  • ሰኞ፣ ጥር 11
  • ማክሰኞ፣ ጥር 12
  • ረቡዕ፣ ጥር 13
  • ሐሙስ፣ ጥር 14
  • ዓርብ፣ ጥር 15
  • ቅዳሜ፣ ጥር 16
  • እሁድ፣ ጥር 17
  • ሰኞ፣ ጥር 18
  • ማክሰኞ፣ ጥር 19
  • ረቡዕ፣ ጥር 20
  • ሐሙስ፣ ጥር 21
  • ዓርብ፣ ጥር 22
  • ቅዳሜ፣ ጥር 23
  • እሁድ፣ ጥር 24
  • ሰኞ፣ ጥር 25
  • ማክሰኞ፣ ጥር 26
  • ረቡዕ፣ ጥር 27
  • ሐሙስ፣ ጥር 28
  • ዓርብ፣ ጥር 29
  • ቅዳሜ፣ ጥር 30
  • እሁድ፣ ጥር 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
es21 ገጽ 7-17

ጥር

ዓርብ፣ ጥር 1

ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19

ሁሉም ታማኝ የአምላክ ሕዝቦች፣ የተሰጣቸውን የአገልግሎት ተልእኮ ‘በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይፈልጋሉ። (2 ጢሞ. 4:5) ምክንያቱም ይህ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ልናከናውነው ከምንችለው ከየትኛውም ሥራ ይበልጥ አስፈላጊና አጣዳፊ ነው። ሆኖም የምንፈልገውን ያህል ጊዜ ለአገልግሎቱ መስጠት ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚሻሙብን ሌሎች አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ስንል በቀን ውስጥ ረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅብን ይሆናል። ከዚህም ሌላ ተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነት ሊኖርብን አሊያም ከሕመም፣ ከመንፈስ ጭንቀት ወይም የዕድሜ መግፋት ከሚያስከትላቸው ችግሮች ጋር እየታገልን ሊሆን ይችላል። ያለንበት ሁኔታ ለይሖዋ አገልግሎት የምናውለውን ጊዜ የሚገድብብን ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ኢየሱስ ሁላችንም የመንግሥቱን ፍሬ በእኩል መጠን ማፍራት እንደማንችል ያውቃል። (ማቴ. 13:23) ይሖዋ ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በእሱ አገልግሎት የምናከናውነውን ማንኛውንም ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ዕብ. 6:10-12፤ w19.04 2 አን. 1-3

ቅዳሜ፣ ጥር 2

ዲያብሎስ . . . ውሸታምና የውሸት አባት [ነው]።—ዮሐ. 8:44

ሰይጣን ሙታንን አስመልክቶ የሚያስፋፋቸው ውሸቶች በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያስከትላሉ። ከእነዚህ ውሸቶች መካከል፣ የሞቱ ሰዎች በእሳት እንደሚቃጠሉ የሚገልጸው የሐሰት ትምህርት ይገኝበታል። እንደነዚህ ያሉት ትምህርቶች የአምላክን ስም ያጎድፋሉ። እንዴት? የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ የዲያብሎስ ዓይነት ባሕርይ ያለው እንዲመስል ስለሚያደርጉ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ምን የሚሰማው ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት የጭካኔ ድርጊት እንደሚጠላ ይናገራል። (ኤር. 19:5) ሰይጣን ሞትን አስመልክቶ የሚናገራቸው ውሸቶች፣ ሰዎች ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ እንዳይሰጡ አድርገዋል። (ማቴ. 20:28) ሰይጣን የሚናገረው ሌላው ውሸት ደግሞ ‘ሰዎች የማይሞት ነፍስ አላቸው’ የሚለው ነው። ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ሁሉም ሰው ለዘላለም መኖር ይችላል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ እኛ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል ክርስቶስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ መስጠቱ አስፈላጊ አልነበረም ማለት ነው። የክርስቶስ መሥዋዕት ይሖዋና ኢየሱስ ለሰው ዘር ያሳዩት ከሁሉ የላቀ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አንዘንጋ። (ዮሐ. 3:16፤ 15:13) ውድ የሆነውን የቤዛውን ስጦታ ዋጋ የሚያሳጡት ትምህርቶች፣ ይሖዋንና ልጁን ምንኛ ያሳዝኗቸው ይሆን! w19.04 14 አን. 1፤ 16 አን. 8-9

እሁድ፣ ጥር 3

“ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” ተብሏልና፤ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።—1 ቆሮ. 2:16

ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ተመዝግበው የሚገኙት ምን ላይ ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተናገራቸውና ያደረጋቸው በርካታ ነገሮች በአራቱ ወንጌሎች ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ያላቸው ሰዎች በመንፈስ ተመርተው የጻፏቸው ሌሎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ደግሞ ኢየሱስ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አስተሳሰብ እንድናውቅ ይረዱናል። የኢየሱስ ትምህርቶች ሁሉንም የሕይወታችንን ዘርፎች ይዳስሳሉ። በመሆኑም ‘የክርስቶስ ሕግ’ በቤታችን፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የምናደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ይነካል። (ገላ. 6:2) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ይህን ሕግ መማር እንችላለን። በመንፈስ መሪነት በተጻፉት በእነዚህ ዘገባዎች ላይ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ መመሪያዎችና ትእዛዞች መሠረት ሕይወታችንን በመምራት ይህን ሕግ እንደምንታዘዝ እናሳያለን። የክርስቶስን ሕግ ስንታዘዝ ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ሁሉ ምንጭ የሆነውን አፍቃሪ አምላካችንን ይሖዋን እንታዘዛለን።—ዮሐ. 8:28፤ w19.05 3 አን. 6-7

ሰኞ፣ ጥር 4

ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።—2 ጢሞ. 3:13

ሰዎች ዲያብሎስን የሚያስደስት ድርጊት መፈጸማቸው እንዴት የሚያሳዝን ነው! ሆኖም ይሖዋ፣ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ጠንቅቆ ያውቃል። የሚደርስብንን ሥቃይ በሚገባ ይረዳል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማጽናኛ ይሰጠናል። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን በማምለካችን በጣም ታድለናል፤ “በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።” (2 ቆሮ. 1:3, 4) በተለይም ፆታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወላጆቻቸው ችላ ያሏቸው ወይም በሚቀርቧቸው ሰዎች ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ልጆች ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ከሁሉ የላቀው የመጽናኛ ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (መዝ. 27:10) ይሖዋ በሚወዷቸው ሰዎች በደል የተፈጸመባቸውን ሁሉ እንደሚቀበል ዳዊት እምነት ነበረው። ይሖዋ እንዲህ የሚያደርገው እንዴት ነው? በታማኝ አገልጋዮቹ አማካኝነት ነው። ከእኛ ጋር አብረው ይሖዋን የሚያገለግሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን፣ መንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አብረውት ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን ወንድሞቼ፣ እህቶቼና እናቶቼ በማለት ጠርቷቸዋል።—ማቴ. 12:48-50፤ w19.05 15-16 አን. 8-9

ማክሰኞ፣ ጥር 5

ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10

በምናጠናበት ጊዜ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ከሚገቡን ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? በየዕለቱ የአምላክን ቃል የምናጠናበት ጊዜ መመደብ እንዳለብን ምንም አያጠያይቅም። ለሳምንታዊው የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሚመደቡት ምዕራፎች እንዲቀንሱ የተደረገው ባነበብነው ነገር ላይ የምናሰላስልበትና ተጨማሪ ምርምር የምናደርግበት በቂ ጊዜ እንድናገኝ ነው። ግባችን የተመደበውን ክፍል አንብበን መጨረስ ብቻ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ልባችንን እንዲነካውና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ እንዲረዳን መፍቀድ ሊሆን ይገባል። (መዝ. 19:14) በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የምናጠናው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ነው። በመሆኑም ለጥቅሶቹ በተለይም በጉባኤ ላይ ለሚነበቡት ጥቅሶች ልዩ ትኩረት ስጡ። በጥቅሶቹ ላይ ያሉት ቁልፍ ቃላት ወይም ሐረጎች የአንቀጹን ዋና ሐሳብ የሚደግፉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። በተጨማሪም ጊዜ ወስዳችሁ በጥቅሶቹ ላይ ለማሰላሰልና እነዚህን ጥቅሶች በግል ሕይወታችሁ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ጥረት አድርጉ።—ኢያሱ 1:8፤ w19.05 27 አን. 5፤ 28 አን. 9

ረቡዕ፣ ጥር 6

የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው።—ዮሐ. 4:34

ኢየሱስ ለአገልግሎት የነበረው አመለካከት ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበኩ ሥራ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። በተቻለው መጠን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ሲል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ከቤት ወደ ቤትም ሆነ ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ቦታዎች ይሰብክ ነበር። የኢየሱስ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ያተኮረው በአገልግሎቱ ላይ ነበር። እኛም ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ በመከተል በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለሰዎች ምሥራቹን የምንሰብክበት አጋጣሚ እንፈልጋለን። በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመካፈል ስንል የራሳችንን ምቾት መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ነን። (ማር. 6:31-34፤ 1 ጴጥ. 2:21) በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ልዩ አቅኚ፣ የዘወትር አቅኚ ወይም ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ። ሌሎች ደግሞ አዲስ ቋንቋ ለመማር ወይም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ለማገልገል የሚያስችላቸውን እርምጃ ወስደዋል። ሆኖም አብዛኛው የወንጌላዊነት ሥራ የሚከናወነው አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ በሚጥሩ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነው። ሁኔታችን ምንም ሆነ ምን፣ ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። w19.04 4 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ጥር 7

ይሖዋ ሆይ፣ የአፌ ቃልና በልቤ የማሰላስለው ነገር አንተን ደስ የሚያሰኝ ይሁን።—መዝ. 19:14

እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በትንሹም ቢሆን በሌሎች የመቅናት ወይም የምቀኝነት ዝንባሌ አለኝ?’ (1 ጴጥ. 2:1) ‘በአስተዳደጌ፣ በትምህርት ደረጃዬ ወይም በሀብቴ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እኩራራለሁ?’ (ምሳሌ 16:5) ‘እኔ ያሉኝ ነገሮች የሌሏቸውን ወይም ከእኔ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጌ እመለከታለሁ?’ (ያዕ. 2:2-4) ‘የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸው ነገሮች ይማርኩኛል?’ (1 ዮሐ. 2:15-17) ‘የሥነ ምግባር ብልግና እና ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች ያስደስቱኛል?’ (መዝ. 97:10፤ 101:3፤ አሞጽ 5:15) ራስህን ለመመርመር ለሚያስችሉት ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ፣ ለውጥ ማድረግ ያለብህ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ይጠቁምሃል። ጓደኞቻችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። (ምሳሌ 13:20) በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን የሚረዱን አይደሉም። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ግን ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞች እናገኛለን። “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” የምንነቃቃው ወይም የምንነሳሳው በስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ነው።—ዕብ. 10:24, 25 ግርጌ፤ w19.06 12 አን. 13-14

ዓርብ፣ ጥር 8

በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል።—ምሳሌ 19:11

የይሖዋ ዓላማ በአሁኑ ጊዜ እንደምናየው በችግርና በመከራ የተሞላ ሕይወት አልነበረም። በመሆኑም አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመው፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢናገር የሚያስገርም አይሆንም። (ኢዮብ 6:2, 3) ግለሰቡ ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ እኛ የተሳሳተ ነገር ቢናገርም እንኳ በዚህ ቶሎ መናደድ ወይም እንዲህ በማለቱ በእሱ ላይ መፍረድ የለብንም። አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጠመው ሰው፣ አንዳንድ ጊዜ ምክር ወይም እርማት ሊያስፈልገውም ይችላል። (ገላ. 6:1) ሽማግሌዎች ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? የኤሊሁን ምሳሌ መከተላቸው ይጠቅማቸዋል፤ ኤሊሁ የኢዮብን ስሜት እንደተረዳለት በሚያሳይ መንገድ በጥሞና አዳምጦታል። (ኢዮብ 33:6, 7) ኤሊሁ ምክር የሰጠው የኢዮብን አመለካከት ከተረዳለት በኋላ ነው። የኤሊሁን ምሳሌ የሚከተሉ ሽማግሌዎች፣ ምክር የሚሰጡትን ሰው በትኩረት የሚያዳምጡት ከመሆኑም ሌላ ግለሰቡ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ካደረጉ በኋላ ምክር ቢሰጡ ግለሰቡ ምክሩን መቀበል ይበልጥ ቀላል ይሆንለታል። w19.06 22-23 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ጥር 9

ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።—ሥራ 5:29

በእገዳ ሥር ብትሆን ይሖዋን ማምለክህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው? ቅርንጫፍ ቢሮው ለጉባኤህ ሽማግሌዎች መመሪያዎችና ጠቃሚ ሐሳቦች ይሰጣል። ቅርንጫፍ ቢሮው ከሽማግሌዎች ጋር መገናኘት ካልቻለ ደግሞ ሽማግሌዎቹ አንተም ሆንክ የጉባኤው አባላት በሙሉ ይሖዋን ማምለካችሁን እንድትቀጥሉ ይረዷችኋል። በመጽሐፍ ቅዱስ እና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር የሚስማማ መመሪያ ይሰጧችኋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ዕብ. 10:24, 25) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 65:13, 14፤ ሉቃስ 12:42-44) በመሆኑም የይሖዋ ድርጅት የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ማበረታቻ እንድታገኝ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አንተስ ምን ማድረግ ትችላለህ? በእገዳ ሥር ከሆንክ መጽሐፍ ቅዱስህን እንዲሁም ሌሎች ጽሑፎችህን የምትደብቅበት ቦታ አዘጋጅ። የታተሙትንም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጁትን እነዚህን ውድ መንፈሳዊ ጽሑፎች በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉበት ቦታ ላይ ፈጽሞ አትተዋቸው። ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ይዘን ለመቀጠል እያንዳንዳችን አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን። w19.07 10 አን. 10-11

እሁድ፣ ጥር 10

በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ።—1 ቆሮ. 9:22

ላለፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት በዓለም ላይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖት ነበራቸው። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ግን በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው። ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖት እንደሌላቸው በግልጽ ይናገራሉ። (ማቴ. 24:12) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳንዶች ሕይወታቸው ያተኮረው ተድላን በማሳደድ ላይ ስለሆነ ወይም የኑሮ ጭንቀት ትኩረታቸውን ስለከፋፈለባቸው ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 8:14) ቀደም ሲል ሃይማኖተኛ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በአምላክ መኖር ማመናቸውን ትተዋል። ሌሎች በአምላክ መኖር ቢያምኑም ሃይማኖት ጊዜ ያለፈበት፣ አላስፈላጊ እንዲሁም ከሳይንስና ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣም እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ከጓደኞቻቸውና ከአስተማሪዎቻቸው አሊያም ከመገናኛ ብዙኃን ይሰማሉ፤ በአምላክ መኖር ለማመን የሚያበቃ አሳማኝ ማስረጃ ግን አግኝተው አያውቁም። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ገንዘብና ሥልጣን ለማግኘት በሚስገበገቡ የሃይማኖት መሪዎች ድርጊት የተነሳ ሃይማኖትን ጠልተዋል። በአንዳንድ አገሮች፣ መንግሥታት በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥለዋል። w19.07 20 አን. 1-2

ሰኞ፣ ጥር 11

ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ፤ እንዲሁም ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ አለመሆኑን አውቃችሁ ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።—1 ቆሮ. 15:58

ክርስቲያኖች ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ለማዳበር አካላዊ ጥንካሬ አያስፈልጋቸውም። እንዲያውም አካላዊ ጥንካሬያቸው እየቀነሰ የመጣ በርካታ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን ለመቀጠል ያላቸው ቁርጠኝነት ይበልጥ ተጠናክሯል። (2 ቆሮ. 4:16) አንተም ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ስታገለግል ቆይተህ ይሆናል፤ በአሁኑ ወቅት ግን የጤንነትህ ሁኔታ በማሽቆልቆሉ የቀድሞውን ያህል ማድረግ አትችል ይሆናል። ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ እሱን በታማኝነት በማገልገል ያከናወንከውን ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ ሁን። (ዕብ. 6:10) በአሁኑ ወቅት ያለህበትን ሁኔታ በተመለከተ ደግሞ፣ ለይሖዋ ያለን ፍቅር የሚለካው በእሱ አገልግሎት ማከናወን በምንችለው መጠን ላይ እንዳልሆነ አስታውስ። ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን እንደምንወደው የሚያሳየው አዎንታዊ አመለካከት መያዛችንና አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረጋችን ነው። (ቆላ. 3:23) ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ ከምንችለው በላይ አይጠብቅብንም።—ማር. 12:43, 44፤ w19.08 3 አን. 6፤ 5-6 አን. 11-12

ማክሰኞ፣ ጥር 12

ሰዎች መልካም ሥራችሁን [እንዲያዩ] ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።—ማቴ. 5:16

ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሚያከናውኑት “መልካም ሥራ” አማካኝነት ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባል። (ማቴ. 5:14, 15፤ 1 ጴጥ. 2:12) የትዳር ጓደኛሽ የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ፣ ከጉባኤሽ አባላት ጋር ተገናኝቶ ያውቃል? በስብሰባዎች ላይ አብሮሽ እንዲገኝ ጋብዢው። (1 ቆሮ. 14:24, 25) የቤተሰባችን አባላት በሙሉ አብረውን ይሖዋን ቢያገለግሉ ደስ ይለናል። ይሁንና የቤተሰባችን አባላት የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ ወደ እውነት ላይመጡ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመን በእነሱ ውሳኔ ራሳችንን ልንወቅስ አይገባም። ደግሞም የምናምንበትን ነገር እንዲቀበል ማንንም ሰው ማስገደድ አንችልም። ይሁን እንጂ የቤተሰባችሁ አባላት፣ ይሖዋን ማገልገላችሁ ምን ያህል ደስታ እንዳስገኘላችሁ መመልከታቸው ሊያሳድርባቸው የሚችለውን በጎ ተጽዕኖ አቅልላችሁ አትመልከቱት። ስለ እነሱ ጸልዩ። በዘዴ መሥክሩላቸው። እነሱን ከመርዳት ወደኋላ አትበሉ! (ሥራ 20:20) ይሖዋ ጥረታችሁን እንደሚባርክላችሁ እርግጠኛ ሁኑ። የቤተሰባችሁ አባላት መልእክታችሁን ለመስማት ፈቃደኛ ከሆኑ ደግሞ መዳን ያገኛሉ! w19.08 18-19 አን. 15-17

ረቡዕ፣ ጥር 13

የሰውነት መብራት ዓይን ነው። ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል።—ማቴ. 6:22

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ትኩረታችንን ከሚከፋፍሉ ነገሮች በመራቅ ኑሯችንን ቀላል አሊያም በአንድ ግብ ወይም ዓላማ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ እንዳለብን መናገሩ ነበር። ኢየሱስ ራሱ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ ላይ በማድረግ ምሳሌ ትቶልናል፤ ደቀ መዛሙርቱንም ትኩረታቸው ምንጊዜም በአገልግሎታቸውና በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲሆን አስተምሯቸዋል። እኛም ‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ በመፈለግ’ ሕይወታችን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር የምናደርግ ከሆነ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ማቴ. 6:33) በአገልግሎታችን ላይ ትኩረት ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ኑሯችንን ቀላል ማድረግ ነው፤ ይህም ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁትና እንዲወዱት ለመርዳት የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ እንድናገኝ ይረዳናል። ለምሳሌ በሳምንቱ ውስጥ ለአገልግሎት የምናውለው ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንድንችል ሰብዓዊ ሥራ በምንሠራበት ሰዓት ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንችል ይሆን? ረዘም ያለ ጊዜ ከሚወስዱብን መዝናኛዎች ላይ የተወሰነ ጊዜ መቀነስ እንችል ይሆን? w19.04 5-6 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ጥር 14

ከፍ ባለውና ቅዱስ በሆነው ስፍራ እኖራለሁ፤ ደግሞም የተሰበረ ልብ ካለውና መንፈሱ ከተደቆሰው ጋር እሆናለሁ።—ኢሳ. 57:15

በይሖዋ አገልግሎት የበርካታ ዓመታት ተሞክሮ ያላቸው ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገልግሎት ምድብ ለውጥ አጋጥሟቸዋል። ለእነዚህ ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ብዙዎቹ በዚያ የአገልግሎት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ስለቆዩ ለአገልግሎት ምድባቸው ከፍተኛ ፍቅር እንደነበራቸው ግልጽ ነው። አንዳንዶች ከተሰማቸው ሐዘን ለማገገምና ከአዲሱ ሁኔታቸው ጋር ለመላመድ ጊዜ ወስዶባቸዋል። ሆኖም ቀስ በቀስ፣ ያጋጠማቸውን ከባድ ሁኔታ መወጣት ችለዋል። በዚህ ረገድ የረዳቸው ምንድን ነው? ከሁሉ በላይ፣ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ነው። ራሳቸውን የወሰኑት ለአንድ ዓይነት ሥራ፣ መብት ወይም ኃላፊነት ሳይሆን ለአምላክ እንደሆነ ተገንዝበዋል። (ቆላ. 3:23) በየትኛውም ሁኔታ ሥር ይሖዋን በትሕትና ማገልገላቸው ያስደስታቸዋል። ይሖዋ ‘ስለ እነሱ እንደሚያስብ’ ስለሚያውቁ ‘የሚያስጨንቃቸውን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ይጥላሉ።’ (1 ጴጥ. 5:6, 7) ግሩም ባሕርይ የሆነውን ትሕትናን ማዳበራችን ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ይጠቅማል። ትሕትና፣ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሻለ መንገድ ለመወጣት ያስችለናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ ወዳለው አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። w19.09 6-7 አን. 15-17

ዓርብ፣ ጥር 15

የይሖዋ መመሪያዎች ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ . . . እነሱን መጠበቅ ትልቅ ወሮታ አለው።—መዝ. 19:8, 11

ይሖዋ ዳዊትን የቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን የመላው እስራኤል ብሔር ራስ አድርጎ ሾሞታል። ዳዊት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ይህን ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀም ከባድ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። (2 ሳሙ. 11:14, 15) ሆኖም የተሰጠውን ተግሣጽ በመቀበል ለይሖዋ እንደሚገዛ አሳይቷል። በጸሎት አማካኝነት የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል። እንዲሁም ይሖዋ የሰጠውን ምክር ለመታዘዝ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። (መዝ. 51:1-4) ከዚህም በተጨማሪ ትሑት በመሆን ከወንዶች ብቻ ሳይሆን ከሴቶችም ጭምር ምክር ተቀብሏል። (1 ሳሙ. 19:11, 12፤ 25:32, 33) ዳዊት ከስህተቱ የተማረ ሲሆን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት መርቷል። ለይሖዋ መገዛት ምን ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ተገንዝቦ ነበር። በዛሬው ጊዜም ለይሖዋ ሥልጣን በሚገዙና የእሱን ፍቅራዊ ምክር ችላ በሚሉ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ይታያል። ለይሖዋ የሚገዙ ሰዎች “ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ።”—ኢሳ. 65:13, 14፤ w19.09 17 አን. 15፤ 19 አን. 21

ቅዳሜ፣ ጥር 16

ከዚህ በኋላ አየሁ፤ . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ . . . በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር።—ራእይ 7:9

በ1935 የይሖዋ ምሥክሮች እጅግ ብዙ ሕዝብ “በዙፋኑና በበጉ ፊት [ለመቆም]” ቃል በቃል በሰማይ መሆን እንደማያስፈልገው ከዚህ ይልቅ ይህ አገላለጽ ምሳሌያዊ እንደሆነ ተገነዘቡ። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሚኖሩት ምድር ላይ ቢሆንም የይሖዋን ሥልጣን በመቀበልና ለእሱ ሉዓላዊነት በመገዛት ‘በዙፋኑ ፊት እንደቆሙ’ ያሳያሉ። (ኢሳ. 66:1) እንዲሁም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ‘በበጉ ፊት ይቆማሉ።’ በማቴዎስ 25:31, 32 ላይ ተመሳሳይ አገላለጽ እናገኛለን፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ክፉዎችን ጨምሮ “ሕዝቦች ሁሉ” በክብራማ ዙፋኑ ላይ በተቀመጠው በኢየሱስ ‘ፊት እንደሚሰበሰቡ’ ተገልጿል። እነዚህ ሕዝቦች የሚሰበሰቡት ምድር ላይ እንጂ ሰማይ ላይ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ የተደረገው ማስተካከያ ምክንያታዊ ነው። ይህ ማስተካከያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ብዙ ሕዝብ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ የማይናገረው ለምን እንደሆነ ግልጽ ያደርጋል። በሰማይ ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ቃል የተገባለት አንድ ቡድን ብቻ ነው፤ የዚህ ቡድን አባላት ከኢየሱስ ጋር ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው የሚገዙት’ 144,000 ሰዎች ናቸው።—ራእይ 5:10፤ w19.09 28 አን. 9

እሁድ፣ ጥር 17

እናንተ ለእሱ ታማኝ የሆናችሁ ሁሉ፣ ይሖዋን ውደዱ!—መዝ. 31:23

ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲለዩ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጣችን ብቻውን በቂ አይደለም። ከእውነተኛው ሃይማኖት ይኸውም ከይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ጎን ለመቆም ቁርጥ አቋም መውሰድ አለብን። ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሁለት መንገዶች እስቲ እንመልከት። አንደኛ፣ የይሖዋን የጽድቅ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መደገፋችንን መቀጠል ይኖርብናል። ዓለም የሚመራባቸውን መሥፈርቶች ልንቀበል አይገባም። ለምሳሌ ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ብልግና አንደግፍም፤ ይህም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጋብቻንና ግብረ ሰዶማውያን የሚከተሏቸውን የአኗኗር ዘይቤዎች ያካትታል። (ማቴ. 19:4, 5፤ ሮም 1:26, 27) ሁለተኛ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ይሖዋን ማምለካችንን መቀጠል አለብን። በስብሰባ አዳራሾቻችን፣ ካልተቻለ ደግሞ በግል ቤቶች ውስጥ ሌላው ቀርቶ በድብቅ እንኳ በመሰብሰብ እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ለአምልኮ አብረን የመሰብሰብ ልማዳችንን በፍጹም መተው የለብንም። እንዲያውም “ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን [ማድረግ]” ይኖርብናል።—ዕብ. 10:24, 25፤ w19.10 15-16 አን. 6-7

ሰኞ፣ ጥር 18

ይሖዋ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ [ነው]።—ዘፀ. 34:14

ይሖዋ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል፤ ለደስታችን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ደግሞ መዝናኛ ነው። እንዲያውም የአምላክ ቃል “ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም” ይላል። (መክ. 2:24) ይሁንና በዓለም ላይ ያለው አብዛኛው መዝናኛ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። ሰዎች ልል የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ እንዲሁም የአምላክ ቃል የሚያወግዛቸውን ነገሮች አቅልለው እንዲመለከቱ ይባስ ብሎም እነዚህን ነገሮች እንዲወዱ ያበረታታል። ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንፈልጋለን፤ በመሆኑም በአንድ በኩል “ከይሖዋ ማዕድ” እየተመገብን በሌላ በኩል ደግሞ “ከአጋንንት ማዕድ” መቋደስ አንችልም። (1 ቆሮ. 10:21, 22) በአንድ ገበታ ላይ አብሮ መመገብ ብዙውን ጊዜ የወዳጅነት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ዓመፅን፣ መናፍስታዊ ድርጊትን፣ የሥነ ምግባር ብልግናን ወይም ሌሎች ሥጋዊ አስተሳሰቦችንና ምኞቶችን የሚያስፋፉ መዝናኛዎችን የምንመርጥ ከሆነ የአምላክ ጠላቶች ካዘጋጁት ገበታ እየተመገብን ያለን ያህል ነው። እንዲህ ማድረግ ራሳችንን የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያበላሽብናል። w19.10 26 አን. 2፤ 29-30 አን. 11-12

ማክሰኞ፣ ጥር 19

ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ።—2 ጴጥ. 1:21

አንድ ባሕረኛ ነፋሱ እንዲረዳው ከፈለገ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይኖርበታል። በመጀመሪያ፣ መርከቡ ነፋሱ በሚነፍስበት አቅጣጫ እንዲጓዝ ማድረግ አለበት። ደግሞም መርከቡ ከነፋሱ አቅጣጫ ርቆ ወደብ ላይ ከቆመ ወደፊት መሄድ አይችልም። ሁለተኛ፣ መርከበኛው ሸራውን ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ይኖርበታል። ነፋሱ ቢኖርም እንኳ መርከቡ ወደፊት መጓዝ የሚችለው ነፋሱ ሸራውን ካገኘው ብቻ እንደሆነ የታወቀ ነው። በተመሳሳይ እኛም በይሖዋ አገልግሎት መጽናት የምንችለው የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ካገኘን ብቻ ነው። ይህ መንፈስ እንዲረዳን ከፈለግን ሁለት እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። በመጀመሪያ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት በሚያስችሉን እንቅስቃሴዎች መካፈል አለብን። ሁለተኛ፣ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች አቅማችን የፈቀደውን ያህል የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ በሌላ አባባል ሸራችንን ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ይኖርብናል። (መዝ. 119:32) እንዲህ ካደረግን መንፈስ ቅዱስ እንደ ማዕበል ያሉ ተቃውሞዎችንና ፈተናዎችን ተቋቁመን ወደፊት እንድንገፋ ይረዳናል። w19.11 9 አን. 8፤ 10 አን. 11

ረቡዕ፣ ጥር 20

ሰላሜን እሰጣችኋለሁ።—ዮሐ. 14:27

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን ላይ በጣም ተጨንቆ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በክፉ ሰዎች እጅ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሊገደል ነው። ሆኖም ኢየሱስን ያስጨነቀው ከፊቱ የሚጠብቀው ሞት ብቻ አልነበረም። አባቱን በጣም የሚወደው ከመሆኑም ሌላ እሱን ማስደሰት ይፈልጋል። ኢየሱስ ይህን ፈታኝ ወቅት በታማኝነት ከተወጣ የይሖዋ ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያውቃል። ኢየሱስ ሰዎችንም ይወድ ነበር፤ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው ታማኝነቱን ጠብቆ በመሞቱ ላይ እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ በጣም ተጨንቆ የነበረ ቢሆንም ውስጣዊ ሰላሙን አላጣም። ኢየሱስ “የአምላክ ሰላም” ማለትም አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ውድ ዝምድና በመመሥረቱ ምክንያት የሚያገኘው ውስጣዊ መረጋጋት ነበረው። ይህ ሰላም አእምሮውንና ልቡን አረጋግቶለታል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ማናችንም ብንሆን ኢየሱስ የደረሰበት ዓይነት ከባድ ፈተና እንደማይደርስብን የታወቀ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስን የሚከተል ማንኛውም ክርስቲያን ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመዋል። (ማቴ. 16:24, 25፤ ዮሐ. 15:20) በዚህም የተነሳ ልክ እንደ ኢየሱስ የምንጨነቅበት ጊዜ ይኖራል። w19.04 8 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ጥር 21

የመንፈስን እሳት አታጥፉ።—1 ተሰ. 5:19

‘በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ የመታቀፍ መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሕዝቦቹን እየባረከ እንደሆነ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ሰጥቶናል። በእርግጥም አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች አሉን። (1 ተሰ. 5:18) ታዲያ ይሖዋ የሚጠቀምበትን ድርጅት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የምናገኛቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ነው። በተጨማሪም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በመካፈል ድርጅቱን እንደምንደግፍ ማሳየት እንችላለን። (1 ቆሮ. 15:58) ይሖዋ የምናቀርበውን መሥዋዕት እንዲቀበለው በእሱ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ጥረት እናድርግ። ይሖዋን በአመስጋኝነት ስሜት ተነሳስተን እናገልግለው። ለይሖዋ ባለን ልባዊ ፍቅር ተነሳስተን ለእሱ ምርጣችንን መስጠታችንን እንቀጥል። እንዲሁም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እየባረከው ያለውን ድርጅት በሙሉ ልባችን እንደግፍ። እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ይሖዋ የእሱ ምሥክሮች እንድንሆን የሰጠንን መብት ከፍ አድርገን እንደምንመለከት እናሳያለን! w19.11 25 አን. 17-18

ዓርብ፣ ጥር 22

በእኔ የሚያምን ሁሉ . . . ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።—ዮሐ. 14:12

ኢየሱስ ይህን ሲል እንደ እሱ ተአምራት እንደምንፈጽም መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ተከታዮቹ የሚሸፍኑት የአገልግሎት ክልል ስፋት፣ የሚሰብኩላቸውና የሚያስተምሯቸው ሰዎች ብዛት እንዲሁም ይህን ሥራ የሚያከናውኑበት ጊዜ ከእሱ እንደሚበልጥ መናገሩ ነበር። ሰብዓዊ ሥራ የምትሠራ ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በሥራ ቦታዬ የምታወቀው ታታሪ ሠራተኛ በመሆኔ ነው? ሥራዬን በሰዓቱ ለመጨረስና አቅሜ በፈቀደው መጠን ጥሩ አድርጌ ለመሥራት እጥራለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች ‘አዎ’ የሚል መልስ ከሰጠህ የአሠሪህን አመኔታ ታተርፋለህ። በተጨማሪም አንተን የሚመለከቱ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማዳመጥ ሊነሳሱ ይችላሉ። ከስብከቱና ከማስተማሩ ሥራ ጋር በተያያዘ ደግሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የምታወቀው ትጉ በመሆኔ ነው? ለሰዎች ምሥራቹን ለመመሥከር በሚገባ እዘጋጃለሁ? ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ሳልዘገይ ተመላልሶ መጠየቅ አደርጋለሁ? በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች አዘውትሬ እካፈላለሁ?’ መልስህ ‘አዎ’ ከሆነ በሥራህ ደስታ ታገኛለህ። w19.12 5 አን. 14-15

ቅዳሜ፣ ጥር 23

ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።—ኤፌ. 5:33

ልጅ ለመውለድ የወሰኑ ባልና ሚስት፣ ‘መውለድ ያለብን መቼ ነው? እንዲኖረን የምንፈልገውስ ስንት ልጅ ነው?’ በሚሉት ሁለት አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ጥሩ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ውይይት ለማድረግ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው? እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል የምንለውስ ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ‘ልጅ እንውለድ ወይስ አንውለድ’ የሚለው ጉዳይ መወሰን ያለበት ትዳር ከመመሥረቱ በፊት ነው። ይህ ጊዜ ለውሳኔ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ ተጋቢዎቹ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ መሆን አለመሆናቸውን መወያየት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ከተጋቡ በኋላ ልጅ ሳይወልዱ ቢያንስ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ለመቆየት ወስነዋል፤ ምክንያቱም ልጆችን መንከባከብ ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል። ስለዚህ ልጅ ሳይወልዱ ለተወሰነ ጊዜ መቆየታቸው የትዳር ሕይወት ከሚያስከትለው ለውጥ ጋር ለመላመድና እርስ በርስ ይበልጥ ለመቀራረብ እንደሚያስችላቸው ይሰማቸዋል። w19.12 23 አን. 4-5

እሁድ፣ ጥር 24

እውነተኛ ወዳጅ . . . ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17

በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ውጥረት የሚፈጥሩ ይባስ ብሎም ስሜትን የሚጎዱ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች በጠና ታመዋል አሊያም የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተዋል። ሌሎች ደግሞ የቤተሰባቸው አባል ወይም የቅርብ ወዳጃቸው እውነትን መተዉ ጥልቅ ሐዘን አስከትሎባቸዋል። በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ብዙ ችግር የደረሰባቸው ክርስቲያኖችም አሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? ታማኝ ወዳጅ ሁኑ። ታማኝ ወዳጆች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ መሥዋዕት ይከፍላሉ። ፒተር የተባለ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ፒተር በፍጥነት እየተባባሰ የሚሄድና ሕይወቱን የሚያሳጣው ሕመም እንዳለበት ተነገረው። ባለቤቱ ካትሪን እንዲህ ብላለች፦ “ፒተር ስላለበት በሽታ በሰማንበት ቀን ወደ ሕክምና ቀጠሯችን የወሰዱን በጉባኤያችን የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ነበሩ። እነዚህ ባልና ሚስት ዜናውን እንደሰሙ፣ በዚህ አስጨናቂ ወቅት ምንጊዜም ከጎናችን ለመሆን ወሰኑ፤ ደግሞም እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ አልተለዩንም።” በእርግጥም የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት እንድንቋቋም የሚረዱ እውነተኛ ወዳጆች በእጅጉ ያጽናኑናል! w20.01 8 አን. 1፤ 9 አን. 5፤ 10 አን. 6

ሰኞ፣ ጥር 25

ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ . . . በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።—ሥራ 2:4

በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በደርብ ላይ ከተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርት አንዱ ብትሆን በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀባህ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አያድርብህም። (ሥራ 2:5-12) ይሁንና ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡት እንዲህ ባለ አስደናቂ መንገድ ነው? ደግሞስ ይህ የሚሆነው በሕይወታቸው ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው? አይደለም። በመጀመሪያ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ስለሚቀባበት ጊዜ እንመልከት። በጴንጤቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት፣ 120 ገደማ የሚሆኑት እነዚህ ክርስቲያኖች ብቻ አልነበሩም። በዚያው ዕለት ወደ በኋላ ላይ 3,000 የሚያህሉ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ቃል የገባውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የተቀቡት ሲጠመቁ ነው። (ሥራ 2:37, 38, 41) ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን ሁሉም ክርስቲያኖች፣ በተጠመቁበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል ማለት አይደለም። ሳምራውያን በመንፈስ የተቀቡት ከተጠመቁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። (ሥራ 8:14-17) ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ደግሞ የተቀቡት ገና ሳይጠመቁ ነበር፤ በእርግጥ ይህ የተለመደ ሁኔታ አይደለም።—ሥራ 10:44-48፤ w20.01 20-21 አን. 2-4

ማክሰኞ፣ ጥር 26

ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ።—ዮሐ. 17:26

በአራቱ የወንጌል ዘገባዎች ላይ ብቻ ኢየሱስ “አባት” የሚለውን መጠሪያ 165 ጊዜ ገደማ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ይህን ያህል ደጋግሞ የተናገረው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ሰዎች ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባት አድርገው እንዲመለከቱት ለመርዳት ነው። (ዮሐ. 17:25, 26) ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን ከያዘበት መንገድ ስለ እሱ ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ምንጊዜም የኢየሱስን ጸሎት ይሰማ ነበር። ጸሎቱን ከመስማትም ባለፈ ምላሽ ይሰጠው ነበር። (ዮሐ. 11:41, 42) ኢየሱስ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመው አባቱ እንደሚወደውና እንደሚደግፈው ተጠራጥሮ አያውቅም። (ሉቃስ 22:42, 43) አፍቃሪ አባት የሆነው ይሖዋ፣ ኢየሱስ ምንጊዜም የአባቱ ድጋፍ እንደማይለየው እንዲተማመን አድርጓል። (ማቴ. 26:53፤ ዮሐ. 8:16) ይሖዋ፣ ኢየሱስ ጨርሶ ጉዳት እንዳይደርስበት ባይጠብቀውም ፈተናዎችን በጽናት እንዲወጣ ረድቶታል። ኢየሱስም፣ የሚደርስበት ማንኛውም ዓይነት ጉዳት ጊዜያዊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ዕብ. 12:2) ይሖዋ የኢየሱስን ጸሎት በመስማት፣ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በማቅረብ፣ ሥልጠና በመስጠትና በመደገፍ ለእሱ ያለውን ፍቅር አሳይቷል።—ዮሐ. 5:20፤ 8:28፤ w20.02 3 አን. 6-7, 9

ረቡዕ፣ ጥር 27

ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ። . . . እንቅፋት አትሁኑ።—1 ቆሮ. 10:31, 32

በአንድ ዓይነት ልማድ መካፈል ይኖርብን እንደሆነና እንዳልሆነ ስንወስን፣ ውሳኔያችን በሌሎች በተለይም በእምነት ባልንጀሮቻችን ሕሊና ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ልናስብ ይገባል። ማንም በእኛ ምክንያት እንዲሰናከል አንፈልግም! (ማር. 9:42) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችንም ቢሆን ሳያስፈልግ ቅር ማሰኘት አይኖርብንም። ፍቅር፣ ሰዎችን አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለማነጋገር ያነሳሳናል፤ እንዲህ ማድረጋችን ደግሞ ይሖዋን ያስከብረዋል። ከሰዎች ጋር መጣላት ወይም ባሕላቸውን ማንቋሸሽ እንደሌለብን የታወቀ ነው። ፍቅር ኃይል እንዳለው አንዘንጋ! አፍቃሪ በመሆን ለሰዎች አሳቢነትና አክብሮት ስናሳይ፣ የሚቃወሙን ሰዎች አመለካከት እንኳ እንዲቀየር ልናደርግ እንችላለን። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችሁ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲታወቅ አድርጉ። (ኢሳ. 43:10) ቤተሰቦቻችሁና ጎረቤቶቻችሁ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች መሆናችሁን አስቀድመው ካወቁ፣ ሐዘን በሚደርስበት ወቅት በምትወስዱት አቋም ያን ያህል ላይበሳጩ ይችላሉ። የአምላክ ቃል ሞትን በተመለከተ የሚያስተምረውን እውነት ደግፈን በምንወስደው አቋም ፈጽሞ ልናፍር አይገባም።—ሮም 1:16፤ w19.04 17-18 አን. 14-16

ሐሙስ፣ ጥር 28

ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ።—1 ቆሮ. 15:9

አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አብረውት ነበሩ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ክርስቲያን የሆነው ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ነው። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ‘ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ’ ሆኖ ቢሾምም ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የመሆን ልዩ መብት አላገኘም። (ሮም 11:13፤ ሥራ 1:21-26) ጳውሎስ እነዚህን 12 ሐዋርያት ባገኙት መብትና ከኢየሱስ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ቅርርብ ከመመቅኘት ይልቅ ባለው ረክቶ ኖሯል። ባለን የምንረካና ትሑት ከሆንን እንደ ጳውሎስ፣ ይሖዋ ኃላፊነት የሰጣቸውን ሰዎች እናከብራለን። (ሥራ 21:20-26) ይሖዋ የተሾሙ ወንድሞች የክርስቲያን ጉባኤን እንዲመሩ ዝግጅት አድርጓል። እነዚህ ወንድሞች ፍጹማን ባይሆኑም ይሖዋ እንደ “ስጦታ” አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ኤፌ. 4:8, 11) እነዚህን የተሾሙ ወንድሞች ስናከብርና የሚሰጡንን መመሪያ በትሕትና ስንታዘዝ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ጠብቀን መኖር እንችላለን። w20.02 17 አን. 13-14

ዓርብ፣ ጥር 29

እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።—1 ዮሐ. 4:19

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከመጀመርህ በፊትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አድናቆት ይኖርህ ይሆናል። ለኢየሱስም ፍቅር አዳብረህ ሊሆን ይችላል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተዋወቅክ በኋላ ደግሞ ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስትህ ይሆናል። ሆኖም እነዚህን መልካም ነገሮች መውደድህ ብቻውን ራስህን ለይሖዋ እንድትወስንና እንድትጠመቅ ያነሳሳሃል ማለት አይደለም። ለመጠመቅ የሚያነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ አምላክ ያለህ ፍቅር ነው። ከሁሉም አስበልጠህ ይሖዋን የምትወደው ከሆነ ማንኛውም ሰው ወይም የትኛውም ነገር ይሖዋን ከማገልገል እንዲያግድህ አትፈቅድም። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ለመጠመቅ እንድትነሳሳ ብቻ ሳይሆን ከተጠመቅክ በኋላም ለእሱ ታማኝ ሆነህ እንድትጸና ይረዳሃል። ኢየሱስ ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን መውደድ እንዳለብን ተናግሯል። (ማር. 12:30) ለይሖዋ እንዲህ ያለ ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ባሳየን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን እኛም በምላሹ እንድንወደው ያነሳሳናል። w20.03 4 አን. 4-5

ቅዳሜ፣ ጥር 30

አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።—2 ጢሞ. 4:5

አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ሲባል ምን ማለት ነው? በአጭር አነጋገር፣ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ሲባል በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ማለት ነው። ሆኖም ይህ በአገልግሎት ከምናሳልፈው ጊዜ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ይሖዋ አገልግሎቱን ለማከናወን ለተነሳሳንበትም ምክንያት ትኩረት ይሰጣል። ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን በሙሉ ነፍሳችን የምናከናውነው፣ ይሖዋንና ሰዎችን ስለምንወድ ነው። (ማር. 12:30, 31፤ ቆላ. 3:23) አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ሲባል ሁለንተናችንን ለእሱ መስጠት ማለት ነው፤ ይህም አቅማችን እስከፈቀደው ድረስ ኃይላችንንና ጉልበታችንን ለእሱ አገልግሎት ማዋልን ይጠይቃል። ለተሰጠን ውድ የስብከት ሥራ አድናቆት ካለን ምሥራቹን በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ ጥረት እናደርጋለን። የምንፈልገውን ያህል ጊዜ በስብከቱ ሥራ ማሳለፍ አንችል ይሆናል። ሆኖም ይህ የምንወደው ሥራ ነው። በመሆኑም ችሎታችንን በማሻሻል የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ምሥራቹን ለመስበክ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። በዚህ መንገድ ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠት እንችላለን። w19.04 2-3 አን. 3-4፤ 3 አን. 6

እሁድ፣ ጥር 31

በእሱ ዘንድ እውነት [የለም]።—ዮሐ. 8:44

የሰይጣን ውሸቶች የሰዎችን ሐዘንና ሥቃይ አባብሰዋል። ልጃቸውን በሞት ያጡ ወላጆች አምላክ ልጃቸውን እንደወሰደው ምናልባትም መልአክ እንደሚያደርገው ይነገራቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ውሸት ልጃቸው የሞተባቸውን ወላጆች ያጽናናቸዋል ወይስ ሐዘናቸውን ያባብሰዋል? በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች፣ ሰዎችን ማሠቃየታቸውና የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርት የሚቃወሙ ግለሰቦችን እንጨት ላይ አስረው ማቃጠላቸው ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት ሐሰት የሆነውን የገሃነመ እሳት ትምህርት ይጠቅሱ ነበር። ስፓኒሽ ኢንክዊዚሽን በመባል ስለሚታወቀው የሮም ካቶሊክ ችሎት የሚናገር አንድ መጽሐፍ እንደገለጸው ይህን የጭካኔ ድርጊት ከፈጸሙት ሰዎች አንዳንዶቹ “በገሃነመ እሳት ለዘላለም መሠቃየት ምን ሊመስል እንደሚችል [ለመናፍቃኑ] በተወሰነ መጠን እያሳዩአቸው እንደሆነ ይሰማቸው ነበር።” መጽሐፉ አክሎ እንደገለጸው እነዚህ ሰዎች ይህን ድርጊት የፈጸሙት፣ መናፍቃኑ ከመሞታቸው በፊት ንስሐ የሚገቡበትና ከገሃነመ እሳት የሚድኑበት አጋጣሚ ለመስጠት ብለው ሊሆን ይችላል። በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የሞቱ ዘመዶቻቸውን ማምለክ፣ ማክበር ወይም የእነሱን በረከት ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። በመሆኑም ለሙታን መሥዋዕት ያቀርባሉ፣ ተዝካር ያወጣሉ እንዲሁም ሙት ዓመት ያከብራሉ። ሌሎች ደግሞ የሞቱ ዘመዶቻቸው ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ስለሚፈሩ እነሱን ለማስደሰት ጥረት ያደርጋሉ። የሚያሳዝነው ግን በሰይጣን ውሸቶች ላይ የተመሠረቱ እምነቶች እውነተኛ መጽናኛ አያስገኙም። እንዲያውም አስፈላጊ ላልሆነ ጭንቀት አልፎ ተርፎም ፍርሃት ይዳርጋሉ። w19.04 14 አን. 1፤ 16 አን. 10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ